Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 06 October 2012 14:08

በኢትዮጵያ ከ12 ሚሊዮን በላይ የአዕምሮ ሕሙማን እንዳሉ ይገመታል

Written by 
Rate this item
(2 votes)

አንድ ሳይካትሪስት ሐኪም ለ2 ሚ. ሕዝብ
ዓለም አቀፍ ደረጃ ያሟላ የአዕምሮ ሕክምና ሆስፒታል በኮተቤ እየተሰራ ነው
ከአንጎል ሕመም አንፃር ስናየው የሰው ልጅ የአዕምሮ ሁኔታ ሃይማኖታዊ በሆነ መልኩ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ በተለያየ እምነት ትልቅ ተፅዕኖ ስር ሊገባ ይችላል፡፡ እነዚህ ተፅዕኖዎች ባደገበት ማኅበረተሰብ፣ በግለሰቦች ወይም አንዳንድ ጊዜ በቡድን ደረጃ
በባህርይም በተግባርም ወጣ ያሉ ነገሮች ሊገለጹበት ይችላሉ - ከእምነቱ አንፃር፡፡ ስለዚህ የሰው ባህልና እምነት እንደሚፈቅደው እንደ አንድ ማሳያ ሊሆን የሚችለው፣ በሌላው አገርና በእኛ አገር ያለው የተለያየ ይሆናል፡፡ ሁላችንም የሰው ልጆች ነን፡፡
==========
የአዕምሮ ሕመምተኛ ነበር፡፡ በሽታው እንደጀመረው ዘመዶቹ የተለያዩ ባህላዊና ሃይማኖታዊ  የፈውስ ዘዴዎችን ሳይሞክሩለት እንዳስቀሩ መገመት ይቻላል፡፡ ነገር ግን ዘመናዊ ሕክምና ወደሚሰጥበት ሆስፒታል እንዳላመጡት በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡
እየቆየ ሲሄድ ሕመሙ ስለባሰበት በኃይል መወራጨት፣ ራሱን መጉዳት፣ ደግና መጥፎውን ያለመለየት፣… በአጠቃላይ መረበሽና ማስቸገር ሲጀምር፣ በእግር ብረት አስረው ምግብና ውሃ እያቀበሉት አንዲት ትንሽ ጎጆ ውስጥ አስቀመጡት፡፡ በዚህ ዓይነት ለ13 ዓመት ታስሮ ከኖረ በኋላ፣ ሌላ የአዕምሮ ሕመም ያጋጠመው ሰው አማኑኤል ስፔሻላይዝድ የአዕምሮ ሆስፒታል ታክሞና ድኖ ተመለሰ፡፡
የአዕምሮ በሽተኛው ታክሞ መዳን ወሬ እንደተሰማ የአካባቢው ነዋሪዎች “ይኼኛውም ቢድንም ባይድንም ለማንኛውም እስቲ እንሞክርለት” በማለት ገንዘብ አዋጥተው ያንን የ13 ዓመት የአዕምሮ ሕመምተኛ እስረኛ ወደ አማኑኤል ሆስፒታል አመጡት፡፡ በሽተኛው ዘመናዊ ሕክምና እንዳገኘ ተሻለው፡፡ ነገር ግን 13 ዓመት ታስሮ የቆየው እግሩ አልዘረጋ ብሎት፣ ያልታሰበ የዕድሜ ልክ አካላዊ ችግር ፈጠረበት፡፡
በሕዝቡ ግንዛቤ ማነስና ለበርካታ ዘመናት በኅብረተሰቡ ውስጥ ሰርፆና ተንሰራፍቶ በኖረው ጎጂ ልማዳዊ አሰራሮች ተፅዕኖ የተነሳ፣ በዘመናዊ ሕክምና በቀላሉ መዳን ይችሉ የነበሩ የአዕምሮ ሕሙማን፣ ዕድሉን ባለማግኘታቸው ብቻ፣ በበሽታው የሚሰቃዩትን ዜጎች ቤት ይቁጠረው፤ በተለይ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ፡፡
በአገራችን ከ15-20 በመቶ የአዕምሮ ሕሙማን እንደሚኖሩ የሚገምቱ ባለሙያዎች አሉ፡፡ ይህ አኀዝ በጣም ትልቅ ነው፡፡ የኢትዮጵያን ሕዝብ ቁጥር 80 ሚሊዮን ይገመታል ብንል፣ ከ12 እስከ 16 ሚሊዮን ዜጎች የአዕምሮ በሽታ ሰለባ ናቸው ማለት ነው፡፡
ዶ/ር ዳዊት አሰፋ፤ የአማኑኤል ስፔሻላይዝድ የአዕምሮ ሆስፒታል ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ የአዕምሮ በሽታ ምንድነው? መንስኤውስ? ሕክምናስ አለው? ይድናል? አንድ ሰው የአዕምሮ በሽታ ሕሙም ነው የሚባለው ምን ሲሆን ነው? ኀብረተሰቡ የአዕምሮ በሽታን እንዴት ነው የሚረዳውና የሚያየው? ሕሙማኑንስ እንዴት ተቀብሎ ነው የሚያስተናግደው?... የሚሉ ጥያቄያችን አንስተን ከዶ/ር ዳዊት ጋር ያደረግነውን ቃለ-ምልልስ በዚህ መልኩ አቅርበናል፡፡
=========
የአዕምሮ ሕመም ምንድነው?
የአዕምሮ ሕመም የተለያዩ አገላለፆች አሉት፡፡ በአንድ በኩል ማኀበረሰቡ ትክክለኛ መስተጋብር ነው ብሎ ከሚወስደው አካሄድ ወጣ ያሉ ባህርይ፣ በሐሳብ ወይም በተግባር ሊገለጹ የሚችሉ ተደጋጋሚ ድርጊቶች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እነዚያ ወጣ ያሉ ባህርያት በኀብረተሰቡ ወይም በግለሰቡ ላይ ተፅዕኖ ሲያደርሱና ግለሰቡ ተጽዕኖአቸውን ሊቆጣጠረውና ሊያስተካክለው ከሚችለው በላይ ሆኖ ዕርዳታ የሚያስፈልገው ሆኖ ሲገኝ በሙያው ዘርፍ ያ ሰው የአዕምሮ ችግር ገጥሞታልና ሕክምና ያስፈልገዋል የሚል እምነት ያሳድራል፡፡ ይኼኛው አገላለጽ የተሻለ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡
የአዕምሮ ሕመም መንስኤ ምንድነው?
የአዕምሮ ሕመም መንስኤ ይህ ነው ብሎ አንድን ነገር ነጥሎ ለማቅረብ የሚያመች አይደለም፡፡ በጥቅሉ ስንወስደው የተፈጥሮ ወይም ባዮሎጂያዊ ምክንያቶች ይኖራሉ፡፡ ለምሳሌ የተፈጥሮ ተጋላጭነት የምንለው ነገር ይኖራል፡፡ ስለዚህ አንድ ሰው ለአዕምሮ ሕመም ተጋላጭ ሊሆን ይችላል፡፡
የተፈጥሮ ተጋላጭነትን በተለያየ መንገድ ልንረዳ እንችላለን ወይም የተለያዩ መገለጫዎች ሊኖሩት ይችላል፡፡ ለምሳሌ በቅርብ ቤተሰብ ዘንድ ወይም በዘር ተደራራቢ የሆነ የአዕምሮ ሕመም ታሪክ ያለበትን ሰው ተጋላጭ  የመሆን ዕድል አለው ብለን ልንወስድ እንችላለን፡፡ ነገር ግን ተጋላጭነት ወይም የተፈጥሮ ምክንያት ብቻ በራሱ የአዕምሮ ሕመም አያመጣም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ማኀበራዊና ሥነ-ልቦናዊ ምክንያቶች ተደርበው ሲመጡ ነው ወደ አዕምሮ ሕመም የሚደርሱት፡፡
እኛ በሕክምናው አጠራር ይህን ምክንያት ባዮሳይኮሶሻል እንለዋለን፡፡ የተፈጥሮ፣ የሥነ ልቡናና ማኀበራዊ ችግሮች አንድ ላይ ተደራርበው በአንድ ወቅት ሲደርሱ፣ ሲመጡ፣ ሲቀጣጠሉ ያ ሰው ወደ ሕመም ጫፍ ይገፋና ወደ አዕምሮ ሕመምተኛነት ይደርሳል ማለት ነው፡፡
አንድ ሰው የአዕምሮ ሕመምተኛ ነው የሚባለው መቼ ነው? መገለጫዎችስ አሉት?
ይኼ በጣም ጥሩ ጥያቄ ነው፡፡ ምክንያቱም የብዙ ሰዎች ጥያቄ ነው፡፡ ይህ ጥያቄ በትምህርትና በሥራም ላይ ሆነን በተለያዩ አጋጣሚዎችና በተወሰነ ደረጃ ራሳችንን የምንጠይቀው ነገር ይኖራል፡፡ ምክንያቱም የአዕምሮ ሕሙማን የሚያሳዩት ምልክት ወይም የአዕምሮ ሕሙማን መገለጫ አድርገን የምንወስዳቸው ምልክቶች በሙሉ በጤነኛ ሰዎች ዘንድ አሉ፡፡
አንዱና ዋነኛም የአዕምሮ ሕመም መገለጫ ከልክ ያለፈ ጥርጣሬ የሚሆንበት ጊዜ አለ፡፡ ለምሳሌ ሰዎች ይከተሉኛል ሲ አይ ኤ ይከተለናል፣ መንግስት ይከታተለናል፡፡ ጉዳት ሊያደርሱብን ያደመቡን፣ ያመፁብን ሰዎች አሉ፣ የሚሉ ነገሮች ከልክ ያለፉ ጥርጣሬዎች ናቸው፡፡ መጠርጠርን በጥርጣሬነቱ ብቻ ስንወስደው፣ ጤነኛም ሰው ካጋጠመው ነገር ተነስቶ ሊጠራጠር ይችላል፡፡
ለምሳሌ አንድ ሰው ቢሮው ውስጥ ሆኖ እየሰራ ሳለ፣ ከጎኑ ባለው ክፍል ቦንብ ቢፈነዳ እስከተወሰነ ጊዜ ድረስ የተራመደበትን መንገድ ሁሉ አያምነውም፡፡ ቀኑን ሙሉ አገሩ ሁሉ ቦንብ የተቀበረበት ሊመስለው ይችላል፡፡ ይኼ ተፈጥሯዊና አስፈላጊም ጥርጣሬ ነው - ራስን ለማዳን ስለሚጠቅም፡፡ ሌላው ደግሞ የማታውቀው ሰው እየሳቀ ጣቱን ወደ አንተ ሲጠቁም ካየህ “እኔን ይሆን?” ብለህ ትጠራጠራለህ፡፡ ስለዚህ ጥርጣሬ በጥርጣሬነቱ ሁሉም ሰው ውስጥ አለ፡፡
