Sunday, 29 May 2022 00:00

የሠብአዊ መብት ቅኝት በኢሠመጉ ምርመራ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

 "--ከግድያው ባሻገር በኢዜማ፣ አብን፣ ነፃነትና እኩልነት ፓርቲ፣ እናት ፓርቲ አባላትና አመራሮች ላይ እስራት፣ ድብደባ፣ ማዋከብና የንብረት ማውደም ድርጊት መፈፀሙም በሪፖርቱ ተጠቁሟል፡፡ በዚህም 85 ያህል የኢዜማ አባላትን ጨምሮ ከ145 በላይ በሚሆኑ ግለሰቦች ላይ እስርና ድብደባን ጨምሮ የተለያዩ የመብት ጥሰቶች እንደተፈፀመባቸው ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡--"
          
            የኢትዮጵያ ሠብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሠመጉ) ከ2011 እስከ 2014 ዓ.ም በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች የተፈፀሙ የሠብአዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከተ ከሰሞኑ ባወጣው ባለ 68 ገፅ መደበኛ ሪፖርቱ ይፋ አድርጓል፡፡
የምርመራ ሪፖርቱ በሁለት ዋነኛ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ሲሆን፤ አንደኛው ክፍል ከ6ኛው ሃገራዊ ምርጫ ጋር ተያይዞ በተፈፀሙ የመብት ጥሰቶች፣ ሁለተኛው ክፍል ደግሞ በተለያዩ አካባቢዎች በተለያየ መልክ በተፈፀሙ የሠብአዊ መብት ጥሰቶች ላይ አተኩሯል፡፡
ከምርጫ ጋር ተያይዞ በአማራና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ብሔራዊ ክልሎች የተፈፀሙ ህገ ወጥ ድርጊቶችንና የመብት ጥሰቶችን የዳሰሰው ሪፖርቱ፤ በሰብአዊ መብት ጥሰት ደግሞ በሲዳማ፣ በደቡብ፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝና  በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልሎች ከ2011 እስከ 2014 የተፈፀሙ ድርጊቶችን ዳስሷል፡፡
 ከ6ኛው ሃገራዊ ምርጫ ጋር
ተያይዞ የተፈፀሙ የሠብአዊ መብት ጥሰቶች
ከ6ኛው ሃገራዊ ምርጫ ጋር ተያይዞ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ኢዜማ፣ ነፃነትና እኩልነት፣ እናት ፓርቲ፣ የቁጫ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ፓርቲና ጋሞ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ በተሰኙ የፖለቲካ ድርጅቶች አባላት ላይ ከግድያ እስከ እስርና ማዋከብ እንዲሁም ህጋዊ መብቶችን የማሳጣት ድርጊቶች መፈፀማቸውን ሪፖርቱ ዳስሷል፡፡
ከምርጫው ጋር በተያያዘ ለምርጫ ስራ ሲንቀሳቀሱ በነበሩ የኢዜማ አንድ ወጣት አባልና የህብር ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ አንድ አባል በአሰቃቂ ሁኔታ ተደብድበው ግድያ እንደተፈፀመባቸው ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡ ኢሠመጉ ባደረገው ምርመራ፤ ከምርጫው ሂደት ጋር በተያያዘ ዘጠኝ የኢዜማ የደቡብ ክልል አባላት፣ አንድ የቁጫ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ አባል፣ አንድ የነፃነትና እኩልነት  ፓርቲ አመራር አባል ከፍተኛ ድብደባ ተፈፅሞባቸው ለአካል ጉዳት መዳረጋቸውን አረጋግጧል፡፡
