Print this page
Sunday, 05 June 2022 00:00

የተባባሰው የሰብአዊ መብት ጥሰትና የኢሰመጉ ሽልማት

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 "አብዛኞቹ የመብት ጥሰቶች በቸልታ ነው የሚታለፉት"

          የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) ባለፉት 30 ዓመታት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ በአገሪቱ የሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩና የመብት ጥሰቶች እንዲጋለጡ ላበረከተው የጎላ አስተዋጽኦ ከአምነስቲ ኢንተርናሽናል የጀርመን ክፍል የ2022 የሰብአዊ መብቶች ሽልማትን ከሰሞኑ ተሸልሟል።
ተቋሙ ስላገኘው ሽልማት፣ በቅርቡ ስላወጣው የሶስት አመታት የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ሪፖርቱ እንዲሁም በወቅታዊ የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ይዞታ ጉዳይ የኢሰመጉን ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ገመቹን የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ እንደሚከተለው አነጋግሯቸዋል።



             ኢሰመጉ ለሽልማት የበቃው በምን ተግባራቱ ነው?
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ ለሽልማት የበቃው ባለፉት 30 ዓመታት ውስጥ በሰብአዊ መብት ጥሰቶች ላይ ላደረገው ምርመራና ለሰብአዊ መብቶች መከበር ላበረከተው አስተዋፅኦ ነው። የተሰጠው ሽልማት እጅግ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ለሰብአዊ መብቶች መከበር ለሚሰሩ ቡድኖችና ግለሰቦች የሚሰጥ ነው። እንግዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው ሁኔታ ይታወቃል። ባለፉት 30 ዓመታት አስከፊ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ተከስተዋል፤ ምንም እንኳን አሁንም ድረስ የምናያቸው ነገሮች የሰብአዊ መብት አያያዝ ላይ ጥያቄ የሚፈጥሩ ቢሆንም ማለት ነው። ነገር ግን ባለፉት 30 ዓመታት በኢሰመጉ ስር ሆነው ለሰብአዊ መብት መከበር የታገሉ በርካቶች ሲታፈኑ፣ ሲገደሉ፣ ከሃገር ሲሰደዱ ህይወታቸው ሲመሰቃቀል ነበር። ስለዚህ ሽልማቱ ለእነዚህ ሁሉ እውቅና የሚሰጥ ነው ማለት ነው።
ኢሰመጉ ከለውጡ በኋላ ራሱን እንደገና ለማጠናከር እያደረገ ያለው ጥረት ምን ያህል እየተሳካለት ነው? አሁንስ በምን ቁመና ላይ ይገኛል?
ሁሉም እንደሚያውቀው በ2001 ዓ.ም የወጣው የበጎ አድራጎትና ሲቪል ማህበራት አዋጅ በጣም አፋኝ ነበር። በገንዘብ አጠቃቀም ራሱ 90 በመቶ ከሃገር ውስጥ 10 በመቶ ብቻ ከውጪ እርዳታ እንዲቀበሉ የሚደነግግ ነበር። በዚያ ላይ የአስተዳደራዊና ስራ ማስኬጃ ተብለው የተቀመጡ ህጎች እጅግ በጣም አሳሪ ከመሆናቸው የተነሳ ኢሰመጉ በጣም አስቸጋሪ ጊዜ አሳልፏል። አሁን ለውጥ ከመጣ በኋላ አዋጁም የተሻሻለ በመሆኑ በተሻሻለው አዋጅ መሰረት ነው የምንንቀሳቀሰው። ነገር ግን አሁንም ያልተሻገርናቸው ችግሮች አሉብን። በሀገር ውስጥ ገንዘብ የማሰባሰብ ሁኔታ አስቸጋሪ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ የውጪ ሰዎች የየራሳቸው ፍላጎት ስላላቸው እርዳታ ሰጪዎችን በጥንቃቄ መምረጥ አለብን። በዚህ መሀል በጥንቃቄ ነው እየተጓዝን ያነው። በአሁን ወቅት የአምስት ዓመት እቅድና ፍኖተ ካርታ አዘጋጅተናል። አወቃቀሩን እንደገና ከልሰናል፤ በተጨማሪም የተለያዩ ተጨማሪ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶችን ለመክፈት ጥረት እያደረግን ነው። በአጠቃላይ ድርጅታዊ ስራችንን ከፍ ሊያደርጉ የሚችሉ ስራዎችን እያከናወንን ነው። ባለሙያዎችንም እያሰለጠንን ነው።
በቅርቡ ከ2011 እስከ 2014 በኢትዮጵያ የተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን የተመለከተ ሪፖርት አውጥታችኋል። ይህ ሪፖርት በመላ ሃገሪቱ የተፈጸሙ ጥሰቶችን የዳሰሰ ነው የሚል እምነት አላችሁ?
