Saturday, 28 May 2022 14:40

አገጭህን ይዞ የሚለምንህ እምቢ ብትል በጥፊ ሊልህ!

Written by 
Rate this item
(3 votes)


             ከዕለታት አንድ ቀን አንድ አዝማሪ፣ ንጉሥ ግብር ገብቶ፣ ግብሩ ከተበላና ከተጠጣ በኋላ፤ ልዩ አስተያየት የሚያደርግላቸው መኳንንትና መሳፍንት ብቻ ሲቀሩ፤ ንጉሡን የሚያወድሱ አያሌ ግጥሞችን እየደረደረ በጣም አድርጎ አስደሰታቸው፡፡
ንጉሡም፤
“ንሳ አንተ አጋፋሪ፣ ና አንድ ኩታ ሸልምልኝ!” ይላሉ፡፡
 አዝማሪ ኩታውን ይደርባል፡፡ ከዚያም ውዳሴ-ንጉሡን ይቀጥላል፡፡
አሁንም ንጉሡ እጅግ ደስ ይላቸውና፤
“ንሳ አንተ አጋፋሪ፤ ሠናፊል ከወረደህ-ቆየኝ ሸልምልኝ!”
አዝማሪ ሽልማቱን ተጎናጸፈ!
ደገመ ሌላ ውዳሴ-ንጉሥ፡፡
ንጉሡ፤
“አንድ ካባ ደርብለት አጋፋሪ! አንድ ብርሌም ይጠጣ!” አሉ፡፡
ካባ አገኘ አዝማሪ፡፡ ብርሌዋንም በአንድ ትንፋሽ አንደቀደቃት! ሽልማቱ እያሰከረው መጣ! ድምፁም ከቀድሞው እጅግ ጮክ፣ እጅግ ጎላ አለ፡፡
ቀጥሎ ልኩን አለፈና ንጉሡን ዘለፈ፡፡ እንዲህ አለ፡-
“የንጉሥን አጫዋች፣ማን ደፍሮ ሊነካ
የሹሙንስ መሬት ማ ረግጦ ሊለካ
የሚመካ ካለ ፣በካባው ይመካ
የንጉሥ ዘመድ መሆን፣ ያሸልማል ለካ!”
ንጉሡ ተናደዱ፡፡
“ንሣ አንተ አጋፋሪ! ይሄን አዝማሪ የለበሰውንም፣ ያለበስከውንም ሁሉ ግፈፍልኝ! ከዚያ ቀጥለህ አርባ ጅራፍ አልብስልኝ!”
አዝማሪ፤ “በአፍ ይጠፉ፣ በለፈለፉ” እንደተባለው ሆነ፡፡ እራቁቱን አርባ ጅራፍ ቀመሰ!
ከጅራፉ በኋላም፤
“መወደስ ለጅራፍ፤ ከሆነ ነገሩ
አቀንቃኞች ሁሉ፣ ´አፍ-እላፊን´ ፍሩ!”
ሲል ዘፈነ ይባላል፡፡
*   *   *
ንጉሥ ምንም ሙገሳን ቢወድድ፣ ጥቂት  ዘለፋ የደረሰበት ዕለት የጭቃ ጅራፉን ያመጣዋል፡፡ አፋሽ አጎንባሽ፣ ዐባይ አድር-ባይ፣ ከሐዲ-ይሑዲ ሁሉ ይህ ጉዳይ ይመለከተዋልና “አሃ!” ብሎ ቢያዳምጥ የአባት ነው!
ታላላቅ የዓለም መንግስታት ኢትዮጵያን አወደሷት በተባለ ሰሞን- “ጠርጥር! ነገር አለ!” ብሎ ማሰብ ተገቢ ነው፡፡ “ሊበሏት ያሰቧትን አሞራ ጅግራ ናት ይሏታል” ነውና እግርን ሰብስቦ፣ ዐይንን አጥብቦ ማሰብ ያሻል፡፡
“ከዐሥር ዓመት የትግል እንቅስቃሴ ይልቅ፣ የአንድ ዓመት አብዮታዊ ሁኔታ፣ ህዝብን ያነቃዋል” ይላል የሩሲያው ሌኒን፡፡ ህዝብ በሸፍጥ የማይታለልበትና በጉልበት የማይበገርበት ደረጃ አንድ ቀን እንደሚደርስ፣ እያደርም “በቃኝ፣ አልገዛም” እንደሚል፣ ማንም መሪ ሊስተው አይገባም፡፡
የዛሬ የሀገራችን ፖለቲካ፤ “የሚያብድና የሚያድግ አይታወቅም” የሚባል ዓይነት ሆኗል፡፡ “ዘይት ተወደደብን” ሲባል፤ “ዳቦ በሙዝ ብሉ”፣ “ትራንስፖርት ተወደደብን” ሲባል፣ “በእግር መሄድ ጀምሩ” መባል እንደ ፖለቲካል-ኢኮኖሚያዊ መፍትሔ መቆጠር የተጀመረበት ዘመን ሆኗል፡፡
እንግዲህ በዚህ ላይ የማያባራ ጦርነት አለ፡፡ የአምራች ወጣት ኃይል እልቂት! የበሽታና ድርቅ  አባዜ! የህዝቦች መፈናቀል! ምኑ ቅጡ!
“ራሴን ያመኛል´ኮ፣ራሴን ይመቱኝ ይሆን?” አለ አሉ፤ አንድ ወደ ጦርነት ዘማች፡፡
በአንጻሩ ደሞ አንድ ከጦርነት ተመላሽ፤
“ጦርነቱ እንዴት ነበር?” ተብሎ ሲጠየቅ፣
