Saturday, 04 June 2022 14:31

መንግስት የሀገሪቱን የዲሞክራሲና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ እንዲያሻሽል ፓርቲዎች አሳሰቡ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

  “ሀገር በህግና ሥርዓት እንጂ በአፈና አትመራም”
                                           
            መንግስት በወንጀል የጠረጠራቸውን ግለሰቦች በህግ አግባብ ብቻ በቁጥጥር ስር እንዲያውል የጠየቁ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፤ መንግስት የሀገሪቱን የዲሞክራሲና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ እንዲያሻሽል አሳስበዋል።
“ሀገር በህግና ስርዓት እንጂ በአፈና አትመራም” በሚል መሪ ቃል በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የጋራ የአቋም መግለጫ ያወጡት እናት ፓርቲ፣ መኢአድ እና ኢህአፓ፤ መንግስት ብዙ ተስፋ የተጣለበትን ለውጥ ወደ ኋላ የሚመልስ ተግባር እያከናወነ ነው ሲሉ ወቅሰዋል፡፡
ብዙ ተስፋ የተጣለበትን ለውጥ ገዥው ፓርቲ መጨረሻውን ለበጎ ሳያውለው እየቀረ ነው ያሉት ፓርቲዎቹ፤ በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ ዲሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶችን እየተደፈጠጡ፣ በምጣኔ ሀብት በኩል ከፍተኛ ማሽቆልቆል እየተፈጠረ እንዲሁም የህዝብን ስነ ልቦና እና ማህበራዊ ግንኙነቶች የሚያቃውሱ ተግባራት እየተከናወኑ ነው ብለዋል፡፡
በሀገሪቱ ታሪክ የመጀመሪያ ነው በሚያስብል ሁኔታ ባለፈው ሚያዝያ ወር ምግብ ነክ ያልሆኑ ሸቀጦች አማካይ የዋጋ ግሽበት 36.6 በመቶ፣ የምግብ ነክ ሸቀጦች ዋጋ ደግሞ 42.9 በመቶ መድረሱን በመግለጫቸው ያወሱት ፓርቲዎቹ፤ በብዙ ምክንያቶች ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውና የመንግስት ሰራተኞች ለከፍተኛ የኑሮ ቀውስ ተዳርገዋል ብለዋል፡፡
የሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት ክፉኛ በመቃወሱ በርካቶች ድርጅቶቻቸው እየተዘጉ ከስራ ውጪ መሆናቸውን፣ የግብርና ግብዓቶች ዋጋ በእጅጉ መጨመሩንና ገበሬው ላይ ጫና ማሳደሩን፣ ይህም በቀጣይ ቀውሱን ለመፍታት የሚደረግን ጥረት አዳጋች እንደሚያደርገው ጠቁመዋል - መንግስት ችግሩን ለመፍታት ዳተኝነት እያሳየ መሆኑን በመግለጽ፡፡
ህብረተሰቡ በኢኮኖሚ አቅሙ እየተዳከመ መሆኑ ሳያንስ ስነ ልቦናውንና ማህበራዊ መስተጋብሩን በሚያናጋ መልኩ በተለይ በአዲስ አበባ የነገ አገር ተረካቢ ተማሪዎች ላይ አዲስ ማንነትን ለመጫን የሚደረግ ጥረት መኖሩን ጠቁሟል- መግለጫው፡፡
ይህም ሁኔታ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ተረጋግተው እንዳይማሩ እያደረገ መሆኑን የጠቆመው የፓርቲዎቹ መግለጫ፤ ከዚህ ባሻገር አዲስ አበባ ላይ የመኪና ስርቆት፣ ግድያና አፈናን የመሳሰሉ ወንጀሎች እየተበራከቱ መሄዳቸው አሳሳቢ መሆኑን አመልክቷል፡፡
በሌላ በኩል፤ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ያልተቋጨው ጦርነት የትግራይ፣ የአማራና አፋር ክልሎችን እያዳከመ መሆኑን፣ አካባቢው በዚህ ሁኔታ ላይ ባለበት በአማራ ክልል ህግ ማስከበር በሚል የተጀመረው ዘመቻ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚያስፈልገው መሆኑን ፓርቲዎቹ ጠቁመዋል፡፡
#በአሁኑ ወቅት በአማራ ክልል እየተደረገ ያለው መንግስታዊ አፈና የማህበረሰብን ቅስም መስበር፣ የሀይል ሚዛንን ማስጠበቅ፣ አጉል የስልጣን ስጋት፣ መሪ ማሳጣትና በዚህ አጋጣሚ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን፣ ምሁራንን፣ ጋዜጠኞችንና የማህበረሰብ አንቂዎችን የማሳደድ ተግባር ነው; ብለዋል፤ በመግለጫቸው፡፡
ፓርቲዎቹ ባወጡት ባለ 8 ነጥብ አቋማቸው፤ መንግስት ማህበረሰቡን በሀይማኖት በወንዝና በቡድን እየከፋፈለ ለመምታትና ለማፈን የሚያደርገውን ጥረት እንዲያቆም፣ የህግ ማስከበር እርምጃዎች በራሳቸው ህግን ያከበሩ እንዲሆኑ ጠይቀዋል።
በህግ ማስከበር ሰበብ የታሰሩ ያሏቸው ጋዜጠኞች፣ የማህበረሰብ አንቂዎች፣ ፋኖዎች፣ ምሁራን፣ የፀጥታ ተቋማት አባልና አመራሮች እንዲለቀቁ፤ መንግስት በወንጀል ጠርጥሬያቸዋለሁ ካለም ህጋዊ መንገዶችን ተከትሎ ለፍትህ እንዲያቀርብ ጥሪ አቅርበዋል። በተጨማሪም መንግስት በፋኖ ላይ የያዘውን አቋም መልሶ እንዲፈትሽም ጠይቀዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ህልውናን የሚያጠፉ ያልተገቡ አካሄዶች እንዲታረሙ፤ የኑሮ ውድነትን የሚቀርፉ ማሻሻያዎችና ስልቶች እንዲነደፉም ፓርቲዎቹ በአፅንዖት አሳስበዋል።


Read 8676 times