Tuesday, 07 June 2022 06:25

ወንጀል ሲበዛ፣ ስጋት ሲበረታ፣ ሽጉጥ ታጣቂ ይበረክታል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የአሜሪካ ቁጥሮች ምን ይላሉ?

በወር 1 ሚሊዮን ሰዎች ሽጉጥ ይገዛሉ።
260 ሚሊዮን ነው፤ በሕጋዊ መንገድ የተገዛና የተመዘገበ የግል መሳሪያ ብዛት።
ከ100 ሚሊዮን በላይ ነው፤ ያልተመዘገበና ከጥቁር ገበያ የተገዛ፣ የተሰረቀ ወይም የተዘረፈ የግል መሳሪያ ብዛት።
ከ400 ሚሊዮን ይበልጣል፤ አሜሪካዊያን በግል የታጠቁት የሽጉጥና የጠመንጃ ብዛት።
በመላው ዓለም ካለው የግል መሳሪያ መካከል፣ 46 በመቶው አሜሪካ ውስጥ የሚገኝ ነው።
በዓመት ከ100,000 በላይ የግል መሳሪያ፣ የዝርፊያ ሲሳይ ይሆናሉ። ዛሬ፣ ዛሬ ከመኪና ውስጥ መስረቅ እየተበረከተ ነው። ቺካጎ እና አትላንታ በመሳሰሉ ከተሞች፣ የመሳሪያ ስርቆት በእጥፍ ጨምሯል።
በዓመት ውስጥ፣ በአንድ ከተማ (በሂዩስተን) ብቻ ከ3,600 በላይ የግል ጠመንጃ፣ ከመኪና ተሰርቀዋል ይላል - ዎልስትሪት ጆርናል። መንስኤና መዘዝ አለው።
ባለፉት ሁለት ዓመታት፣ የግድያ ወንጀል በ30% ጨምሯል - በምድረ አሜሪካ። በአመት 10ሺ ገደማ የነበረው የመሳሪያ የግድያ ብዛት፤ አምና ወደ 14ሺ ደርሷል። ወንጀል ሲበዛ ደግሞ፣ ጠመንጃ የሚገዛ ሰው ይበረክታል።
በትምህር ቤት፣ በሆስፒታል፣ በመዝናኛ ቦታዎች… የተገኘውን ሰው ሁሉ በእሩምታ የመግደል፣ አላፊ አግዳሚ ላይ ደርዘን ጥይቶችን የማርከፍከፍ ጥቃትም ተባብሷል። ከ20 ዓመት በፊት፣ በዓመት በአማካይ 20 ሰው አይሞትም ነበር። በ2007 በኋላ፣ የሟቾች ቁጥር፣ በዓመት ወደ 30 ጨምሯል። ከ2012 ወዲህ ደግሞ፣ በአማካይ፣ የዓመቱ ከ40 በላይ ሰዎች ይሞታሉ - በክፉ የጅምላ እሩምታ።
የወንጀለኞች ዋና ትጥቅ፣ በስርቆት ወይም በዝርፊያ የተገኘ ጠመንጃ ነው። ከ100 ባለጠመንጃ ወንጀለኞች መካከል፣ 85 ያህሉ፤ መሳሪያቸውን የሚያገኙት በስርቆት ነው፤ ወይም ከዘራፊዎች በመግዛት።
ከመኪና ውስጥ የጠመንጃ ስርቆት በእጥፍ የጨመረውስ ለምንድን ነው? ለግል መሳሪያ አዲስ የሆኑ ጀማሪ የሽጉጥ ባለቤቶች፣ ሁሌም፣ ለስርቆት የተመቻቹ ናቸው። ባለፉት 5 ዓመታት ደግሞ፣ ሽጉጥ የሚገዙ ጀማሪ ሰዎች በዝተዋል።
                      ዮሃንስ ሰ


                         በዓመት ከ10 ሚሊዮን የሚበልጡ አሜሪካዊን፣ የግል መሳሪያ ይገዛሉ። የአብዛኞቹ ምርጫ ደግሞ ሽጉጥ ነው። የባለፈው ዓመት ገበያ ግን፣ የቀድሞቹን ያስንቃል። ከ20 ሚሊዮን በላይ ዜጎች፣ የግል መሳሪያ ለመግዛት ገበያ ወጥተዋል (ከሱፐርማርኬት፣ ከጦር መሳሪያ መደብር፣ ወይም በኢንተርኔት)።
