Saturday, 28 May 2022 15:19

ሥዩምን በ"ሦስቱ እንባዎች"

Written by  ገብረ ክርስቶስ ለማ
Rate this item
(0 votes)

   "--ሌላው ሰው ከራሱ ጋር የግል ሱባዔ ሲይዝ በዓለም የፍረጃ መዝገብ እብደት ተደርጎ መመዝገቡ አይቀሬ ነው፡፡ ነገር ግን ሰው ከራሱ ወዲያ መካሪ፣ ከራሱም በቀር ተመካሪ የለውምና ራሱን ይዞ ሱባዔ የገባ ዕለት፣ በእለቱ በምትወጣው ፀሐይ ላይ ሳይቀር ሙቀት የመጨመር ስልጣን ያገኛል፡፡--"
                  ገብረ ክርስቶስ ለማ


            እያነሱ ይበሉት ዘንዳ ምግብ ከጠረጴዛ ተሰጣ፡፡ እድምተኛም፣ ሆድምተኛም ጠቢብ አይዶል፤ ከየአይነቱ፣ እንደየፍላጎቱ መሳ፡፡ ስዩምም በድንኳኑ ከሺህ ዘጠኝ መቶ ሰባዎቹ ጀምሮ ግብር ሲያበላ፤ ከእድምተኛም እጅ ሲጎርስ እነሆ ከአሁን ደረሰ፡፡ የጎረሰው ቢያበረታው፤ አሜን ያለው ምርቃቱ አቅም ቢሆነው፤ እነሆ እያነሱ ይዘፍኑት ዘንዳ፣ እያነሱም ያዜሙት ዘንዳ ግጥም ስዩም ድንኳን ተሰጣ፡፡ ብሎም የግብሩ ዝግጅት ከፍታ በትዕግስት ለተጠባበቁት የደጋሹ ወዳጆች፣ ከመልካሙ ወይን ግብዣ ሊያደርግ፣ እነሆ እያነሱ ይፈጥሩት ብሎም እያነሱ ይኖሩት ዘንዳ የጥንቱ የተውኔት ወይን ከስዩም ግብር ታየ፡፡
ሥዩም ተፈራ ገጣሚ፣ ተዋናይ፣ የመድረክ አዘጋጅ፣ የተውኔት ጸሐፊና አዘጋጅ፡፡ ገጣሚነቱን በ#ሦስቱ እንባዎች; መጽሐፉና ለማቱሳላ ዕድሜ ቁጥሮች በጎደሉት በወረቀት ህትመት ባልተያዙ በሳል ግጥሞቹ መገንዘብ እንችላለን፡፡
ሥዩም እንዲህ ይላል፤ ‹‹ትንሽ የመንደር ውስጥ ጠጠር እንጂ፣ ተራራ አያነቅፍም››
ግጥሞቹ ሩቅ አይደሉም፡፡ ስለ ህዋ ከመመርመርና በዚያም ውስጥ የህላዌን ስልተ-መገለጥ ከማብሰልሰል ይልቅ፣ በቅርቡና አብሮ ባለ ነገር ላይ ተክዞ፣ ተለኩሶ ከሚከስም የክብሪት እንጨት ወይንም እስኪገጠብ ተጭኖ፣ ቆስሎ ከሚሞት አህያ የምንሻልበትን የውበት ንቅናቄ ለመፍጠር ይጥራል፡፡ ለዚህም ምስክር ይሆን ዘንድ፣ ለአንድ ህፃን ልጅ ከእናቱ ጀርባ የሚቀርበው፤ በአንፃሩ ከራሱ ጀርባ የሚርቀው የለምና፣ እኛም ህፃን የነበርን ወጣቶች፣ ወጣቶችም የነበርን ጎልማሶች ነን ወይም እንሆናለንና ጉዳዩ ሳይታከከን ማለፍ ስለማይችል የጥያቄው ሰለባ መሆናችን አልቀረም፡፡ እንዴት?
ምንድን ነው ጀርባ?
አምስት ስሜቶች የካዱት
ምስጢረ ድብቅ አውድማ
አናሸት..አናይበት
      አንቀምስበት በሱ አንሰማ
                    ምንድን ነው ጀርባ?
የነፍሳችን ስስ አውታር
ውጥር የስጋ ግድግዳ
ስሜት የመሸገበት ቦይ
ሰግዳዳ የዥረት ሜዳ

እንዳላየነው የሃሳብ ሀገር
የማናውቀው የቅርብ ባዳ
                  ምንድን ነው ጀርባ?
አይሳቅ፣ አይለቀስበት ገላ
ስሜት ያልተጣፈበት አምባ
አይረገዝ፣ አይወለድበት ገፅ
ቁንጅናው ሚዛን አይገባ…
                 ምንድን ነው ጀርባ?
ተደግፈነውም ቆመን
የማይሰማን ቅርበቱ
ለጠፈር የሚዘረጋ ዐይን
ጀርባን ዞሮ አለማየቱ