እንደዛ የሚል እምነት የለንም። ነገር ግን የሰብአዊ መብት ጥሰት ምርመራ ሲሰራ የትኩረት መጠን ከሌለን አስቸጋሪ ነው የሚሆነው። ለምን ከተባለ አንደኛ አቅም ያስፈልጋል፣ የሰው ሃይል ያስፈልጋል። በእነዚህ በሁለቱ መሟላትና ብቃት ነው የምርመራ አድማሳችን የሚወሰነው። እንደፍላጎታችን ቢሆን ሁሉንም መዳሰስ ብንችል ደስተኞች ነን። ነገር ግን የአቅም ውስንነት ስላለብን መርማሪዎቻችን የደረሱባቸውን አካባቢ ብቻ ነው ለመዳሰስ የተቻለው። ከዚህ ባለፈ ምርመራ የምናደርግባቸውን አካባቢዎች እንደ ናሙና ነው የምንመለከተው። ሁሉም ቦታዎች የተከሰቱትን እናጥና ብንል ግን በኛ አቅም የሚቻል አይሆንም። በጣም ሰፊ የሰው ሃይልና ሃብት ያስፈልጋል። ከዚህ አኳያ ነው ውስንነቶች ሊኖሩበት የሚችለው።
ባለፉት ሶስትና አራት አመታት በየቦታው ስለሚፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች አጫጭር ሪፖርቶች ስታወጡ ነበር። እነዚህን ሪፖርቶች ተመስርቶ በመንግስት በኩል ተጠቃሽ የሆነ የማስተካከያ እርምጃ ተወስዷል የሚል እምነት አላችሁ?
በአብዛኛው በዝምታ ነው የሚያልፈው። የምናወጣቸውን ሪፖርቶች መንግስት ተመልክቶ እርምጃ ሲወስድ እምብዛም አይታይም። አንዳንድ ጊዜ እርምጃዎች ሲወሰዱ የምናይባቸውም አጋጣሚዎች አሉ።
ለምሳሌ?
ለምሳሌ የተፈናቀሉ ሰዎችን መልሶ ማቋቋምን በተመለከተ አዲስ አበባ ላይ ከመሬታቸው ተገቢ ካሳ ሳይሰጣቸው የተፈናቀሉትን በማቋቋም ረገድ እርምጃዎች ተወስደዋል። በተረፈ ግን መንግስት ብዙዎቹን ጥሰቶች በቸልታ ነው የሚያልፈው። በቅርብ ጊዜ እንኳ እየተፈጠሩ ያሉትን ብንመለከት ጋዜጠኞች፣ የማህበረሰብ አንቂዎች፣ ግለሰቦች በህገ-ወጥ መንገድ ለቀናት የት እንዳሉ እንኳ እንዳይታወቁ በማድረግ የማሰር ሁኔታ፣ ሰዎችን ያለ ፍርድ ቤት ማዘዣ ማሰርና ፍ/ቤት ሳይቀርቡ ማቆየት የመሳሰሉ ድርጊቶች በስፋት ነው እየተፈጸሙ ያሉት። እኛ ይሄ ነገር ተገቢ አይደለም እያልን በየጊዜው ሪፖርት እናደርጋለን። ነገር ግን የሚሰማ ጠፍቶ ድርጊቶቹ ከእለት ወደ እለት እየጨመሩና እየሰፉ የሄዱበት ሁኔታ አለ። ይሄን መንግስት በጅምሩ መቅጨት ሲገባው በቸልታ እያለፈው እየተመለከትን ነው። የሰብአዊ መብት ጥሰት ፈጽመዋል ተብለው በየሪፖርቱ የሚዘረዘሩ አካላት ላይ የህግ እርምጃ እየወሰደ አለመሆኑ፣ ከዚያም በላይ በራሱ አስፈጸሚ አካላት ላይ ጭምር እርምጃ ወስዶ ማስተካከል አለመቻሉ አሳሳቢ ነው። ለተፈጸሙ ድርጊቶች ይቅርታ ሁሉ መጠየቅ ይጠበቅበታል። ነገር ግን አብዛኞቹ በቸልታ ነው የሚታለፉት። አሁን የመንግስት ቸልተኝነት በማየሉ ድርጊቶቹ እየተለመዱ መሄዳቸውን እናስተውላለን። በዚህም ድሮ በመንግስት አካላት ብቻ ይፈጸሙ የነበሩ የመብት ጥሰቶች አሁን በሌላም በጎንዮሽ እየተፈጸሙ እየተመለከትን ነው። ከዚህ አንጻር መንግስት ሃላፊነቱን በአግባቡ እየተወጣ ነው ለማለት ያስቸግራል።
በሃገሪቱ ለሚስተዋሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ዋነኛው መንስኤ ምንድን ነው?
ከ2010 እስከ 2013 ባሉት ድርጊቶች ላይ ሌላ የትንታኔ ስራ እየሰራን ነው ያለነው። ያ ትንተና ሲጠናቀቅ ዝርዝሩን መናገር ይቀላል። ነገር ግን በዚህ ወቅት የተፈጸሙ ድርጊቶች መነሻቸው ምንድን ነው? አባባሽ ሁኔታዎች ምንድን ናቸው? ተዋናዮቹ እነማን ናቸው? የመብት ጥሰቶቹ በበፊቱና በአሁኑ መካከል ያላቸው አንድነትና ልዩነት ምንድን ነው? አውዳቸው ምን ይመስላል የሚለው በዝርዝር እየተጠና ነው።
በአሁን ሁኔታ የሚታዩ ግኝቶችን በግርድፍ ብንመለከት እንኳ የሃይማኖት፣ የብሄር መልክ ያላቸውን ማንሳት እንችላለን። በዚህ ውስጥ የመንግስት አካላት፣ ሌላው ማህበረሰብ ያለው ድርሻ ምንድን ነው የሚለው በደንብ መተንተን አለበት። አፈናውንም ብንመለከት በአመዛኙ በሚፈጠሩ ችግሮች ውስጥ የመንግስት አካላት እጆች እንዳሉበት ማስተዋል ይቻላል። ጥቅል ሁኔታውን በቅርቡ ተንትነን እናቀርባለን። በየአካባቢውም ውይይቶች እያደረግን ነው ያለነው። አሶሳና ባህር ዳር ላይ አድርገናል። ሃዋሳ፣ አዲስ አበባና አዳማ ላይ የሚቀጥል ይሆናል። ስለዚህ በእነዚህ ቦታዎች የሚደረጉ ውይይቶችን ግብአት አድርገን በቀጣይ የምናወጣው ዝርዝር ሪፖርት ይኖረናል። የ30 ዓመቱን ሂደት መነሻ አድርገን በተለይ ደግሞ ከ2010 ጀምሮ ለምንድን ነው ነገሮች እየተባባሱ የመጡት የሚለውን የምናይበት ይሆናል።
ባለፉት ሶስት ዓመታት የተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በአመዛኙ በየትኛው አካል ነው የተፈጸሙት? ምርመራችሁ ምን ያመለክታል?