ከላይ በተዘረዘሩት ፓርቲዎች አባላትና አመራሮች ላይ ከተፈፀሙ የግድያና የአካል ጉዳት ድርጊቶች በተጨማሪ በርካቶች ከማህበራዊ ህይወት እንዲገለሉና  የሥነ ልቦና ጉዳት እንዲደርስባቸው መደረጉን፣ በርካቶች ንብረታቸው መውደሙን ሪፖርቱ በዝርዝር አመልክቷል፡፡
በምርጫው ወቅት በዚሁ በደቡብ ክልል ተፎካካሪ በነበሩ ፓርቲዎችና ተወዳዳሪ አባሎቻቸው ላይም በቀጥታ በምርጫው እንዳይሳተፉ ከማድረግ ጀምሮ የተለያዩ የማዋከብና ማስፈራራት ዛቻዎች፣ ድብደባና እገታዎችን በመፈጸም ጫናዎች መደረጋቸውን ሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡
የኢዜማ 5 አባላትን ጨምሮ የተለያየ ፓርቲዎች አባላትና አመራሮች የንግድ መደብሮች፣ የግል ንብረቶችና ሃብቶች መዘረፋቸውን ያመለከተው ሪፖርቱ፤ በምርጫው ሂደት አምስት የኢዜማ አባላት ታስረው ኋላም በዋስ የተፈቱ መሆኑን፣ ነገር ግን 132 የሚሆኑ አባላት ሪፖርቱ እስከተጠናከረበት ግንቦት 2014 ድረስ በእስር ላይ እንደሚገኙ ኢሠመጉ አስረድቷል። የሌሎች ፓርቲ አባላትም በእስር ላይ እንደከረሙ በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡
በአማራ ክልል ከምርጫው ጋር ተያይዞ ግድያን ጨምሮ የተለያዩ  የመብት ጥሰቶች መፈፀማቸውን ያረጋገጠው ሪፖርቱ፤ ሁለት የአብን አባላት "ለአብን የምርጫ ቅስቀሳ ለምን ታደርጋላችሁ?" በሚል መገደላቸውን አመልክቷል፡፡
ከግድያው ባሻገር በኢዜማ፣ አብን፣ ነፃነትና እኩልነት ፓርቲ፣ እናት ፓርቲ አባላትና አመራሮች ላይ እስራት፣ ድብደባ፣ ማዋከብና የንብረት ማውደም ድርጊት መፈፀሙም በሪፖርቱ ተጠቁሟል፡፡ በዚህም 85 ያህል የኢዜማ አባላትን ጨምሮ ከ145 በላይ በሚሆኑ ግለሰቦች ላይ እስርና ድብደባን ጨምሮ የተለያዩ የመብት ጥሰቶች እንደተፈፀመባቸው ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡
በተለያዩ አካባቢዎች የተፈፀሙ
የሠብአዊ መብት ጥሰቶች
ኢሠመጉ በተለያዩ አካባቢዎች የተፈፀሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በመረመረበት ሪፖርቱ፣ ከ2011 ጀምሮ የተፈፀሙ ግድያዎችን ጨምሮ ምንም አይነት ካሳና ምትክ ሳይሰጥ አርሶ አደሮችን ማፈናቀል ያሉ የመብት ጥሰቶችን ዳስሷል፡፡
በሲዳማ ክልል ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ ከመሬታቸው ያለምንም የካሳ  ክፍያ የተፈናቀሉ 179 አርሶ አደሮች ያሉበትን አሳዛኝ ሁኔታ በሪፖርቱ አካትቷል፡፡
በሲዳማ ክልል ሄይኒናታ ገጠር ቀበሌ ገበሬ ማህበር ውስጥ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደሮች፣ ለፖሊስ ኮሌጅ ማስፋፊያ በሚል ከመሬታቸው መፈናቀላቸውን፣ ከብዙ ክርክር  በኋላ በአጠቃላይ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ካሳ እንዲከፈላቸው ቢወሰንም እስከ ዛሬ ድረስ ካሳው እንዳልተከፈላቸውና ሰሚ አጥተው በከፋ እንግልት ውስጥ እንደሚገኙ ሪፖርቱ አትቷል፡፡
