Print this page
Saturday, 28 May 2022 15:16

የመጽሐፍ ምልከታ - "ሆህያተ ጥበብ"

Written by 
Rate this item
(6 votes)

   የመጽሐፉ አርእስት፡- ሆህያተ ጥበብ፡-
                                ለጸሓፍያን፣ ለተርጓምያንና ለአርታዕያን
                                ደራሲ፡- ዶ/ር ተስፋዬ ሮበሌ
                                የታተመበት ዓመት፡- 2022 ዓ.ም
                                የገጽ ብዛት፡- 210+፰
                                አሳታሚ፡- ተስፋ ዐቃብያነ ክርስትና ማኅበር
                               ተመልካች፡- ናይእግዚ ኅሩይ



                 ‹የዐማርኛ ፊደል ገበታ ተመሳሳይ (አንድ ዐይነት) ድምፅ ያላቸውን ፊደሎቹን ይዞ መቀጠል አለበት›፣ ‹የለም ልናስወግዳቸው ነው የሚገባው›፣ የሚሉት አሳቦች ከኹለት ትውልድ በላይ ምሁራንን ሲያከራክር ኖሯል፡፡ እነዚኽን ባለአንድ ዐይነት ድምፅ ሞክሼ ፊደሎች ይዘን መቀጠል ብቻ ሳይኾን፣ በየትኞቹ ቃሎች ላይ እንደሚገቡም ጠንቅቀን ማወቅ አለብን የሚለውን ተሟጋች ወገን ደግፈው ዶ/ር ተስፋዬ ሮበሌ መጽሐፍ አሳትመዋል፡፡ እኔ የዚኽ መጽሐፍ ተመልካችም እንደ ባለሙያ ሳይኾን፣ ስለ ጕዳዩ የሚቀርቡትን ክርክሮች በግል ተነሣሽነት ሲያጤን እንደኖረ ሰው ስለ መጽሐፉ የተመለከትኹትን ለማጋራት እሞክራለኹ፡፡
ደራሲው በገጽ [፭]
‹‹የይዘትም ሆነ የአቀራረብ ስሕተትም ሆነ ግድፈት ቢስተዋል፣ የችግሩ ሙሉ ተወቃሽ እኔው ብቻ መሆኔ ይታወቅ፡፡ ሐያስያን ዐደራ፣ ወደ እኔ ብቻ አነጣጥሩ›› ብለዋልና፣ ደራሲውን ‹ይበሉ እንግዲኽ፣ ለሒስ ባይበቃም፣ ምልከታዬን ይዩልኝ› እላቸዋለኹ፡፡
ከመጽሐፉ ጥሩ ጎኖች ልነሣ። የመጀመሪያው የሽፋን ሥዕሉ ነው። ከመጽሐፉ ጭብጥ ጋር የሚስማማ፣ ዐይነ ግቡ ሥዕል ነው፡፡ መጽሐፉን የራስ ለማድረግ ይጋብዛል፡፡ ሌላው ጥሩ ጎን፣ የደራሲው መልካም ቅናት ነው፡፡ ርግጥ በኔ ምልከታ የደራሲው መልካም ቅናት አንፀባራቂ እንዳይኾን ያጠለሹ አንዳንድ ችግሮች መጠረግ ይኖርባቸዋል፡፡
ምናልባትም እንደተጨማሪ መልካም ጎን ሊጠቀስ የሚችለው፣ መጽሐፍ ጽፎ፣ አዘገጃጅቶ የማሳተምን ከባድ ጕዞ መከወናቸው ነው፡፡
ባጠቃላይ ምልከታዬ፣ መጽሐፉ ቢያንስ ዐሥር የስሕተት ዐይነቶች የሚገኙበት ስለመሰለኝ፣ በየአርእስታቸው ልዘርዝራቸውና የመጽሐፉ አንባቢዎችም፣ ደራሲውም ያመኑበትን ይቀበሉ፡፡
፩. አርእስት
የመጽሐፉ ችግር ከአርእስቱ ይጀምራል፡፡ ‹‹ሆህያተ ጥበብ›› ምን ማለት ነው? ‹የጥበብ ሆህያት› ማለት ነው። ርግጠኛ ነኝ ደራሲው ማለት የፈለጉት ‹የሆህያት [አጻጻፍ] ጥበብ› ነው፡፡ የግእዙን አካሄድ የሳቱ ይመስለኛል፡፡ ይኹንና፣ ይህን ለመረዳት በቂ የግእዝ ዕውቀት እንዳላቸው ከሌሎች የ‹ፌስ ቡክ› መጣጥፎቻቸው አስተውያለኹ፡፡
ለምሳሌ፡- ‹አብያተ ክርስቲያን› ምን ማለት ነው? ‹የክርስቲያን ቤቶች› ማለት ነው። ከግእዝ በተዋሰው በዚኽ የማዛረፍ ሥልት ዐማርኛ በርካታ ስያሜዎችን ይጠቀማል (አብያተ መጻሕፍት፤ ሕገ መንግሥት…)። ሌላ ምሳሌ፡- ‹ጥበበ ሰሎሞን› ስንል ‹የሰሎሞን ጥበብ› ማለታችን ነው፡፡ እነዚኽን ምሳሌዎች ያቀረብኹት ደራሲው በአርእስት አጻጻፋቸው መሳሳታቸውን በግልጽ ለማሳየት ነው፡፡
እና ደራሲው፣ ‹ለማለት የፈለግኹት የጥበብ ሆህያት ነው› ካሉ ደግሞ፣ ከመጽሐፉ ጭብጥ ጋር የማይገናኝ ይኾናል፡፡ ስለዚኽ፣ መጻፍ የነበረበት ‹ጥበበ ሆህያት› ተብሎ ነበር፡፡
በማውጫው ገጽ ለምዕራፍ አንድ የሰጡት ስያሜ ‹‹ሆህተ ጥበብ›› ይሰኛል፡፡ ‹ሆህያተ ጥበብ› ለማለት የፈለጉ ይመስለኛል። ወይስ ‹የጥበብ በር (መግቢያ)› የሚል ትርጕም ፈልገው ኖሯል? ያ ደግሞ የሚጻፈው በ‹ኀውት ኀ› ‹ኆኅተ ጥበብ› ተብሎ ነው፡፡ ስለ ፊደል ተጨንቀው ባዘጋጁት መጽሐፍ እንዲኽ ያለ ስሕተት ሳገኝ፣ ደራሲው በርግጥ ምን ለማለት ነው የፈለጉት እያልኹ እታወካለኹ፡፡
በነገራችን ላይ የመጽሐፍ ወይም የጽሑፍ ስያሜ ‹አርእስት› እንጂ ‹ርእስ› እንደማይባል ለአንባቢዎቼ ማስታወስ ሻለኹ፡፡
፪. የፊደል ግድፈትና ልውጠት
ምንም እንኳ ከብዙ መጽሐፎች ጋር ሲተያይ የዶ/ር ተስፋዬ መጽሐፍ በመልካም ታርሞ ቢታተምም፣ ስለ ቋንቋ ሊያውም ስለ ፊደል የሚያወራ መጽሐፍ ከአንድና ኹለት በላይ የትየባ ስሕተት ሊገኝበት ባልተገባ ነበር። ‹‹ምክንያትና ተምኔት›› ብለው በሰየሙት መግቢያቸው ላይ፣ ‹‹‹ሰው ሆኖ አይስት እንጨት ሆኖ አይጥስ የለም››› የሚለውን አባባል ጠቅሰው ሥራቸው ፍጹም አለመኾኑን ነግረውናል፡፡ እኔም ፍጽምናን ባልጠብቅም፣ ስሕተታቸው ግን በዐይነትም በቊጥርም በዛ፡፡
