Saturday, 04 June 2022 14:51

መዥገር ቁምነገረኛ እንዲባል ቁርበት ላይ ተጣብቆ ይሞታል!

Written by 
Rate this item
(5 votes)


              ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ንጉሥ ባለሟሎቻቸውንና የቅርብ አማካሪዎቻቸውን ሰብስበው፤ ዙፋን ችሎት ላይ፡-
“እስቲ በመንበሬ ዙሪያ ችግር ካለ ምንም ይሁን ምን፣ ሀሳባችሁን ግለጹልኝ?” አሉ።
አንደኛው ሹም ተነስተው፤
“ንጉሥ ሆይ፣ አንድ ሠላሳ አጋሠሥ ቢገዛ ጥሩ ነው” አሉ።
ንጉሡም፣
“ለምን አስፈለገ?” ሲሉ ጠየቁ።
ሹሙም፣
“በእርሶ ዙሪያ ያሉ መኳንንቶችን “እሺታ!” እንድንጭንበት ነው። ሁሌ “እሺ” እንባላለን የጠየቅነው ግን በሥራ ላይ አልዋለም”
ንጉሥ፣
“ገብቶናል። አፈንጉሥ ይሄንን አስፈጽመህ፣ ውጤቱ በጽሁፍ ይድረሰኝ” አሉ።
“ሌላስ?” አሉና ጠየቁ።
ቀጥሎ ሌላው የተከበሩ ባለሟል ድንገት ብድግ አሉና፤
“ንጉሥ ሆይ!
በዙሪያዎ ብዙ ጅቦች ሾመዋልና ቢጠነቀቁ ጥሩ ነው። እኔ የቆየሁ ባለስልጣንዎ ነኝ። እንግዲህ የሥጋቴን ያህል ሀሳቤን ገልጫለሁ።” አሉ።
ንጉሥ፤
“እሺ፣ በዚህ ላይ ሀሳብ ወይም አስተያየት ያለው አለ?” ሲሉ ጠየቁ።
ይሄኔ ከአዲሶቹ ተሿሚዎች አንዱ፤
“ንጉሥ ሆይ!
እንደተባለው እኛስ አዳዲስ ጅቦች መጥተናል እሺ። ግን አንድ አሮጌ አህያ ለስንታችን ሊሆን ነው? ያውም እርስዎን ደስ እንዲልዎ እንብላው ካልን!” አሉ።
አዳዲሶቹ ሹማምንት አጨበጨቡ።
ንጉሡ ሳቁና፤
“መልካም በዙፋኔ ዙሪያ ያላችሁ ባለሟሎቼ ሁላችሁም ለኔው ክብር እንደምትዋጉ አውቃለሁ። ተስማምታችሁና ተግባብታችሁ ትቀጥላላችሁ። ለሁለታችሁም፣ ሳያዳሉ ጸጥታ የሚያስከብሩ ኃይሎች መኖራቸውንም አትርሱ - አደራ!” ብለው ምክራቸውን ለገሱ ይባላል።
***
በማንኛውም አገር የለውጥ ሂደት ውስጥ የነባር ሥርዓትና አዲስ ሥርዓት መምጣትና መጋጨት የተለመደ ሂደት ነው። በተለይም ደግሞ አሮጌው ጨርሶ ዕቃውን ሳያወጣ፤ አዲሱ ዕቃውን ሙሉ በሙሉ ሳያስገባ በሚፈጠረው የሽግግር እንጥልጥሎሽ ወቅት፣ መናቆር፣ መፋጠጥ፣ ከታደሉም ዲሞክራሲያዊ ውይይት የማድረግ እንቅስቃሴ ውስጥ መግባት አዘውትረን ያየነው ሁነት ነው። የመንግሥት ጠንክሮ መቆም የሚታሰበውም እዚህ ላይ ነው።
ነጋድራስ ገ/ህይወት ባይከዳኝ የሚሉትን ማዳመጥ በእጅጉ ይጠቅማል። እነሆ፡-
