Saturday, 04 June 2022 15:04

ይድረስ ለሼህ ሙሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ፡- ሚድሮክ “የውጭ አልጋ የቤት ቀጋ” ሆኖብናል - ይድረሱልን!

Written by 
Rate this item
(2 votes)

  ክቡር ሆይ!
በቅድሚያ የአክብሮት ሰላምታ አቀርባለሁ። ዛሬ ይህቺን ጦማር በአዲስ አድማስ ጋዜጣ በኩል እንድጽፍልዎ ግድ ያለኝ በእኔ በራሴ ላይ፣ በሌሎች ሰራተኞች ላይ እንዲሁም በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ አባል ኩባንያዎች ላይ እየደረሰ ያለውን እውነታ ክቡርነትዎ እንዲያውቁትና ከአላህና ከመንግስት በታች ውሳኔ እንደሚሰጡን በማሰብ ነው፡፡
ይህ ጽሁፍ አራት ክፍሎች አሉት። ክፍል አንድ መግቢያ ሲሆን፤ የሚድሮክ ኢንቨስትመንትና አስተዋጽዖ ምን እንደሆነ በአጭሩ ለመዳሰስ ይሞከራል፡፡ ከዚሁ በመቀጠል እኔ የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ ማን እንደሆንኩና ይህንን ጽሁፍ ለመጻፍ ለምን እንደተነሳሳሁ በእኔ ላይ የደረሰውን በደል ለክቡርነትዎና ለአንባብያን በሚመጥን መልኩ ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡ ክፍል ሦስት ትኩረት የሚያደርገው በእኔን መሰል ግፉአን የሚድሮክ ሰራተኞች ዙሪያ ይሆናል፡፡ አዲሱ “የሚድሮክ” አመራር እኔን ብቻ ሳይሆን ሚድሮክን ለረጅም ዓመታት ያገለገሉ (Memory of MIDROC ሊባሉ የሚችሉ) በርካታዎችን በሁለት መስመር ደብዳቤ እንደ አሮጌ ቁና ወርውሯቸው በረንዳ አዳሪና ለማኝ አድርጓቸዋል፡፡ ይህንን ጽሁፍ እንድጽፍ ዋነኛ ገፊ ምክንያት የሆነኝ በእኔ ላይ የደረሰው በደል ብቻ ሳይሆን በእነዚህ የስራ ባልደረቦቼ ላይ የደረሰው ግፍና መከራ ስለሆነ፤ በክፍል ሁለት ጽሁፌ ሰፋ ያለ መረጃ ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡
አሁን በአቶ ጀማል አህመድ ፊት አውራሪነት የሚመራው የሚድሮክ ሊደርሺፕ ጉዳት እያደረሰ ያለው በእኔና በሰራተኞች ላይ ብቻ አይደለም። የሚድሮክ ኢንቨስትመንቱም እየተጎዳ ነው። ቀደም ሲል ሚድሮክ “ሜቴክን” ሆኖ ነበር። አሁን ደግሞ “ስኳር ኮርፖሬሽንን ሆኗል” እየተባለ ይታማል፡፡ በክፍል ሦስት ጽሀፌ፣ አሁን ያለው የሚድሮክ አመራር እየወሰዳቸው ባሉ የተሳሳቱ ግብታዊ እርምጃዎች ምክንያት በሚድሮክ ኩባንያዎች ላይ ጥፋት እየደረሰ በመሆኑ፣ ይህንን በተመለከተ ህዝብም፣ መንግስትም፣ ባለ ሃብቱም ማወቅ አለባቸው ብዬ ያሰባሰብኳቸውን መረጃዎች ለማሳየት እሞክራለሁ፡፡
ከዚሁ ጋር በማያያዝ ህዝብና መንግስት ይህንን ሁሉ የመሬት ሃብት ለሚድሮክ የሰጠው ሀገርና ህዝብን ተጠቃሚ ያደርጋል ብሎ ነው። ሚድሮክ ያን ሁሉ ሃብት ይዞ የእንቁላል፣ የጥራጥሬ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ፣… ዋጋ ጣሪያ መንካት ነበረበት? ሚድሮክ በተሰጠው መሬት ያለማው ውጤት ምንድነው? በዋጋ ማረጋጋት ዙሪያ ምን ሚና ተጫወተ? ወዘተ. የሚሉት ጥያቄዎች በዚሁ በክፍል 3 ጽሁፌ ይዳሰሳሉ፡፡
ክፍል አራት የመፍትሄ ሀሳቦች የሚቀርቡበት ነው፡፡ እንደ እኔ ያለ ለረጅም ዓመታት በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ስር ባሉ ኩባንያዎችና በኮርፖሬት ሊደርሺፕ ደረጃ የሰራ ሰው ልዩ ልዩ ችግሮችን በመዘርዘር ብቻ ጽሁፉን ሊደመድም አይገባውም ብዬ አምናለሁ፡፡ በመሆኑም፤ ሚድሮክን እግር ተወርች ቀፍድደው የያዙት ዋና ዋና ችግሮች ምን ምን ናቸው? የሚድሮክ ሊቀ መንበር እንደመሆንዎ (እንደ የበላይ አመራርነትዎ) እነዚህን ችግሮች ለማስወገድ በእርስዎ በባለሃብቱ በኩል ምን ምን እርምጃዎች ሊወሰዱ ይገባል?... የሚሉትን ጥያቄዎች የሚመልሱ የመፍትሄ ሃሳቦችና ምክረ ሃሳቦች የሚቀርብ ይሆናል፡፡ በዚሁ መሰረት በዛሬው ክፍል አንድ ጽሁፌ ትኩረት ወደማደርግበት ጉዳይ እናምራ…
ሚድሮክ እና ሼህ አላሙዲ ምን አደረጉ?
ክቡር ሆይ!
