Tuesday, 07 June 2022 06:41

“ይህን ያህል የሊቃውንት ሀገር ሆናለች እንዴ!”

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ገና “ግንቦት ገባ እኮ!” ነው ብለን ሳይበቃን ሽው ብሎ መውጣቱ ነው ማለት ነው! ደግነቱ የምንገረምበት ነገር ከመብዛቱ የተነሳ አለፍነው እንጂ ነገርዬው የሚገርም ነው፡፡ እናማ...“ጊዜው እንደ ጉድ ይሮጣል!” እንባባላለን፡፡ ስሙኝማ... ቅሽምሽም ያለ  ጥያቄ ለመጠየቅ ግሪን ካርድ ይሰጠንና... አለ አይደል... ጊዜው መሮጡን ነው እንጂ ማን እንደሚያሳድደው፣ ወይም ማን እያሳደደው እንደሆነ ምነዋ ጠይቀን አናውቅ! ልክ ነዋ፡፡ አሁን ለምሳሌ “ወሩ ከመግባቱ ለምንድነው ፈጥኖ የሚወጣው?” የሚል ጥያቄ ቢነሳ የእኔ ቢጤው... “ከእነኚህ ከራሳቸው ጋር እንኳን ሀያ አራት ሰዓት በሰላም ማሳለፍ እያቃታቸው ካሉ ጋር ሠላሳ ቀን ሙሉ ሳቃስት የምከርመው ምን በወጣኝ!” እያለ ነው ብሎ ሊመልስ ይችላል፡፡ አሀ...የመቀሸም መብታችንን አትነካኩብና!
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ!...አንድዬ!
አንድዬ፡- ማነው?
ምስኪን ሀበሻ፡- አ...አንድዬ፣ ምስኪኑ ሀበሻ ነኛ!
አንድዬ፡- ያው የቀድሞው ምስኪኑ ሀበሻ ነህ?
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ! ግራ አጋባኸኝ እኮ...ያው የቀድሞው ምስኪኑ ሀበሻ ነኝ እንጂ ሌላ ማን ልሆን እችላለሁ?
አንድዬ፡- ማስረጃ ካልሰጠኸኝ እንዴት ልመንህ!
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ!!!
አንድዬ፡- ምስኪኑ ሀበሻ እኔስ ምን ላድርግ ብለህ ነው! እኔ እኮ የምለው... የመለዋወጥ ፍጥነታችሁ እኮ ግራ ግብት የሚል ነው፡፡ እዚህ ናችሁ ስላችሁ እዛ! እሺ እዛ ናቸው ስላችሁ ተመልሳችሁ እዚህ! እኔ ነኝ መላ ቅጡ የጠፋኝ እናንተ?
ምስኪን ሀበሻ፡- እኛ ነን እንጂ አንድዬ፣ እኛ ነን እንጂ! ግን አንድዬ፣ ዛሬ በጣም፣ በጣም ነው ቅር የተሰኘሁብህ፡፡
አንድዬ፡- ምን አደረግሁ ምስኪኑ ሀበሻ? ገና ከመገናኘታችን ምን አደረግሁ!
ምስኪን ሀበሻ፡- ይኸው ስንት ጊዜ ከርሜ ስመጣ እንዴት ሰነበትክ፣ እንዴት ከረመክ አላልከኝም፡፡ ደ..ደግሞ....
አንድዬ፡- ደግሞ ምን?
ምስኪን ሀበሻ፡- ደግሞ ማስረጃ ካላመጣህ አላምንህም አልከኝ፡፡
አንድዬ፡- እምምም....
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ ምነው ዝም አልከኝ? ካጠፋሁ ይቅርታ! አንድዬ አሁን፣ አሁን ብዙዎቻችን የምናወራውን ስለማናውቅ ነው እኔንም ያዘባረቀኝ፡፡
አንድዬ፡- ስማኝ ምስኪኑ ሀበሻ...እየሰማኸኝ ነው?
ምስኪን ሀበሻ፡- አዎ አንድዬ፣ እየሰማሁኝ ነው፡፡
አንድዬ፡- እንደበፊቱ ቢሆን ኖሮ እንዲህ አይነት ነገር ስትናገር ምን እል ነበር መሰለህ....
ምስኪን ሀበሻ፡- ምን ትል ነበር አንድዬ?
አንድዬ፡- ያው እንደተለመደው ምስኪኑ ሀበሻ ሆድ ብሶት ነው እል ነበር፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡- አዎ አንድዬ፣ ሆድ ብሶኝ ነው፡፡ ዘንድሮ እንዴት ሆድ እንደባሰኝ፣ እንዴት ሆድ እንደባሰን አልነግርህም፡፡
አንድዬ፡- አትቸኩላ ምስኪኑ ሀበሻ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡- እሺ አንድዬ፣ እሺ፡፡ ለመደብኝ፣ ለመደብን መሰለኝ፡፡
አንድዬ፡- ጎሽ! ጎሽ! ጎሽ! ምስኪኑ ሀበሻ አሁን አስደሰትከኝ፡፡ ለመደብን አይደል ያልከው?
ምስኪን ሀበሻ፡- አ...አዎ...አዎ፣ አ...
አንድዬ፡- በል ምን ይገርምሀል ብለህ ጠይቀኝ፡፡ ጠይቀኛ!
ምስኪን ሀበሻ፡- ምን ይገርምህል አንድዬ?
