Print this page
Saturday, 04 June 2022 15:25

ትውልድን ለመገንባት - ዘመንን ለመዋጀት

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በመጀመሪያ በዚህ ጽሑፍ ለቀረቡት አብዛኞቹ ሐሳቦች መነሻ የሆኑኝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በቅርቡ ለባለስልጣናት ባዘጋጁት ስልጠና ላይ ያቀረቧቸው ሐሳቦች በመሆናቸው፣ በቅድሚያ ላመሰግን እወዳለሁ። የምደግፈው እና የማመሰግነው ነገር እንዳለ ሁሉ የምቃወመውም ነገር የለም ማለት ግን አይደለም፡፡ ትውልድን የመገንባት -ዘመንን የመዋጀት ጉዳይ ሃይማኖትንና ሥነ አገዛዝን /ፖለቲካን/ አንድ ነጥብ ላይ የሚያገናኝ የጋራ ጉዳይ ነው።
ሀ/ ዓላማዎች
ከዓላማዎቹ እንነሳ፣ በመሠረቱ ማናችንም ብንሆን በዙሪያችን ያሉ ሰዎች፣ አብሮ ኗሪዎች፣ አብሮ ሠሪዎች፣ አብሮ አምላኪዎች ወዘተ… ለምናደርጋቸው ማናቸውም ነገሮች በመልካም ምግባር መልካም ምላሽ የሚሰጡን ሆነው ብናገኛቸው ደስ ይለናል፡፡
ማናቸውም ጎረቤቶቼ ያስቀመጥኩትን እንዳያነሱብኝ፣ ንብረቴንም ሆነ ሕይወቴን የማይጎዱ፣ ክብሬን የማያሳንሱ እንዲሆኑ እፈልጋለሁ፡፡ ሌላው ቀርቶ ራሳችን ድንገት ከሥነ- ምግባር ወጥተን ብንሳሳት እንኳ ለይቅርታ የተዘጋጁ እንዲሆኑ፣ ሰዎች መሆናችንን፣ እንደምንሳሳት እና ችግራችንን እንዲረዱልን እንሻለን፡፡ ይህ ማለት በአጭሩ አብረን የምንኖረው ኅብረተሰብ በመልካም ሥነ- ምግባር የታነጹ ሆነው እንዲገኙ እንመኛለን፤ እንወዳለን፡፡
ደግሞም የአንድ ኅብረተሰብ ጥሩነት የሚለካው ባለው የሥነ -ምግባር ባህል አማካኝነት ነው፡፡ ይህንን ሳይንሱም ያረጋገጠው እውነት በመሆኑ የሚከራከርበት ሰው እምብዛም ያለ አይመስለኝም፡፡ በአስተሳሰብ እና በዕውቀት፣ በሥነምግባር እና በክህሎት የዳበረ ሰብዕና ያለው ኅብረተሰብ ብዙ ነገሮቹ የተቃኑለት ይሆናል፡፡
ይልቁንም ትውልዱ በዘረኝነትና በጽንፈኝነት፣ በዝግነት አክራሪነትና በዋልታ ረገጥነት፣ በሞራል የለሽነትና በሥነ ምግባር እጦት ለሀገር ያፈጠጠ ጠንቅ እመሆን ደረጃ በደረሰበት በአሁኑ ጊዜ፣ ትውልዱን የመገንባትና ዘመንን የመዋጀት ሐሳብ እጅግ አስፈላጊና አንገብጋቢ ጉዳይ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
ለ/ ችግሮች
