Saturday, 04 June 2022 14:52

ይግባኝ ለአንባቢያን ከአሜሪካ ቪዛ ባሻገር

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(3 votes)

   በ29ኛው ኦሎምፒያድ ቻይና፤ በ19ኛው የዓለም ዋንጫ፣ በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫና በ5ኛው ቻን ደቡብ አፍሪካ፤ በ14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናና በ21ኛው የዓለም ዋንጫ ራሽያ...           ይህን ፅሁፍ በስፖርት አድማስ ላይ የቀረበው በአዲስ አበባ በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ አሰራር ላይ ለአንባቢያን ይግባኝ ለማለት ነው፡፡ ከ42 ቀናት በኋላ በኦሬጎን አሜሪካ  18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና እንደሚካሄድ ይታወቃል፡፡ በዚሁ ዓለም አቀፍ የስፖርት መድረክ ላይ የምሰራበትን አዲስ አድማስ ጋዜጣና ኢትዮጵያ በመወከል የምሳተፍበት እድል ነበረኝ፡፡ የአሜሪካ ኤምባሲ ግን አስፈላጊውን ቪዛ ግልፅ ባልሆነና በማያሳምን ምክንያት  ከልክሎኛል፡፡ በዓለማችን ግዙፍ የአትሌቲክስ መድረክ ላይ በሚዲያ ባለሙያነት መሳተፍ አገርን ወክለው ከሚሰለፉ አትሌቶች እኩል መታየት ነበር። በዓለም ሻምፒዮናው ላይ በብቃት ለመስራት የሚያስችል የስራ ልምድና እቅድ  የነበረኝ ቢሆንም ኤምባሲው ላቀረብኩት የቪዛ ማመልከቻ ተገቢውን  ትኩረት ባለመስጠቱና ትብብር ባለማድረጉ ይህን የፅሁፍ አቤቱታ በይፋ ለማቅረብ ግድ ሆኖብኛል፡፡
የኦሬጎን 22 ግብዣና የቪዛ ማመልከቻው
የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናው በምድረ አሜሪካ የሚካሄደው በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ነው። ከ200 በላይ አገራትን የሚወክሉ ከ2ሺ በላይ አትሌቶችን በሚያሳትፈው ሻምፒዮናው ከ3ሺ በላይ የሚዲያ ባለሙያዎችን ከዓለም ዙርያ ያሰባስባል። በስፖርት ሚዲያው ለሚሰሩ ባለሙያዎች ለየአገራቱ በሚሰጠው የተሳትፎ ኮታ መሰረት የኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር ባካሄደው ምርጫ እድሉን ካገኙት ጋዜጠኞች አንዱ ነበርኩ። በሻምፒዮናው ለመሳተፍ ከማህበሩ  ባገኘሁት አክሰስ ኮድ አማካኝነት በዓለም አትሌቲክስ ማህበር ድረገፅ በኩል አስፈላጊ መረጃዎችና የሚጠየቀውን መስፈርት በማሟላት ምዝገባውን አከናወንኩ፡፡ ወደ አሜሪካ ኤምባሲ ለቃለምልልስ ከገባሁበት 76 ቀናት ቀደም ብሎም ማርች 7 ላይ  የዓለም ሻምፒዮናውን በኦሬጎን ከሚያዘጋጀው ኮሚቴ የሚዲያ ኦፕሬሽን ክፍል   የአክሪዴቴሽን ደብዳቤ አደረሰኝ፡፡ በዓለም ሻምፒዮናው የሚዲያ ስራዎችን ለማከናወን መፈቀዱን የሚገልፅ ደብዳቤ ነበር፡፡  ወደ አሜሪካ ኤምባሲ ገብቶ አስፈላጊውን ቪዛ ለመጠየቅ ከዓለም ሻምፒዮናው አዘጋጅ ተጨማሪ የግብዣ ደብዳቤ ማግኘት ወሳኝ ነበር፡፡ ይህ ደብዳቤም ማርች 19 ላይ ከዓለም ሻምፒዮናው ብሄራዊ አዘጋጅ ኮሚቴ ዋና ስራ አስፈፃሚ በሆኑት ሳራህ ማሲይ ተፈርሞ ተላከልኝ፡፡