ጥርጣሬ የአዕምሮ ሕመም ምልክት ተደርጎ ሊወስድ የሚችለው እነዚያ ጥርጣሬ የፈጠሩት ነገሮች መኖር ያመኖራቸው ብቻ ሳይሆን ከልክ ሲያልፉ ነው፡፡ ጥርጣሬው ሰው ሊቀበለው ከሚችለው በላይ ሲሆን ወይም የአካባቢው ማኀበረሰብ እምነቱና ባህሉ ከሚፈቅደው በላይ ሲሆን የሕመም ምልክት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡
በሌላም በኩል ጥርጣሬው በሰውዬው ማኀበራዊ ሥነ-ልቡናዊ፣ የሥራ ሕይወቱ ላይ ተፅዕኖ ሲያደርስ የሕመም መገለጫ ተደርጎ ሊታይ ይችላል፡፡ ለምሳሌ ጥርጣሬው ከልክ አልፎ እየተከታተሉኝ ነው ካለ ሰውዬው ከቤት አልወጣም፣ ሥራ አልሄድም፣ ሰላዮች ከሥራ ቦታ ሊይዙኝ መ/ቤቱን ከበዋል፤ ሊይዙኝና ሊያጠቁኝ ይችላሉ ብሎ ከቤት ላይወጣ፣ አገር ሊለቅ ይችላል፡፡ እዚህ ደረጃ ላይ ሲደርስ ተጽዕኖው ከፍተኛ ይሆናል፡፡ ይህንን ጥርጣሬ ኀብረተሰቡ ወይም የአካባቢው ሰው የማይቀበለው የማይካፈለው ከሆነ ሰውዬው ታሟል ማለት ያስችላል፡፡
አንዳንድ የማናያቸው ነገሮች አሉ፡፡ ለምሳሌ ፈጣሪ አለ ይባላል፡፡ ስለዚህ አንድ ሰው “ፈጣሪ አለ” ቢል የሕመም ምልክት አድርገን አንወስደውም፡፡ ይህን የምናደርገው ማረጋገጫ ያመጣል ወይም ያቀርባል በሚል እሳቤ ሳይሆን ኅብረተሰቡና  የአካባቢው ሰዎች ስለሚቀበሉት የሕመም ምልክት ማድረግ አንችልም፡፡
ዋናው ነጥብ ሰውዬ የሚለውና የሚታየውም ነገር ባለበት ማኅበረሰብ ባህል ሃይማኖት፣ … ተቀባይነት አለው ወይ? ወይም ሰዎች ሐሳቡን ይጋሩታል ወይ? የሚለው ነው፤ ምናልባትም     ሲ አይ ኤ የእውነት ሰውዬውን እየተከታተለ ሊሆን ይችላል፡፡ ያ ሲሆን ትክክለኛም ጥርጣሬ ሊሆን ይችላል፤ ሰዎችም ሊያውቁ ይችላሉ፡፡ እንዲሁም የአካባቢው ሰው በሆነ ጉዳይ ላይ አንድ ላይ ስጋት ሊገባው ይችላል፡፡ ጉዳዩ ሶሻል (ማኅበራዊ) ከሆነ የሕመም ምልክትነት ተደርጐ ሊወሰድ አይችልም፡፡ ነገር ግን ጥርጣሬው መሠረት የሌለውና  ከማኅበረሰቡ አመለካከትና አተያይ ውጭ ሲሆን በበሽታ ምልክትነት ሊወሰድ ይችላል፡፡
ሌላው በዋነኛ ሊጠቀስ የሚችለው ምልክት ሌላው ሰው የማይሰማው ድምፅ ይሰማኛል ሲል ነው፡፡
ኅብረተሰቡ ስለ አዕምሮ ሕመም ያለው ግንዛቤና አመለካከት ምንድነው? ተፅዕኖስ አለው? ግንዛቤውን ለማሻሻል ምን እየተሠራ ነው?
ኅብረተሰቡ ስለ አዕምሮ በሽታ ያለውን አመለካከትና ግንዛቤ በጥቅሉ እንየው ከተባለ፣ ከአዕምሮ ሕክምና አኳያ ዝቅተኛ ነው የሚል ግምት ነው ያለኝ፡፡ ይህን የምልበት ምክንያት በምሠራበት ቦታ የኅብረተሰቡ የግንዛቤ ደረጃ ምን ላይ እንደሆነ የሚያሳዩ ሁኔታዎች በተደጋጋሚ ያጋጥሙናል፡፡ ለምሳሌ ከሁለት ዓመት በፊት ያጋጠመኝ ሁኔታ አንድ ማሳያ ይሆናል፡፡
የሰውዬው ዕድሜ በ35 ዓመት ይገመታል፡፡ ያ ሰው ከ13 ዓመት ሕመም በኋላ ነው ወደ እኛ የመጣው፡፡ 13ቱን ዓመት ይረብሸናል ያስቸግረናል ብለው በእግር ብረት ታስሮና ገለል አድርገው በአንድ ጉረኖ ውስጥ አስቀምጠውት ነው የኖረው፡፡ አሁንም ወደዚህ የመጣው፣ በአካባቢው በአዕምሮ በሽታ የታመመ ሰው አማኑኤል ሆስፒታል ታክሞ ዳነ የሚል ወሬ ሰምተው ነው፡፡ የሰውዬው ቤተሰብ ኢኮኖሚያዊ አቅም ደካማ ስለሆነ፣ የአካባቢው ነዋሪዎች “እከሌ’ኮ ታክም ዳነ፤ እስቲ ይኼኛውንም ወደዚያ ሆስፒታል ልከን ውጤቱን እንየው” ብለው ገንዘብ አዋጥተውለት መጣ፤ ሕክምናውን አግኝቶ በጣም ተሻለው፣ አዕምሮው ደህና ሆነ፡፡
ትልቅ ችግር የሆነበት 13 ዓመት ሙሉ ታስሮ የቆየበት እግሩ መዘርጋት አልቻለም፡፡ እንግዲህ ሌላ ችግር ተፈጠረበት ማለት ነው፡፡ ሰውየውም በጣም ያዘነበት ነገር ይኼ ነው፡፡ “13ቱን ዓመት አጥቼዋለሁ፣ ባክኗል፤ እንዳልኖርኩ ቁጠሩት፡፡ ያ ሳያንስ አሁን አዕምሮዬ ድኖ ከአሁን በኋላ እግሬ ሳይንቀሳቀስ ምን ዓይንት ሕይወት ነ ው የምኖረው?” በማለት በጣም አዘነ፡፡ ቤተሰቡ ግራ በመጋባትና የሚያደርጉትን ባለማወቅ የወሰዱት እርምጃ እንደሆነ እንዲያየውና ከአሁን በኋላ ምንም ማድረግ ስለማይቻል መቀበል እንዳለበት ተነጋግረን በግማሽ ተቀብሎታል፡፡ በቤተሰቦቹ ላይ ግን በጣም አዝኗል፡፡
ይህን ችግር ያነሳሁበት ምክንያት ወደ እኛ ሳይመጡ የቀሩ እንደዚህ ዓይነት ጉዳዮች ብዙ ይኖራሉ፡፡ ወደ ሕክምና ከሚመጡትም በኅብረተሰቡ ውስጥ በአዕምሮ ሕክምና ዙሪያ ክፍተት እንዳለ የሚያመለክቱ በጣም ብዙ ምሳሌዎች አሉ፡፡
በየፀበሉ፣ በየእምነት ቦታው፣ በባህላዊ ሕክምና መስጫ፣ … ያለውን የአዕምሮ ሕሙማን ቁጥር ማንም ሰው ተዘዋውሮ ቢያይ፣ ሰዎች ከዘመናዊ ሕክምና ውጭ በባህላዊና ልማዳዊ መንገድ ሕሙማንን ለማዳን የሚያደርጉት ትግል በጣም አስገራሚ ነው፡፡
ያንን የሚያደርጉት ግን አውቀው አይደለም - ባለማወቅ ነው የሚያደርጉት፡፡ ያለው የሰብአዊ አያያዝ ሁኔታም ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ነው፡፡ ዘመናዊ ሕክምና ምንም ኢ-ሰብአዊ ነገር የለውም፤ መድኃኒት መውሰድ ወይም በምክክር የምታደርገው ነው፡፡ ዘመናዊ ሕክምና ይህ መሆኑን ቢያውቁ የመጀመሪያ ምርጫቸው ያደርጉት ነበር፡፡ ነገር ግን ከተለያየ ባህልና እምነት አንፃር፣ በዚህ መልኩ ይፈወሳል በሚል የሚታሰሩ፣ የሚገረፉ፣ አካላዊ ጉዳት የሚደርስባቸው በርካታ የአዕምሮ ሕሙማን አሉ፡፡ ሰዎች እንዲህ ዓይነት ነገር ውስጥ የሚገቡት ከመቸገራቸው የተነሳ ስለሆነ ክፍተቱን ከዚህ አንፃር ማየት ይቻላል፡፡
በኀብረተሰቡ ዘንድ ለአዕምሮ ሕመም መንስኤ ምንድነው? ይህስ ነገር ሰው በሳይንስ እንዲጠራጠር አያደርግም? እነዚህ ምክንያቶችስ በሳይንስ ምን የህል ተቀባይነት አላቸው?
በሕክምና ሂደት ከምንገነዘበውና በግሌ ከማየው በመነሳት መናገር እችላለሁ፡፡ ከዚህ አኳያ፣ ከጥቂት ቤተሰቦችና ግለሰቦች በስተቀር፣ እጅግ በርካታ የአዕምሮ ሕመምተኞች ወደዚህ ሆስፒታል የሚመጡት፣ የሕመሙ መንስኤ ሰይጣን፣ ጋኔል፣ ቃልቻ፣ ጥንቆላ፣ ድግምት፣ ዛር፣ ቡዳ፣ መድኃኒት አጠጥተውት፣ … በማለት የተለያዩ ቦታዎች ሙከራ ተደርጐላቸው ሳይሳካ ሲቀር ነው፡፡ እነዚያ ታማሚዎች ደግሞ አብዛኞቹ በሽተኞች እዚህ መጥተው በዘመናዊ ሕክምና ሲድኑ ያያሉ፡፡
ስለዚህ ይኼ ሁኔታ እምነቱን ጥያቄ ውስጥ ሊያስገባ ይችላል ማለት ነው፡፡ ያ ሰው የታመመው በሰይጣን፣ በቃልቻ፣ … ሳይሆን እንደማንኛውም አካል አዕምሮው ስለታመመ ነው ወደሚለው ያስኬዳል፡፡
ድምፅ እሰማለሁ፣ አገሩ ሁሉ አድሞብኛል የሚል በሽተኛ ድምፁም ይጠፋል፤ ሰዎች ሁሉ አድሞብኛል የሚለውን ሐሳብ እርግፍ አድርጐ ይተዋል - የሳምንታት መድኃኒት ወስዶ ብቻ፡፡
ነገር ግን መድኃኒቱን መውሰድና ሕክምናውን መቀጠል ይኖርበታል፡፡ ይህ ደግሞ እንደማንኛውም የአካል ክፍል አዕምሮው የተጐዳ ወይም የተዛባ ክፍል ነበረው፤ ያ ክፍል ደግሞ በመድኃኒት ተስተካክሏል የሚል መልዕክት ነው ከትምህርትም ከልምድም ያገኘነው - እውቀትና እውነት፡፡