የትውልዱን አለመሠራት የሚጠቁሙ ማህበራዊ ህመሞች እዚህም እዚያም እየታዩ ነው፡፡ አቋም የለሽነት እና የአቋም መዋዠቅ በብዙዎች መታየት፣ የባህል አስተሳሰብ እና የመመሪያ ሥነ ርዕዮት አለመታወቅ፣ የሱሰኛነት እና ጠጪነት መስፋፋት፣ የተምሳሌታዊ ሰው መጥፋት፣ የባህል አፈንጋጮች እና ጸረ ኅብረተሰቦች ቁጥር መበራከት፣ የሙስና እና ብልሹ አሠራር መስፋፋት ወዘተ… ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው፡፡
እንደሚታወቀው ዲሞክራሲም ፍጹም ሥርዓት አይደለም፤ የራሱ አሉታዊ ጎኖች አሉት፡፡ የዲሞክራሲ እና የሊበራላዊነት መቀንቀን ይዞት የመጣው የሞራል አልባነት ችግርም አለ፡፡ በዚህ ላይ ለሞራል ድህነቱ ትልቅ መድኀኒት ሊሆነን ይችል የነበረው ግብረገባዊው የጋራ እሴታችን አለመታወቅ ወይም ተመሳሳይ ግንዛቤ አለመያዝ ሌላው እንቅፋት የሆነብን ነገር ነው፡፡
ሐ/ መፍትሔዎች
በጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ መሠረት፤ በ20ኛው እና በ21ኛው ክ/ዘመን የታዩ የኢትዮጵያችን ትውልዶች በ5 ሊታዩ የሚችሉ ናቸው፡፡
ወግ አጥባቂውና አርበኛው ትውልድ
ህልመኛው ትውልድ
ውል የለሹ ትውልድ
ባይተዋሩ ትውልድ እና
ገና መሰረቱን በማጠንከር ላይ የሚገኘው የመደመር ትውልድ ናቸው፡፡
አዲሱ ትውልድ ብዙ መረጃ ያለው፣ ብዙ የሚያውቅ የሚመስል፣ ነገር ግን ትክክለኛ ምርጫ ማድረግ የማይችል፣ በሥነ ምግባርም ደካማ ነው፡፡ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ አክራሪነትም እየተስፋፋ ነው፡፡ ስለዚህ ሀገሪቷ ላለባት ዘርፈ ብዙ ችግሮችና ላላት ትልቅ ህልም የሚመጥን ትውልድ ቀርጾ ማውጣት፣ ትውልድን እንደገና መሥራትና ማስተማር የግድ ነው፡፡
እንደኔ እንደኔ የዚህ ትውልድ መሪዎች፣ የሐሳብ መሪዎች፣ የፖሊሲ መሪዎች፣ የዕውቀት መሪዎች፣ የሞራል መሪዎች፣ የባህል መሪዎች፣ የኪነ ጥበብ ሰዎች እና የመገናኛ ብዙሃን ሰዎች ወዘተ… ከሥርዓተ-ትምህርቱ ሌላ በተጨማሪነትና በመፍትሔነት ልንሠራቸው ከሚገቡንና ልንከተላቸው ከሚገቡን ስልቶች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡ ዓላማችን መልካም ትውልድን መገንባትና ዘመንን መዋጀት ነው፡፡
በመጀመሪያ ምን ዓይነት ሀገር፣ ምን አይነት ትውልድ መፍጠር እንደምንፈልግ መግባባት እና በሥርዓተ-ትምህርቱም ማካተት አለብን፡፡