ከዚያ በኋላ ለአሜሪካ ኤምባሲ የቪዛ ማመልከቻውን ለማስገባት  መሯሯጥ ነበረብኝ። በጉዳይ አስፈፃሚ በኩል በኤምባሲው ድረገፅ  የሚገኘውን የኤሌክትሮኒክስ ማመልከቻ ፎርም ለመሙላት በቅድሚያ  በአቢሲኒያ ባንክ በኩል  በአሜሪካ የሚጠየቀውን የኮቴ ክፍያ 8320 ብር ከፈልኩ፡፡  የቪዛ ማመልከቻውን እያማከረ እንድሞላ ላደረገው ባለሙያም ተጨማሪ 750 ብር ከከፈልኩ በኋላ  በኤምባሲው ቆንስላ ለሚቀጥለው ቃለምልልስ ቀጠሮ እንዲያዝልኝ አመለከትኩ፡፡  ኤምባሲው በኤሌክትሮኒክ ምላሹ ያደረሰኝ የቀጠሮ ቀን ያልጠበቅኩት ነበር፡፡ ልሳተፍ ካቀድኩበት የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናው 3 ወራትን  አሳልፎ አኮቶበር 4 , 2023  ላይ ነበር ቀጠሮው፡፡ በወቅቱ የኤምባሲው ምላሽ የቪዛ ማመልከቻውን ለምን እንዳስገባው ሳይስተውል ቀጠሮውን በደፈናው መግለፁ አበሳጭቶኛል፡፡ ለቪዛ ማመልከቻው እያማከረኝ ከሰራው ባለሙያ ጋር በመነጋገር የቀጠሮ ቀኑ ከሻምፒዮናው በፊት እንዲቀየርልኝ በመጠየቅ ድጋሚ አመለከትኩ፡፡ የአሜሪካ ኤምባሲም ይህን ተከትሎ ሜይ 23, 2022  ላይ በቆንስላው ለሚደረግልኝ ቃለምልልስ ቀጠሮ መያዙን በመልዕክቱ አሳወቀኝ፡፡
በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናው ላይ የግል ሚዲያን በመወከል ለመሳተፍ ብዙ ውጣውረድ አለው፡፡ አትሌቶች ለተሳትፎ የሚያበቃቸውን ሚኒማ ማሟላት እንደሚያስፈልጋቸው ጋዜጠኛ ደግሞ ለስራ ወደ ተጋበዘበት አገር ለመጓዝ ከአትሌቲክስ ፌደሬሽን ወይንም ከሚመለከተው ሌላ አካል የተለየ ድጋፍ አያገኝም፡፡ የጉዞውን ሙሉ ወጭ በራሱ ወይንም በሚወክለው ሚዲያ በኩል መሸፈኑ ግድ ሲሆን ለዚህ ደግሞ ከተለያዩ አካላት የስፖንሰርሺፕ ድጋፍ ማግኘት ያስፈልጋል፡፡ ይህን ድጋፍ ለማግኘት ደግሞ ቪዛ መያዝ ወሳኝ ይሆናል። ከአሜሪካ ኤምባሲ ቆንስላ ጋር ቃለምልልስ ለማድረግ በአውሮፓውያን አቆጣጠር ሜይ 23 ላይ የያዝኩት የቀጠሮ ቀን ደረሰ፡፡ ቃለምምልሱን የማደርገው 4 ሰዓት ላይ ቢሆንም ልክ 2 ሰዓት ተኩል አዲስ አበባ ሽሮ ሜዳ አካባቢ  የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ደርሼ ነበር፡፡ የኤምባሲው ቅጥር ግቢ ከእኔ ቀድመው በተገኙ በርካታ የቪዛ አመልካቾች ተጥለቅልቋል። በኤምባሲው መግቢያ በር ላይ የነበረውን ጥብቅ ፍተሻ በማለፍ ወደቅጥር ግቢው ገብቼ ለእንግዶች በተዘጋጀው የማረፊያ ቦታ ለቃለምልልሱ እስክጠራ ዙርያ ገባውን እያማተርኩ በትእግስት ተራዬን መጠበቅ ጀመርኩ፡፡ ደጅ ከነበረው የማረፊያ ቦታ ወደፅህፈት ቤቱ ገብቼ አሁንም ሌላ ተራ ከያዝኩ በኋላ ሁለት ወንድና ሴት የኤምባሲው ቆንስላዎች በመስኮታቸው በኩል ተራው የደረሳቸውን አመልካቾች ልዩ ቃለምልልስ በማድረግ እያስተናገዱ ናቸው፡፡ ሴቷ ቆንስላ በአማርኛ ታወራ ስለነበር እሷ በደረሰችኝ እያልኩ በልቤ እየተመኘሁ ቆየሁ። ተራዬ ስደርስ ግን የተጠራሁት ወንዱ የአሜሪካ ቆንስላ በቆመበት መስኮት ነበር፡፡ ከኦሬጎን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ብሄራዊ አዘጋጅ ኮሚቴ የተላከልኝልን Visa Invitation Letter እንዲሁም ሁለት የድጋፍ ደብዳቤዎች ከፓስፖርቴ ጋር በማያያዝ መስኮቷ ስር በነበረችው ክፍተት ለቆንስላው አቀበልኩት፡፡ ከኦሬጎን የዓለም ሻምፒዮና አዘጋጅ ኮሚቴ (Oregon22, LLC) አስፈላጊው