ወደ እኔ ጉዳይ ከመግባቴ በፊት ሚድሮክ በሀገራችን ስላከናወናቸው ተግባራት በአጭሩ ማውሳት እወዳለሁ፡፡ እንደሚታወቀው ሼህ ሙሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት የጀመሩት ከደርግ ውድቀት በኋላ ነው፡፡ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ ተቋቁሞ በደርግ መንግስት ይዞታ ስር የነበሩ የልማት ድርጅቶችን መሸጥ ሲጀምር ሼህ ሙሐመድ አክሳሪና ሊዘጉ የተቃረቡ ተቋማትን በመግዛት በርካታ ኢትዮጵያውያንን ከስራ አጥነትና ከበረንዳ አዳሪነት አድነዋል፡፡ ተጨማሪ አዳዲስ ኩባንያዎችንም በማቋቋም ኢንቨስትመንታቸውን አስፋፍተዋል፡፡ የሥራ እድል ፈጥረዋል፡፡
ከኢንቨስትመንቱ በተጨማሪ በበጎ አድራጎት ስራቸው የሚታወቁት ሼህ ሙሐመድ በአሁኑ ወቅት በመላ ሀገሪቱ ከ80 በላይ ኩባንያዎች አሏቸው፡፡ በእነዚህ ኩባንያዎችም በአጠቃላይ እስከ 100 ሺህ የሚደርሱ ቋሚ፣ ጊዜያዊና የኮንትራት ቅጥር ሠራተኞች የሥራ እድል አግኝተዋል ተብሎ ይገመታል፡፡ ይህም የሰው ኃይል ሼህ ሙሐመድን ከመንግስት ቀጥሎ ብዙ የሥራ እድል የፈጠሩ ባለሃብት ያደርጋቸዋል፡፡
ሼህ ሙሐመድ ያከናወኑትን ሀገራዊ በጎ ተግባራት ዘርዝሮ ለመግለጽ አስቸጋሪ ቢሆንም ከሌሎች ባለሀብቶች ለየት የሚያደርጋቸውን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በብዙዎች ዘንድ “የቁርጥ ቀን ልጅ” እየተባሉ የሚጠሩት ሼህ ሙሐመድ ሸራተን ሆቴልን የሰሩት በእንግዳ ተቀባይነቷ በምትታወቀው ሀገራችን የሀገር መሪዎች ማረፊያ አጥተው ወደ ጎረቤት ሀገር ሄዱ እንዳይባል፤ የሀገር ገጽታ እንዳይበላሽ በማሰብ ነበር፡፡
ሸራተን ሆቴል በተሰራበት አካባቢ ለነበሩ አምስት መቶ አባወራዎች በሲኤምሲ መንገድ በተለምዶ አልታድ ሚካኤል የሚባለው አካባቢ ቤት ሰርተው በነፃ ሰጥተዋል፡፡ በወልዲያ ከተማ የዳሸን ባንክ ህንፃ በተሰራበት አካባቢ ለተነሱ የከተማዋ ነዋሪዎች “ሚድሮክ” የተሰኘ መንደር መስርተው፣ ቤት ሰርተው በነፃ ሰጥተዋል፡፡ በቆሼ አደጋ ለደረሰባቸው፣ በሶማሌና በኦሮሚያ በተከሰተው ግጭት ለተፈናቀሉ፣… እርዳታና ድጋፍ አድርገዋል፡፡ በኦሮሚያ፣ በአፋርና በደቡብ ክልሎች በድርቅ ምክንያት እንስሳት እንዳያልቁ መኖ አቅርበዋል፡፡ የሚድሮክ ኩባንያዎች ባሉበት አካባቢ ለሚገኙ ማህበረሰቦች መንገድ፣ ት/ቤት፣ ውሃ፣ መብራት፣… እንዲገባ አድርገዋል፡፡ የሀገር ሀብት የሆኑ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎችንና ታዋቂ ግለሰቦችን በተለያየ ጊዜ አሳክመዋል፡፡ በምግብ እጦት ምክንያት አዙሯቸው እየወደቁ መማር ለተቸገሩ በሺህ የሚቆጠሩ ተማሪዎች መመገቢያ የሚሆን በዓመት 26 ሚሊዮን ብር በጀት መድበዋል፡፡ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት ከመንግስት ጎን ቆመዋል፡፡ በዚያው ወቅት ለተከሰተው ድርቅና ርሃብም እህል ወደ ኢትዮጵያ እንዲገባ በማድረግ ወገናቸውን ታድገዋል። ሀገሪቱ የዶላር እጥረት ሲያጋጥማት በመቶ ሺህ የሚቆጠር ዶላር አስመጥተው ዳሸን ባንክ እንዲቀመጥ በማድረግ ወቅታዊ ችግሩ እንዲፈታ ጥረት ማድረጋቸው ይታወቃል፡፡ ለህዳሴ ግድብ ግንባታ በአንድ ጊዜ ያዋጡት አንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር ለሌሎች ባለ ሀብቶችና ዜጎች ትልቅ የሞራል ብርታትና መነሳሳት መፍጠሩ ይታወቃል፡፡ ሁለተኛው ሚሊኒየም ሲከበር በስድስት ወራት ውስጥ የሚሊኒየም አዳራሽን አስገንብተው ለበዓሉ እንዲደርስ አድርገዋል። በአንድ ወቅት የአፍሪካ ህብረትን ዋና ከተማ ከኢትዮጵያ ለማንሳት ሲዶለት ለመሪዎች የሚሆን ምቹ የትራንስፖርት አቅርቦት ለመስጠት በሁለት ሳምንት ውስጥ 60 ዘመናዊ መርሰዲስ አውቶሞቢሎችን በአውሮፕላን አጓጉዘው በማምጣት ለመንግስት መስጠታቸውና ያንን ክፍተት መሙላታቸው ታሪክ የመዘገበው ሀቅ ነው፡፡