ምን አይነት፣ ለሚለው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የስልጠና ዝግጅት መልስ አለው፡፡ ህብረ ብሔራዊ አንድነቷ የተጠበቀ፣ የወንድማማችነት እሴቶቿ የጸናላት፣ የሲቪክ ባህል የዳበረባት፣ ቀጠናዊ ትስስርን ያጎለበተች፣ የሰዋዊነትንና የሀገራዊነትን ሚዛን የጠበቁ አርበኛ እና ሀገር ወዳድ ዜጎች ያሉባትና በርካታ ሀገራዊ የኩራት ምንጭ የሚሆኑ ተምሳሌታዊ ሰብዕናዎች የሚያፈሩባት ማለትም በሳይንሱ እንደነ ዶ/ር አክሊሉ ለማ፣ በስፖርቱ እንደነ ሻለቃ ሀይሌ ገብረስላሴ እና ሻለቃ ደራርቱ ቱሉ፣ ሌሎችም ያሉ በኢኮኖሚም፣ በዲሞክራሲም፣ በወታደራዊ አቅምም፣ በኪነ ጥበብም፣ በዓለም አቀፋዊ ሚናም ወዘተ… በየዘርፉ የሚያፈሩባት ሀገር መፍጠር የሚል ነው፡፡  
እንዲፈጠር የሚፈለገው የመደመር ትውልድ የማወቅ ጉጉት ያለው፣ ውብ ሥራን የሚያደንቅ፣ ሀገር የሚወድ- አርበኛ፣ ሰብዓዊ ክብር የገባው፣ የውይይት ባህልን ያዳበረ ወይም ጥልቅ ውይይትን የተለማመደ፣ ችግሮቹን በውይይት የሚፈታ ወዘተ… መልካም ትውልድ እንዲሆን ማስቻል ነው፤ ድንቅ ነው፡፡
በዚህ ላይ ትውልዱ ሥርዓታዊ የሆነ፣ የዕድገት ርዕዮት ያለው እና ምጣኔን እና የማዕከል ምጽዋትን ባህል ያደረገ ቢሆን ደግሞ ምን ያህል ወርቃማ ትውልድ እንደሚሆን አስቡት፡፡ ግን ደግሞ አንድ ክፍተት ይታየኛል፡፡ በ150 ዓመታት ውስጥ አመጣጣችን እንዴት እንደሆነ እና ወዴት መሄድ እንደምንፈልግ እንደተጠቀሰ ሁሉ ማን መሆናችን፣ ይዘን የመጣነው የጋራ እሴታችን ምን እንደሆነ፣ በአጭሩ ኢትዮጵያዊነት ማለት ምን እንደሆነ፣ የጋራ መግባባት የተያዘ አይመስልም፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ዝግጅት ሙሉ ለሙሉ ልንቀበለው የምንችል ሆኖ ሳለ ይህን ክፍተት ሳይሞላ አልፏል፡፡
ሁላችንን ሊያግባባን የሚችል ከሆነ ከሥነ ዜጋ እሴቶች ጋር በማያያዝ የቀረበውን የኢትዮጵያዊነት እሴቶች መግለጫ እንመልከት።
የሚከተሉትን ዝርዝር የኢትዮጵያዊነት እሴቶች ከፊታቸው ‹‹ኢትዮጵያዊነት›› በመዝጊያቸው ‹‹ነው›› የሚሉትን ቃላት እየጨመራችሁ እንድታነቡት እጋብዛለሁ፡፡
ሃይማኖተኛነት ፣ (የሕዝብ ቆጠራ ውጤቱም ይህን ይገልጻልና፡፡)
ግብረገብነት እና ሥርዓት አክባሪነት፣ (በጨዋ ደንብ መኖር ይመከራል፤ ያስመሰግናል፡፡)
አስተዋይነት፣ (ከጭምትነት የመነጨ፣ ነገር ግን እየተዳከመ የመጣ፡፡)
ሚዛናዊነት እና ፍትሐዊነት፣ (ባይኖረን እንኳ የሚፈለግ፡፡)
ቅንነት እና እውነተኛነት፣ (የተናገሩት ከሚጠፋ… እንዲሉ፡፡)
ባለሰንደቅ ዓላማነት፣ (ከጋራ ዓላማ የሚመነጭ የግለሰቦች እና የቡድኖች ሚና እና ዓላማ፡፡)