ቪዛ የአሜሪካ ኤምባሲ እንዲሰጠኝ የተፃፈው ደብዳቤ አስቀድሜ እንደጠቀስኩት በዋና ስራ አስፈፃሚዋ የተፈረመና በሻምፒዮናው ወቅት የማርፍበት ሆቴል ተጠቅሶ አስፈላጊው ሁሉ ትብብር እንዲደረግልኝ የሚጠይቅ ነበር፡፡  በኢትዮጵያ የግል ህትመት ሚዲያ ታሪክ ከ22 ዓመታት በላይ በመስራት ከሚታወቀው አዲስ አድማስ ጋዜጣ ደግሞ ያፃፍኩት ደብዳቤ ለ18 ዓመታት በጋዜጣው የስፖርት አምድ አዘጋጅነት እንደምሰራ ተጠቅሶ፤ በሳምንታዊው የአማርኛ ጋዜጣ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናውን ሰፊ ሽፋን እንድሰጥ መወሰኑ ተገልጿል፡፡ በተጨማሪም ታላላቅ የዓለም ስፖርት መድረኮችን በመዘገብ የነበረኝን ሰፊ  ልምድ በዝርዝር የገለፀው የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ደብዳቤ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናው የተመደብኩበትን ስራዬን ካከናወንኩ በኋላ ወደ ነበርብኩበት ሃላፊነት በመመለስ ስራዬን እንደምቀጥል ከመጠቀሱም በላይ ለጉዞዬ የሚያስፈልገውን ሙሉ ወጭዬን በጋዜጣው በኩል በማገኛቸው ስፖንሰሮች እንደምሸፍንም ተብሯርቷል፡፡  ከኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር በፕሬዝዳንቱ የተፃፈው የድጋፍ ደብዳቤም አባልነቴ ከመጠቀሱም በላይ የዓለም አቀፉ የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር AIPS አባል እንደሆንኩና ለዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናው ሰፊና ልዩ ዘገባዎችን እንድሰራ የሚያስችለው ቪዛ በመስጠት ትብብር እንዲደረግልኝ የሚጠይቅ ነበር፡፡
ቃለምምልስ ከአሜሪካ ኤምባሲ ቆንስላ ጋር
የአሜሪካ ኤምባሲው ቆንስላ ቃለምልልሱን ሲጀምር  የሰጠሁትን የድጋፍ ደብዳቤዎች ሊያነብ ይቅርና በአግባቡ እንኳን አልተመለከታቸውም። በደብዳቤዎቹ ላይ የተጠቀሱትን ፍሬ ነገሮች ለመመልከት እና እንደቆንስላነቱ እኔን ለማማከር የተመደበትን ሃላፊነት ወደጎን ማድረጉን ነው የታዘብኩት፡፡ ከፊት ለፊቱ የሚገኘውን  ኮምፒውተር አለፍ አለፍ እያለ ሲመለከት ቆይቶ በመጀመርያ ያቀረበልኝ ጥያቄ ወርሃዊ ገቢዬን ጠየቀኝ፡፡ መቼም በአፍሪካ አህጉር የሚገኝ ጋዜጠኛ ኤምባሲው በሚጠይቀው መስፈርት አሜሪካ ከሄደ በኋላ ጥገኝነት ጠይቆ የሚተወው ሃብት ንብረት ይኖረዋል ብሎ በመገመት አይመስለኝም፡፡ በስፖርት አምድ አዘጋጅነት ከምሰራበት አዲስ አድማስ ጋዜጣ ሌላ የት እንደምሰራ ነበር ያስከተለው _ጥያቄ፡፡ በቅርቡ ስራውን በጀመረው አራዳ ኤፍኤም 95.1 ላይ በሬጌ ላይ የሚያተኩርና በሳምንት ለሶስት ሰዓት የሚቀርበው የጥበብ ሞገድ ዋና አዘጋጅ እና አቅራቢ ሆኜ እንደምሰራ ነገርኩት፡፡ ከምላሼ በኋላ የኮምፒውተሩን ቁልፎች ሲነካካ ቆይቶ ያቀረበልኝ ቀጣዩ ጥያቄ ልጅ አለህ ወይ የሚል ነበር፡፡ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናን በሚዲያ ባለሙያነት ከመዘገብ ጋር የኑሮዬ ሁኔታ ምን ያገናኘዋል በሚል ስሜት እየተደናገርኩ ልጅ የለኝም ብዬ መለስኩለት። ከዚያም አሜሪካ ውስጥ ዘመድ አዝማድ እንዳለኝና ከማን ጋር ነው የምትኖረው? የሚሉ ጥያቄዎችን አከታትሎ አነሳ፡፡ አሜሪካ አገር ዘመድ እንደሌለኝ፤ አገሬ ላይ  ከቤተሰቦቼ ጋር እንደምኖር ገለፅኩለት፡፡