አንድዬ፡- የሚገርመኝማ ምን መሰለህ፤ ‘የጅብ ችኩል ቀንድ ይነክሳል’ ብላችሁ የምትተርቱት እናንተው፡፡ ይኸው ቀንድ ነክሳችሁ መከራችሁን የምታዩት እናንተ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡- እሱስ ልክ ነው አንድዬ፡፡
አንድዬ፡- ‘የቸኮለች አፍሳ ለቀመች’ ብላችሁ የምትተርቱት እናንተው፡፡ ይኸው አፍስሳችሁ፣ አፍስሳችሁ መልቀሙ ያቃታችሁ እናንተው። ምስኪኑ ሀበሻ፣ የእኔ የሚባል አላቃሚ ማግኘትም እኮ ከባድ ነው፡፡ አይደለም እንዴ?
ምስኪን ሀበሻ፡- ል...ልክ ነው አንድዬ፡፡
አንድዬ፡- እና ለሁሉም ነገር የሚያጣድፋችሁ ምንድነው? ግርም የሚል ነው እኮ! ከዚህ ቀደም የቸኮሉት የት ደረሱ? ንገረኛ የት ደረሱ?
ምስኪን ሀበሻ፡- የትም አንድዬ፣ የትም፡፡
አንድዬ፡- እነሱ ባክነው፣ ሌላውን አባከነው ሀገርን አላባከኑም!  እነሱ ቸኩለው በሠሩት ስህተት  ይኸው እናንተ መከራችሁን እየበላችሁ አይደል! ወይንም... የእናንተኑ አነጋገር ለመጠቀም ዋጋ እየከፈላችሁ አይደል?
ምስኪን ሀበሻ፡- ምን ጥያቄ አለው አንድዬ፣ ምን ጥያቄ አለው!
አንድዬ፡- እና ይሄን ካወቃችሁ፣ አሁን እናንተ በጥልቅ ሳታስቡ በስሜት ብቻ በችኩልነት የምታደርጉት ለመጪው ትውልድ አደጋ ሊሆን ይችላል፣ ውሎ ድሮ ሀገር ሊጎዳ ይችላል ብላችሁ ማሰብ ምነው አቃታችሁ?
ምስኪን ሀበሻ፡- እሱ ነው እኮ ግራ የሚገባው አንድዬ! እኛም እኮ...
አንድዬ፡- ይቅርታ፣ ምስኪኑ ሀበሻ...ላቋርጥህ....
ምስኪን ሀበሻ፡- ኸረ ችግር የለውም አንድዬ፡፡
አንድዬ፡- ግን ምን ነካኝ ምስኪኑ ሀበሻ?
ምስኪን ሀበሻ፡- ምን...ምኑ... አንድዬ?
አንድዬ፡- ቅድም ጀምሬ ያለማቋረጥ ስለፈለፍ ዝም ብለህ ትሰማኛለህ! ይበቃሃል አትለኝም?
ምስኪን ሀበሻ፡- እንዴ አንድዬ! ለምን ብዬ ነው እንደዛ የምልህ? እንዲህ አይነት ነገር እኮ አንተ ካልነገርከን ሌላው ጣት ይቀሳሰርብናል እንጂ ማንም  አያማክረንም፡፡
አንድዬ፡- እና የለፍላፊ እጥረት ያለባችሁ ይመስል እኔ ልጨመርበት?
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ፣ እንደእሱ ማለት ሳይሆን...
አንድዬ፡- ቆይ አታቋርጠኛ! አየህ አሁን እኮ እናንተ ዘንድ የሚያወራ ሳይሆን የማያወራ ማግኘት ነው የሚያስቸግር፡፡ ከተናጋሪ ይልቅ አድማጭ  ማግኘት ነው የሚያስቸግር፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡- አን...
አንድዬ፡- ምስኪኑ ሀበሻ... ምነው! ምነው! አታቋርጠኝ ብዬህ፡፡ ዛሬ ብቻ ለፍልፌ ይውጣልኝ፡፡ ምን ይደረግ ያው ከምን የዋለች ጊደር ትሉ የለ...አንተ ስቀልድ ነው፣ ደግሞ አኩርፍ አሉ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡- ኸረ እኔ አላኮርፍም አንድዬ።
አንድዬ፡- ምስኪኑ ሀበሻ ከመሰነባበታችን በፊት አንድ ጥያቄ ልጠይቅህ...
ምስኪን ሀበሻ፡- ጠይቀኝ አንድዬ፣ ጠይቀኝ፡፡
አንድዬ፡- እንደው እናንተ ሀገር ሁሉም የፖለቲካ ሊቅ፣ ሁሉም የህክምና ሊቅ፣ ሁሉም የኤኮኖሚ ሊቅ፣ ሁሉም የዓለም አቀፍ ጉዳይ ሊቅ...ብቻ ሁሉም ሰው በሁሉ በኩል ሊቅ የሆነው እንዴት ነው? ይህን ያህል የሊቃውንት ሀገር ሆናለች እንዴ! እኔ እኮ ሊቆቹን ሁሉ በአንድ ቦታ ብቻ የሰበሰብኩ አይመስለኝም ነበር!
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ...
አንድዬ፡- ስማኝ ምስኪኑ ሀበሻ፣ በሚቀጥለው ጊዜ እኔ ዘንድ ስትመጣ በሁሉም ነገር ሊቅ ነኝ ከሚለው መሀል ስለ ሀገሩ ሀያ አምስት በመቶ የሚሆን እውቀት ያለው  ስንቱ እንደሆነ በግምትም ቢሆን አጣርተህ ናልኝ፡፡ ሰላም ግባ!
ምስኪን ሀበሻ፡- አሜን አንድዬ፣ አሜን!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 641 times