የምንዳቤ ታጋይነት፣ (ሁለንተናዊ ዕድገት) (ቢያንስ በዘመነ አክሱም የነበረን፡፡)
ገንቢ ጽናት፣ (ገንቢ ያልሆነ ጽናትም አለና፤) (ለለውጥ አለመቸኮል፣ ለለውጥ አለመለገም፣ እስከ ገባው ድረስ፡፡)
ልዩ ወንድማማችነት፣ (ኢትዮጵያዊ ወንድማማችነት፣) (የመረዳዳት፣ የመጠያየቅ፣ የምጽዋት ባህል)
የዜጎች ክብር፣ የሽማግሌዎች ሞገስ፣
መቻቻል እና አቃፊነት፣
እንግዳ ተቀባይነትና የምርቃት ምስጋና፣
ጨዋነትን ያስቀደመ ጀግንነት፣
የገዘፈ አንድነት ያነሰ ልዩነት፡፡
እነዚህን 14 የኢትዮጵያዊነት እሴቶች በግለሰብ ጉዳይ የሚተገበሩ፣ በእርስ በእርስ ጉዳይ የሚተገበሩና በሀገር ጉዳይ የሚተገበሩ ብለን በ3 ልንከፍላቸው እንችላለን፡፡
አንድ ኢትዮጵያዊ እነዚህ እሴቶች ባይኖሩት እንኳ የሚያስመሰግኑት ምግባሮች እነዚህ እንደሆኑ ያውቃል፡፡
ግብረገባዊ የጋራ እሴታችን ግለኝነትን፣ ሊብራልነት እና ሴኩላሪዝምን ከሚያቀነቅነው ከምዕራቡ ዓለም ማንነት የተለየ እና ማህበራዊነትንና መንፈሳዊነትን የተላበሰ እንደሆነ ተረድታችሁና አጢናችሁ እንድታልፉ በትህትና እጠይቃለሁ፡፡
ከጋራ ሥነ-ልቦናችን እና ከጋራ ባህላችን ውስጥ የሚነቀፉ ምግባሮች እና ልምምዶች እንዳሉ አይካድም፡፡
ቁጥር ሁለት ማድረግ የሚገባን ይኽን ለመሳሰሉ መልካም ባህሎቻችን የሕግ ዕውቅናና የሕግ ጥበቃ መስጠትና አጉል ባህሎችን መዋጋት ነው፡፡
አንድ ሚድሮክ ውስጥ የሚሰሩ ምሑር “ከሥርዓተ-ትምህርታችን ጀምሮ ሁሉንም ነገር ኢትዮጵያናይዜሽን ማደረግ አለብን፤” ሲሉ በዚሁ ጋዜጣ ላይ መግለጻቸውን አንብቤአለሁ፡፡ይኽም አስፈላጊና ጠቃሚ ነጥብ መረሳት የለበትም፡፡
በኦሮምኛ ሄራ የሚባል እንደ ሕገ -መንግስት ራሱን የቻለ የባህል ሕግና የተለየ ምክር ቤት እንዲኖር ያሳሰቡ ቅን ኢትዮጵያውያንንም በኢሳት ቴሌቭዥን አይተናል፡፡ እባካችሁ የኢትዮጵያዊነት ኀይሎች የመፍትሔ ሐሳብ መሰንዘራችንን እንቀጥል፡፡
ሦስተኛው ማድረግ የሚገባን ነገር የማስታወቂያ መሠረታዊ መርሆዎችን መቀየር ነው፡፡ መቼም የማስታወቂያ ኀይልና መዘዝ ብዙ ነው፡፡ ይሄንን እዚህ መዘርዘር ያለብን አይመስለኝም፡፡ የማስታወቂያ ልምድ ከምዕራባውያኑ የመጣ እንደመሆኑ መርሆዎቹም የነርሱን ፍልስፍና የተከተለ ነው፤ ሊብራልነትን፡፡ ለምሳሌ በታዋቂ ሰዎች ሳይሆን በዐዋቂዎች፣ በዝነኞች ሳይሆን በጨዋነት በዘለቁ ሰዎች እንዲቀርብ ማድረግ ትልቅ የሥነ-ምግባር አንድምታ ይኖረዋል፡፡ ምርቱና አገልግሎቱ የፈታው የኀብረተሰብ ችግር ሲኖርና የኃላፊነት መንፈስን ሲያንፀባርቅ፣ቄንጥ ያልበዛበት፣ የሥነ-ምግባራዊነት ድባብ ያለው እናም ከባህልና ከጨዋነት የወጣ አንድምታ የማይሰጥ እንዲሆን ቢደረግ፣