እንደ ዕድሜ ጠቢብነት
ከኋላ ጥላው መጋፋቱ
                ምንድን ነው ጀርባ?
እያንዳንዱ ተስፋ በመሰልቸት ይጠበቃል። ፍጥረት ለሞቱ ህይወት እንደሚያስፈልገው እንዲሁ ተስፈኝነቱም ስልቹነቱን ትሻለች፡፡ መጪውን ተስፋ ማድረግስ ያለውን ከመሰልቸት አይደለምን? ህይወት የመውለድና የሞት መፈራረቅ ብቻ አለመሆኗን እውስጧ ያሉ ብሽቅና ድንቅ ቀናት የሚፈጥሩት ከሞት ወዲያ የማይዘነጉ አሻራዎች ምስክሮች ናቸው፡፡ ለዚህም እንደ ማሳያ ይሆነን ዘንድ በስዩም ግጥሞች ውስጥ በዚሁ ጉዳይ ላይ የተነሳውን እንይ…
እንደሚሞት አውቆ መውለድ
መቅበር ወልዶ፤ ወልዶ መሞት
ጠግቦ ቆይቶም ለመራብ
እንዲራቡ አውቆ መብላት፤
ሁሉ ነገር ብልጥነት ነው
መሳው ደግሞ ጅልነት፡፡…
ህይወት እኩሏን ብልጠት፣ እኩሏን ደግሞ ጅልነት እንደሆነች ገጣሚው ያነሳል፡፡ አንድ ነገር ከስም ወዲያ አንድ ነገር ብቻ አለመሆኑን፣ አንዲት ብርትኳን የተባለች እንስት በአንድ ጊዜ ለልጆቿ እናት፣ ለወንድሟ እህት፣ ለባሏ ሚስት፣ ጋዜጠኛም፣ ዋናተኛም ልትሆን መቻሏ፤ አንድ ነገር አንድ አይነት ጥቅም አለመስጠቱን ያሳየናል፡፡ ብሎም በሕይወትና በሞት፣ በረሃብና በጥጋብ መሃል ያለውን ለመሰንበት የሚደረገውን የምርምር ፍኖት ብልጠት ሲለው፣ ስርአት የማስቀጠሉን ጉዳይ ደግሞ ጅልነት አድርጎ ለማሳየት ይጥራል፡፡
በዚህ ሁሉ መሃል ግን በቃል ተጠልፋ ከስንኞች እልፍኝ ያልገባች ትልቅ የፍልስፍና ሃሳብ ያረገዘች፣ ኮሶ ከመጠጣት ወዲያ ከምላስ እንደሚቀር መራር ቃና፤ ግጥሙ ከተደመጠበት ቅፅበት ወዲያ ከልብ ግድግዳ ተለጥፋ የምትቀር አንዲት ቃና አትጠፋም፡፡ ‹‹እንዲሁ›› የምትል። ‹‹እንዲሁ›› የፍጥረት ሁሉ መተዳደሪያ ሕግ መሆኑን ይሄ የሥዩም ተፈራ ግጥም ያሳየናል። ሰው እየሆነ ካለው ነገር ላይ አንዳች የሚቀይረውና የሚጨምረው እንደሌለውና ‹‹እንዲሁ›› የሚለውን ቃል  የፍጥረት ሁሉ ፈጣሪ መሆኑን የተገነዘበው ገጣሚው፣ ለዕጣ ፈንታው ያደላ የሰውን ልጅ የህይወት ስንክሳር ሊያስቃኘን ሲፈልግ…
…እንደሚሞት አውቆ መውለድ
መቅበር ወልዶ፣ ወልዶ መሞት… ይለናል፡፡ እንዴት ካልንም… እንዲሁ……
ሌላው ሰው ከራሱ ጋር የግል ሱባዔ ሲይዝ በዓለም የፍረጃ መዝገብ እብደት ተደርጎ መመዝገቡ አይቀሬ ነው፡፡ ነገር ግን ሰው ከራሱ ወዲያ መካሪ፣ ከራሱም በቀር ተመካሪ የለውምና ራሱን ይዞ ሱባዔ የገባ ዕለት፣ በእለቱ በምትወጣው ፀሐይ ላይ ሳይቀር ሙቀት የመጨመር ስልጣን ያገኛል፡፡ ስለዚህም በማሰብ፣ ገጣሚው ከአንድ ራሱ በተወያየው እውነት ዓለምን ሊረዳበት ‹‹የራስ ከራስ ጨዋታ›› ብሎ ሲነሳ እናያለን፡፡ በዚህም የራሱ ጉባዔ ባፀደቀው ረቂቅ፤ ክሱት የዓለምን ሃቅ በብርቱ ሲነቀንቅ እናያለን፡፡ እንዴት? እነሆ ግጥም…
ውሃ ሽቅብ አይሄድ
ብትሉ ምን ግዴ
          ሲካብ እያያችሁ
ውቅያኖስ አየሩ
ደመናስ ውሃ አይደል
           ገላውን ካያችሁ?
ከሞት ውልደት አይቀድም
ይህንንም ብሎ
            የነፍስን መንትያ
ሕይወት ከሞት ጋር
በሽልነት እድሜው
አብሮ እንዳልተኛ
በነኚህ በሦስቱ ስንኞች ውስጥ እያንዳንዱ ሕይወት በሞት እንደሚጠበቅ እናያለን፡፡ ሰው በሕይወት ከመኖሩ ይልቅ፣ በሞት አቅም  የመኖሩ ጉዳይ ላይ ትኩረት ይሰጣል፡፡ የዚህ ሐሳብ ግልጥ አማርኛ  ለመኖር ከምንመገባቸው ነገሮች ውስጥ ከነሕይወቱ  ሕይወት ያስቀጠለ አንድም ፍጡር አለመኖሩንና፤ በአንፃሩ ሞቶ የማኖር ግብራቸው ጎልቶ መውጣቱን ነው፡፡ ሰውንም ጨምሮ፡፡


Read 1392 times