ባህላዊ አሠራር ትክክል ነው፣ አይደለም ብሎ ማረጋገጫ ማቅረብ አይቻልም፡፡ ከተገኘው ውጤት በመነሳት ወደ ኋላ ሄደን አይሆንም ማለት ነው እንጂ፤ መንፈሳዊ ነገርን በሳይንሳዊ መንገድ ማረጋገጥ አይቻልም - አካሄድና መንገዳቸው የተለያየ ስለሆነ፡፡
ከዘመናዊ ሕክምና ውጭ በመንፈሳዊ ዕርዳታ በኩል ሲታይ አንዳንድ ጊዜ ደህና ለውጥ የሚታይባቸው ሰዎች አሉ፡፡ በጭንቀት፣ በድባቴ (በድብርት) በተለያየ የአዕምሮ እክል፣ የተጠቁ ሰዎች “መንፈሳዊ ዕርዳታ አግኝተን ተሻለን” የሚሉ ድብርት ያለባቸው ሰዎች አጋጥመውኛል፡፡  ነገር  ግን ያ ሰይጣን ለመሆኑ ወይም እምነቱ እርግጠኛ ለመሆኑ ምክንያት መሆን ይችላል ወይ? የሚል ጥያቄ ማንሳት ይቻላል፡፡
ምክንያቱም በእኛም ዘንድ እነዚህ ሰዎች ምክር በምንለው ሳይኮቴራፒ ሊድኑ ይችላሉ፡፡ ቀላል ጭንቀት ወይም ድብርት ያለበት ሰው በምክክር ይድናል፡፡ ስለዚህ የአዕምሮ ችግር ኖሮበትም ባለው መንፈሳዊ ዕርዳታና ድጋፍ መዳንም ሊኖር ይችላል፡፡ ያ ግን በመንፈሳዊ ዕርዳታ ስለዳነ፣ በእርግጠኝነት ሰይጣን ነበር ማለት አያስኬደንም፡፡ ምክንያቱም የመንፈሱ መታደስ፣ ያለው ሰላማዊ ሁኔታ፣ ተስፋ፣ … ሰዎችን ሊያድን ይችላል፡፡
ይህን የምልበት ምክንያት አንዳንድ ጊዜ የአዕምሮ ሕሙማንን የምንይዝበትን አኳኋን፣ እነሱን የምንመለከትበትን መንገድ ሁሉ ስለሚቀይረው ነው፡፡ ጋኔል ነው፣ ሰይጣን ነው፣ … ስንል በሰይጣን የተያዘ ማለት፡፡ አንድ ሰው በሰይጣን የተያዘ ከተባለ ደግም ብዙ ጊዜ ወደ ኢ-ሰብአዊ ድርጊት የመሄድ ነገር ሊኖር ይችላል፡፡ ያንን ሰው ከሰይጣን ጋር አቆራኝተን ካየነው መፍራት፣ መስጋት ሊኖር ይችላላ፡፡ ከሰው ተራ የወጣ አድርገን ከመቁጠር አንፃር፣ ጠንካራ እርምጃዎችን ለመውሰድ በመሞከር ድብደባ፣ ማሰር፣ ማንገላታት፣ … ሊኖር ይችላል፡፡ በተለይ ታማሚው መንፈሳዊ እውቀቱ በሳል ባልሆነ ሰው እጅ ሲገባ ሁኔታውን አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡
አንዳንድ ጊዜ ሰይጣን ይዟቸዋል የተባሉ ሰዎች ታስረውና ቀዝቃዛ ውሃ ውስጥ ተነክረው በመስቀል እየተመቱ “ልቀቅ” ሲባሉ፣ “እሺ! እለቃለሁ” ይላል፡፡ “ምስህ ምንድነው?” ሲባል ደግሞ “አተላ፣ ዶሮ ኩስ፣ …” ይላል፡፡ አንዳንድ ጊዜም ድምፁን ለውጦ በማይታወቅ ቋንቋ ይናገራል፡፡ ይህ ነገር እንዴት ነው የሚሆነው? በሳይንስ የሚታወቅ ነገር አለ?
እንግዲህ ትልቁ ችግር የሚመጣው ከፍ ሲል እንደጠቀስኩት ነው፤ ክፍተቱም ያለው እዚያ ላይ ነው፡፡ መንፈሳዊ ነገርን በሳይንሳዊ መልኩ ማረጋገጥም፣ አይሆንም ማለትም ስለማይቻል ከማየውና በሥራ ከሚያጋጥመኝ ሁኔታ በመነሳት ሙያዊ አስተያየት ልስጥ፡፡ ነገር ግን ትክክለኛ ማረጋገጫ ተደርጐ ሊወሰድ አይችልም፡፡
ከአንጎል ሕመም አንፃር ስናየው የሰው ልጅ የአዕምሮ ሁኔታ ሃይማኖታዊ በሆነ መልኩ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ በተለያየ እምነት ትልቅ ተፅዕኖ ስር ሊገባ ይችላል፡፡ እነዚህ ተፅዕኖዎች ባደገበት ማኅበረተሰብ፣ በግለሰቦች ወይም አንዳንድ ጊዜ በቡድን ደረጃ በባህርይም በተግባርም ወጣ ያሉ ነገሮች ሊገለጹበት ይችላሉ - ከእምነቱ አንፃር፡፡ ስለዚህ የሰው ባህልና እምነት እንደሚፈቅደው እንደ አንድ ማሳያ ሊሆን የሚችለው፣ በሌላው አገርና በእኛ አገር ያለው የተለያየ ይሆናል፡፡ ሁላችንም የሰው ልጆች ነን፡፡
አንዱን ሰይጣን (ጋኔል) የሚይዘው፣ ሌላውን የማይዝበት ምክንያት ግልጽ ነው ወይ? የሚል ጥያቄ ማንሳት ይቻላል፡፡