ደግሞም እንደ ገቢአቸው እና ትርፋቸው በመቶኛ የሚከፈል ክፍያ እንዲሆን ቢደረግ፣ ብዙ ችግሮች ይቀርፋሉ ብዬ አስባለሁ፡፡
በተለይ የሃይማኖት ብዙሃን ማሳወቂያዎች በገቢ እጥረት እንዳይቸገሩ፣ትውልድ የማነፅ ሥራቸውን ያለችግር እንዲገፉበት የሚያደርግ እንዲሁም ከፖለቲካ ተፅዕኖ የሚያላቅቃቸውና ከመሳቀቅም የሚያድናቸው ይሆናል። በተጨማሪም በተለይ ለሕፃናት ተብለው የሚከፈቱ ጣቢያዎች ከቅድመ ሁኔታ ጋር ማስታወቂያ ማስተላለፍ ቢፈቀድላቸውና ቅድመ ሁኔታውም መርሁን/አሠራሩን/ ማስተካክል ሆኖ፣ ማስታወቂያዎች፣- -ወላጆች ላይ ትኩረት ያደረጉ፣
- ልጆች ወላጆቻቸውን እንዳያስቸግሩ የሚመክሩ፣
- ለተያያዥ የሥነ-ምግባር መልዕክቱ አፅንኦት የሰጠ፣
- በአጭሩ ከምርቱ ይልቅ ሥነ-ምግባርን ያጎላ መልእክት የያዘ እንዲሆን ቢደረግ ፣እነርሱም በገቢ እጥረት አይዘጉም፤ አዲሱ ትውልድም እየተቀረፀ ይመጣል፡፡
በአራተኛነት ማድረግ የሚገባንና ማድረግ የምንችለው ፕሮጀክትና መከተል ያለብን ስልት፣ ያለንና የምንገነባው ግብረገባዊ ሰብዕናና ባህል ከባዕድ ባህል ወረራ አንዲጠበቅ ከደራሲዎችና ከአዘጋጆች ድርሰት /ስክሪፕት/ መርጦ እየገዛ አርሞና አመቻችቶ ሠርቶ የሚያሰራጭ የሥነ-ምግባራዊ ፊልም ጣቢያ መጀመር ነው፡፡
የዘመኑ ሌላው ኒውክሌር ፊልም ነው። የፊልምን ኃይልና የወጣቱን ስሜታዊነት እየተጠቀሙ የባህል ወረራ የከፈቱብን ብዙሃን መገናኛዎች ቁጥራቸው እየጨመረ ነው፡፡ ይኽን ዓይነቱን የብዙኀን መገናኛ ተፅዕኖ የምናሸንፈው እሾኽን በእሾኽ በሚለው መርህ ይመስለኛል፡፡
አንዳንድ ደራሲዎች ለምን ሥነ-ምግባራዊ መልዕክት ያለው ድርሰት /ስክሪፕት/ እንደማይጽፉ ሲጠየቁ ፣ ‹‹ጥበብ በነፃነት ውስጥ ነው፣ የምትሰራው፤ ስሜታችን የመራንን ሁሉ መጻፍ አለብን፤›› ይላሉ፡፡ ‹‹ያካለ ነፃነት ጥበብ የለም፤ዕድገት የለም፤›› ይላሉ፡፡
በመሠረቱ ጥበብ የሚፈልገው ራስን ማሳመን ነው። እንዲህ ባይ የጥበብ ሰዎች በካፒታሊስታዊ ድርሰት ፍልስፍና ስለተሸወዱና ወይም ራሳቸውን በበቂ ስላላዘጋጁ ብቻ ይህን የሚሉ ይመስለኛል።
ሁለት ዓይነት ሰዎች አሉ፤ ከሐሳባቸው ስሜታቸው የሚቀድምና ከስሜታቸው ሐሳባቸው /ጥያቄአቸው/ የሚቀድም። አዕምሮ ወይ በስሜት ይነቃቃል ወይ አልበርት አንስታይን እንዳለው መጠየቅን ባለማቋረጥ ይነቃቃል። ደራሲዎች የትኛውን ሊሆኑ ይገባል?
