Saturday, 04 June 2022 14:27

ከህግ አግባብ ውጭ የታሰሩ ጋዜጠኞች እንዲፈቱ ተጠየቀ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 ለጋዜጠኞች መብት ጥበቃ የሚሟገተው አርቲክል 19 የተሰኘው ዓለማቀፍ ተቋም፤ በኢትዮጵያ ከ20 በላይ ጋዜጠኞችና የሚዲያ ባለሙያዎች መታሰራቸው በእጅጉ እንዳሳሰበው ጠቁሞ፤ በእስር ላይ የሚገኙት ጋዜጠኞችና የሚዲያ ባለሙያዎች በአስቸኳይ እንዲፈቱ መንግስትን ጠይቋል፡፡
መንግስት ለመረጃና ሚዲያ ነፃነት ያለውን ቁርጠኝነት ጋዜጠኞቹን በአስቸኳይ በመፍታት እንዲያረጋግጥና የሚዲያ ሰዎችን ከማዋከብ እንዲቆጠብ አርቲክል 19 ጥሪውን አቅርቧል፡፡      
መንግስት ከሰሞኑ በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ላይ የሚሰሩ ጋዜጠኞችን ህግ ከማስከበር እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር ማድረጉን ተከትሎ ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለ እንደሚገኝ የጠቆመው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት በበኩሉ፤ መንግስት በቁጥጥር ስር ካደረጋቸው ጋዜጠኞች መካከል አሁንም ፍርድ ቤት ያልቀረቡና የታሰሩበት ቦታ የማይታወቁ ጋዜጠኞች መኖራቸው እንዳሳሰበው ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
በቅርቡ የፀደቀውና ተግባራዊ እየተደረገ ያለው የመገናኛ ብዙሃን አዋጅም ሆነ የኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ፤ ጋዜጠኞች ከስራቸው ጋር በተያያዘ ከፍርድ ቤት መደበኛ ክስ በፊት እንዳይታሰሩ ይከለክላል ያለው ም/ቤቱ፤ ከጋዜጠኝነት ስራቸው ጋር በተያያዘ የፈጸሙት የህግ ጥሰትም ሆነ የስነ-ምግባር ግድፈት ካለ በመገናኛ ብዙሃን ፖሊሲውም ሆነ በአዋጁ እውቅና ለተሰጠው የእርስ በእርስ ቁጥጥር ስርዓት ተግባራዊ ማድረጊያ አማራጭ ዘዴ ሊቀርቡና ሊዳኙ ይገባል እንጂ ጋዜጠኞችን አስሮ የምርመራ ጊዜ መጠየቅ በህገ መንግስቱ እውቅና ያገኘውን ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን የሚጋፋ ነው፤ ብሏል፡፡
ጋዜጠኞች በሰሯቸው ስራዎች ሃላፊነት መውሰድ እንዳለባቸውና መጠየቅ እንደሚገባቸው እንደሚያምን የጠቆመው ምክር ቤቱ፤ ሆኖም ከህገ- መንግስት ጀምሮ እውቅና ያገኘው ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን እንዳይጋፋ ህግና ስርአትን በተከተለ መልኩ እንዲሆን አሳስቧል፡፡
በተመሳሳይ የመብቶች ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ) እና 7 የተለያዩ ማህበራት ሰሞኑን ባወጡት የጋራ መግለጫ፤ በኢትዮጵያ በጋዜጠኞች ላይ የዘፈቀደ እስር እየተፈፀመ መሆኑን በመጠቆም፤ ድርጊቱን አውግዘዋል፡፡
 ባለፉት ሁለት ሳምንታት 18 ጋዜጠኞችና የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በድንገተኛ ዘመቻ መታሰራቸውን የጠቀሱት ማህበራቱ፤ ጋዜጠኞች የህግ መተላለፍ ከተገኘባቸው እንደ ማንኛውም ዜጋ በፍትሃዊ የህግ ሂደት ተጠያቂ ሊሆኑ ይገባል ብለዋል። ነገር ግን በየጊዜው የሚደረጉ የጋዜጠኞች እስር በተደጋጋሚ ከህግ አግባብ ውጭ እየተፈጸሙ ነው ሲሉ ተችተዋል።
ይህ የህግ አግባብን ያልተከተለ አሰራር ለህግ የበላይነት፣ ለሚዲያ ነፃነት፣ ለጋዜጠኞች ደህንነትና ለኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት አደጋ የሚጋርጥ በመሆኑ አጥብቀን እናወግዛለን ያሉት ማህበራቱ፤ በእስር ላይ የሚገኙ ጋዜጠኞችና የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በአስቸኳይ ከእስር ተለቀው የህግ የበላይነት እንዲከበር ጥሪ አቅርበዋል።

Read 8387 times