“አይ እንደፈራነው አይደለም፡፡ አሥራ አራት ሆነን ዘምተን እኔ ደህና ተመልሻለሁ!” አለ አሉ፡፡ “ፈሪ የእናቱ ልጅ ነው” ይላል አበሻ ሲተርት፡፡
አንድ ጊዜ ክሊንተን ሮዚተር የተባለ አሜሪካዊ የፖለቲካ ተንታኝ ምሑር፤ “ያለ ዲሞክራሲ አሜሪካ  የለችም፡፡ ያለ ፖለቲካ ዲሞክራሲ የለም። ያለ ፖለቲካ ፓርቲዎችም ፖለቲካ የለም” ብሎ ነበር፡፡
ማርጋሬት ሚሼል የተባለችው ደራሲ ደግሞ፤ “ጦርነት ልክ እንደ ሻምፓኝ መጠጥ ነወ፣ አንዴ ከገቡበት በጀግናም በጅልም ራስ ላይ እኩል ይወጣል” ትለናለች ( War is like champagne, it goes to the heads of fools as well as brave-men at the same speed) ይሄ ማለት ልባምም ልበ-ቢስም እኩል ዝነኛና ጀግና የመባል ዕድል አላቸው እንደማለት ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ አገራችን ሁኔታ ደግሞ በትንሽም በትልቅም ጉዳይ፣ አንዴ ወይ በተደጋጋሚ፣ታስረው አምነስቲ ኢንተርናሽናል ጭምር ያስፈታቸው “የድንገቴ ፖለቲከኞች” አይተናል፡፡ ከዚያ ማን ይችላቸዋል? በየመድረኩ ደስኳሪ፣ በየሰርጉ ጨፋሪ፣ በየለቅሶው ሙሾ አውራጅ እነሱ ብቻ ይሆናሉ! ከእኒህ ይሰውረን እንጂ ምን ይሏል? ከኒህ በላይስ የድል አጥቢያ ዐርበኛ የታል? በተለይ ከ1960ዎቹ ወዲህ፣ አብዛኛው ፖለቲካ፣ የፖለቲካ ድርጅት/ፓርቲ፣ የፍትህ አካል፣ የአስተዳደር ኤጀንሲና የደህንነት መሥሪያ ቤት ወዘተ… ለስሙ የህዝብ ግንኙነት በራቸውን መክፈት ቢጀምሩም፣ ብዙዎቹ የጓሮ በር አላቸው፡፡ ስለሆነም፣ግማሽ-ጎፈሬ፣ግማሽ ልጩ ናቸው!!
አገርን መከላከል ታላቅ ሚናና የአገር ወዳድነት ምልክት ነው። አገርን ማጥፋት ደግሞ ኃላፊነትን መካድና ወንጀለኝነት ነው። የጥፋት መልዕክተኝነት ነው! የውጪ ኃይሎች መቼም በኢትዮጵያ ጉዳይ ተኝተው አያውቁም። የእነሱ ጉዳይ አስፈጻሚ የሆኑት አምስተኛ ረድፈኞች (5th columnists እንዲል መጽሐፉ) ከውስጥ ይቦረቡሯታል። ይህ በየዘመኑ ያየነው፣ የታዘብነውና ምኔም የምንዋጋው ክስተት ነው። ታላላቅ መንግሥታትም ባገኙት መንገድ በጎረቤት አገርም፣ በማህል አገርም፤ ገንፎው ሲያቃጥል በማንኪያ፣ ሲበርድ በእጅ ለመቀራመት፣ እንደተለመደው አፍሪካን በመቀራመት አጀንዳቸው (Scramble for Africa) ሩጫቸውን  አላቆሙም። በዚያ ሳቢያም ሱዳን፣ ግብፅ፣ ሶማሊያ፣ ዩጋንዳ፣ ኬንያ… መንኳኳት የማይለያት አገር ካደረጓት  ውለው አድረዋል።
እነዚህን ጎረቤቶቻችንን የውስጥ- ዓርበኛ አድርገው የሚንቀሳቀሱት ኃያላን አገሮች “ቢቻል በካሮት ባይቻል በበትር” (Carrot and stick) የሚለውን ጨዋታቸውን ሳያሰልሱ እየተጓዙበት ነው። “አያያዙን አይተው ጭብጦውን ቀሙት” የሚለውን ተረት በጥሞና ማሰብ ብልህነት ነው። አለመዘናጋት ወሳኝነት አለው። ትልቁ ቁም-ነገር ግን፣ ኃያላን ኃይሎች በባሌም ይምጡ በቦሌ፣ በውስጥ- አርበኛም ይዋጉ “በቀኝ-መንገደኛ”፣ የአገርን ጉዳይ ቸል አለማለት ነው። ጉልበተኛ፤ “አገጭህን/ይዞ የሚለምንህ፣ እምቢ ብትል በጥፊ ሊልህ!” የሚለውን የአበው ብሂል፣ መቼም አለመርሳት ለአገር ታላቅ/ውለታ መዋል ነው! ዛሬም እንንቃ፣ ልብ-እንግዛ፣ እንትጋ!

Read 11520 times