የቆንስላው የመጨረሻው ጥያቄ ከኢትዮጵያ ውጭ በቅርቡ  የተጓዝከው የትነው የሚል ነበር። ‹‹ራሽያ›› ብዬ መለስኩ፡፡ ‹‹ለምን›› ብሎ ንቀት በሞላበት ሁኔታ ሲጠይቀኝ በመስኮት ያቀበልኩትን ፖስፖርትና የድጋፍ ደብዳቤዎች በጭራሽ እንዳላነበበ አረጋገጥኩ። በ2018 እኤአ ላይ ራሽያ ባዘጋጀችው 21ኛው የዓለም ዋንጫ የሚዲያ ባለሙያ ሆኜ እንደተሳተፍኩ፤ ስራዬንም በተሳካ ሁኔታ በመፈፀም ወደ አገሬ እንደተመለስኩ ብገልፅለትም ምላሼን ከልቡ የሰማኝ አልመሰለኝም፡፡ ከዚያ በኋላ ለማውራት የፈለግኩትን  እንኳን ለመቀጠል እድሉን ሳይሰጠኝ  በመስኮቷ በኩል ባለችው ክፍተት አንዲት ውሃ ሰማያዊ ቀለም ያላትን ብጣሽ ወረቀት ወረወረልኝ። ጎን ለጎን የሆነ ነገርም አውርቷል። አልሰማሁትም እንጅ ምናልባትም፡፡ ይቅርታን እንኳን ሳያስቀድም የአሜሪካ ኤምባሲ ቪዛውን እንደማይሰጠኝ ይሆናል የተናገረው፡፡ ከመስኮቱ ዘወር ብዬ ወረቀቷን አነበብኳት፡፡ ቪዛውንም እንደተከለከልኩም ተረዳሁ። የእኔን የቪዛ ማመልከቻ በአግባቡ ተመልክቶ፤ ያቀረብኳቸውን የድጋፍ ደብዳቤዎች አገናዝቦ፤ ቃለምልልስ አድርጎና አማክሮ እንዲያስተናግደኝ በኤምባሲው የተመደበው ቆንስላ የሰጠኝ ባለሰማያዊ ቀለም ብጣሽ ወረቀት ለቪዛ አመልካቾች በዘፈቀድ የሚታደል መሆኑን ለመገመት አይከብድም፡፡ በወረቀቷ ላይ ቪዛውን ለመከልከል የተጠቀሰው ደንብና ዝርዝር ማብራርያን ለመረዳት ያስቸግራል፡፡ ‹‹እርስዎ አሜሪካን አገር ከሄዱ በኋላ ወደ አገርዎ እንዲመለሱ የሚያስገድድዎ ቁርኝቶች....› ምናምን ይላል፡፡ አሜሪካ ሄደህ በዚያው ትጠፋለህ የሚል ድምዳሜ ላይ ቆንስላው መድረሱን ያመለክታል፡፡ በአጠቃላይ የአሜሪካ ኤምባሲ ለቪዛ ማመልከቻው የሰጠኝ ምላሽ በሙያዬ ላገኝ የምችለውን ዓለም አቀፍ ልምድ የሚያበላሽ ፤ የምሰራበትን ጋዜጣ የማያከብርና ኢትዮጵያ በዓለም አትሌቲክስ ላይ ያላትን ውጤታማነትና ክብር ከግምት ያላስገባ ነው፡፡
 ከኦሬጎን 22 በፊት ...
በኦሬጎን አሜሪካ ከሚካሄደው 18ኛው ዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በፊት በስፖርት አምድ አዘጋጅነት ባሳለፍኳቸው 18 ዓመታት የነበረኝን ልምድ እንደማጠቃለያ ማቅረብ እፈልጋለሁ፡፡  በ2008 እኤአ ላይ  ቤጂንግ ባስተናገደችው 29ኛው ኦሎምፒያድ የዋዜማ ሰሞን በአዲስ አበባ ከሚገኘው የአገሪቱ ኤምባሲ ባገኘሁት  ግብዣ ለአምስት ቀናት  ጉብኝት ወደ ታላቋ ቻይና የተጓዝኩ ሲሆን የቤጂንግና የናይንጂንግ ከተሞችን ጎብኝቻለሁ፡፡ ታላቁን የቻይና ግንብ፤ በቤጂንግ ከተማ የሚገኘውን ፎርቢድን ሲቲ የተባለ ታሪካዊ ስፍራ፤ የታይናሜን አደባባይ፤ በቤጂንግ ከተማ የሚገኙ ታላላቅ ሬስቶራንቶችን፤ የወደብ ከተማዋን ናይጂንግ ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ጋዜጠኞች ጋር ተዘዋውሮ የመጎብኘት እድል አግኝተናል፡፡ ከቻይና መልስም በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ‹‹5 ቀናትን በቻይና›› በሚል ርእስ ያዘጋጀሁትን ፅሁፍ ለሶስት ሳምንታት በተከታታይ በማቅረብ በአዲስ አበባ ከሚገኘው የቻይና ኤምባሲ የምስጋና መልዕክት ደርሶኛል፡