ሼህ ሙሐመድ ያከናወኗቸው ሀገራዊ አሻራ የታተመባቸው ተግባራት በርካታ ናቸው፡፡ ለማስታወስ ያህል እነዚሁ ይበቃሉ። እነዚህ ሁሉ በጎ ተግባራት ለሚወዷት ሀገራቸው ያደረጉት እንጂ ተጨማሪ ሀብት የሚፈጥርላቸው ኢንቨስትመንት አልነበረም። “የችግሮች መፍቻ ታግሎ መስራት፣ ተስፋ አለመቁረጥ፣… ነው” የሚሉት ሼህ ሙሐመድ፤ “ለምንድነው በሀገርዎ ላይ መዋዕለ-ንዋይ ማፍሰስ የሚወዱት?” ተብለው ሲጠየቁ የሚሰጡት መልስ፤ “ምኞቴ በሀገሬ በየወሩ አንድ አንድ ፋብሪካ መክፈት ነበር… የሀገሬ ወጣቶች ሀገራቸውንና ራሳቸውን ጠቅመው በዓለም ታዋቂ እንዲሆኑ ነው ፍላጎቴ፡፡ በሀገር ቤት ያሉ ኩባንያዎቼ ከሚያፈሩት ሀብት 5 ሣንቲም ወስጄ አላውቅም፡፡ እዚያው በዚያው ኢንቨስትመንት እንዲያስፋፉና ብዙ ወጣቶች የሥራ እድል እንዲያገኙ ነው ምኞቴ” ነው የሚሉት ሼህ ሙሐመድ፡፡
ተደጋግሞ እንደሚነገረው የሼህ ሙሐመድ ኢንቨስትመንት በትርፍ ላይ የተመሰረተ ኢንቨስትመንት አይደለም፡፡ ይህንን በተመለከተ ዶ/ር አረጋ ይርዳው "የፒራሚዱ ጫፍ" በሚለው መጽሐፍ፤ “የሙሐመድ ዓላማ ወገንን መርዳት ነው፡፡ ደካማ ሰራተኛ ቢሆን እንኳ ሊሰራው ወደሚችለው ስራ እንዲዛወር ይደረጋል እንጂ አይባረርም፡፡ ‘ተውት፡፡ ገለል አድርጉት እንጂ ደመወዙን አትከልክሉት’ ነው የሚለው ሙሐመድ…” የሚል ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡
እኚህ ኢትዮጵያን ወዳድ፣ እኚህ ወገናቸውን አፍቃሪ ደግ ሰው፣ እንዲህ ያለ ሰብእና እያላቸው በአቶ ጀማል አህመድ ፊት አውራሪነት አሁን ሚድሮክን የሚመራው ኃይል ሰራተኛውን የሚያምሰው ለምን ይሆን? መቼም ሩህሩሁና ደጉ ሼህ ሙሐመድ “ሰራተኛ አባሩ፣ የራሳችሁን ኢምፓየር ገንቡ” የሚል መመሪያ ሰጥተው እንዳልሆነ ሙሉ እምነት አለኝ፡፡
ክቡር ሆይ!
ወደ ራሴ ጉዳይ ልለፍ… ብዙ ጊዜ ስለሌሎች የማውቀውን ምስክርነት መስጠት እንጂ ስለራሴ መናገርም ሆነ መጻፍ አልወድም፡፡ ያደግኩበት ማህበረሰብም እንዲህ ያለውን “እኔ - እኔ - እኔ…” ማለትን እንደ “አላስፈላጊ መቅለብለብ” የሚቆጥር በመሆኑ ስለራሴ በግልጽ የመናገር ድፍረት አልነበረኝም። በዚህም ምክንያት ራሴን ባለመግለጼ በበርካታ አጋጣሚዎች ያጣኋቸው በረከቶች ብዙ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ፤ ቀደምት አበው “ካለመናገር ደጃዝማችነት ይቀራል” ያሉት ያለ ምክንያት ስላልሆነ፣ እነሆ ዛሬ ይህንን ሁሉ ድንበር ጥሼ ስለ ራሴ “በትንሹ” ለመናገር እወዳለሁ፡፡
አብዱራህማን አህመዲን እባላለሁ፡፡ የተወለድኩት በሰሜን ወሎ፣ በየጁ አውራጃ፣ በሐብሩ ወረዳ፣ “ጊራና” በምትባል የአርሶ አደር መንደር ነው፡፡ በእድሜዬ ጎልማሳ ሆኛለሁ፡፡ ባለ ትዳርና የአራት ልጆች አባት ነኝ፡፡ ሁለተኛ ዲግሪ ድረስ ተምሬያለሁ፡፡ በተለያዩ የግልና የመንግስት መስሪያ ቤቶች፣ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ከ27 ዓመታት በላይ በስራ ዓለም አሳልፌያለሁ። ፖለቲከኛም ነበርኩ፡፡
ኢዴፓን በመመስረት ከፍተኛ አመራር አባል በመሆን አገልግያለሁ፡፡ በምርጫ 97 አሸንፌ የፓርላማ አባልም ነበርኩ፡፡ ከፓርቲ አባልነት ከለቀቅሁ 12 ዓመታት ተቆጠሩ፡፡ ከሰኔ 2002 ዓ.ም ወዲህ የየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ አባል አይደለሁም፡፡ በሀገሬ ጉዳይ ግን ባገኘሁት አጋጣሚ ሁሉ ሃሳቤን አካፍላለሁ፡፡