የፊደል ግድፈት ያልኋቸው፡- ሀ. መጻፍ ሲገባቸው የተረሱ ፊደሎችን (ለምሳሌ፣ በገጽ 13 ‹የደበበ› ለማለት ‹‹ደበበ››፣ በገጽ 41 ‹ሆህያትን› ለማለት ‹‹ሆያትን›› ወዘተ)፣ ለ. እንደ ዐረም ያለቦታቸው የገቡ ፊደሎችን (ለምሳሌ፣ በገጽ 46 ‹መጽሐፋቸው› ለማለት ‹‹በመጽሐፋቸው››፣ በገጽ 56 ‹ግእዝ› ለማለት ‹የግእዝ› ወዘተ) እና ሐ. በተሳሳተ ፊደል የተተኩ ፊደሎችን (ለምሳሌ፣ በገጽ 4 ‹አስተማሪዬ› ለማለት ‹‹አስተማርዬ››፣ በገጽ 9 ‹ጸሓፌ ተውኔቶች› ለማለት ‹‹ጸሓፊ ተውኔቶች፣ በገጽ 21 ‹ኮሌጅ› ለማለት ‹‹ኮሎጅ››፣ በገጽ 59 ‹በወጉ› ለማለት ‹‹በወጕ››) ነው፡፡
‹ሞክሼ ሆህያት በአግባቡ መጻፍ አለባቸው› የሚል ክርክር አንግቦ የተነሣ መጽሐፍ፣ ቢያንስ በዚኽ እንኳ ስሕተት ሊገኝበት አይገባም ብዬ እሞግታለኹ፡፡ ለምሳሌ፣ በገጽ 19 የግርጌ ማስታወሻ ኹለት ጊዜ በ‹ዐዳዲስ› ፈንታ ‹‹አዳዲስ›› ብለው ጽፈዋል፡፡ ሌሎችም ብዙ አሉ፡፡ ‹የሚቈይ› ለማለት ‹‹የሚቆይ›› (ገጽ 15)፣ ‹ለማሥረጽ› ለማለት ‹‹ለማስረጽ›› (ገጽ 17)፣ ‹በዐጪሩ› ለማለት ‹‹በአጭሩ›› (ገጽ 45፤ በርግጥ ‹ዐጭር›ም ተቀባይነት አለው) ወዘተ። እነዚኽን ስሕተቶች በ‹ፊደል ልውጠት› ሥር አካትታቸዋለኹ፡፡
አንዳንድ ቃሎች በመነሻቸው እንደ ‹ረ›ና ‹ሰ› ያሉ ድምፆች ሲኖሯቸው፣ ‹እ› በሚል ድምፅ እንድንነሣ ግድ የሚለን የድምፅ አፈጣጠር ሕግ አለ፡፡ ለምሳሌ፣ ‹ርሱ› ለማለት ‹እርሱ› እንላለን፤ ‹ስፖርት› ለማለት ‹እስፖርት› እንላለን፡፡ ሙያዊ ትንታኔውን እዚኽ ማቅረብ ባልችልም፣ ፕሮፌሰር ባየ በመጽሐፋቸው ‹‹ስርገት›› በሚል ንዑስ አርእስት ያብራሩትን መመልከት ይቻላል (ባየ ይማም፣ የአማርኛ ሰዋስው - የተሻሻለ ሁለተኛ እትም (አሳታሚ ያልተጠቀሰ፡- አዲስ አበባ፣ 2000 [ዓ.ም])፣ 59-65፡፡)፡፡
ስለዚኽ፣ በምንጽፍበት ወቅት የንግግር ጠባይ ተጽዕኖ እንዳያደርግብን መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ፣ በገጽ 21 ‹ርባታቸውንም› ለማለት ‹‹እርባታቸውንም›› ብለዋል፡፡
፫. የጥቅስ አወሳሰድ
በዚኽ ሥር የመደብኋቸው ስሕተቶች የሚከተሉት ናቸው፡፡
ሕጋዊ ስሞችን በሕገ ወጥነት ማስተካከል፡፡ ግለሰብም ኾነ ተቋም ‹ስሜ ነው› ብሎ ያስመዘገበውን እንዳለ ወስደን እንጠቀማለን እንጂ አንዲት ፊደልም ትኹን አንዲት ጭረት የመለወጥ ሥልጣን የለንም። ለምሳሌ፣ ‹አዲስ አበባ› ትክክለኛ አጻጻፉ ‹ዐዲስ አበባ› መኾኑን የደስታ ተክለ ወልድ መዝገበ ቃላት ያስተምረናል፡፡ ዶ/ር ተስፋዬም፣ እኔም ትምህርቱን ተቀብለን አስተካክለን ለመጻፍ ወስነናል፡፡ ይኹንና፣ የ‹አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ›ን ስያሜ ግን ‹አ›ን በ‹ዐ› ለውጠን ‹ዐዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ› ብለን መጻፍ አንችልም፡፡ ይህ ተቋም በሕግ የተመዘገበና የሰውነት ሥልጣን/መብት ያለው በመኾኑ፣ ‹ስሜ እንዲኽ ነው› የማለት መብቱን ያለመቀበል መብት የለንም። ዶ/ሩ እንዲኽ ያለ ስሕተት በተደጋጋሚ ፈጽመዋል፡፡ ሌላ ምሳሌ ለማቅረብ፣ ደራሲ ሀዲስ አለማየሁ ስማቸውን የሚጽፉበትንና ያሳተሙበትን ፊደል ለውጦ (ዶ/ር ተስፋዬ እንደመሰላቸው አስተካክለው) ማተም ‹‹እኔ ዐውቅልኻለኹ›› ማለትም አይደል?
ዶ/ር ተስፋዬ፣ የሚጠቅሷቸውን ምንጮች ኹሉ በትክክል ይጠቅሳሉ ብዬ ለማመን አንዳችም ምክንያት ስላሳጡኝ ራሴው ኹሉንም ለመፈተሽ ተገድጃለኹ። እስቲ አኹን ያንድን መጽሐፍ ስያሜ በትክክል መገልበጥ አዳጋች የሚኾነው ለምንድን ነው? በገጽ 5፣ በ7ኛው የግርጌ ማስታወሻ የፕሮፌሰር አምሳሉን መጽሐፍ የጠቀሱበት መንገድ፡- ሀ. የፊደል ግድፈት፣ ለ. የሥርዐተ ነጥብ ስሕተትና ሐ. የ‹ገንዘብ› አመልካቿ ‹የ› አላስፈላጊ አገባብ ይታዩበታል፡፡ ስሕተቶቹን በየአርእስታቸው ገልጫለኹ፡፡
የሌላ ሰው ሥራ ሲጠቀስ በቀጥታ እንደተጻፈው እንጠቅሳለን እንጂ ማሻሻያ አናደርግም፡፡ በመደበኛው የትምህርት ዓለም እንዲኽ ያለው ጕዳይ ‹F› እንደሚያሰጥ እንኳን ዶ/ር ተስፋዬ እኔም ዐውቃለኹ፡፡ ደግሞም ራሳቸው እንኳ ከፍቅር እስከ መቃብር መጽሐፍ ሲጠቅሱ እንዲኽ ብለዋል፡- ‹‹የሆሄና የሥርዐተ ነጥብ ስሕተቱን ሳላስተካክል፣ እሳቸው በጻፉበት መንገድ ዐቅርቤዋለሁ›› (ገጽ 50)፡፡ እንዲኽ ያለ ማሳሰቢያ መስጠታቸው ተገቢ የሚኾነው፣ የአጠቃቀስን ሥርዐት የማያውቅ አንባቢ፣ ‹ዶ/ሩ አሳስተው ገለበጡ› ብሎ እንዳይከሳቸው ስለሚረዳ ነው፡፡