በ2010 እኤአ ላይ ደግሞ የአፍሪካ አህጉር በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ የዓለም ዋንጫን የማዘጋጀት እድል አግኝታ ደቡብ አፍሪካ 19ኛውን የዓለም ዋንጫ ስታስተናግድ ከቢቢስ ዎርልድ ሰርቪስ ትረስት ጋር በትብብር በቀረፅኩት የሚዲያ ፕሮጀክት ወደ ጆሃንስበርግ ከተማ ተጉዣለሁ፡፡ ከዓለም ዋንጫው ጋር በማያያዝ በደቡብ አፍሪካ ተሰድደው ስለሚኖሩ ኢትዮጲያውያኖች ህይወት በስፋት ለመዘገብ በተቀረፀው የሚዲያ ፕሮጀክት ‹‹ህይወት የሚያስከፍለው የደቡብ አፍሪካ ጉዞ›› በሚል ርእስ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ በተከታታይ ያቀረብኩት የጉዞ ማስታወሻ በተመሳሳይ ፕሮጀክቶች በመላው አፍሪካ ተጉዞው የነበሩ ሌሎች የህትመት ሚዲያዎች ካቀረቧቸው ፅሁፎች ጋር ተወዳድሮ በማሸነፉ ከቢቢሲ ዎርድል ትረስት የምስክር ወረቀት እና የላፕቶፕ ሽልማትን አግኝቼበታለሁ፡፡
በ2013 እኤአ ላይ የኢትዮጲያ ብሄራዊ ቡድን ከ31 ዓመታት በኋላ ወደ አህጉራዊው ውድድር በመመለስ በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ለመሳተፍ ሲበቃ የእግር ኳስ ፌደሬሽን ባመቻቸው እድል ከሌሎች 26 የስፖርት ጋዜጠኞች ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመጓዝም በቅተናል፡፡ በአፍሪካ ዋንጫው ላይ የስፖርት ጋዜጠኞች ከፍተኛ ልምድ ከማግኘታችን ባሻገር ከዚያው ጆሃንስበርግ ለዋልያዎቹ ብቸኛውን ግብ ካስቆጠረው አዳነ ግርማ ጋር ልዩ ቃለምምልስ በመስራት ለህትመት አብቅቻለሁ፡፡ አህጉራዊውን የእግር ኳስ ውድድር ከስፍራው በመዘገብ ከመስራቴም በላይ በተለያዩ ከተሞች ከሚኖሩ ኢትዮጲያውያን ጋር ቃለምልልሶችን በመስራት በጋዜጣ እና በኦንላይን ታትመው ለአንባቢዎች ተሰራጭተዋል፡፡ ከአንድ አመት በኋላም እዚያው ደቡብ አፍሪካ ላይ በ2014 እኤአ ላይ በተካሄደው የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮንሺፕ ቻን ዋልያዎቹ በነበራቸው ተሳትፎ ላይ ከሄኒከን ኢትዮጲያ በተገኘ ድጋፍ ከሌሎች የሚዲያ ባለሙያዎች ጋር በመሳተፍንም ሰርተናል፡፡
በ2013 እኤአ ላይ ደግሞ ላይ በዓለም አትሌቲክስ ማህበር፤ በኢትዮጲያ የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበርና በዓለም አቀፉ የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር ያገኘሁት እድል ደግሞ ሞስኮ ያስተናገደችውን 14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለመዘገብ ነበር፡፡ በራሽያዋ መዲና ሞስኮ የዓለም ሻምፒዮናውን ለመዘገብ በነበረኝ የ13 ቀናት ቆይታም በስፖርት ጋዜጠኝነት በተለይም ከፍተኛ ልምድ ባካበትኩበት የአትሌቲክስ ስፖርት በስፋት የምሰራበት እድል አግኝቼ በአግባቡ ተጠቅሜበታለሁ፡፡ ከ9 ዓመት በፊት  14ኛው የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በሞስኮው ሉዚንሂኪ ስታዲየም ለ10 ቀናት ሲካሄድ በስፖርታዊ ጋዜጠኝነት ዘመኔ  ታላላቅ ተሞክሮዎችን አግኝቻለሁ፡፡ በዓለም ሻምፒዮናው በወንዶች 10000 ና በሴቶች 1500ሜ የፍጻሜ ውድድር በፊት ከቢቢሲ ራዲዮ ስፖርት ጋር የቅድመ ውድድር ውይይት አድርጌያለሁ። በኢትዮጲያ አትሌቶችና አትሌቲክስ ዙርያ  ከዴንማርክ ቲቪ ጋር፤ ከደቡብ ኮሪያ ስፖርት ጋዜጣ ጋር፤  ከቱርክ አትሌቲክስ መጽሔት ጋር ፤ ከሁለት የስዊድን ጋዜጦች ጋር እንዲሁም ከታዋቂ የጃማይካ ጋዜጠኞች ጋር ልዩ ቃለመጠይቆች ሰጥቻለሁ። በኢትዮጲያ የስፖርት ጋዜጠኝነት ፈርቀዳጅ ከሆኑትና በዓለም ስፖርት አመራርነት ከፍተኛ ልምድ ካላቸው ጋሽ ፍቅሩ ኪዳኔ በሌኒንግራድ ሆቴል ተገናኝተን አስደናቂ ታሪኮችን አውግተናል። በወቅቱ የዓለም ሻምፒዮናው ከሚካሄድበት ሞስኮ ልዩ ቃለምልልሶችን  ከኢትዮጵያውያን አትሌቶች ጥሩነሽ ዲባባ፣ መሐመድ አማን፣ መሰረት ደፋር፣ ሶፊያ አሰፋ፣ ኢብራሂም ጄይላን፣ ሌሊሳ ዴሲሳ፣ ታደሰ ቶላ በመስራት ዘገባዎቼን አቅርቢያለሁ፡፡ ከትውልደ ኢትዮጵያዊት ስዊድናዊት አትሌት አበባ አረጋዊ ፤ በወቅቱ ለእንግሊዝ ድርብ የወርቅ ሜዳሊያ ካሸነፈው ሞ ፋራህ፤ በማራቶን የኦሎምፒክ እና የዓለም ሻምፒዮን ዩጋንዳዊው ሮበርት ኪፔሪቶች ፤ ከታዋቂው  አሜሪካዊው የርቀት ሯጭ በርናርድ ላጋት እንዲሁም ከጃማይካዊው ዩሲያን ቦልት አጫጭር ቃለምልልሶችን በመስራት ለስፖርቱ አድናቂዎች በምሰራበት ጋዜጣ አዲስ አድማስ በኩል አቅርቢያለሁ፡፡ ከስፖርቱ ባሻገር በሞስኮ ከተማ ከሚገኙ ታዋቂ ኢትዮጲያውያን ጋር ሰፊ ቃለምልልሶች ያደረግኩ ሲሆን ና በመላው ራሽያ ስለሚኖሩ ኢትዮጲያውያን የሚተረኩ መረጃ በመሰብሰብ ተንቀሳቅሻለሁ፡፡ በሞስኮ ለ11 ቀናት በነበረው ቆይታዬ በመቶዎች የሚቆጠሩ የማስታወሻ ፎቶዎችን ከሩሲያ ተወላጆች እና ከዓለም ዙሪያ ከመጡ የአትሌቲክስ አፍቃሪዎች ጋር በመነሳት ከማሳለፍ በላይ በስፖርት ጋዜጠኝነት ተመድቤ እሰራበት ከነበረው የሉዝንስኪ ስታድዬም በማህበራዊ ሚዲያ ይህኑ ተመክሮ እያገራሁ ልዩ ትኩረት ስቢያለሁ፡፡ ስለሞስኮ ቆይታዬም  የጉዞ ማስታወሻዎችን በማዘጋጀት ወደ አገር ቤት ከተመለስኩ በኋላ በዚሁ አዲስ አድማስ ጋዜጣ  ላይ ለተከታታይ ሳምንታት በማቅረብም እንዲነበብ አድርጊያለሁ፡፡
በመጨረሻም  በ2018 እኤአ ላይ ራሽያ ባስተናገደችው ግዙፉ የዓለም የስፖርት መድረክ ዓለም ዋንጫ ላይ አስደናቂ ተሳትፎ ለማድረግ በቅቻለሁ።  በ21ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ ደግሞ ኢትዮጵያን በመወከል የምሰራበትን እድል ያገኘሁት በፍሪላንስ የፎቶ ጋዜጠኛነት ነበር፡፡  ከዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ፊፋ ለተገኘው እድል የኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበርና የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ጋዜጠኞች ማህበር አባል መሆኔ ካደረገው አስተዋፅኦ ባሻገር  በህትመት ሚዲያው የነበረኝ የረጅም ግዜ አገልግሎት እድሉን ፈጥሮልኛል፡፡ በርግጥ በዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ውድድሮች ላይ ኢትዮጵያውያን በፎቶ ጋዜጠኝነት የነበራቸው ተሳትፎ ጠንካራ አለመሆኑ አውቃለሁ፡፡ ስለዚህም በእግር ኳስ ፌደሬሽንና በስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር የቀረበውን እድል ለመጠቀም ስነሳ የበኩሌን አስተዋፅኦ ማድረግ እንደምችል በማመን ነበር፡፡ በከፍተኛ የሙያ ፍቅርና ትጋት ለምሰራው የስፖርት ጋዜጠኝነትም ተጨማሪ እውቀቶችና ወሳኝ ልምዶች በዓለም ዋንጫው እንደሚፈጠሩም ስለማውቅ ልዩ ጉጉት አድሮብኛል።  