በሚድሮክ ውስጥ - በዶ/ር አረጋ ዘመን
በ2006 ዓ.ም ከዩኒቲ ዩንቨርስቲ በኢኮኖሚክስ በማስተርስ ዲግሪ ከተመረቅኩ በኋላ እንደማንኛውም ስራ ፈላጊ የስራ ቅጥር ማመልከቻ ጽፌ ለሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ ለዶ/ር አረጋ ይርዳው አቀረብኩ። ራሳቸው ዶ/ር አረጋ 45 ደቂቃ የፈጀ ቃለ ምልልስ (Interview) አደረጉልኝ፡፡ ከሳምንት በኋላ ተጠራሁ፡፡ በአልፋልፋ ፕሮጄክት የማርኬቲንግ ኦፊሰር ሆኜ በታህሳስ 2007 ዓ.ም ተቀጥሬ ስራ ጀመርኩ፡፡
አልፋልፋ የተሰኘውን የእንስሳት መኖ ለኢትዮጵያ አርሶ አደሮች ለማስተዋወቅ ባደረግኩት ጥረት በአንድ ዓመት 1 ሚሊዮን ኪሎ ግራም አልፋልፋ ለመሸጥ ቻልኩ፡፡ ሁለት ጊዜ ወደ ውጪ ሀገር ኤክስፖርት አደረግኩ፡፡ በዚህ ስራዬ የተደሰቱት ዶ/ር አረጋ፣ የኤልፎራ የገበያና ሽያጭ አገልግሎት ስራ አስኪያጅ አድርገው ሾሙኝ፡፡ በዚህም ኃላፊነቴ በ5 ወራት ውስጥ የኤልፎራን የእርሻ ምርቶች ወደ ዋናው መ/ቤት አምጥቼ በአትክልት ተራ እና በኩዊንስ ሱፐር ማርኬት በመሸጥ የሚድሮክን ምርቶች ወደ ህዝብ ለማድረስ ብዙ ለውጦችን አስመዘገብኩ። እነዚህ እንቅስቃሴዎቼ የኤልፎራን የምርቶች እዚያው ማሳ ላይ በመሸጥ ለሚያጭበረብሩ ሰዎች የተወደዱ አልሆኑም፡፡ ቀደም ሲል የነበረውን ብክነትና ሌብነት የሚያጋልጥ በመሆኑ እዚያ መቆየቴ አልተፈለገም፡፡
ዶ/ር አረጋ ጠሩኝና “አብዱራህማን ጥሩ እየሰራህልኝ ነው፡፡ ነገር ግን እኛ ቤት ጥሩ የሚሰራ ሰው አይወደድም፡፡ ስምህ እንዲጠፋብኝ አልፈልግም፡፡ ለተወሰነ ጊዜ ወደ ሌላ ኩባንያ ላዛውርህ ነው፡፡ እዚያም የምታስተካክልልኝ ነገር አለ…” አሉኝ፡፡ በዚህ መሰረት ደመወዜን ከፍ በማድረግ፣ የገበያና ሽያጭ ስራ አስኪያጅ አድርገው ወደ ዴይላይት አፕላይድ ቴክኖሎጂስ ኩባንያ አዛወሩኝ፡፡ ዴይላይት 2 ዓመት ገደማ ከሰራሁ በኋላ ዶ/ር አረጋ ወደ ቢሯቸው አስጠሩኝ። “ከፍ ያለ ኃላፊነት ልሰጥህ ነው። ከዚያ በፊት ግን አልፋልፋ ፕሮጄክት ላይ ቀደም ሲል ስለሰራህና የጽሁፍ ችሎታም ስላለህ የአልፋልፋ ፕሮጄክትን ታሪክ የያዘ መጽሄት ማዘጋጀት ስለምፈልግ አንድ ጽሑፍ አዘጋጅ” አሉኝ፡፡ የአልፋልፋ ፕሮጄክትን ታሪክ ከጅማሬ አንስቶ በዚያ ወቅት የደረሰበት ደረጃ ድረስ የነበረውን ሂደት በአንድ ወር ጽፌ አጠናቀቅኩና ለዶ/ር አረጋ አስረከብኩ፡፡
ዶ/ር አረጋ አሁንም አስጠሩኝና የኤልፎራ ምክትል ዋና ስራ አስኪያጅ አድርገው ሊሾሙኝ መሆኑን ነገሩኝ፡፡ ደብዳቤው ሲደርሰኝ ኃላፊነቴን ተቀብዬ ስራ ጀመርኩ፡፡ ወዲያውኑ በኩዊንስ ሱፐር ማርኬት የገበሬዎች መደብር (Farmers Market) እንዲቋቋም ጥረት አደረግሁ፡፡ ኤልፎራ ሁሉም ባገኘው አጋጣሚ ሰርቆ ኪሱን ለማደለብ የሚራወጥበት ተቋም ነው፡፡ ኃላፊነት እንደተረከብኩ የሌብነት ቀዳዳዎችን መድፈን ስጀምር በደመወዛቸው ሳይሆን በዝርፊያ መኖር የለመዱ ሰዎች እየየውነው ያቀልጡት ጀመር፡፡ በዚያ ላይ በኢትዮጵያ የእርሻ ባለሙያ የሌለ ይመስል ዶ/ር አረጋ በርካታ የደቡብ አፍሪካ ዜጎችን ከፍ ባለ ደመወዝ እየቀጠሩ ለእርሻ ስራ ያመጡ ጀመር፡፡ ይሄ ደግሞ በቋፍ ላይ ያለውን ኤልፎራን ወጪ የሚያንርና ለኪሳራ የሚዳርግ በመሆኑ እንዲህ ያለውን ሁኔታ መቀበል አስቸገረኝ፡፡ በመሆኑም፤ በውስጥ ምክክር አልሳካ ሲለኝና ሰሚ ሳጣ “ጥልቅ ተሓድሶ በሚድሮክ መንደር” በሚል ርእስ አንድ ጽሁፍ አዘጋጀሁና በብእር ስም በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ አወጣሁ፡፡ በዚያ ጽሁፍ ዶ/ር አረጋን ስማቸውን ጠርቼ ተቸኋቸው። ጉድለታቸውን አሳየኋቸው፡፡ መፍትሄውን አመላከትኳቸው… ነገር ግን ሰውየው በዚህ አልተደሰቱም፡፡ እናም ከኃላፊነቴ አነሱኝ፡፡ ነገር ግን የጻፍኩት እውነት በመሆኑ ጽሁፉ ተባዝቶ በሁሉም ኩባንያዎች ቦርድ ላይ እንዲለጠፍ አደረጉ፡፡ እኔንም ከመቅጣት ይልቅ ወደ ራሳቸው ቀረብ በማድረግ የህዝብ ግንኙነት አማካሪ አድርገው አስቀመጡኝ፡፡