ስለዚህ ሁሉም ሰው የሚኖረው እንደ የእምነቱ ይሆናል ማለት ነው፡፡ መጨረሻም ላይ እውነታ የሚፈጠረው በአዕምሮ ነው የሚሆነው፡፡  አዕምሮህ በሚታወክበት ጊዜ የምታንፀባርቃቸው ነገሮች ሁሉ የማኅበረሰቡን እምነትና ባህል የተከተለ ነው የሚሆነው፡፡
አንድ የኢትዮጵያ ገበሬ አዕምሮው ሲታመም ሲአይኤ ይከተለኛል አይልም፡፡ ገበሬው ጐረቤቴ መተት (መድኃኒት) አደረገብኝ ነው ማለት የሚችለው፡፡ አንድ የሰለጠነ ምዕራባዊ ማኅበረተሰብ አባል የሆነ የአዕምሮ ሕመምተኛ ስጋት የሚፈጠርበት በጣም በተራቀቁ ሳይንሳዊ ጉዳዮች ሊሆን ይችላል፡፡ ለምሳሌ፣ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያ ጭንቅላቴ ውስጥ ቀብረው በየሄድኩበት በዚያ መሳሪያ እየተከታተሉኝ ነው፡፡ ስለዚህ ጨረር እየላኩብኝ በዓይኔ ላይ ተፅዕኖ ፈጥረዋል፣ ዓይኔን ችግር ውስጥ ከተዋል … ይላል፡፡ እነዚህን ውስብስብ ነገሮች ደግም ከባህላዊ እምነት አኳያ ነው የሚያገኘው፡፡ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ የሚንፀባረቀውን ነገር በማየት ብቻ ያ ነገር ሆኗል ማለት አይቻልም፡፡ ከሙያ አንፃር ማለት የምችለው “ይህ ሰው ታሟል” ብቻ ነው፡፡ ከታመመ በኋላ በሚያደርገው፣ በሚለው በሚያምንበት ነገር ሁሉ የሚጠየቀው እንደ ግለሰብነቱ ሳይሆን በማኅበረሰቡ ነው፡፡ የማኅበረሰቡ እምነትና ባህል፣ ሳይታመምም መገለጫው ይሆናል፤ ሲታመም ደግሞ ከቁጥጥር ውጭ ስለሚሆን ያ ነገር በደንብ ይታያል፤ ይገለጻል፡፡
በመደብደብ ጫና ሲበዛባቸው ላለመጐዳት እንደ ማምለጫ የሚጠቀሙበት ሕሙማን እንዳሉ በጣም ግልፅ ነው፡፡ ሁሉም ናቸው ማለት ግን አልችልም፡፡ ካየሁት ነገር መናገር የምችለው፣ እዚህ መጥተው ከተሻላቸው በኋላ ጨንቆኝ’ኮ ነው እንደዚያ ያልኩት፡፡ “ሰይጣን ነህ? ከየት መጣህ? እንዴት ያዝከው/ካት?” ብለው ወጥረው ሲይዙኝና ዱላው ሲበዛብኝ “እሺ እወጣለሁ” ብያለሁ ያሉ በርካታ ሰዎች አጋጥመውናል፡፡ ይህን የምለው የእምነቱንና የባህሉን አካሄድ ሙሉ በሙሉ ውድቅ ለማድረግ ወይም ማረጋገጫ ሰጠሁ ለማለት አይደለም፡፡ ካየሁት ከማውቀው ተነስቼ ነው፡፡
የባህልና ሃይማኖት ተፅዕኖ በአዕምሮ ሕሙማን ላይ የሚያደርሱት ተፅዕኖ ምን ያህል ነው?
በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ በእርግጥ ባህልንና ሃይማኖትል የማይለዩ የአዕምሮ ሕመም ዓይነቶች ብዙ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ስኮዞፍሬኒያ የምንለው ስጋትና ጥርጣሬ የሚለገጽባቸው ሰዎች በየትኛውም ዓለም አሉ፡፡ ስርጭታቸውም ከሞላ ጐደል እኩል ነው፡፡ በኢትዮጵያም ሆነ በአሜሪካ ከመቶ ሰዎች አንዱ ስኮዞፍሬኒያ አለበት ተብሎ ነው የሚታመነው፡፡
ባህልና እምነቱ ተፅዕኖ የሚያደርገው መገለጫው ላይ ነው፡፡ በሁለቱም አገሮች መገለጫው ጥርጣሬ ነው፡፡ ነገር ግን በጥርጣሬው የተነሳ ኢትዮጵያ ያለውና አሜሪካ ያለው ሰው የሚሉት የተለያየ ነው፡፡ ስለዚህ ባህልና እምነቱ ይዘቱን ይለውጠዋል፡፡ የሕመሙ መሠረታዊ መገለጫ ግን ተመሳሳይ ነው፡፡ ነገር ግን በእምነት ውስጥ ያለ ሰው የእግዚአብሔርን ድምፅ ሊሰማ ይችላል፡፡ በቴክኖሎጂ በተራቀቀ ዓለም ያለ ሰው የዩፎ ድምፅ ይሰማኛል ሊል ይችላል፡፡
በኅብረተሰቡ ውስጥ ያለውል የአዕምሮ ሕመም ግንዛቤ ክፍተት ለማጥበብ ምን መደረግ አለበት? እናንተስ ምን እየሠራችሁ ነው?