ብዙ ጣጣ የለውም። ገንዘብ ያለው፣… እና እድሜው 21 ዓመት የደረሰ፣… እና ከወንጀል ጋር ያልተነካካ ማንኛውም ዜጋ፣ የግል መሳሪያ መግዛት ይችላል።
የመሳሪያ አያያዝና አጠቃቀምን ከነጥንቃቄው አሟልቶ ለማወቅ፣ የአንድ ሳምንት ስልጠና ያስፈልግ ይሆናል። አይ፤ አያስፈልግም። ሽጉጥ መፈታታት፣ ማጽዳት፣ መገጣጠም፣… በአስተማማኝ ቦታ ቆልፎ ማስቀመጥ፣ የእያንዳንዱ ሰው ሃላፊነት ነው። ንብረቱን እንዲጠብቅ እና ለዚህም ስልጠና እንዲወስድ የሚያስገድድ አዋጅ አይወጣም። የግል መሳሪያ ለመግዛት፣ ልዩ እውቀት እና ልምድ አያስፈልገውም።
ሽጉጡንና ጠመንጃውን በትክክለኛ መንገድ ፈትሾና አረጋግጦ በአግባቡ ለመታጠቅስ? እዚህ ላይ ስልጠና ያስፈልጋል። ብዙ አይደለም። የአንድ ቀን ስልጠና ብቻ። በአጭሩ፣ ሽጉጥ መግዛትና ሽጉጥ ታጥቆ መንቀሳቀስ ይለያያሉ።
የግል መሳሪያ መግዛት፣… ፈቃጅና ከልካይ የለውም። በሕገመንግስት የተጻፈለት፣ በጠቅላይ ፍርድ ቤት የተመሰከረለት፣ የእያዳንዱ ሰው መብት ነው። የእድሜ ማረጋገጫ ይቀርባል። ከወንጀል ጋር እንዳልተነካካ በኢንተርኔት ከኤፍቢአይ መረጃ ይጣራል። በቃ፣ የግል መሳሪያ ባለቤት ይሆናል። ወደ መቶ ሚሊዮን የሚጠጉ አሜሪካዊንም፣ በዚህ መንገድ መሳሪያ ገዝተዋል።
ሽጉጥ ታጥቆ መንቀሳቀስ ግን፣… ሌላ ጉዳይ ነው። አሳማኝ ምክንያት ማቅረብና ፈቃድ ማግኘት ያስፈልጋል። አንዳንዶቹ ግዛቶች፣ ጥያቄ ላቀረበ ሁሉ ፈቃድ ይሰጣሉ። የአንድ ቀን ስልጠና መውሰድ ግን፣ ግዴታ ነው። የአተኳኮስ ችሎታ ማሳየት አለብህ የሚሉም አሉ።
በፍሎሪዳ ግዛት፣ ሽጉጥ አቀባብሎ አንድ ጥይት መተኮስ በቂ ነው። አንዳንዶቹ ግዛቶች ግን፣ የትጥቅ ፈቃድ ለማግኘት፣ በአካል መለማመድም አያስፈልግም።
ሽጉጥ በመዳፍ ጨብጦ፣ የጣቶች አቀማመጥ አስተባብሮ፣ የሰውነት አቋቋም አስተካክሎ፣ እጅ አንስቶ፣ ክንድ ዘርግቶ. በአንድ ዓይን መሳሪያውን ወደ ኢላማ አነጣጥሮ፣ አተነፋፈስና የጣት እንቅስቃሴ ጠብቆ፣ ማቀባበልና መልሶ ወደ አፎቱ መመለስ፣ ወይም መተኮስና መድገም፣… ይሄ ሁሉ ጥያቄ የለም። የአንድ ሰዓት የመማሪያ ቪዲዮ ማየት በቂ ነው - በቨርጂኒያ ግዛት።
ምናለፋችሁ፣ ሽጉጥ የመታጠቅ ፈቃድ እንደ ልብ እየሆነ ነው። ከ20 ሚሊዮን በላይ አሜሪካዊያን የመታጠቅ ፈቃድ አግኝተዋል።
ለነገሩ፤ መሳሪያ ለመግዛት ብቻ ሳይሆን ታጥቆ ለመንቀሳቀስም፣ የመንግስት ፈቃድ አያስፈልግም የሚሉ ክልሎች በዝተዋል። ከአሜሪካ ግዛቶች መካከል ግማሾቹ፣ ማለትም 25 ግዛቶች፤ “ሽጉጥ ታጥቆ መንቀሳቀስ መብት ነው። ፈቃድ አያስፈልግም” ብለው አውጀዋል።