ያ ወቅት በየአካባቢው ወጣቶች በመላ ሀገሪቱ ህዝባዊ እንቅስቃሴ የሚያደርጉበት ወቅት ስለነበር ብዙ የተለፋበት የአልፋልፋ ፕሮጄክትን ጨምሮ በርካታ የሚድሮክ እርሻዎች ችግር ውስጥ የገቡበት ወቅት ነበር፡፡ የእኔ ስራና ኃላፊነት ደግሞ እርሻዎች የሚገኙባቸውን የመንግስት አካላት፣ እርሻዎቹ የሚገኙባቸውን ማህበረሰቦች እና የሚድሮክ ኩባንያዎች መልካም ግንኙነት እንዲኖራቸው የህዝብ ግንኙነት ስራ መስራት ነበር፡፡ በዚያ ወቅት በርካታ የሚድሮክ እርሻዎች በወጣቶች ተቃጥለው፣ በርካታ ንብረት ወድሞ፣ ሃብትና ንብረት ተዘርፎ ስለነበር በየአካባቢው እየሄድኩ መረጃዎችን በማሰባሰብ ክስ እንዲመሰረት አደረግኩ፡፡ ብዙ አጥፊዎች ታሰሩ፣ ተቀጡ… ተጨማሪ ጥፋት እንዳይከሰት በተለይም በኦሮሚያ ከየአካባቢው የሀገር ሽማግሌዎች እና ከአባ ገዳዎች ጋር በመሆን ብዙ የመከላከል ስራ ተሰራ፡፡ ነገሌ ቦረና፣ መልጌ ወንዶ፣ ሻሸመኔ፣ ሀዋሳ፣ ወንጂ፣ ኩሪፍቱ፣ አዳማ፣ ሞጆ፣ መተሃራ፣ ቆቃ፣ አሰላና ወደ ሌሎችም አካባቢዎች በመሄድ የኤልፎራ፣ የጂቱ፣ የዋንዛ ኩባንያ መሬቶች በአካባቢ ወጣቶች እንዳይወሰዱ ጥረት አድርጌያለሁ። በዚሁ ወቅት ሁለት ሦስት ጊዜ የጥይት እሩምታ ወርዶብኛል፡፡ መንገድ ተዘግቶብኛል። የመኪናዬ ጎማ እንዲፈነዳ ተደርጓል፡፡ ዛቻና ማስፈራሪያውም ብዙ ነው። ሁሉንም እንደአመጣጡ እያስተናገድኩ ከዶ/ር አረጋ እና ከአቶ ጌታቸው ሓጎስ ጋር በመመካከር በርካታ ተግባራትን ያከናወንኩ ቢሆንም የተጀመሩ ስራዎች ሳይጠናቀቁ ዶ/ር አረጋ ከኃላፊነት ተነሱ፡፡
በሚድሮክ ውስጥ - በአቶ ጀማል ዘመን
ዶ/ር አረጋ ከኃላፊነት ከተነሱ በኋላ አቶ ጀማልን የሚያውቅ ሰው ስለ እኔ ለአቶ ጀማል ነገራቸው፡፡ ራሳቸው አቶ ጀማል ደወሉልኝ። የትምህርና የስራ ልምዴን በኢሜይል ላኩላቸው። ማስረጃዎቹን ካዩ በኋላ ወደ ቢሯቸው እንድመጣ ቀጠሮ ያዙልኝ፡፡ በጥሩ መንፈስ አነጋገሩኝ፡፡ በመጨረሻም ወደ እርሳቸው ቢሮ እንደሚወስዱኝ ነግረውኝ ተለያየን፡፡ መስከረም 10 ቀን 2013 ዓ.ም ከአቶ ጀማል በተጻፈ ደብዳቤ ኤልፎራን ለቅቄ የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የቢዝነስ ዴቨሎፕሜንት ስራ አስኪያጅ ሆኜ ተሾምኩ፡፡ ናኒ ህንፃ 7ኛ ፎቅ ቢሮ ተሰጠኝ፡፡
ወደ አቶ ጀማል ቢሮ ከተዛወርኩ በኋላ በአራት ወራት ውስጥ የስራ መደቤ ሦስት ጊዜ ተቀያይሯል፡፡ ደመወዜም በ3 ወራት ጊዜ ውስጥ ሦስት ጊዜ ጭማሬ ተደርጎልኛል፡፡ የቢዝነስ ዴቨሎፕሜንት ስራ አስኪያጅ፣ የቢዝነስ ዴቨሎፕሜንት ዳይሬክተር በመጨረሻም የኮሙኒኬሽንና ፕሮሞሽን ኮርፖሬት ዳይሬክተር ሆኜ ደመወዜም ብር 55,500.00 ሆኖ እንድሰራ ታህሳስ 19 ቀን 2013 ዓ.ም የተጻፈ ደብዳቤ ተሰጥቶኛል፡፡
ኃላፊነቱ ከተሰጠኝ በኋላ ባደረግኩት የስራ እንቅስቃሴ ለ35ቱ ኩባንያዎች የገበያና ሽያጭ ኃላፊዎች ስልጠና በመስጠት ኩባንያዎቹ ተናበው፣ ተቀናጅተውና ተደጋግፈው (Synergy ፈጥረው) እንዲሰሩ አድርጌያለሁ፡፡ የ35ቱን ኩባንያዎች የ5 ዓመት ስትራቴጂክ ፕላን ረቂቅ ሰነድ ከሌሎች ጋር በመሆን (ኮሚቴውን በመምራት ጭምር) አዘጋጅቻለሁ፡፡ ከETV ጋር ውል በመፈራረም በየሳምንቱ ረቡዕ ማታ ከምሽቱ 3፡30 – 4፡00 ሰዓት በቴሌቪዥን ጣቢያው ለሚቀርቡ ፕሮግራሞች ፎርማት በመቅረጽ ስራ አስጀምሬያለሁ፡፡ ሌላው ቀርቶ እስከ አሁን ድረስ በETV የሚድሮክ ፕሮግራም መሸጋገሪያ ሙዚቃ ራሴ በመፍጠር አበጋዙ ሽኦቶን በማሰራት የሚድሮክ ልዩ መታወቂያ (icon, symbol) የሆነ በመሳሪያ የተቀነባበረ ሙዚቃ በማዘጋጀት፣ ያ ሙዚቃ ሲሰማ፣ ሁሉም ሰው ሚድሮክን እንዲያስታውስ ለማድረግ ጥረት አድርጌያለሁ።