በደቡብ ክልል በተለይም የም ዞን አርባ ምንጭ ዙሪያ በአርሶ አደሮች ላይ ዘርፈ ብዙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መፈፀማቸው በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡ በአካባቢው የቀበሌ አስተዳደርና አመራሮች ከተፈፀሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መካከል የአርሶ አደር ሚስቶች ላይ ፆታዊ ጥቃት መፈፀም፣ ለአካባቢው ነዋሪዎች በነፃ የመጣን የእርዳታ እህል በነፍስ ወከፍ 50 ብር እያስከፈሉ ማደል፣ የአርሶ አደሮችን የጋራ የግጦሽ መሬት ለግለሰቦች መሸጥ የመሳሰሉ ድርጊቶች ይገኙባቸዋል፡፡
በደቡብ ክልል የተፈፀሙ ግድያዎችን በተመለከተ ደግሞ በደራሼ እና በኩስሜ ብሔረሰብ መካከል ካለው የማንነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ የአካባቢው ባለስልጣናት በሚፈጥሩት ውስብስብ ችግር የተነሳ ዘጠኝ የኩስሜ ብሔረሰብ አባላት መገደላቸውን፣ 23 ለጉዳት መዳረጋቸውን እንዲሁም 24 የብሔረሰቡ አባላት ታስረው እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡
በተመሳሳይ በደቡብ ክልል ሃላባ ዞን አርሶ አደሮች ተገቢው መብት ሳይጠበቅላቸው ከመሬታቸው የማፈናቀል ድርጊትን መፈፀሙን ሪፖርቱ በዝርዝር አመልክቷል፡፡
በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ደግሞ ከ2011 እስከ 2013 ድረስ በተለያዩ ወረዳዎች የጉምዝ፣ ኦሮሞ፣ አማራና ሌሎች ብሔር ተወላጆች ላይ በተለያየ መንገድ ግድያዎች መፈጸማቸው እንዲሁም  በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ መፈናቀላቸው ተጠቅሷል - በሪፖርቱ፡፡
በኦሮሚያ ክልል በተለይ በመንግስትና በሸኔ መካከል ባለው ግጭት የተነሳ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ሸመኔ ፈፅሞታል በተባለ ጥቃት በቅርቡ ማለትም በመጋቢት ወር 34 ንፁሀን ሰዎች መገደላቸውን፣ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ፈንታሌ ወረዳ 12 ሰዎች መገደላቸውን፣ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን እና ምስራቅ ወለጋ ዞን በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች 55 ሰዎች መገደላቸውን፤ በእነዚህ ዞኖችና ወረዳዎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ለአካል ጉዳትና ለእስር መዳረጋቸውንም ሪፖርቱ ከሟቾች የፎቶና  የአድራሻ መግለጫ ጋር ስማቸውን በዝርዝር አስቀምጧል፡፡
ኢሠመጉ በ69 ገፆች ባዘጋጀው የምርመራ ሪፖርቱ ማጠቃለያ፣ መንግስት ሊወስዳቸው ይገባል ያላቸውን የመፍትሄ አቅጣጫዎችም አመልክቷል፡፡ በዚህም መንግስት ከ6ኛው ሃገራዊ ምርጫ ጋር ተያይዞ የተፈፀሙ የመብት ጥሰቶችን በተመለከተ ድርጊቱ ከተፈፀመባቸው ፓርቲዎች ጋር በመመካከር ለቀጣዩ ምርጫ እንዳይደገሙ የሚያደርግ መፍትሔ እንዲያበጅ ጠቁሟል፡፡
በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ለተፈፀሙና በሪፖርቱ ለተካተቱ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች የሚመጥኑ የእርምት እርምጃዎች እንዲወሰዱ፣ ድርጊቶቹ ድጋሚ እንዳይፈፀሙ የሚያስችሉ የጉዳት ቅድመ መከላከል ስራዎች እንዲሰሩ፣ የማህበረሰብ ቅራኔዎች እንዲፈቱ፣ ተጎጂዎች ካሳ እንዲያገኙ፤ ህዝብን ለእንግልት፣ ብዝበዛና ሰቆቃ የዳረጉ አካላት በህግ እንዲጠየቁ ኢሠመጉ አሳስቧል፡፡Read 2122 times