የመብት ጥሰት በየትኛውም አካል ቢፈጸም መንግስትም ተጠያቂ መሆኑ አይቀርም፡፡ ምክንያቱም መንግስት የሁሉንም ዜጎች የሰብአዊ መብት ማክበር ብቻ ሳይሆን የማስከበር ግዴታና ሃላፊነትም አለበት። አሁን አብዛኛው የመብት ጥሰቶችን ስንመለከት ከጎንዮሽ ጥቃት የሚመነጩ ናቸው። የጎንዮሽ ስንል ወንድም ከወንድሙ መጋጨት አይነት ነው። እንደማሳያ ሀዋሳ ላይ፣ ሻሸመኔ ላይ ሌሎች ቦታዎችም የተከሰተውን ብናይ ወንድም በወንድም ላይ አይነት ይዞታ ያላቸው ናቸው። ነገር ግን ይሄ ማለት የመንግስት አካል እጁ የለበትም ማለት አይደለም። ድርጊቱን ማስቆም ያለመቻልን ጨምሮ የዜጎችን ደህንነት ያለማስጠበቅም ሁሉ ተጠያቂ ያስደርጋሉ። በዚህ መልኩ የታሰሩ የከተማ ከንቲባዎች አሉ። ማህበረሰብ ዝም ብሎ ግጭት ውስጥ አይገባም። ለኳሽ ሃይል ያስፈልጋል። ያ ሃይል አንዳንዱ ከተፎካካሪ ፓርቲ ሌላው ደግሞ ከገዢው ፓርቲ ሊሆን ይችላል። ብዙዎቹ ግጭቶች መነሻቸው ከጀርባቸው ሌላ አላማ በያዙ አካላት የሚመጣ ነው። በሰፊው እየተፈጸመ ያለው የመብት ጥሰት የጎንዮሹ ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በመንግስት አካላት ሰዎችን የማፈን፣ አስሮ የማንገላታት አይነት ድርጊቶች እየተበራከቱ ነው። ሃይማኖትና ብሄር ሰፊውን ቦታ ይውሰዱ እንጂ ከዚህ በፊት በግጦሽ መሬት ተጣልተው ወዲያው ይታረቁ የነበሩ ማህበረሰቦች ጭምር ነገሩ ወደ ሌላ እየተለወጠባቸው ግጭቱ እንዲበረታ ሲደረግም ይስተዋላል።
በአሁን ወቅት የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በጥቅሉ ምን ደረጃ ላይ ናቸው? ከቀድሞ እየተሻሻሉ ነው ወይስ እየተባባሱ ነው?
በኛ ግምገማ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከጋዜጠኞች አኳያ እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች አሳሳቢ ሆነዋል። በሌላ በኩል የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከፍ እያሉ የመጣበት ሁኔታ አለ። ይህን ስንል ሰዎች በወንጀል ተጠርጥረው መያዝና መመርመር የለባቸውም ማለታችን አይደለም፤ ዋናው ሂደቱ ተገቢውን የህግ አግባብ ተከትሎና የግለሰቦቹን መብት ባከበረ መልኩ መሆን አለበት። ያለ ፍርድ ቤት ትእዛዝ ሰዎችን ማሰርና መደበቅ ትልቅ የመብት ጥሰት ነው።
የታሰሩ ጋዜጠኞችና የሚዲያ ባለሙያዎችን ጉዳይ ኢሰመጉ እንዴት ይመለከተዋል? ጉዳዩንስ ምን ያህል በትኩረት እየተከታተለው ነው?
ኢሰመጉ ሰዎች ያለ አግባብ ሊታሰሩ እንደማይገባ ደጋግሞ ይገልጻል። የታሰሩም ሰዎች በአፋጣኝ ፍ/ቤት እንዲቀርቡ ይወተውታል። ሰዎች ከታሰሩ በኋላ የት እንዳሉ እንዳይታወቅ በሚያደርጉ፣ ፍ/ቤት በጊዜው በማያቀርቡ፣ እስረኛን በሚያንገላቱ ላይ መንግስት እርምጃ እንዲወስድ እንጠይቃለን። አሁን በቅርቡ ያሉ ሁኔታዎችንም በቅርበት እየተከታተልን ነው ያለነው። የት ናቸው? ምን ላይ ናቸው? ኢትዮጵያ ውስጥ ምን እየተካሄደ ነው? የሚሉ ጉዳዮችን በአንክሮ እየተከታተልን ነው።

Read 1049 times
Administrator

Latest from Administrator