‹‹ጻፍ ጻፍ የሚል ስሜት ከውስጤ ይገፋኛል፤ ስለዚህ እጽፋለሁ፡፡›› ማለት፣ በቂ አይደለም። ራስን በብዙ ማዘጋጀት ያስፈልጋል፤ ብዙ ማንበብና ወይም ብዙ ማሰላሰል፤ አዕምሮን በስሜት ሳይሆን በጥያቄ መምራት ያስፈልጋል። ይህን ስል የድርሰቶችን ካፒታሊስታዊነት ብቃወምም፣ ደረቅ ይሁኑ የሚል አመለካከትም የለኝም። ይልቁንም ትምህርታዊ መስተፍስህ እንዲሆኑ፣ ወይም ልማታዊነትንና መስተፍስሀዊነትን አብረው የያዙ እንዲሆኑ ማድረግ ይቻላል፤ ባይ ነኝ። በግጥሙም ቢሆን ዋናው ሐሳብ፣ ስሜትና ምናብ ተዋህደው መገኘታቸው ነው። ማለትም ሐሳብ የቀደመበት ስሜትና ምናብ። ይህ አይቻለንም፤ ይጸንብናል፤ ለሚሉ ግን እንደ ፈቃደኝነታቸው ድርሰታቸውን /እስክሪፕታቸውን/ ማቅረብ እና መሸጥ ይችላሉ። ጎበዝ አዘጋጆች አፅመ ድርሰቱ ይበቃቸዋል ።ሌላውን መልዕክት ሥነ- ምግባራዊ እንዲሆን አድርጎ ማስተካከልና ደግሞ መጻፍና መሥራት አያቅታቸውም።
በአምስተኛነት ማድረግ የሚገባን፣ ይሄን እንኳን አልቋጨሁትም፣ ለውይይት የማቀርበው ነው። ይህም ለመገናኛ ብዙኃን መድብለ-እሳቤያዊ ሥርዓት መስጠት ነው። ማለትም ሐሳብ ከምላሽ ጋር /ከተቃወሞ ጋር/ የሚቀርብበት። ምንአልባት ደግሞ ተቃራኒዎች ቢኖሩና ባህላችንን ያለአግባብ ቢያንኳስሱ በሁለት መንገድ አፀፋዊ ምላሽ አያይዞ እንዲቀርብ ማድረግ የሚል ነው።
አንደኛ፣ ይዘቱን የተመለከተ ምላሽ፣ ለምሳሌ ከባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር ወይም ከሌላ ከሚመለከተው አካል የተሰጠውን አያይዞ እንዲያቀርብ እና ወይም ባህልንና ሥነ- ምግባርን የሚጠብቁ ማስታወቂያዎችንና ማሳሰቢያዎችን በየጣልቃው እንዲለቁ በሕግ ማስገደድ የሚል ነው። ይህ ሁኔታ ከተሳካ ልማታዊነትንና ዲሞክራሳዊነትን የሚያስታርቅ መርህ ተገኘ ማለት ነው፤ በሥነ-ምግባር የታነጸ መሪና ተረካቢ ትውልድ ሊፈራ ቻለ፤ ፈዋሹም ኪኒን ተገኘ ማለት ነው።
በስድስተኛነት ማድረግ ያለብን፣ ያለንን የሃይማኖት መቻቻል ባህል ለማዝለቅ የኢትዮጵያ ሃይማኖቶች ጉባኤ ወይም መሰል ሐሳብ ያላቸው ቡድኖችና ግለሰቦች የሃይማኖቶችን የጋራ እሴት የሚያዳብሩ መጽሔትና ጋዜጣ ወይም ሬድዮና ቴሌቪዥን እንዲኖራቸው ማድረግ ነው።
በመቀጠል በልማታዊና ትምህርታዊ መንገድ ትውልድን የመገንባትና ዘመንን የመዋጀት አስፈላጊነትንና ጠቃሚነትን የሚገልጹ አብነቶችን በትንሹ ጠቅሰን እንለፍ።
መ .መረጃዎችና መገለጫዎች