ከገጽ 25-26 የሀዲስ አለማየሁን ሥራ ሲጠቅሱ ግን የትየለሌ ስሕተት ሠርተዋል፤ ቢያንስ 34 ስሕተቶች ናቸው፤ ማወቅ ከፈለጋችኹ። ፊደል ይለውጣሉ፣ ፊደል ያሳስታሉ፣ ሥርዐተ ነጥብ ይለውጣሉ/ያስገባሉ፣ አንቀጽ መለያውን ያስወግዳሉ፣ ደግሞም ያልጨመሩትን ክፍት ቦታ ይጨምራሉ፡፡
ጥቅም ላይ የዋሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ከየትኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጕም እንደተወሰዱ አልተጠቀሰም፡፡ ለምሳሌ፣ ገጽ 39፡፡ ይህ ወቀሳ የጠቀሱትን የግሪክ መጽሐፍ ቅዱስም ይጨምራል፡፡
፬. ተሳቢ አመልካቿ ‹ን›
በዐማርኛ ሰዋስው እንደ ‹ን› መከራውን ያየ እንደሌለ በዐሥር ጣቴ ፈርማለኹ። ከ1983 ዓ.ም ወዲኽ በታተሙ ሥራዎች ላይ የማደርገው ቅኝት ካስገነዘበኝ ጕዳዮች አንዱ ይቺ መከረኛ ‹ን› ጕስቊልናዋ እየባሰ መምጣቱን ነው። ጋዜጦችና መጽሔቶችማ ቅንጣትም ግድ ያላቸው አይመስለኝም፡፡ ‹የሞት መድኀኒት ነው ፈልገኽ አምጣ› ብባል እንኳ በዚኽ ረገድ ንጹሕ ኅትመት ማግኘት መቻሌ ያጠራጥረኛል (አላገኝም!)፡፡
ደራሲው ከዐማርኛ በተጨማሪ ቢያንስ ሦስት ቋንቋዎች እንደተማሩና ግእዝንም በራሳቸው ተነሣሽነት በግላቸው እንደሚያጠኑ ዐውቃለኹ (በማኅበራዊ ‹ሚዲያ› ከምከተላቸው ጥቂት ሰዎች አንዱ ናቸውና)፡፡ በቋንቋዎች ጥናት ውስጥ ተሳቢንና ሳቢን፣ ተደራጊንና አድራጊን (ደራጊን) የሚለዩ የሰዋስው ሕጎችን ማጥናት ቀላል አይደለም፡፡ ዐማርኛም ከዚኽ ነጻ ባለመኾኑ፣ አፋቸውን የፈቱበትና እንጀራቸውን የሚያበስሉበት ጸሓፊዎች ሳይቀሩ የሚሠሩት ስሕተት ቆርቆሮ ሲቧጠጥ የሚሰጠውን ስሜት ይፈጥርብኛል፡፡
መቼም በዚኽ የምልከታ መጣጥፍ ስለ ‹ን› አገባብ ትንታኔ እንድሰጥ አይጠበቅብኝም፡፡ ጥቂት ግን ከመጽሐፉ ችግሮችን እየነቀስኹ ላሳይ፡፡
በገጽ 12፣ የግርጌ ማስታወሻ 14፣ ‹‹ማደሪያዬን ከእግዚአብሔር ከዋክብት በላይ አደርጋለሁ ያለው ሰይጣን፣ አምላክ በትዕቢቱ መጠን ቊልቊል አምዘግዝጎ ወርውሮታል›› በሚለው ዐረፍተ ነገር ውስጥ፣ ሀ. ‹‹ወርውሮታል›› ሳቢ ግስ በመኾኑ፣ ለ. ‹‹ሰይጣን›› የታወቀ (እሙር) በመኾኑ ‹‹ያለው›› የሚለው ቃል የግድ ‹ን›ን መውሰድ ይኖርበታል፡፡
በገጽ 20፣ የግርጌ ማስታወሻ 30፣ ‹‹ስለ ቋንቋው ያለን ዕውቀት፣ ቢያንስ የፉከራችን ያህል እንዳልሆነ ልቡናችን ያውቀዋል›› በሚለው ሐረግ ውስጥ ‹‹የፉከራችን›› የግድ ‹ን›ን መውሰድ ይኖርበታል፡፡
በገጽ 22፣ ‹‹ትልቁ የዐማርኛ ሊቅ ደስታ ተክለ ወልድ፣ ኢትዮጵያውያን ለቋንቋቸው ትኵረት እንዲሰጡ በመከሩትን ማነቃቂያ ግጥም እናጠቃልል›› በሚለው ዐረፍተ ነገር ውስጥ ‹በመከሩት› ላይ ‹ን› የገባችው በምን አግባብ ነው? ፈጽሞ ስሕተት ነው፡፡ ደግሞም ‹በመከሩበት› ተብሎ ሊስተካከልም ይገባል፡፡ በሌላ በኩል፣ ግሱን ከተደራጊነት ወደ አድራጊነትና ሳቢነት ቀይረን እንዲኽ ልንጽፈውም እንችላለን፡- ‹… ትኵረት እንዲሰጡ የመከሩበትን ማነቃቂያ ግጥም በመጥቀስ እናጠቃልል›፡፡
በዚኽ ዐይነት የተሠሩ በርካታ ስሕተተቶች በመጽሐፉ ውስጥ ይገኛሉ። ‹ን› እንደምን ባሉ ሰዋስዋዊ ሕጎች ጥቅም ላይ እንደምትውል ለመረዳት የፕሮፌሰር ባየን ጨምሮ በርካታ ሥራዎች በይነ መረብ ላይ ይገኛሉ፡፡ ርግጥ ብዙ ጥናታዊ ሥራዎች የሚገኙት በእንግሊዝኛ ስለኾነ፣ ጥናቱ ኹሌም አይቀልም፡፡ ስለ ቋንቋ መጽሐፍ የሚጽፍ ሰው ግን መሠረታዊ የኾነ ዕውቀት እንዲኖረው ይጠበቃል፡፡
፭. ኢወጥ አጻጻፍ
በአንድ በኩል የሆህያት አጠቃቀማችን ሊስተካከል እንደሚገባ እየወተወቱ፣ በሌላ በኩል ራሳቸው ደራሲው ሆህያቱን ሙሉ ለሙሉ በትክክል አይገለገሉባቸውም፡፡ ደራሲው በቀጥታና በተዘዋዋሪ እንደነገሩን፣ የሆህያት አገባብን በተመለከተ የሚከተሉት ደስታ ተክለ ወልድ ያዘጋጁትን መዝገበ ቃላት ቢኾንም፣ እየመረጡ የሚተዉኣቸው ሆህያት ግን አሉ። ለምሳሌ፣ ‹ኸ›ና ዝርያዋን ሙሉ ለሙሉ አይጠቀሙም፡፡
ለምን ይህን ማድረግ እንደመረጡ ምክንያታቸውን ቢያስረዱን ለመቀበል ወይም ለመሞገት ያስችለኝ ነበር፡፡ ለጊዜው ግን ስሕተትነቱን መናገር እችላለኹ፡፡