ቢሆንም ግን፣ ስልጠና ጥሩ ነው። የትምህርትና የስልጠና ጥቅሙ፣ ፈቃድ ለማግኘት ብቻ አይደለም። የስልጠና ትርፉ፣ የግል መሳሪያን በአግባቡ ለመጠቀም፣ ለመተኮስና ኢላማ ለመምታት ብቻ አይደለም። ወደ ዚያ የሚያደርስ መጥፎ አጋጣሚ አይመጣ ይሆናል። የከፋ ነገር ከመጣ ግን፣ ሽጉጥ መምዘዝና መተኮስ ካልቀረ፣ ኢላማን የመምታት ችሎታ ቢኖር ጥሩ ነው።
ነገር ግን፣ የጦር መሳሪያን በዋዛ ላለማየትም ይጠቅማል - ስልጠና። “የአደገኛ ነገር ባለቤት” መሆን፣ የዚያኑ ያህል አስተዋይነትን እንደሚጠይቅ ለመረዳት፣ የሃላፊነት ስሜትን በተግባር ለመጨበጥ ይረዳል - የጥቂት ቀናት ትምህርትና ልምድ። በተለይ ጥሩ አሰልጣኝ ከተገኘ፤ የእድሜ ልክ ትምህርት ይገበዩበታል።
ጎበዝ ባለሙያ፣ በጦር መሳሪያ አይቀልድም። በዘፈቀደ መሳሪያውን እያነሳ አይጥልም። እንደ መጫወቻ፣ ወዲህና ወዲያ አያወናጭፍም። እንደ ተራ እቃ፣ ባገኘው ቦታ ላይ ጦር መሳሪያውን አያስቀምጥም። ብዙ ሰዎችም፣ ፈጠነም ዘገየም፣ ሽጉጣቸውን ወይም ጠመንጃቸውን በጥንቃቄ የመያዝ፣ በአስተማማኝ ቦታ የማስቀመጥ ልምድ ያገኛሉ።
በተለይ፤ ወላጆቻቸው ባለጠመንጃ ባለሽጉጥ ከነበሩ ጠንቃቃነትን መለማመድ ለልጆች ከባድ አይሆንም። እንደ ባህል ነው። ከመቶ ቤተሰብ ውስጥ 40 ወይም 50 ያህሉ፣ የጦር መሳሪያ ባለቤት ናቸው -በአሜሪካ። የመሳሪያ ባለቤቶች፣ በአማካይ ቢያንስ 2 የግል መሳሪያ ይኖራቸዋል።
ወላጆች ባለ ሽጉጥ ባለ ጠመንጃ ከነበሩ፣ ልጆችም በዚው ልማድ የመሳሪያ ባለቤት ቢሆኑ አይገርምም። አዲስ አይሆንባቸውም። የአያያዝና የአጠቃቀም ጥንቃቄ፣ ገና በልጅነታቸው ይዋሃዳቸዋል - ፍላጎት ካላቸው። ከወላጅ ከቤተሰብ የመማርና የመለማመድ እድል ላልነበራቸው ሰዎች ግን፣ ነገሩ ፈታኝ ነው።
ሞባይልና ማማሰያ፣ ማበጠሪያና ኩባያ ብቻ የለመደ እጅ፣ “የጦር መሳሪያን አደገኛነት” ከምር ለመገንዘብ፤ ይቸገራል። በሃሳብ ደረጃ ማዳመጥና መማር አይከብደውም። ነገር ግን፣ ከስሜቱና ከመንፈሱ ጋር ለማላመድ፣ እውቀቱን ከምር ከግል ማንነቱ ጋር ለማዋሃድ፣ ቀላል አይሆንለትም።
እዚህ ላይ ነው ችግሩ። አሁን አሁን፣ ወደ መሳሪያ ሸመታ እየጎረፉ ያሉት አሜሪካዊያን፣ ሽጉጥ አጠገብ ደርሰው የማያውቁ ጀማሪዎች ናቸው። እንደ ኤሚሊያ፣ እንደ ስታርሌት፣ እንደ ቶያ ተከር ዓይነት የሽጉጥ ገበያተኞች ናቸው የበረከቱት።