አስተሳሰብን፣ እምነትን፣ ድርጊትን፣ … ለመቀየር የመጀመሪያው ትልቅ መሳሪያና እርምጃ ትምህርት ነው፡፡ ዋናው ጥያቄ ትምህርቱ በምን መልኩ መሆን አለበት የሚለው ነው፡፡ እንደ ተማሪና አስተማሪ አንዱ ሰጪ ሌላው ተቀባይ ሆኖ መቀጠል ወይም የአዋጅ ጉዳይ መሆን ያለበት አይመስለኝም፡፡ በዚያ መልኩ መሄድ ለውጥ የሚያመጣ አይመስለኝም፡፡
ከተማ ያለው ሰው የአማኑኤል ሆስፒታል የአዕምሮ ሕሙማን መታከሚያ መሆኑን በደፈናው ሊያውቅ ይችላል፡፡ ነገር ግን ትምህርቱ ጥልቀት ባለውና እምነትን ሊያስለውጥ፣ ከዕለት - ተዕለት ሕይወት ጋር ሊዋሃድ በሚችል መልኩ መሆን የሚችለው ከትምህርቱ በተጓዳኝ አብረን መሥራት ስንችል ነው፡፡ የአዕምሮ ሕክምና ባለሙያዎች ትምህርት ሲሰጡ ከላይ ማውረድ ብቻ ሳይሆን፣ ከማኅበረሰቡ ጋር አብረው  ማሰብ አለባቸው፡፡
ትምህርቱን የሚሰጡት ሰዎች በሙሉ የኅብረተሰቡን ባህልና እምነት ጠንቅቀው መረዳት አለባቸው፡፡ ከዚያም መረዳት፣ አብሮ መኖርና አብሮ ማሰብ ይመጣል፡፡ እንደዚያ ከሆነ እኛም ወደ ኅብረተሰቡ፣ ኅብረተሰቡም ወደ እኛ የሚያስተላልፈው ነገር ይኖራል፡፡ በዚያ መልኩ መማማር ሲኖር ትክክለኛ ለውጥ ሊመጣ ይችላል፡፡ የምንኖርበትና ውጤት የምንፈልግበት ስለሆነ፣ እምነትና ባህልን ሳያውቁና ሳይገነዘቡ ማጣጣል እንዲሁ በደፈናው ማናናቅና ማጣጣል አይገባም፡፡ ለምሳሌ ኤች አይ ቪ ላይ በተወሰነ ደረጃ አብሮ መሥራት ተችሏል፡፡
የመንግሥት ቁርጠኝነት ጠንካራ ሆኖ ከቀጠለ፣ የባህልና የእምነት መሪዎችን መያዝ እንችላለን፡፡ መረዳዳቱ በዚያ ደረጃ ሊጀመር ይችላል፡፡ እነሱ ከተረዱ የሚከተላቸውን ማኅበረሰብ ለማስረዳት ከእኛ ይልቅ እነሱ የቀረቡ ናቸው፡፡ የተሻሉም ናቸው፤ ከእምነትና ከባህሉ ጋር አዋህደው መግለጽ ይችላሉ፡፡
ሁሉም ሰው በቀን ውስጥ ለተወሰነ ደቂቃ ያብዳል የሚባለው እውነት ነው? “እብድ” የሚለው ቃልስ የአዕምሮ ሕመምን ይገልጻል?
ከቃሉ ብንነሳ “እብድ” የሚለውን ቃል የማይወዱና በፍፁም መጠቀም የለብንም የሚሉ ባለሙያዎች ብዙ ናቸው፡፡ ቃል-ቃል ነው፡፡ የሰው ስሜትና የሚገዛው ሐሳብ እንደየማኅበረሰቡ ነው፡፡
“እብድ” የሚለውን ቃል ማበረታታት፣ መገለልና መድሎን ያስፋፋል የሚል ነው ስጋቱ፡፡ ሌላም ቃል ለውጠን ለስድብ ከተጠቀምንበት ትርጉም የለውም፡፡ አዲስ ቃል ተክተን የአዕምሮ ሕመም፣ የአዕምሮ መታወክ፣ … እያልን ብናወራ ጥሩ ነው የሚል  ሐሳብ ያላቸው ሰዎች አሉ፡፡ ሁሉም ሰው ለአጭር ጊዜ ያብዳል የሚለው አገለላጽ ነው፡፡ እኛ ስኮዞፍሬኒያ የምንለው ነው በእኛ አገር ትርጉም እብድ የሚባለው፡፡ ከዚህ አንፃር ትክክለኛውን የእብደት መገለጫ እንጠቀም ከተባለ፣ ለአጭር ጊዜ ማበድ የሚባል ነገር የለም፡፡ አንድ ሰው ስኪዞፍሬኒያ ነው ከተባለ የረዥም ጊዜ በሽታ ነው፡፡ ነገር ግን የረዥም ጊዜውን በሽታ የመሰለ ይከሰታል ለማለት ከሆነ፣ አልፎ አልፎ ሊያጋጥም ይችላል፡፡ ለምሳሌ ሰዎች አንድ ነገር በእጃቸው ይዘው፣ ፀጉራቸው ላይ አስረው፣ በእግራቸው አጥልቀው፣ … ለጊዜውና ለቅፅበት ያ ነገር ያለበትን ቦታ ይረሳሉ ወይም ያጣሉ፡፡ ያ እብደት አይደለም፤ ከትውስታ ጋር የተያያዘ የአዕምሮ ሥራ ነው፡፡ እብደት ማለት ከልክ ያለፈ ጥርጣሬና ድምፅ መስማት ናቸው፡፡
አማኑኤል ስፔሻላይዝድ የአዕምሮ ሆስፒታል መች ተመሠረተ? በቀን፣ በወር፣ በዓመት ምን ያህል ሕሙማን ያክማል? አምና  ምን ያህል ሰው አከማችሁ? የሕሙማን መስተንግዶስ እንዴት ነው?