“የሚበላውን እና የሚለብሰውንም ያጣ ድኻ፣ የተወለደበትን አገር የሚወድበትን ምክንያት ያጣልና ያገሩ መንግስት ቢበረታ ወይም ቢጠፋ ግድ የለውም። ስለዚሁም መንግሥት የሚጠቀምበት፤ ያገሩ ሀብት በጥቂቶች ሰዎች እጅ ሲሰበሰብ፣ አይደለም። ያገሩን ሀብት በመላው ህዝቡ ሲከፋፈለው ነው እንጂ። የሀብታሞች አኗኗርና የሰራተኛው አኗኗር ዐይነቱ እንበል-መጠን የሚራራቅበት አገር፣ መንግስቱ ከጥፋት አፋፍ እንደደረሰ ያስረዳል። የኢትዮጵያንም ህዝብ ሁኔታ ብንመለከት እንደዚሁ ያለ ጥፋት እንዳይደርስ ያስፈራል” ይላሉ።
 ይህንን ያሉት ከአራት-አምስት አሥርት ዓመታት በፊት ነበር። በደጉ ጊዜ እንደማለት ነው። ከዚያ እስከዚህ ድረስ መንግስታት ተለዋውጠዋል። ድርጅቶች ፈርሰዋል። ድርጅቶች ተፈጥረዋል። በፖለቲካ ድርጅቶች ውስጥ መከፋፈሎች ተካሂደዋል። አንጃዎች ተመስርተዋል። ቀኝና ግራ ዘመም ተባብለው ተገዳድለዋል። ይህን የሚገልጥልን የሀገራችን ጥሩ ተረት፤
 “ትዋደዳላችሁ? በጣም።
ትጣላላችሁ? ይሄማ ቁም-ነገራችን!” የሚለው ነው።
በመንግስትም በኩል የሚያደርጋቸውን ድርድሮች፣ ስምምነቶች፣ ሚስጥሩን ቢናገርና አገር እስካልጎዳ ድረስ፣ ለህዝብ ቢያሳውቅ መልካም ነው። አለበለዚያ “የሹክሹክታ ጋብቻ፣ ለፍቺ ያስቸግራል” እንደሚባለው እንዳይሆን አስቀድሞ ማሰብ የተሻለ ይሆናል። በዚሁ ላይ የአድር-ባዮች፣ አጨብጫቢዎችና የወሬ አቀባዮች እክል ሲጨመርበት በዕንቅርት ላይ ጀሮ ደግፍ ይሆናል። ያም ሆኖ የእንዲህ ያሉቱ ዕጣ-ፈንታ እንኳ ምን እንደሆነ ከወዲሁ እየታዘብን ነው። ትውፊቱ እንደሚነግረንም፤
“አንዲት የቤት እንስሳ፣ በውልደቷ የጣር ሰሞን
 ልጇን ትበላለች አሉ፣ ምጥ የጠናባት እንደሆን!” የሚለው ግጥም ውስጥ ያለ ነው። የአገልጋይነት እና ሎሌነት አስተሳሰብ የቆየ ካንሰር- አከል በሽታ ነው በሀገራችን። የተለያየ ቀለም ይቀባል እንጂ ጌታ ካለ ሎሌ መኖሩ፣ አሌ የማይባል ሀቅ ነው። ሎሌ ለጊዜው ቢመቸው ወይም ቢሾም እንኳ ከታዛዥነት አይወጣም። አበሻ ሲተርት፤ “ጫማ ምን ክብር ቢኖረው፣ ሁል ጊዜ እግር-ስር ነው!” የሚለው ይሄንን ነው። ያም ሆኖ መላ-ነገሩን ስንመለከተው፣ ፖለቲካዊ ጭቆናን ከመፈጸምና ኢኮኖሚያዊ ብዝበዛን ወይም ሌብነትን ከመፈጸም አንጻር፣ “መዥገር ቁምነገረኛ እንዲባል ቁርበት ላይ ተጣብቆ ይሞታል! “ የሚለው አባባል በአመርቂ ሁኔታ ይገልጸዋል። ከዚህ ይሰውረን!Read 11838 times