ዶ/ር ተስፋዬ፣ ፊደሎቻችንን እንዳሉ ጠብቀን ማቈየት አለብን በማለት በተደጋጋሚ እየሞገቱና ‹ፊደሎቻችን መቀነስ አለባቸው› በማለት የሚከራከሩትን እየነቀፉ ጽፈዋል፡፡ ሙግታቸውን እቀበላለኹ፡፡ ሄደው ሄደው ግን ገጽ 127 ሲደርሱ (ጠላታችኹ ክው ይበል) በድንጋጤ አፌን አስከፈቱኝ፡፡ እየቀፈፈኝም ቢኾን የጻፉት ይህ ነው፡- ‹‹ከዚህ አንጻር የ ‹ኀ› ዝርያ ያላቸው ዋሕደ ድምፅ ፊደላት፣ ጠቀሜታ የላቸውም ማለት ነው (ቢያንስ ይህ መጽሐፍ አይመለከታቸውም)››። ምክንያታቸውን ከፍ ብለው ሲያስቀምጡ፡- ‹‹ኁኍ፣ ኆኈ መካከል ልዩነት ያላቸው ቃላት፣ በጕልኅ ተመዝግበው አላየንም፤ ቢያንስ እኔ አላውቅም፡፡ ይህ ደግሞ በ‹ኈ› ጓዝ አንጻር የምንደክመው አንዳችም ድካም (ምርምር) እንደሌለ አብሣሪ ነው›› ብለዋል። ስለማያውቁት ጕዳይ መጽሐፍ ባይጽፉና እንዳከበርኋቸው ቢቈዩልኝ እመርጥ ነበር፡፡ ‹‹እኔ አላውቅም›› ካሉ ለማወቅ መድከምና ምርምር ማድረግ እንጂ፣ ‹እንኳን ድካም ቀረልኝ፤ የምሥራች› ይባላል? እና፣ እነዚኽን አራት ፊደሎች በሣጥን አኑረው ሲያበቁ በትልቅ ‹X› ይሰርዟቸዋል፡፡
ይበልጥ የገረመኝ ደግሞ፣ በገጽ 52፣ ያንዳንድ ዋሕደ ድምፅ ፊደሎች (እነ‹ጔ›፣ እነ‹ኴ›) ‹‹አስፈላጊነት ምን እንደ ሆነ እኔ አላውቅም›› ካሉ በኋላ፣ ‹‹መኖራቸው ግን ጥሩ ነው፡፡ አስፈላጊ በሆነ ጊዜ እንጠቀምባቸዋለንና፤ እንዲሁም የቋንቋችን የታሪክ ክፍል ስለሆኑ ይዞ መቆየቱ ተገቢ ነው›› በሚል ይደመድማሉ፡፡ በመደምደሚያው ሙሉ ለሙሉ እስማማለኹ። ታዲያ መደምደሚያው እነ‹ኈ›ንም እንደሚመለከት ለዶ/ሩ ማሳሰብ እወዳለኹ፡፡
አለቃ ኪዳነ ወልድም፣ አለቃ ደስታም መዛግብተ ቃላታቸውን ያዘጋጁት የ‹አበገደ›ን ቅደም ተከተል ይዘው ነው። የ‹ሀለሐ›ው ቅደም ተከተል ትክክል አለመኾኑንና ልንጠቀምበት እንደማይገባም በምክንያት ተከራክረዋል፡፡ ዶ/ር ተስፋዬ እነዚኽን ሊቃውንት የሚያከብሩና የሚከተሉ እንደመኾናቸው፣ ለፊደላችንም ተቈርቋሪነታቸውን የሚያሳይ መጽሐፍ እንደማዘጋጀታቸው፣ የ‹አበገደ›ን ቅደም ተከተል እንዲቀበሉ እለምናቸዋለኹ፡፡ ይህን የምለው፣ ወደ ፊት በ‹ሀለሐ› የቃሎችን ቅደም ተከተል አዘጋጅተው ሥራቸውን ሊያቀርቡ በገጽ 94 ቃል ስለሚገቡ ነው፡፡
ፊደሎቻችን ስም አላቸው። ለምሳሌ፣ የ‹በ› ስም ‹ቤት› ነው፡፡ በዕለታዊ ኑሮአችን የፊደሎቹን ስም መጠቀም ስለማያስፈልገን፣ ፊደሎቹን በድምፃቸው እንጂ በስማቸው ባናውቃቸው አያስገርምም። ነገር ግን ድምፃቸው ተመሳሳይ የኾኑትን እነ‹አ›ን፣ እነ‹ሰ›ን ለመለየት ‹አልፋው አ›፣ ‹እሳቱ ሰ› ወዘተ እያልን እንጠቅሳቸዋለን። እንደ እውነቱ ግን እነዚኽ ስሞች ልማዳዊ እንጂ ትክክለኛ አለመኾናቸውን ከኹለቱ ታላላቅ መዛግብተ ቃላት መረዳት ይቻላል፡፡ ስለዚኽ ምሁራዊ የኾኑ ሥራዎች ልማዳዊውን ባይከተሉ መልካም ይመስለኛል። ደራሲው ልማዳዊውን ለመከተል ምክንያት ካላቸው ደግሞ ያቅርቡልንና እንሞግተው፡፡
አንዳንዴ ‹‹መካከል››፣ ሌላ ጊዜ ‹‹መኻል›› እያሉ ይጽፋሉ፡፡ ምናልባት በተለያየ ዐውድ ውሱን ትርጕም አስይዘዋቸው ይኾናል ብዬ ዐስቤ ነበር፤ ግን ልማዳዊ ስሕተት መሰለኝ።
፮. ግምታዊ አጻጻፍ
በጥናትና በምክንያት የተደገፈ ሥራ የሚያቀርብ ምሁር የ‹ይመስለኛል›ን አጻጻፍ እንደ ኮሮና ሊሸሽ ይገባል፡፡ የግል አስተያየት እንኳ ከግል ስሜት የጸዳና በእጅ ላይ ካሉ መረጃዎች የሚነሣ መኾን ይኖርበታል። መጽሐፍን ያኽል ነገር ሲያዘጋጁ በፌስ ቡክ ከሚጽፉበት መንገድ ሊለዩት ይገባል። ርግጥ፣ በዚኽ ረገድ ያገኘኹት ችግር ጥቂት ቢኾንም፣ ከጸሓፊው ትልቅ ማንነት አንጻር በቀላሉ የማልፈው አልኾነም፡፡
በገጽ 5፣ ‹‹‹እኔ በግሌ ሞክሼ ሆህያትን መጠበቅ ለምን አስፈለገ?› እንዲሁም ‹ሞክሼ ሆህያትንና ዋሕደ ድምፅ ፊደላትን ጠብቆ መጻፍ እንዴት ይቻላል?› በሚለው ጕዳይ ላይ የተጻፈ መጽሐፍ አላየሁም›› ይላሉ፡፡ ለምን አላዩኣቸውም? አርእስታቸው እንዲኽ እሳቸው እንደፈለጉት ቃል በቃል ባይገጥሙም ጥቂት ሥራዎች አሉ፡፡ ደግሞም፣ በመጽሐፍ ብቻ ሳይኾን በጆርናል መጣጥፎች ውስጥ፣ በኹለተኛና ሦስተኛ ዲግሪ ማሟያ ጽሑፎች (ዲማጾች) ውስጥ፣ በታተሙና በበይነ መረብ በተሠራጩ መጽሔቶች ውስጥ፣ በየመዝገበ ቃላቱ መቅድም ውስጥ ጭብጡን የተመለከቱ ክርክሮች ሲጻፉ ኖረዋል፤ በሌሎች ቋንቋዎች ጭምር፡፡ ፈለግ-ፈለግ ቢያደርጉ ያገኟቸው ነበር፡፡ ከ‹‹ዋቢ መጻሕፍት›› ዝርዝራቸው እንደተረዳኹት በቂ መረጃ አልሰበሰቡም፡፡
በገጽ 39፣ ‹‹በዚህ ረገድ የሰማሁት አንድ ታሪክ አለ›› ብለው ያልተረጋገጠ ታሪክ ይነግሩናል፡፡ ለተነሡበት የክርክር አሳብ ታሪኩ ማለፊያ ምሳሌነት ቢኖረውም፣ አንደኛ፣ በሕይወት የነበሩ ሰዎችን ስለሚጠቅስ ያልተረጋገጠን ነገር በሰዎቹ ስም ማሠራጨት ትክክል አይደለም። ኹለተኛ፣ ታሪኩ ሃይማኖታዊ በመኾኑ በእውነት ላይ ያልተመሠረተ ታሪክ በመጥቀስ የሃይማኖቱን ተከታዮች መጐሻሸም አስፈላጊነቱ አይታየኝም፡፡