እንደ ሲንጋፖር፣ ጃፓንና ቻይናን የመሳሰሉ ሀገሮች የሕዝባቸው አእምሮ ላይ በመሥራታቸው አሁን የደረሱበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል። ሩቅ ሳንሄድ በሀገራችን ታሪክ ትልቁን ስፍራ ይዞ የሚገኘው የአክሱም ስልጣኔ እንዲህ ታይቶ የማይታወቅ የአንድ ሺህ ዓመት ተከታታይ ስልጣኔና ዕድገትን ሊያሳይ የቻለው ተተኪና ተረካቢ ትውልዶችን እያስተማረና እያሰለጠነ ያወጣ ስለነበር ነው፣ ብለው የሚያምኑ አሉ ።
ይህን ካደረግን በሥነ- ምግባር የታነጸ ምርታማ ትውልድ መፍጠር ብቻ ሳይሆን ፣ በስሜት ሳይሆን በምክንያታዊነት የሚመራ ትዉልድ ፈጠርን ማለት ነው። ይህም ለዘረኝነትና አክራሪነት ጥሩ መፍትሄ የሚሆን ነው። የተሰራ ትውልድ ዋናው መገለጫው ሥርዓታዊነትና ምኩናዊነት ነዉ ።
ሠ. መነሻዎችና ሂደቶች
ምዕራባውያን ከአራት መቶ አመት በፊት ከነበሩበት ድህነትና ኋላ ቀርነት ወደ ዛሬዉ ዕድገትና ስልጣኔ የመጡበትን መንገድ በእግረ መንገድ የሚጠቁም አንድ ጽሑፍ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ አንብቤአለሁ።
በመጀመሪያ የፍርድ አስተያየት የሚሆናቸውን ሥነ ርዕዮት ቀረጹ፤ ከማንነነታቸውም ጋር እንዲዛመድ አደረጉ ወይም ማንነታቸውን ከርዕዮቱ ጋር አስማሙ ፤ ከርዕዮቱም ተነስተው ሕግጋትን ቀረጹ፤ ከዛም ሥርዓተ- ትምህርትን ፣ከዚያም ኪነ-ጥበብንና ሚዲያን አስፋፉ፤በመጨረሻም የትውልድ ቀረጻቸውና ሥልጣኔአቸው እውን ሆነ።
እኛም ማድረግ ያለብን ይህንኑ ነው፤ የሚጀምረው ከሐሳብ መሪዎች ነው ። የትውልድ መሪዎች ሁሉ ቀዳሚ ኃላፊነት አለብን ።
  ነገር ግን ምዕራባውያን ሕዝበ መሠረቱን የሠሩት ቤተ ውይይቶችን ልማድ በማድረግ ፣በልማታዊነት መንገድ ሆኖ ሳለ ይህን መተዋቸው፣ ለወንጀለኛነት መበራከትና የሕይወት ትርጉም እየጠፋባቸው ራሳቸውን ለሚያጠፉ ሰዎች መበራከት ምክንያት ሆነዋል ።
ረ. ተገቢ እይታና መርሆዎች
ለትውልድ ግንባታ ስንነሳ፣ ርዕዮትና ሥርዓተ- ትምህርት ስንቀርጽ፣ በትውልድ ግንባታ ስም ትውልድ የሚያፈርሰውን የአማሳኞችን መንገድ እንዳንከተል ልንጠነቀቅ ይገባል።
‹‹ሰዎች ምን ማሰብ እንዳለባቸው ሳይሆን እንዴት ማሰብ እንዳለባቸው አስተምራቸው፣›› የሚለው ፍልስፍና ተማሪዎች የቤት ሥራ እንዲበዛባቸው ፣ ከብዙ ድምጾችና የሐሳብ ገበያ መካከል እውነትን ሲፈልጉ እንደባተቱ እንዲኖሩ የሚያደርግ አማሳኝ ፍልስፍና ነው።
ከዚህ ይልቅ ‹‹እኛ፣ እውነቱ ይሄ ነው እንላለን፣ ማሰብ የሚገባችሁ እንደዚህ ነው፣ ነገር ግን ስህተት ብታገኙበት የመተቸት መብታችሁ የተጠበቀ ነው፤›› በሚል አቀራረብ ማቅረቡ የተሻለ ነው፤ ከባህላችን ጋርም ይሄዳል።