በፋና ሬዲዮ የሚተላለፈው ፕሮግራምና ማስታወቂያ ፎርማትም እኔ ያዘጋጀሁትና ስራውንም ያስጀመርኩት እኔ ነኝ። የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዌብ ሳይት ዲዛይንም ያሰራሁት፣ በዌብ ሳይቱ ላይ የሚድሮክን ታሪክ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የጻፍኩትና ዜናዎች በየጊዜው እንዲወጡ ስራውን ያስጀመርኩት እኔ ነኝ፡፡
እቅድ አውጥቼ እነዚህን ስራዎች በከፍተኛ ተነሳሽነትና የኃላፊነት ስሜት ለአምስት ወራት እንደሰራሁ በሚያዝያ ወር መጀመሪያ ላይ (2013 ዓ.ም) በኮቪድ ተያዝኩና ሆስፒታል ገባሁ፡፡ ይሁን እንጂ በቴሌቪዥንና በሬዲዮ የሚተላለፉ የ3 ወር ፕሮግራሞችንና ማስታወቂያዎችን ቀድሜ አሰርቼ ያዘጋጀሁ በመሆኑና እኔን ተክቶ የሚሰራ ሰራተኛ ቀጥሬ ስለነበር፣ እኔ ብታመምም የምመራው የስራ ክፍል ስራዎች ሳይስተጓጎሉ ለመቀጠል ችለዋል፡፡
ክቡር ሆይ!
በዚህ መልኩ ሚድሮክ የጣለብኝን ኃላፊነት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳልል፣ በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት ከሰባት ዓመታት በላይ ሳከናውን የቆየሁ ሲሆን መስሪያ ቤቴም ለስራ ትጋቴ የሚመጥን ደረጃና ደመወዝ ከፍሎኛል፡፡ በሂደቱም በቅርብ አለቆቼም ይሁን በበላይ ኃላፊዎች ምንም ዓይነት ቅጣት ተቀጥቼ አላውቅም፡፡ በስራ አፈጻጸሜም የተመሰገንኩ ሰራተኛ ነኝ፡፡ ይሁን እንጂ ልክ የዛሬ ዓመት ማለትም ግንቦት 17 ቀን 2013 ዓ.ም ከኮቪድ ህመሜ በአግባቡ ሳልድን፣ የሐኪም ፈቃድ እያለኝ፣… ለስራዬ ቅድሚያ በመስጠት ወደ ቢሮዬ ሄድኩ፡፡ በእለቱ ከሚድሮክ 4 ምክትል ስራ አስፈጻሚዎች (Deputy CEOs) ጋር ቀጠሮ ነበረኝ፡፡ የምመራው ኮርፖሬት የኮሙኒኬሽንና የፕሮሞሽን ዲፓርትሜንት ለሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ አዲስ የስራ ክፍል በመሆኑ ቀጠሮ የያዝኩት ባዘጋጀሁት የዲፓርትሜንቱ መዋቅር ዙሪያ (ከአቶ ጀማል በተሰጠ መመሪያ መሰረት) ከአራቱ የበላይ ኃላፊዎች ጋር ለመነጋገር ነበር፡፡
በእለቱ ከጧቱ በ3፡00 ሰዓት በዋና ስራ አስፈጻሚው ቢሮ ደረስኩ፡፡ የሚድሮክ የአስተዳደር ኃላፊዋ በዚሁ ስብሰባ ላይ እንዲገኙ ስነግራቸው፤ “ትናንት ኢሜይልህን አላየኸውም?” አሉኝ፡፡ “አላየሁትም” አልኳቸው። “ለውጦች አሉ” አሉና ከጠረጴዛቸው መሳቢያ አንድ ወረቀት አውጥተው ሰጡኝ። ርእሱ “የስራ ውል መቋረጥን ይመለከታል” ይላል፡፡ እዚያው ቁጭ ብዬ አነበብኩት፡፡ “መቋጫው ላይ በእጅዎ የሚገኘውን ንብረትና ሰነድ አስረክበው…” ይላል፡፡ ባልጠበቅኩትና ባልገመትኩት ሁኔታ የደረሰኝ መርዶ ቢሆንም አልደነገጥኩም፣ አልተረበሽኩም፡፡ ሌላ ሰው ቢሆን እዚያው ፌንት አድርጎ ይወድቅ ነበር፡፡
ለሰባት ዓመታት ጥይት እየተተኮሰብኝ በየእርሻው በመንከራተት ያገለገልኩበት ሚድሮክ፤ ያለ ምንም ጥፋት፣ የስራ መፈለጊያ (Termination Benefit) አምስት ሳንቲም ሳይሰጠኝ፣ ከኮቪድ ህመሜ ሳላገግም፣ ሌሎችን ውጪ ሀገር ድረስ ልኮ የሚያሳክመው መስሪያ ቤቴ፤ ኮርፖሬት ዳይሬክተር ሆኜ ሳለ ለህክምና ከ400 ሺህ ብር በላይ ወጪ አድርጌ ታክሜ አምስት ሳንቲም ሳይደግፈኝ፣… በግፍ አባሮኛል፡፡
ክቡር ሆይ!