በገጽ 53፣ ስለ ‹ኰ›ና ‹ኮ›፣ ስለ ‹ጎ›ና ‹ጐ›… ሲገልጹ፣ ‹‹እነዚህ ሆህያት አንዱ ከሌላው ጋር ያላቸው ድምፀት አንድ ይሁን እንጂ፣ ግልጋሎታቸው ፍጹም ለየቅል ነው›› ይላሉ፡፡ ድምፀታቸው አንድ መኾኑን ማነው የነገራቸው? ግምታቸውን ነው የሚጽፉልን? በእውነቱ ደፋር ናቸው! ስንት ሊቅ በሞላበት አገር የፊደሎቹን የድምፅ ልዩነት የሚያሳውቃቸው አጡ! እንደለመዱት ‹‹እኔ አላውቅም›› ቢሉ ይሻል ነበር¡ ጨዋው ሕዝብ ባለማወቅ፣ ልሂቆቹም በግዴለሽነት ስላመሳሰሏቸው እንጂ ፊደሎቹስ ግልጽ የድምፅ ልዩነት አላቸው፡፡
፯. አላስፈላጊ ሐተታ
በከፍተኛ ትምህርትና በብዙ መጽሐፎች ደራሲነት በርካታ ዓመቶችን ያሳለፉት ዶ/ር ተስፋዬ በቅጡ እንደሚረዱት፣ ልንጽፍ ከተነሣንበት ጭብጥ ጋር ቀጥተኛ ዝምድና የሌላቸውን ሐተታዎች ማስገባት አንባቢን ከማምታታትና እንዲከተሉልን ከምንፈልገው መስመር ከማውጣት ውጪ ጥቅም የላቸውም። ነቅሼ ላሳይ፡፡
ከገጽ 7-13 ስለ ትሕትና አስፈላጊነት የቀረበው ሐተታ ራሱን ችሎና ተፍታቶ ጥሩ መጣጥፍ ይወጣዋል፡፡ ለዚኽ መጽሐፍ ጭብጥ ግን ግንጥል ጌጥ ነው የኾነው፡፡ ደራሲው የነገረ መለኮት ተማሪ በመኾናቸው ሲጽፉ አንዳንዴ ወደዚያ ሳብ ያደርጋቸዋል። በመግቢያቸው እንደገለጹልንም ይህ ሥራ መጽሐፍ ከመኾኑ በፊት ለማስተማሪያነት (ለሥልጠና) የተዘጋጀ ጽሑፍ ነበር፡፡ የተወሰኑ ተሳታፊዎች በተገኙበት ለሚቀርብ ትምህርት በሚዘጋጅ ጽሑፍና ለሰፊው ሕዝብ ታትሞ በሚቀርብ መጽሐፍ መኻል ግን የዝግጅት ልዩነት ሊኖር እንደሚገባ እሙን ነው፡፡
በዚኽ አላስፈላጊ ሐተታ ውስጥ ከቀረቡት አሳቦች አንዱ፣ ቀደምት ጸሓፊዎች ‹‹ነገሥታትን መለኮት ቀመስ አድር[ጎ] የማቅረብ፣ ሰንካላ አካሄድ ነበራቸው›› የሚል ነው፡፡ ለዚኽም ማስረጃ እንዲኾናቸው ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ ስለ ኃይለ ሥላሴ የጻፉትን ጠቅሰዋል (ገጽ 8-9)፡፡ እንዲኽ ይላል፡- ‹‹‹ሰው ያላንድ ነውር አይፈጠርም፤ የዐፄ ኀይለ ሥላሴ ነውራቸው ሰው ከመሆናቸው በቀር፣ ሌላ ነውር አላገኘንባቸውም፡፡›››
የሐተታው አላስፈላጊነት ሳያንስ፣ የቀኝ ጌታን ገለጻ ርካሽ መወድስ አስመስለው ማቅረባቸው ትርጕሙን እንዳልተረዱት ያሳያል፡፡ በሥነ አመክንዮ ትምህርት ውስጥ እጅግ የተለመደ የአመክንዮ ምሳሌ ላንሣ፡፡ ሰው ሟች ነው፤ ናይእግዚ ሰው ነው፤ ስለዚኽ ናይእግዚ ሟች ነው፡፡ የመጀመሪያዎቹ ኹለት ዐረፍተ ነገሮች እውነት ከኾኑ፣ መደምደሚያውም እውነት ይኾናል፡፡ በዚኽ አካሄድ የቀኝ ጌታ ዮፍታሔን ገለጻ እንየው። ሰው ሲፈጠር ነውር አለበት፤ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ሰው ናቸው፡፡ እነዚኽ ኹለት ዐረፍተ ነገሮች እውነት ከኾኑ፣ እንዲኽ የሚል መደምደሚያ ወደ አእምሯችን ይመጣል፡- ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ነውር አለባቸው፡፡
አወድሶ ‹‹መስደብ››፣ ገድሎ ማዳን በቅኔያዊ ገለጻዎች የተለመደና ነገሥታቱና መኳንንቱም ‹እንዴት ተነካኹ!› ብለው የማይቈጡበት የተመሰገነ ችሎታ ነው። ስለዚኽ፣ ዶ/ሩ እንደመሰላቸው ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ዐፄውን ከመለኮት ለማጠጋጋት ያቀረቡት ርካሽ መወድስ አይደለም፡፡
ይባስ ብሎ ደግሞ፣ ዘለግ ያለ በግሪክ ቋንቋ ላይ የተመሠረተ የቃል ትንታኔ ቀርቦልናል። ያለቦታው ኾነ እንጂ ትምህርቱስ ደግ ነበር፡፡ ቀኝ ጌታ ባቀረቡት የተጋነነ ገለጻ መደነቃቸውን ለማሳየት ዶ/ር ተስፋዬ ‹‹ክራላይዞ!›› ይላሉ። ከዚያ በግርጌ ማስታወሻ ስለ ግሪኩ ቃል ስለ ‹ክራላይዞ› እጅግ ሲበዛ ሙያዊ የኾነ ማብራሪያ ያቀርባሉ፡፡ ማብራሪያው ራሱ ማብራሪያ ታክሎበት በጣም ጠቃሚ የኾነ መጣጥፍ ይወጣዋል፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስና የግሪክኛ ሰዋስው ዕውቀታቸውን ጥልቀት ቢያስረዳኝም፣ ለመጽሐፉ ጭብጥ አስተዋጽኦ የለውም፡፡
የኔም ሐተታ በዛ መሰለኝ፡፡ ይልቅ፣ እግረ መንገዴን ግሪኩን በተመለከተ አንድ ነጥብ ላንሣ፡፡ የግሪኩን አነባበብ ሲጽፉልን መጀመሪያ ‹‹ኪሬዬ››፣ በቀጣዩ መስመር ደግሞ ‹‹ኩሪ›› ብለዋል፡፡ ትክክሉ የትኛው ነው? ለነገሩ፣ ኹለቱም ትክክል አይደሉም፤ ባለኝ መረጃ ትክክለኛ ንባቡ ‹ኪሪየ› ነው። ‹ለማንኛውም› ብዬ የሥራ ባልደረባዬ የኾኑ ግሪካዊ ወዳጄን ስለ ቃሉ አነባበብ ጠይቄአቸዋለኹ፡፡ ስለ ቋንቋቸውና አገራቸው ለዓለም ስላበረከተችው አስተዋጽኦ ተናግረው የማይጠግቡት ባልደረባዬ፣ ዐይናቸው በደስታ ቦግ ብሎ፣ በግሪክኛ በአምስት መንገድ የ‹ኢ› ድምፅ መፍጠር እንደሚቻል በተሰባበረ ጀርመንኛቸው ካስረዱኝ በኋላ ንባቡ ‹ኪሪየ› መኾኑን አረጋግጠውልኛል፡፡ ዶ/ር ተስፋዬን አመሰግናለኹ!