በወላዶቿ፣ በአያቶቿ ቤት ውስጥ፣ ሽጉጥ አይታ አታውቅም - ቶያ ተከር። ቤተሰብ ውስጥ ወሬውን እንኳ አላስታውስም ትላለች። አሁን ግን፣… አገሩ ከተማው ሁሉ አስፈሪ ሲሆን ምን ላድርግ? መኪና እያስቆሙ የሰውን ሕይወት የሚያጠፉ፣ እንደመጣላቸው የሚተኩሱ ታዳጊ ወጣቶችን ታያለህ ብላለች ተከር።
በጥቂት ዓመታት ውስጥ፣ ቺካጎ እንዴት እንደተቀየረች ሳስበው ይገርመኛል ትላለች ሌላኛዋ። መፍትሔው ምን እንደሆነ እንጃ። ግራ በመጋባት ነው ሽጉጥ የገዛሁት ትላለች ኤሚሊያ። በቤተሰባችን በጭራሽ ያልነበረ ነገር ነው ብላለች - ጀማሪዋ ባለሽጉጥ።
ለወትሮው የሽጉጥ የጠመንጃ ገዢዎች ወንዶች ነበሩ። 70 በመቶ ወንዶች፣ 30 በመቶ ሴቶች። ይሄ ግን ያኔ ድሮ ነው።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ቁጥራቸው እየተጠጋጋ ነው። ከወንዶች መካከል 54 በመቶ ያህል፤ ከሴቶች ደግሞ 41 መቶ ባለሽጉጥ ባለጠመንጃ ናቸው - (ከዓመት በፊት Rasmussen ያካሄደው ጥናት)። ነጭ እና ጥቁር አሜሪካዊያን መካከልም፣ ልዩነት እየጠፋ ነው።
ሁሉም አሜሪካዊያን፣ ሴት ወንድ፣ ጥቁር ነጭ፣ ሽጉጥ በመግዛት በኩል፣ ለመጀመሪያ ጊዜ፣ እኩል ለእኩል ሆነዋል። እንዲያውም፣ ዛሬ ዛሬ. ሽጉጥ የሚገዙ ሴቶች ናቸው የበዙት በማለት ይገልጻሉ - የጦር መሳሪያ መደብሮች።
የጦር መሳሪያ ልምድ የሌላቸው ጀማሪ ባለሽጉጦች፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ናቸው። መቼስ ምን ይደረግ? ሕይወታችሁ ንብረታችሁ ከጥቃት አትከላከሉ፤ ራሳችሁን አታድኑ አይባልም። ከሕይወት ክብር በላይ ምን አለ! ምንም!
ግን፣ ሽጉጥ የመግዛት ያህል ነገሩ ቀላል አይደለም።
“ወይ ጀማሪ መሆን” ብለው የለ ባቅኔው።
ጀማሪ መሆን አስቸጋሪ ነው። መቼም፣ ካዝና ውስጥ ቆልፈው ለማስቀመጥ ብቻ፣ ወይም ለመኖሪያ ቤት ጥበቃ ብቻ አይደለም ሽጉጥ የሚገዙት። በየመንገዱም የወንጀል አደጋ አለ። በየሄዱበት ቦታ፣ በገበያና በመዝናኛ አካባቢም የወንጀል ጥቃት ያጋጥማል።
ከመኖሪያ ቤት ውጭም፣ ሽጉጥ ይይዛሉ። መንገድ ላይ ችግር የለም። የስራ ቦታ፣ ገበያ፣ ለጉዳይ የሄዱበት ቢሮ ላይ ሲደርሱ ነው ጥያቄ የሚመጣው። ሽጉጥ ታጥቆ መግባት አይቻልም።
መኪና ውስጥ፣ ከወንበር ስር ይሸጉጡታል፣ የመኪናው የቁሳቁስ ማስቀመጫ ኪስ ውስጥ ያስቀምጡታል። አንዳንዶቹማ፣ በኑሮ ጥድፊያ ሲዋከቡ፣ የጋቢና ወንበር ላይ ሽጉጣቸውን አስጥተው ወደ ጉዳያቸው ይሮጣሉ። ለዚህ ነው፣ በብዙ ቦታ የሽጉጥ ስርቆት ባለፉት ሁለት ዓመታት በእጥፍ የጨመረው።
ወንጀል ሲበዛ፣ ሽጉጥ የሚገዛ ሰው ይበረክታል። የተሰረቀ ሽጉጥም ይበዛል።


Read 7151 times