ዋና ስራ አስፈጻሚው አቶ ጀማልን በዚያ ወቅት ምን እንደነካቸው አላውቅም። ከኋላ ገፊ ነገር ቢኖር ነው እንጂ የሚያባርር ጥፋት አላጠፋሁም። በዚያ ላይ የኮቪድ ህክምና ላይ ነበርኩ። በ5 ወራት በርካታ አዳዲስ ስራዎች ተሰርተዋል። ሲሆን ሲሆን ሽልማት ሲገባኝ... ጎዳና ላይ የወደቁ ሰዎችን ህንፃ ሰርቶ የሚመግበው ሚድሮክ፤ እኔና ቤተሰቤን ለጎዳና ዳርጎናል፡፡ ለእርስዎ ባለኝ አክብሮት እና ኢንቨስትመንቱ እንዳይጎዳ በማሰብ ራሴንና ቤተሰቤን (በተለይም 4 ህፃናት ልጆቼን) መስዋእት አድርጌ ለአንድ ዓመት ታግሻለሁ፡፡
በህይወቴ አድርጌው የማላውቀውን ኩባንያዬ እድል ከሰጠኝ በስራ እንደምክስ ቃል በመግባት አቶ ጀማልን ለምኛለሁ፣ አስለምኛለሁ፡፡ እንዳላጠፋሁ ህሊናዬ እያወቀ አቶ ጀማል ውሳኔውን እንደገና እንዲያዩ ይቅርታ ጠይቄያለሁ፡፡ በዋትስአፕና በኢሜይል በተደጋጋሚ የልመና ማስታወሻዎች ጽፌያለሁ። በአላህ ስም ተማጽኛለሁ፡፡ ለዚህ ሁሉ መልሱ ዝምታ ነው፡፡ ዝምታው ሲበዛ እነሆ ይችን ደብዳቤ ጽፌ፣ አቶ ጀማል በማኔጅመንት አባላት ላይ ይግባኝ የሌለው ውሳኔ በመወሰን “የውጭ አልጋ የውስጥ ቀጋ” መሆኑን ለክቡርነትዎ አቤት ለማለት በቃሁ!
ክቡር ሆይ!
አቶ ጀማል እኔን በግፍ ማባረሩን አራቱም ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚዎች በቁጭትና በጸጸት እንደሚያዩት በተለያዩ ጊዜያት ነግረውኛል፡፡ አንዳንዶቹ “እስቲ የሚቀርበውን ሰው ፈልግና ሽማግሌ ላክበት” የሚል ምክር ሰጥተውኛል፡፡ በዚሁ መሰረት ጋዜጠኛ ሰይፉ ፋንታሁንን ጨምሮ አቶ ጀማልን የሚቀርቡ ሰዎችን ሽምግልና ልኬያለሁ፡፡ ጠብ ያለ ነገር የለም፡፡ ይህን ያህል አቶ ጀማል በእኔ ላይ ለምን ጨከነ? ጥፋቴ ምንድነው? የሚለው ጥያቄ አእምሮዬን ወጥሮ ሲይዘኝ ለሽምግልና የላኳቸውን ሰዎች ጠይቄያቸው የተለያየ መልስ ሰጥተውኛል፡፡ ለአንዳንዶቹ “አብዱራህማን በሸገር ዳቦ ጉዳይ ለጋዜጠኞች በሰጠው መረጃ ምክንያት አዳነች አቤቤ አባረው ብላኝ ነው” ማለቱን ነግረውኛል፡፡ ሌሎች ደግሞ “አብዱራህማን በፌስቡክ ገጹ ስለ አሜሪካ በጻፈው ምክንያት ከአሜሪካ ኤምባሲ አባረው ተብዬ ነው” ማለቱን ነግረውኛል፡፡ ለአንዳንዶቹ ደግሞ በፌስቡክ ገጼ ስለ ኢትዮ ጠቢብ ሆስፒታል በጻፍኩት ጽሁፍ ምክንያት እንዳበረረኝ ነግረውኛል፡፡ ሌሎች ደግሞ “ወሓብያን የሚያወግዝ መጽሐፍ ተርጉመህ በማሳተምህ ጓደኞቹ እነ አቡበከር አህመድ አባር ብለውት ሊሆን ይችላል” ብለውኛል። “ጁንታውን የሚተች ጽሁፍ ስለምትጽፍ ጁንታው አባር ብሎት ይሆናል” ያሉኝም ሰዎች አሉ፡፡
ሁሉም መላምት ነው፡፡ ይሄ ሁሉ ምክንያት ሊሆን የማይችል ውል አልባ ምክንያት ነው፡፡ መቼም ሰው ነኝና ከሰው ልጅ ስህተት፣ ከብረት ዝገት ሊጠፋ አይችልም፡፡ በዚህ ረገድ ከአቶ ጀማል አንድ ደብዳቤ ተጽፎልኛል፡፡ የተጻፈልኝ ደብዳቤ መንፈስ ቅጣትም ማስጠንቀቂያም ሳይሆን ማሳሰቢያ እና የስራ መመሪያ መሆኑን አንብቦ መገንዘብ ይቻላል፡፡ (የደብዳቤውን ቅጂ አያይዣለሁ) ይህም በሸገር ዳቦ ጉዳይ ለጋዜጠኞች የሰጠሁትን “ሸገር ዳቦ 71 ሚሊዮን ብር ከስሯል…” የሚል መረጃ በተመለከተ የተጻፈ ደብዳቤ ነው፡፡
ክቡር ሆይ!