ጉዳዩ ሀገርን የመሥራት ትውልድን የመገንባት ጉዳይ ነውና፣ ያለ ምጥና ያለ መስዋዕትነት አይሳካም። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ እንዳሉት፤ ሀገር የምትሰራው በደም፣ በላብ፣ በጭንቅላትና በልብ ነው። ማለትም መስዋዕትነትን በመክፈል፣ በብዙ ጥረትና በብዙ ድካም፣ በዕውቀት፣ በጥበብና በማስተዋል፣ በአዛኝ ልብ፣ በፍቅር ልብ ነው፤ ሀገር የምትሰራዉ።
ሀገር የምትሰራው በሰፊ ትከሻ ፣በብርቱ ትዕግስት ነው፤ ሀገር የምትሰራው ቀልጦ ብርሃን፣ ሟምቶ ጨው በመሆን ነው። ሀገር የምትሠራው በእምባ ነው፣ በፀሎት ነው፤ ከጅምሩ ያለፉበትንና የሚሄዱበትን በማየት ነው ፤ ሀገር የምትሰራው በብዙ ምክር ነው፤ እጅን በማንጻት /ማንንም ባለመበደል/ ነው፤ እንዲሁም ራስን በመግዛት ነው።
ነገሩ ለመሪዎች እንደሀብታም ጾም ነው፤ ትልቁ ትግል አድርጉ ያሉትን አድርጎ፣ አርአያና ምሳሌ ሆኖ መገኘቱ ነው። ትንሿ ስንፍና የምሳሌነት መጉደል ለዓመታት የተለፋበትን ፍሬ መና ልታደርግ ትችላለች።
ሰ. ተስፋና ሥጋቶች
ሀገሪቱ የጋራ ግብረገባዊ ባህል የነበራትና ጨርሶ የጠፋ ባለመሆኑ ፣ ባህልም በባህርዩ ራሱን የሚከላከልበትና የሚያቆይበት አሰራር ስላለው፣
አሁን ያለው አመራር ይህን መሰል ሐሳብ ፕሮጀክት ብሎ በመያዙ ፣ እንዲሁም
የሀገራዊ ምክክር መርሀ ግብር በመጀመሩና
የቤተ- እምነቶች አዎንታዊ እንቅስቃሴ የተነቃቃ በመሆኑ፣ ለዚህ ሐሳብ መሳካት ተስፋ አንዲታየን የሚያደርጉ ነገሮች ናቸው።
በሌላ በኩል፣
ዘመኑ የሉላዊነት በመሆኑ ፣ መረጃን መገደብ ስለማይቻል ፣
በቅርቡም በኅብረተሰቡ የታየው ዕውቀትን መሠረት ያላደረጉ የባህል ቅጅዎች /ለምሳሌ የወንዶችና የሴቶች አለባበስ /ብርቱ ጥረት እንደሚጠብቀን ስለሚያስገነዝቡን ትልቅ ግብግብና ትልቅ ውድድር እንደሚጠብቀን ይሰማኛል።
ነገር ግን የተጠቀሱትን ነገሮች ሁሉ በቁርጠኝነት፣ አቅማችንን አሟጠን ከተገበረን የሰብዕና ልማቱና የግብረገባዊነት ባህሉ የማይሳካበት ምክንያት የለም።
የስካንዴቪያን ሀገሮችስ በሥነ-ምግባር ባህላቸው ዘልቀው እናያለን አይደል? ያ እንደ ሰውነታችን ከምንመኘው ሥነ- ምግባራዊው አብሮ ኗሪ ጋር በሰላም በፍስሐ መኖር ቻልን፣ ምርታማነት ጨመረ ፣ ሀገራችንም አደገች ማለት አይደል?


Read 5678 times
Administrator

Latest from Administrator