በመጽሐፉ የቃሎች ሰንጠረዦችን የያዙ በርካታ ገጾች ይገኛሉ፡፡ ቃሎቹ የተዘረዘሩት ምሳሌ እንዲኾኑ ነው። ሞክሼ ሆህያት በትክክለኛ ስፍራቸው ካልተቀመጡ ትርጕም እንደሚለውጡ ለማሳየት አንድ ኹለት ገጽ በቂ ነው ብዬ እሞግታለኹ፡፡ ኻያ ሰባት ገጽ ሙሉ (ከ64-90) ከመዛግብተ ቃላት ቀጥታ የተገለበጡ ቃሎችን መዘርዘር አስፈላጊ አይደለም። የደራሲውን ሙግት ላለመቀበል የወሰነ ሰው መዛግብተ ቃላቱ ራሳቸው ቢሰጡትም ሰበብ መፈለጉ አይቀርም፡፡ በዕለታዊ ንግግር በብዛት የምንገለገልባቸውን የተወሰኑ ቃሎች መርጦና የፊደል መጠናቸውንም ከሌላው ጽሑፍ የፊደል መጠን አነስ አድርጎ ለማሳያነት ማቅረብ በቂ ነው፡፡
ከዚያ ደግሞ በያንዳንዱ ሞክሼ ሆሄ የሚጀምሩ ቃሎችን ዝርዝር ከገጽ 95-122 ያቀርቡልናል፤ 28 ገጾች፡፡ በዋሕደ ድምፅ የሚጀምሩ ቃሎች ዝርዝር ከገጽ 128-147ና ከግእዝ የተወሰዱ የዐማርኛ ቃሎች ዝርዝር ከገጽ 187-199 ቀርበዋል፡፡ በሌሎች አርእስት ሥር ለምሳሌነት የቀረቡት ቃሎች ግን ያልተንዛዙ በመኾናቸው የ‹ምሳሌነት› አገልግሎታቸውን በጥሩ ተወጥተዋል። የመጽሐፉ 40% ገደማ ገጾች የተሞሉት ከመዛግብተ ቃላት ቀጥታ በተገለበጡ ቃሎች ነው ማለት ነው፡፡
 ፰. መሠረታዊ ቃሎችን አለመተርጐም
የምርምር ሥራ ሲቀርብ፣ የዋና ዋና ቃሎቹ ትርጓሜዎች እንዲሰጡ የሚጠበቅ ነው። የዚኽ መጽሐፍ ማጠንጠኛ የዐማርኛ ሆህያት ናቸው፡፡ ‹ሆሄ› ምን ማለት እንደኾነ፣ የቃሉ የትመጤነት፣ ከአንድ በላይ ትርጕም አለው እንደኾን ወዘተ ሊመለስ ይገባ ነበር። ቃሉን አለመተርጐም ብቻ ሳይኾን፣ ‹ፊደል› ከሚለው ቃል ጋርም በማለዋወጥ ይጠቀሙበታል። ኹለቱ ቃሎች ትርጓሜያቸው አንድ ነው? ከተለያዩ መዛግብተ ቃላት ጋር አመሳክረው ተዛምዷቸውን ቢያሳውቁን ደግ ነበር። ደግሞም፣ ‹ኅርመት› የሚባል ከፊደል ጋር የተገናኘ ሌላም ቃል መኖሩን ዐውቃለኹ፤ ምናልባት በመጽሐፉ ውስጥ ግልጋሎት ሊሰጥ ይችል ይኾን?
በመጽሐፉ አርእስት ውስጥ ‹‹ጥበብ›› የሚል ቃል ተጠቅመዋል፡፡ በየትኛው ትርጓሜው ከሆሄ ጋር ተያይዞ እንደቀረበ ማብራሪያ ቢቀርብበት መልካም ነበር፡፡ ምንም እንኳ ከዐውዱ መገንዘብ ቢቻልም፣ አንባቢን ለራሱ ግምት ባይተዉት መልካም ይመስለኛል። መጽሐፉ የፈጠራ ሥራ (እንደ ልብ ወለድ ያለ) ባለመኾኑ፣ ‹በአርእስቱ ምን ለማለት እንደፈለግኹ አንባቢያን ይድረሱበት› ማለት አስፈላጊ አይደለም፡፡
ይህ ነጥብ ምናልባት እንደ ትልቅ ስሕተት ላይመዘገብ ይችላል፡፡ መጽሐፉ የተጻፈው ለዐማርኛ አንባቢዎች ነው፡፡ አልፎ አልፎ በሌሎች ቋንቋዎች ከታተሙ ሥራዎች መጥቀስ አስፈላጊ ሊኾን ይችላል፤ ይኹንና፣ መተርጐም ወይም ማብራራት ያስፈልጋል፡፡ እንደ ‹ጆርናል› ባሉ ከፍ ያሉ ምሁራዊ ሥራዎች፣ ግልጋሎት ላይ የዋለን ምንጭ ሳይተረጕሙ እንዳለ ማስቀመጥ የተለመደ ቢኾንም፣ ‹ፋሽኑ› እያለፈበት የመጣ ይመስለኛል፡፡ እንዲኽ ለሕዝብ የሚጻፍ መጽሐፍ ግን ‹ርኅሩኅ› ሊኾንና ወደ ዐማርኛ ሊመልስልን ይገባል፡፡ ደራሲው፣ በግሪክኛ፣ በእንግሊዝኛና በግእዝ ይጠቅሳሉ። አብዛኛው አንባቢ እንግሊዝኛ ይረዳል ቢባል እንኳ፣ ለምሳሌ፣ በገጽ 31፣ የግርጌ ማስታወሻ 9 የተቀመጠው ዐረፍተ ነገር ሙያ-ነክ በመኾኑ በቀላሉ የማይተረጐምልን ብዙ ነን።
፱. የግርጌ ማስታወሻ
ገጽ 12፣ የግርጌ ማስታወሻ 15 ‹‹አንድ ኢትዮጵያዊ ምሁር በአንድ ወቅት›› ለተናገሩት ማጣቀሻ የተቀመጠ ነው። ይኹንና ስማቸው ብቻ ‹‹ዶ/ር መለሰ ወጉ›› ተብሎ ተቀምጧል። ዶ/ር መለሰ እኔ ሳልወለድ ጀምሮ ብዙ ነገር ተናግረዋል፤ በርካታ መጽሐፎችም አሳትመዋል። ስለዚኽ፣ ከተጠቀሱ አይቀር ያን የተናገሩበት ምንጭ በወጉና በሥርዐቱ ሊጠቀስ ይገባ ነበር፡፡
በገጽ 17፣ አራት የግርጌ ማጣቀሻዎች ይገኛሉ (ከ21-24)፤ አራቱም ጐደሎ ናቸው፡፡
በገጽ 17፣ 21ኛው የግርጌ ማጣቀሻ የመጽሐፉን ስምና ገጽ ብቻ የያዘ ነው፡፡ በግርጌ ማስታወሻ አጠቃቀስ ሕግ፣ አንድ መጽሐፍ (ወይም ሌላ ምንጭ) ለመጀመሪያ ጊዜ ሲጠቀስ ሙሉው መረጃ ይቀመጣል፡፡ ማለትም የደራሲው ሙሉ ስም፣ የመጽሐፉ ሙሉ ስም፣ አሳታሚው፣ የታተመበት ከተማ፣ የታተመበት ዓመትና የተጠቀሰው የገጽ ቊጥር፡፡ እነዚኽ ዋናዎቹ ሲኾኑ፣ ተርጓሚ ካለው፣ ከአንድ በላይ ደራሲ ካለው፣ ቅጽ ካለው ወዘተ እነዚኸም መረጃዎች ይካተታሉ፡፡ መጽሐፉ በድጋሚ ሲጠቀስ ግን መረጃዎቹ በሙሉ አይደገሙም፤ ይልቁን የደራሲው የመጀመሪያ ስም ብቻ፣ የመጽሐፉ ስም ማጠር ከቻለ አጥሮና የገጽ ቊጥር ተካትቶ ይጠቀሳል፡፡ መጽሐፉ በተከታታይ ሲጠቀስ ደግሞ ‹‹ዝኒ ከማሁ›› ተብሎ ከገጽ ቊጥር ጋር ይቀመጣል፡፡ ዶ/ር ተስፋዬ ይህንን የአጠቃቀስ ሕግ በሚገባ እንደሚያውቁት ብረዳም፣ ትንንሽ የሚመስሉ ስሕተቶች ሲጠራቀሙ ማወካቸው አይቀርም፡፡
በግርጌ ማስታወሻ፣ የመጽሐፍ ስም በኹለት መንገድ ሊቀመጥ ይችላል። ሀ. ፊደሉን ዘመም በማድረግ፤ ለ. በትእምርተ ጥቅስ ውስጥ በማስገባት፡፡ አንዱን ከአንዱ የሚመርጡ ሕጎች አሉ፡፡ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች፣ አሳታሚዎችና ሌሎች ተቋማት የየራሳቸው ምርጫ አላቸው። ዋናው ነገር አንዱን የአጠቃቀስ ሕግ ከመረጡ በኋላ በወጥነት ያንኑ መከተል ነው፡፡ ይህ መጽሐፍ ግን ሥርዐቱን ይደባልቃል። ለምሳሌ፣ በገጽ 19፣ 28ኛውና በገጽ 29፣ 5ኛው የግርጌ ማስታወሻዎች ትእምርተ ጥቅስ ይጠቀማሉ፡፡
የደራሲ ስምና የኅትመት ዓመት ላይ ‹ከ› ወይም ‹በ› የመሳሰሉ መስተዋድዶች መጨመር አያስፈልግም (ለምሳሌ፣ ገጽ 33፣ የግርጌ ማስታወሻ 11፤ ገጽ 37፣ የግርጌ ማስታወሻ 18)፡፡
አንዳንድ ጊዜ የተጠቃሹ መጽሐፍ ሙሉ መረጃ ላይገኝ ይችላል፡፡ ለምሳሌ፣ በዐማርኛ መጽሐፎች አሳታሚን መግለጽ እየቀረ መጥቷል፡፡ በዚኽ ጊዜ ‹አሳታሚ ያልተጠቀሰ› ብሎ መጻፍ ያስፈልጋል። በገጽ 33፣ የግርጌ ማስታወሻ 11 አሳታሚ ያልተጠቀሰው ተረስቶ ነው ወይስ ስላልተገለጸ?