ሸገር ዳቦን በተመለከተ ለጋዜጠኞች የሰጠሁት መረጃ አንድም ውሸት የለውም፡፡ አሁን ሸገር ዳቦ መክሰሩን አገር ያወቀው ጉዳይ ነው፡፡ ሸገር ዳቦ የደረሰበትን ኪሳራ ለማካካስ እነ አቶ ጀማል የሰሩትን ስህተት ብገልጸው ምን ሊሉ ነው? ከዚህ ውጪ አንድም የጽሁፍ ወይም የቃል ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶኝ አያውቅም፡፡ በዚህ ደብዳቤ የተጻፈው እውነት ነው ቢባል እንኳ በዚህ ደብዳቤ ምክንያት መባረር ነበረብኝ? ደብዳቤው ራሱ ቅጣት አይደለም እንዴ? ነገሩ እስካልተደጋገመ ድረስ በአንድ ወንጀል 2 ጊዜ ቅጣትስ አለ እንዴ?
በሌላ በኩል አንድን ሰራተኛ ድንገት እንዲባረር የሚያደርጉ ነገሮች (የቅጣት ደረጃዎች) በህግ ይታወቃሉ፡፡ ጥፋት ቢኖር እንኳ ከማባረር በመለስ የሚወሰዱ እርምጃዎች ብዙ ናቸው። እኔ ግን ድንገት ነው የተባረርኩት፡፡ በበኩሌ ባለፉት 7 ዓመታት ለሚድሮክ ባደረግኩት ትጋትና አስተዋፅዖ ሽልማት እንጂ መባረር አይገባኝም ብዬ አምናለሁ፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በስራዬ ደካማ ብሆን እንኳ አቅምና ችሎታዬ ወደሚመጥነው ስራ እመደባለሁ እንጂ እንዴት በአንድ ጊዜ እባረራለሁ? አጥፍቼ ቢሆን እንኳ ወይ ከደረጃ ዝቅ ተደርጌ ወይ በደመወዝ እቀጣለሁ እንጂ እንዴት እባረራለሁ? እርስዎ “… ደካማ ሰራተኛ ቢሆን እንኳ ሊሰራው ወደሚችለው ስራ እንዲዛወር ይደረጋል እንጂ አይባረርም፡፡ ‘ተውት፡፡ ገለል አድርጉት እንጂ ደመወዙን አትከልክሉት’…” ያሉትስ ቃል በአቶ ጀማል ዘመን ተግባራዊ አይሆንም?
ክቡር ሆይ!
ዶ/ር አረጋ ስህተታቸውን እንዲያርሙ ብዙዎቻችን ብዙ የውስጥ ትግል አድርገናል። እርስዎም ነገሩን አጥንተው ዶ/ር አረጋ ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ትክክል ነበር። ዶ/ር አረጋ የተነሱት በሚድሮክ ለውጥ እንዲመጣ ነው፡፡ አሁን ግን “ትሻልን ሰድጄ ትብስን አመጣሁ” እንዲሉ ነው የሆነው፡፡ አቶ ጀማል የሚድሮክ የስራ ኃይል የሚፈልገውን ለውጥ መና አስቀርቶታል!
ብዙዎቻችን በሚድሮክ የምንሰራ ሰዎች የሚድሮክ ጥቅማ ጥቅምና ደመወዝ ስቦን አልነበረም ወደ ሚድሮክ የመጣነው፡፡ የእርስዎን ራዕይ፣ የእርስዎን በጎ ሃሳብ፣ የእርስዎን ለሀገርና ለወገን ተቆርቋሪነት ስንሰማ በነበርንበት መስሪያ ቤት የነበረንን ኃላፊነት እየለቀቅን እርስዎን ለማገዝ ነበር የመጣነው፡፡ የሚድሮክ ማኔጅመንት እንዲህ የተዝረከረከና የለየለት አምባገነን ይሆናል ብለን አልገመትንም ነበር። ችግር ቢኖርም በውስጥ ባለ አሰራር ይፈታል የሚል እምነት ነበረን፡፡
አቶ ጀማል አህመድ የራሱን ኢምፓየር ለመገንባት የራሱን ሰዎች እያሰባሰበ ነው፡፡ ለዚህም ይረዳው ዘንድ በቅድሚያ የሚወስደው እርምጃ በዶ/ር አረጋ እና በአቶ አብነት ዘመን የተቀጠሩ ሰዎችን አንድ በአንድ ማባረር ነው። ይህ በመሆኑ ተባራሪዎቹ ሰራተኞች ብቻ ሳይሆኑ ተቋማቱም እየተጎዱ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ሚድሮክ ውስጥ የአንድ ግለሰብ ኢምፓየር እየተገነባ፤ የየኩባንያዎቹ የደም ስር በሆኑ መሪዎች (በማኔጅመንቱ አባላት) ላይ ይግባኝ የሌለው ውሳኔ እየተላለፈ በመሆኑ ለማኔጅመንት አባላቱ ይድረሱልን፡፡ (በሌሎች ሰራተኞች ላይ የደረሰውን በደል በተመለከተ ሳምንት በክፍል 2 ይቀጥላል፡፡)
የምጊዜም አክባሪዎ! አብዱራህማን አህመዲን የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ
የኮሙኒኬሽንና ፕሮሞሽን ኮርፖሬት ዳይሬክተር (የነበርኩ)

Read 5759 times