የዓለም ዋንጫ የዓለማችን ግዙፍ የስፖርት መድረክ እንደመሆኑ በፍሪላንስ ፎቶ ጋዜጠኛነት በመስራት የሚፈጠሩት እድሎች ቀላል ግምት የሚሰጣቸው አልነበሩም፡፡ በዚህ ታላቅ አጋጣሚ ላይ በልዩ ፍቃድ መስራት በሙያዬ አዲስ ምዕራፍ እንደሚከፍትልኝም ማሰቤም አነሳስቶኛል፡፡ ከታላላቅ የፎቶ ኤጀንሲዎች፤ አንጋፋ እና ምርጥ የፎቶ ጋዜጠኞች፤ የቪድዮ ባለሙያዎችና ፕሮፌሽናል  ፎቶግራፈሮች በቅርብ የምገናኝበት መድረክ ነው፡፡ የፎቶ ጋዜጠኛነቱን በተግባር ለመስራትና ለማወቅ ከዓለም ዋንጫ የላቀ መድረክም ሊኖር አይችልም።  በኢትዮጵያ  በተለይም በስፖርት ሚዲያው ለሚሰሩ የፎቶ ጋዜጠኞችና ጥቂት ፎቶግራፈሮች  ፈርቀዳጅ የሚሆኑ ብዙ ታሪኮችና ገድሎችን እንደምሰራበትም ተስፋ አድርጊያለሁ። በ21ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ ከ140 በላይ አገራትን ለሚወክሉ ከ1800 በላይ የፎቶ ጋዜጠኞች፤ ፕሮፌሽናል ፎተግራፈሮች እና የፎቶግራፍ ባለሙያዎች በፊፋ በኩል ፍቃድ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ራሽያ የገባሁት ከ21ኛው የዓለም ዋንጫ መክፈቻ እለት ሁለት ቀናት አስቀድሞ ነበር፡፡  ኢትዮጵያን የወከልኩ የፍሪላንስ ፎቶ ጋዜጠኛ መሆኔን በሞስኮው ሉዝሂንኪ ስታድዬም የፊፋ የሚዲያ ማዕከል በማረጋገጥ ምዝገባዬን አከናወንኩ፡፡ በ21ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ በ11 ከተሞች በሚገኙት 12 ዘመናዊ ስታድዬሞች ተዘዋውሬ መስራት የምችልበት SENBETO GIRUM SEIFU / MEDIA- PHO/ Freelance (ETH) የሚሉና ሌሎች መረጃዎች የሰፈሩበትን ልዩ የዓለም ዋንጫ መታወቂያ ተረከብኩ። በተጨማሪ ከፊፋ  1165 ቁጥር አረንጓዴ ቀለም የፎቶግራፈር የስራ ልብስ ተሰጠኝ፡፡
በ21ኛው የዓለም ዋንጫ ዋዜማ ቀን ላይ ፎቶዎችን በማንሳት ከነበረኝ መልካም አጀማመር በኋላ በፍሪላንስ ፎቶ ጋዜጠኛነት ለ33 ቀናት በራሽያ  የተሳካ ቆይታን ለማሳለፍ በቅቻለሁ።  የፎቶ ጋዜጠኝነቱ  በዓለም ዋንጫ ላይ በዋና ከተማዋ ሞስኮ በሚገኘው ሉዚሂንኪ ስታድዬም እና ዓለም ዋንጫውን ባስተናገዱ ሌሎች 4 የተለያዩ ከተሞች (ስፓርታክ ሞስኮ፤ ኒዚሂኒኖቭጎሮድ፤ ሴንትፒተርስበርግና ሶቺ) ላይ በሚገኙ አምስት  ዘመናዊ ስታድዬሞች ውስጥ በሚደረጉት ጨዋታዎች የተወሰነ ብቻ አልነበረም፡፡ በዋናነት በየከተሞቹ ከሚገኙት ስታድዬሞች ውጭ በተሰማራሁባቸው የተለያዩ ጉብኝቶች እና የጉዞ አጋጣሚዎችን የሚያካትት ነበር፡፡ የየከተማዎቹን ስነህንፃዎች ፤ ታሪካዊ ሃውልቶች እና ቅርሶች፤ ማራኪ ትእይንቶችና ቅፅበቶች፤ የህይወት መልኮችን በማንሳት ከዓለም ዋንጫው ውጭ የተለየ ልምድ ለማግኘት በቅቻለሁ፡፡ በርግጥ ከስታድዬም ውጭ በፎቶ ጋዜጠኝነት ስዘዋወር ባለውለታዬ የነበረችው የካፒታሉ አንተነህ አክሊሉ ያዋሰኝ ኒኮን ካሜራ ነበረች፡፡ በሚገርም ሁኔታ ደግሞ በዓለም ዋንጫ ጨዋታዎች ላይ በየስታድዬሞቹ   የኒኮን እና የካኖን ኩባንያዎች በልዩ ድጋፍ በሚሰሩባቸው ጊዜያዊ ጣቢያዎች በውሰት በሚሰጣቸው ካሜራዎች ተገልግያለሁ፡፡ በ21ኛው የዓለም ዋንጫ ራሽያ ላይ በፍሪላንስ የፎቶ ጋዜጠኛነት በመሰማራት በስታድዬም ውስጥ ውጭ እና በየከተሞቹ በመዘዋወር ያነሳኋቸው ፎቶዎች ብዛት ከ5ሺ በላይ ይሆናል፡፡ በ4 የተለያዩ ከተሞች በሚገኙ አምስት ዘመናዊ ስታድዬሞች 12 ብሄራዊ ቡድኖችን በማሳተፍ የተካሄዱ 15 ግጥሚያዎችን  ከምድብ ማጣርያው አንስቶ፤ በጥሎ ማለፍ፤በሩብ ፍፃሜ ፤ በግማሽ ፍፃሜ እና በፍፃሜ  ላይ በመታደም የፍሪላንስ ፎቶ ጋዜጠኝነቱን በዓለም ዋንጫው ላይ  ሰርቻለሁ፡፡ የዓለም ዋንጫው የፎቶ ጋዜጠኝነት ሜዳ ውስጥ በመግባት፤ በፎቶ እና የሚዲያ ትሪቡኖች በመገኘት ጨዋታዎቹን በምስል በማስቀረት እና በመከታተተል  ከፍተኛ ልምድም ነው ያገኘሁት። በስታድዬም የፎቶ ትሪቡን በመሆንና ሜዳ ውስጥ በመግባት ካነሳኋቸው ፎቶዎች የአርጀንቲና፤ የክሮሽያ፤ የእንግሊዝ፤ የራሽያ፤ የናይጀርያና የኮሎምቢያ ብሄራዊ ቡድኖች ሙሉ ስብስብ፤ የተጋጣሚ አገራት ደጋፊዎች በስታድዬም ውስጥ እና ከስታድዬም ውጭ፤ ጨዋታዎቹን ያስተናገዱ ዘመናዊ ስታድዬሞችን የሚያሳዩ ነበሩ፡፡ በቅርበት ባነሳኋቸው ፎቶዎች ምስላቸውን ለታሪክ ካስቀራኋቸው ተጨዋቾች መካከል ደግሞ  ሜሲ፤ አጉዌሮ፤ ኦቢ ሚኬል፤ ሞሰስ፤ ሞድሪች፤ ፖግባ፤ ሃሪ ኬንና በርካታ የራሽያ ተጨዋቾች … ሌሎችም ይገኙበታል፡፡ በየስታድዬሞቹ የነበሩ የደጋፊዎች ድባብ እና ሁኔታ፤ ከጨዋታው በፊት የበጎ ፈቃደኞችን ባንዲራ የመዘርጋት እና የመጠቅለል እንቅስቃሴ… ሌሎች ትእይንቶችም በካሜራዬ እይታ የገቡ ነበሩ፡፡
በ21ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ ከተሰማሩ የዓለማችን ፕሮፌሽናል ፎቶግራፈሮች እና የፎቶ ጋዜጠኞች የምለየው ደግሞ ከዓለም ዋንጫው ውጭ በነበረኝ እንቅስቃሴ ነበር፡፡ ዋና ስራዬ በነፃ የፎቶ ጋዜጠኝነት ታላቁን የስፖርት መድረክ   በፎቶ ሜዳ ላይ፤ በፎቶ ትሪቢውን በፊፋ ባገኘሁት ፈቃድ መሰረት በየስታድዬሙ ገብቶ መዘገብ ብቻ አልተወሰነም፡፡ የሞስኮ ፤ ኒዚሂኒ ኖቭጎሮድ ሴንት ፒተርስበርግና ሶቺ ከተሞችን ተዟዙሬ በመጎብኘት ልዩ የጉዞ ማስታወሻዎችን ጎን ለጎን በማዘጋጀት ከዓለም ዋንጫው ስታድዬሞች ውጭ  የነበሩ ትዕይንቶችን በፎቶዎች አስቀርቻቸዋለሁ። የቱሪስት መስህቦች፤ ታዋቂ ስፍራዎች፤ ሐውልቶች እና የከተማ ትእይንቶችን የሚያካትተቱ የሚገርሙ የፎቶ ስብስቦች ነበሩ፡፡ ዓለም ዋንጫውን ባስተናገዱ ከተሞች በሚገኙ የቱሪስት መስህቦች፤ አውራ ጎዳናዎች እና ዋና አደባባዮች እንዲሁም የዓለም ዋንጫ የፌሽታ ሲኒማዎች የተዘዋወርኩት ፎቶዎችን እያነሳሁ ብቻ አልነበረም፡፡ የጉዞ ማስታወሻዎቼን ለመፃፍ የሚያግዙ ቃለምልልሶች በመስራት፤ የተለያዩ ታሪካዊ እውነታዎችና ጠቃሚ መረጃዎችን በመሰብሰብ ጭምር ነበር፡፡
የዓለም ዋንጫ ተሳትፎዬ ከእግር ኳሱ የስታድዬም ድራማ ባሻገር በአስተናጋጅ ከተሞች ያሉ አስገራሚ ሁኔታዎች፤ ጠቃሚና አስደናቂ ተመክሮዎች፤ የየከተሞቹ ክላሲክ እና ዘመናዊ ህንፃዎች፤ የመታሰቢያ ሃውልቶች እና የጎበኘኋቸው የተለያዩ ከተሞች ልዩ ምልክቶች… በመተረክ እና ባነሳኋቸው ፎቶዎች በማጀብ የላቀ ልምድ የቀሰምኩበት ሆኗል፡፡ በዚህም በኢትዮጵያ ለሚገኙ የስፖርት ሚዲያ የፎቶ ጋዜጠኞች በሚያገኙት የውጭ እድል ተጠቅመው ከሚጓዙበት ዋና ዓላማ ባሻገር እንዲሰሩ ያነሳሳኋቸው ይመስለኛል።

Read 20947 times