መጽሐፍ የታተመበት ሥፍራ ሲጠቀስ፣ መጀመሪያ የከተማ፣ ቀጥሎ የግዛት (የክልል)፣ ቀጥሎ የአገር ስም ይቀመጣል። በገጽ 33፣ የግርጌ ማስታወሻ 11 ስሕተት ነው። በመሠረቱ፣ የከተማው ስም በቂ ነው፤ አልፎ አልፎ ከተማው ካልታወቀ፣ ወይም ተመሳሳይ ስም ካለው ሌላ ከተማ ለመለየት ነው የግዛት (የአገር) ስም ማካተት የሚያስፈልገው፡፡
፲. ሥርዐተ ነጥብ
በአጠቃላይ ሲገመገም፣ የሥርዐተ ነጥብ ሕጎችንና መርሖችን ለመጠበቅ ያደረጉት ጥረት የሚመሰገን ነው፡፡ በርግጥ፣ አንድ ደራሲ የሚጠበቅበትን ስላደረገ ምስጋና ባያስፈልገውም፣ የዘመኑን የኅትመት ውጤቶች ዝርክርክ የሥርዐተ ነጥብ አጠባበቅ ስመለከት ዶ/ር ተስፋዬ የሰጡትን ትኵረት አደንቃለኹ፡፡ ይኹንና፣ ከዚኽም በላይ ለፍጽምና የቀረበ ሥራ እንዲያቀርቡ አንድ ኹለት ነጥቦች ላንሣ።
በኹለተኛው ምዕራፍ፣ በ‹‹ሥርዐተ ትእምርት›› ንዑስ አርእስት ሥር የዘረዘሯቸው ሥርዐተ ነጥቦች እጅግ ቊንጽል ናቸው፡፡ ራሳቸው በመጽሐፉ ውስጥ ተጠቅመውባቸው ሳለ፣ በዝርዝሩ ውስጥ ግን ያላካተቷቸው ነጥቦችም አሉ። ስለ ሥርዐተ ነጥቦቹ የሰጧቸው ትንታኔዎችም ጕምድምድ ያሉ ናቸው፡፡ ስለ ነጠላ ሰረዝ የጻፉት ይሻላል፤ ዐሥር ነጥቦች አስቀምጠዋል፡፡ የነጠላ ሰረዝ ጥቅም ግን ከዚያም በብዙ ያልፋል፡፡
በውስጥ ሽፋኑ ኹለተኛ ገጽ (በ‹ምግላጹ›፡- ማለትም፣ ስለ መጽሐፉና ስለ ቅጂ መብቱ በሚገለጽበት ገጽ)፣ ሰረዞችን የተጠቀሙት በየትኛው የሰረዝ ሕግ ነው? ስለ ሰረዝ አገልግሎት ሦስት ነጥቦች በገጽ 165 አስፍረዋል፡፡ ከሦስቱ ግን አንዳቸውም በምግላጹ ያለውን አገልግሎት አይጠቅሱም። ለምሳሌ፣ ‹‹ጸሓፊ— ዶክተር ተስፋዬ ሮበሌ›› በሚለው ውስጥ የሰረዟ አገልግሎት ምንድነው? ሳይገባኝ ቀርቶ አይደለም። ግን እዚኽ ስለምትሰጠው አገልግሎት በገጽ 165 አልሠፈረም፡፡ በመሠረቱ፣ ጥቅም ላይ ሊውል የሚገባው ‹‹ጭረት ወሰረዝ (፡-)›› ብለው የጠሩት ትእምርት ነው ብዬ እሞግታለኹ፡፡
ደግሞ፣ ሲፈልጉ ከሰረዟ በኋላ ክፍት ቦታ ይተዋሉ፣ ሲፈልጉ አጠጋግተው ይጽፋሉ። ሲሻቸው ዐጪር ሰረዝ፣ ሲሻቸው ረጅሙን ይጠቀማሉ። ኹለቱ ባጠቃቀም የተለያዩ መኾናቸውን ያማያውቁ ይመስለኝና መልሰው ደግሞ ረጅሙን በተገቢው ስፍራ ሲጠቀሙበት አገኛቸዋለኹ፡፡ ወጥነት ቢኖራቸው ኖሮ እዚኽ ኹሉ ሐተታ ውስጥ ባልገባኹም ነበር፡፡
በመጽሐፉ ካልተዘረዘሩት ሥርዐተ ነጥቦች አንዷ ሰባራ (ታጣፊ፣ ወይም ማዕዘን) ቅንፍ  ([ ]) ነች፡፡ ይኹንና ግን ደራሲው በመጽሐፋቸው ግልጋሎት ላይ አውለዋታል — ምንም እንኳ በተሳሳተ መንገድም ቢኾን! በገጽ 5፣ 7ኛ የግርጌ ማስታወሻ፣ ‹‹የፕሮፌሰር አምሳሉ አክሊሉ፤ የአማርኛን መክሼ ሆ[ሄ]ያት ጠንቅቆ ያለመጻፍ ችግርና መፍትሔው›› በማለት ጠቅሰዋል፡፡
መጽሐፉ በትክክል ሲጠቀስ፡- አምሳሉ አክሊሉ፤ የአማርኛን ሞክሼ ሆሄያት ጠንቅቆ ያለመጻፍ ችግርና መፍትሔ ተብሎ ነው። በግርጌ ማስታወሻ መጽሐፍ ሲጠቀስ እንደ ‹ፕሮፌሰር›ና ‹ዶክተር› ያሉ የማዕርግ ስሞች አስፈላጊ አይደሉም። ይኹንና፣ በዚኽ የግርጌ ማስታወሻ መጽሐፉ የተጠቀሰው በማብራሪያ ሐተታ ውስጥ በመኾኑ፣ የማዕርግ ስማቸው መኖሩ ስሕተት አይደለም፡፡ ‹‹መክሼ›› በ‹ሞክሼ›፣ ‹‹መፍትሔው›› በ‹መፍትሔ› መስተካከል ይኖርባቸዋል፡፡
ዶ/ር ተስፋዬ፣ ‹‹ሆሄያት›› የሚለው ቃል መሳሳቱን አይተዋል፤ ‹ሆሄ› በብዙ ቊጥር ሲጻፍ ‹ሆህያት› ስለኾነ፡፡ ለዚኽም ነው ‹ሄ›ን በታጣፊ ቅንፍ ያኖሯት፡፡ በጥቅስ ውስጥ የታጣፊ ቅንፍ አገልግሎት፣ ደራሲው በጥቅሱ ውስጥ ፊደሉን ወይም ቃሉን መቀየሩን፣ ወይም በጥቅሱ ውስጥ መጨመሩን ማሳየት ነው፡፡ ለምሳሌ፣ ዶ/ር ተስፋዬ ‹ሆ[ህ]ያት ብለው ቢጠቅሱ ኖሮ ልክ በኾኑ ነበር። አንዳንድ ጊዜ በሚጠቀሰው ምንባብ ውስጥ ስሕተት ይኖራል፡፡ የአጠቃቀስ ሕግ ግን ስሕተቱን እንድናርም መብት አይሰጠንም። ይኹንና፣ በታጣፊ ቅንፍ ውስጥ እርማቱን ማኖር (ወይም ሊጨመር የተገባውን መጨመር፣ ወይም መጠነኛ ማብራሪያ ማቅረብ) ይፈቀዳል፡፡ በእንግሊዝኛ ጽሑፎች ውስጥ፣ ጥቅሱ ከነስሕተቱ መጠቀሱን ለማሳየት ‹[sic]› ብሎ ማስቀመጥም ሌላው ያለ አሠራር ነው፡፡ እና፣ ዶ/ሩ ታጣፊ ቅንፍ መጠቀም እንደሚችሉ ገብቷቸዋል፤ አጠቃቀሙን ግን ስተዋል፡፡ በኔ እምነት ግን ቸኵለው ወይም ተያቢ የፈጸመውን ስሕተት ሳያዩ ቀርተው ነው። ምክንያቱም፣ ይህ አሠራር በከፍተኛ የትምህርት ተቋሞችና በምርምር ሥራ ኅትመቶች እጅግ የተለመደ ከመኾኑና፣ ርሳቸውም ለበርካታ ዓመታት በዚኹ ያለፉ ከመኾናቸው የተነሣ ይህን ያጡታል ብዬ ስለማላስብ ነው፡፡