ይህ ሆስፒታል ነባር ነው፡፡ በ1930ዎቹ ነው ተመሠረተው የሚባለው፡፡
ከዚያ በኋላ የተለያዩ ለውጦችና አሠራሮች አካሂዷል፡፡ በፊት እንደተመሠረተ፣ ሕክምናው ይሰጥ የነበረው በቡልጋሪያና በሩሲያ ባለሙያዎች ነበር፡፡ ከዚያ በመቀጠል ደግሞ በ1978 ገደማ የአዕምሮ ሕክምና ነርሶችን ማሠልጠን ተጀመረ፡፡
ከዚያም ወዲህ ነርሶች እየሠለጠኑና በየአቅጣጫው እየተሰማሩ በጤና ጣቢያዎችና በዚህ ሆስፒታል ውስጥ አገልግሎት እየሰጡ ነው፡፡ እነዚህ እንግዲህ አገር በቀል ባለሙያዎች ናቸው ማለት ነው፡፡
ከእነዚህ ነርሶች ቀደም ብሎም ኢትዮጵያውያን ሳይካትሪስቶች (የአዕምሮ ሐኪሞች) በውጭ አገር ሰልጥነው እስካሁንም እያገለገሉ ናቸው፡፡ አሁን ሙሉ በሙሉ ማለት በሚቻል ሁኔታ ሕክምናውን እየሰጡ ያሉት ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ናቸው፡፡
ሆስፒታሉ ሕክምና የሚሰጥባቸው 300 ያህል አልጋዎች አሉት፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ ይያዛሉ፡፡ በተመላላሽ ሕክምና በቀን 400 ሕሙማን ልናይ እንችላለን፡፡ አምና በአጠቃላይ ተመላላሽ ሕክምና ያገኙት 126 ሺህ ያህል ሰዎች ይመስለኛል፡፡
በዚህ ሆስፒታል ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሕክምና ማግኘት ፈልጐ የመጣ ሰው በሙሉ በመጣበት ቀን ህክምናውን አግኝቶ ይመለሳል፡፡ በዚህ አቋም ነው እየሠራን ያለው፡፡ ተመላላሽ ታካሚ ሆኖ ቀጠሮ ተሰጥቶት የተመለሰ ሰው የለም፡፡ ከታከመ በኋላ ግን አልጋ ይዞ ለመታከም ቀጠሮ ሊሰጥ ይችላል፡፡
በአገሪቷ ውስጥ ምን ያህል የአዕምሮ ሕሙማን አሉ?
በግምት ካልሆነ በስተቀር ትክክለኛውን ቁጥር መናገር አስቸጋሪ ነው፡፡ የአዕምሮ ሕመምን በአጠቃላይ ከወሰድን እስከ 20 ፐርሰንት ሊደርስ ይችላል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ከ15 እስከ 20 ፐርሰንት ልንለው እንችል ይሆናል፡፡
ምን ያህል የአዕምሮ ሕመም ሐኪሞች አሉ?
ሳይካትሪስቶች 40 አካባቢ፣ ሳይካትሪስት ነርሶች 400 ያህል ደርሰዋል፡፡ ከሳይካትሪስት ነርሶች ውስጥ በሙያው ላይ ያሉት ግማሽ ያህሉ ናቸው፡፡ ምክንያቱም የተቀሩት የትምህርት ዘርፋቸውን ቀይረው እየተማሩ በሌላ አቅጣጫ ሄደዋል ወይም በተለያዩ ምክንያቶች ሥራቸው ላይ አይደሉም የሚል ግምት ነው ያለኝ፡፡ ከቅርብ ዓመት ወዲህ ሳይካትሪስት ሐኪሞች በየዓመቱ 5፣6፣ እየሠለጠኑ በአሁኑ ወቅት 40 ደርሰዋል፡፡
አንድ ሐኪም ለስንት ሰው ማለት ነው?
ውይይ! በጣም ትንሽ ነው፡፡ 40ዎቹን ሐኪሞች ለኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር ማካፈል ነው፡፡ 80 ሚሊዮን ሕዝብ ለ40 ሲካፈል በጣም ዝቅተኛ ቁጥር ነው፡፡
የአዕምሮ ሕክምናው ለምን በአዲስ አበባ ብቻ ሆነ?
ይኼ እኛንም በጣም የሚያሳስበን ነው፡፡ የሥራ ጫናውም በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ በአገሪቷ ያለው የአዕምሮ ችግር የገጠመው ሰው ሁሉ ወደ አማኑኤል ሆስፒታል ይምጣ ማለት የሚያስኬድ አይሆንም፡፡ የአዕምሮ ችግር ያለበት ሰው እዚህ ይምጣ ቢባል ሥራ መሥራት አይቻልም፡፡ ስለዚህ ችግሩን ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት የአዕምሮ ሕመም በጤና ጥበቃ ሚ/ር ደረጃ ትኩረት እየተሰጠው ነው የሚል እምነት አለን፡፡ አሁን ያለው የአሠራር ሂደት፣ የአዕምሮ በሽታን ከአማኑኤል ሆስፒታል በተጨማሪ በየክፍሉ ባሉ የጤና ተቋማት ሁሉ ከሌላው በሽታ በተጓዳኝ እንዲሰጥ ታቅዷል፡፡ ይህ አሠራር መድሎና መገለሉን ሊቀንስ፣ መቀራረብም ሊጨምር ይችላል፡፡
የተለያዩ ሥልጠናዎችም እየተሰጡ ነው፡፡ በቅርቡ እንኳ 21 ሳይካትሪስቶች በማስትሬት አስመርቀናል፡፡ በየዓመቱም 25 ሳይካትሪስቶች ይመረቃሉ፡፡ ሌሎች ሥልጠናዎችም እየተስፋፉ ነወ፡፡ በኮተቤ ዓለም አቀፍ ደረጃን ያሟላ የአዕምሮ ሕክምና መስጫ ሆስፒታል እየተሠራ ነው፡፡ 60 በመቶው የተጠናቀቀ ስለሆነ በአንድ ዓመት ውስጥ ተጠናቅቆ አገልግሎት ይጀምራል የሚል እምነት አለኝ፡፡

Read 7019 times