ጥቃቅን ነጥቦች
በገጽ [፭]፣ ‹‹ረቂቁን አንብበው […] አስተያየታቸውን ለሚቸሩኝ›› በሚለው ሐረግ ውስጥ፣ ‹‹ለሚቸሩኝ›› ‹ለቸሩኝ› በሚለው ይስተካከል።
በገጽ [፮]፣ ‹‹‹የመጽሐፉን ሽፋን እኔ አዘጋጅልሃለሁ› ብሎ በሁለት ቀን ውስጥ ይህን ውብ ሽፋን ይዞ ከተፍ ያለው፣ ሠዓሊ ተስፋዬ ንጉሤ ነው›› ብለው ካመሰገኗቸው በኋላ፣ በቀጣዩ አንቀጽ፣ ‹‹የመጻሕፎቼን ሽፋን ሁሌም ውብ አድርጎ የሚያዘጋጀው ወንድም ሐዋርያው ጴጥሮስ ነው›› ይላሉ፡፡ በቀጥታ ግን ስለማያመሰግኗቸው በዚኽ ሥራ ተሳታፊ አይመስሉም፡፡ እና ማነው የዚኽን መጽሐፍ ሽፋን ያዘጋጀላቸው? ይህን ጕዳይ በኹለት መንገድ ለመረዳት ሞክሬአለኹ። አንደኛ፣ ‹ምንም እንኳ ለዘወትሩ ወንድም ሐዋርያው የመጽሐፎቼን የሽፋን ገጽ ቢያዘጋጅም፣ ላኹኑ ሠዓሊ ተስፋዬ ነው ያዘጋጀው፡፡ ጠይቄው ኖሮ ቢኾን ግን ሐዋርያው ለዚኽኛውም ያዘጋጅልኝ ነበር› ማለታቸው ነው። ኹለተኛ፣ የሽፋን ገጽ ማዘጋጀትና ለሽፋን ገጹ ግብኣት የሚኾነውን ሥዕል መሣል ኹለት የተለያዩ ችሎታዎች በመኾናቸው፣ ሠዓሊው ያቀረቡትን ሥዕል በመጠቀምና ሌሎች መረጃዎችን፣ ማለትም፡- አርእስቱን፣ የደራሲውን ስምና አሳታሚውን በማካተት፣ እንዲኹም፣ የፊደሎቹን ቅርፅ፣ ቀለምና አቀማመጥ በመወሰን፣ ደግሞም፣ ሥዕሉ በቢጋር (በፍሬም) ተቀንብቦ ሳይኾን፣ ገጹን ሞልቶና ተርፎ እንዲቀመጥ በመወሰን ገጹን ያቀናበሩት ወንድም ሐዋርያው ናቸው› ማለታቸው ነው፡፡ (ግራ ገባኝ እኮ!)
በገጽ 18፣ ‹‹ተማሪዎችን በዲግሪ፣ በማስትሬት ዲግሪ፣ በዶክትሬት ዲግሪ›› በሚለው ሐረግ ውስጥ ‹ተማሪዎችን በመጀመሪያ ዲግሪ› በሚል ይስተካከል፡፡ በተለምዶ ‹ዲግሪ› ስንል ‹የመጀመሪያ ዲግሪ› ማለታችን መኾኑ ቢታወቅም፣ ይህ ምሁራዊ መጽሐፍ ነው፡፡
በገጽ 20፣ ግእዝን የዐማርኛ ‹‹ሴማዊ ጐረቤት›› አድርገው ጽፈዋል። ኹለቱን ቋንቋዎች ጐረቤታሞች ናቸው ማለት በቋንቋዎቹ ጥናት ተቀባይነት ያለው አገላለጽ አልመሰለኝም። ታሪካዊ ግንኙነታቸው ከጐረቤታም ይልቅ ‹ዘመዳም› የሚያደርጋቸው ይመስለኛል፡፡ ‹እያካበድኹ› ይኾንን?
በገጽ 39፣ ‹‹ቅኔ እንድንዘርፍ ዘንድ›› የሚለው ሐረግ ‹ቅኔ እንድንዘርፍ› ወይም ‹ቅኔ እንዘርፍ ዘንድ› በሚል ይስተካከል፡፡
የምልከታዬ ማጠቃለያ
መጽሐፉ፣ ደራሲው እንዳለሙት፣ ከጽሑፍ ጋር የተያያዘ ሥራ ለሚከውኑ ጠቃሚና አንቂ መኾኑን እመሰክራለኹ። በዐማርኛ እንከን አልባ ኅትመት ለማየት (ብዙም) ባንታደልም፣ አንዳንዶች የሚያደርጉት ትግል ቀስ እያለ ለፍሬ እንደሚበቃ ተስፋ አደርጋለኹ፡፡ ስለዚኽ፣ መጽሐፉን ገዝታችኹ እንድትጠቀሙበት ከልቤ እመክራለኹ፡፡ እኔም በተለያየ መንገድ ለመግዛት ሞክሬ ሲያቅተኝ አሜሪካ ለሚኖር ወዳጄ፣ ፍስሐጽዮን ፋንታሁን፣ ‹‹አቤት›› ብዬ ገዝቶ ያለኹበት አገር ድረስ በብላሽ ስለሰደደልኝ አድናቆቴ ይድረሰው። ዶ/ር ተስፋዬም ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋናዬ ይድረሳቸው፤ አምላካችን ዕድሜና ጤና ሰጥቶም ለሌላ ሥራ እንዲያበቃቸው ምኞቴ ነው፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢሜይል አድራሻው፡ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 2258 times
Administrator

Latest from Administrator