Print this page
Tuesday, 07 June 2022 06:43

መንግስት ሆይ፤ የህትመት ውጤቶችን ታደግልን!

Written by  ነፃነት አምሳሉ አፈወርቅ
Rate this item
(0 votes)

ይህን ጽሑፍ ስጽፍ በውስጤ እየተሰማኝ ያለውን ሀዘን ለመግለጽ ያዳግተኛል፡፡ በአንድ በኩልም ስጋት ይንጠኛል፡፡ ሁነኛ ምላሽ ባላገኝም የውስጤን ጥያቄ እያብላላሁ እንደ ቡና ቆሎ ከምቆረጥመው ወደ አደባባይ ባወጣው መልስ ሰጪው አካል ለእኔ እንኳን ብሎ ባይሆን፣ መሆን ያለበትን ተረድቶ ማስተካከያ ቢያደርግ ብዬ፣ አንድም ራሴን ከተወቃሽነት ለማዳን ስል ብእሬን ለማንሳት ተገድጄአለሁ፡፡
ዜናው ከተነገረ ሰንበትበት ብሏል፡፡ የወረቀት ህትመት ላይ ተጨማሪ 70% ክፍያ ስለመወሰኑ የሚያወሳ ነው፡፡ አስደንጋጭ ዜና ነው፡፡ የሚያስደነግጠው መጨመሩ ብቻ ሳይሆን የጨመረበት ልኬት አፍ የሚያሲዝ መሆኑ ነው። “እንኳን እናቴ ሞታ ድሮም አልቅስ አልቅስ; ይለኛል እንደተባለው፣ እንኳን 70% ጭማሪ ተደርጎ ይቅርና በወትሮ ታሪፍም የወረቀት ህትመት እያደር እያሽቆለቆለ መሄዱ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ከወረቀት ህትመት ጋር ንክኪ ያለው ስራ ላይ መሰማራት ወይ ቅብጠት አሊያም እብደት ሆኖ ቢቆጠር ማን ይፈርዳል!
መጻሕፍት ጋዜጦችና መጽሔቶችን የሚያሳትሙ ሰዎች አንደኛውን ሙያቸውን የሙጥኝ ብለው በመያዛቸው እንጂ የሚያጓጓ ጉዳይ ኖሮበት አይደለም፡፡ ከዚህም አለፍ ካለ እስከአሁን ያስለመዱትን ጥቂት አንባቢ ዓይን ላለማስቀየም በምንተህፍረት በእንግድግድ እየተራመዱ ስለመቆየታቸው ማበል አይቻልም። ዘርፉ ትርፋማነት የሌለው ከመሆኑ ባሻገር በኪሳራ እንስራ እንኳ ተብሎ ቢሰራ የወረቀት፣ የቀለምና የማሳተሚያ ዋጋ አድሮ ሰማይ እየነካ ስንቱን ከጨዋታ አውጥቶ በሌላ ሙያ ላይ እንዲሰማራ ግድ ብሎታል፡፡
ከኢህአዴግ የበረሃ መንገደኝነት ወደ መንግስትነት መቀየር ጀምሮ ባሉት ማግስቶች ሜዳ ላይ ፈስሰው ይነበቡ የነበሩ አማራጭ የህትመት ውጤቶች፣ የራሳቸው ደካማ ጎን እንዳለው ሆኖ ጥቅማቸው ግን እንደ ተራ የሚቆጠር አልነበረም፡፡ ቢያንስ ቢያንስ በትንሹም ቢሆን የሚያነብ ማህበረሰብ አይተን ነበር ማለት እንችላለን፡፡ ይህ መነቃቃት አንድም ለኢህአዴግ ዲሞክራሲያዊነት ትልቅ ማሳያ ሆኖ አንድም ህዝቡ የዲሞክራሲን አንድ ሱታፌ አገኘሁ ብሎ እንዲጽናና ሲረዳው፣ በሌላ መልኩ ደግሞ የህትመት ዘርፍ እንደ አሸን ፈልቶ ከወርሃዊ ወደ ሳምንታዊ፣ ከሳምንታዊ ወደ እለታዊ አቅርቦት ሲገባ ተፈላጊ ተነባቢ ተደማጭና ጥሩ አወያይ ሆኖ ለብዙ ባለሙያዎች መፍለቅ የራሱን በጎ አስተዋጽኦ አድርጎ ነበር፡፡ (ነበር ነው ያልኩት!)
ኢህአዴግ ራሱ ተናግሮ ራሱን የሚያደንቅና ለራሱ የሚያጨበጭብ ስለነበር ሃቀኛ ጋዜጠኞችን ማሰር፣ ጸሐፊያንን ማዋከብ፣ ህትመቶችን ማገድ፣ ማተሚያ ቤቶችን ማስፈራራትና ዘርፉ ላይ ከፍተኛ ታሪፍ መጣል የልምጮቹ አይነቶች ነበሩ፡፡ ወዥበር ሲልበትም ቅዳሴ እንደሚሄድ ሰው ማለዳ ተነስቶ ለገበያ የቀረቡ ህትመቶችን ሰብስቦ ወደ ማቃጠያ ሲወስድ አይተን "ልብ ይስጥህ" ስንለው ጭራሽ ህሊና ነስቶት ሞቱን ለማፋጠን ቢላ ወደ መሳል ተሸጋገረ፡፡ እውቀት ማለት አብዮታዊ ዲሞክራሲን መረዳት፣ ልማታዊነትን መተንተን ሆኖ በመተርጎሙ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ከፈተና ግሬድ ሳይሆን ከአባልነት የሚያገኙትን ጥቅም እያሰቡ ጸረ ንባብና ጸረ ሚዲያ ሆነው የስልጣን ወንበሮችን ተቆጣጠሩ፡፡
ንባብ ደህና ሁኚ ያለው ማህበረሰብም አለማንበቡን እንደ ቡራኬ ተቀብሎ እንደ ልቅሶ ቤት ምስር ለቃሚ አንገቱን አቀርቅሮ ከሞባይሉ ጋር ወደ መጋባት ተሸጋገረ፡፡ ሞባይል ነፍሴ ስንቱን ሰው ከቤተሰቡና ከማህበረሰቡ ነጥላ የኪስ ውስጥ አምላክ ሆነችበት፡፡ ንባብና ትውልድ ተኳርፈው በድብታ ውስጥ ሲጓዙ ሀገር በቁም ትቆዝማለች፡፡ ንባብ ያላነቃውን ማህበረሰብ በእድር ጡሩንባ ማንቃት አይቻልም፡፡
መጻሕፍትን ያየን እንደሆነ ትውልዱ ከንባብ ጋር የ80 ፍቺ በመፈጸሙ ፀሐፊያን ብእራቸውን መሳቢያ ውስጥ ቆልፈውበታል፡፡ የታሪክ ሃቲት ላይ ያለን ልዩነት የአዲስ አበባውን ዩኒቨርስቲ የታሪክ ዲፓርትመንት ወደ ማዘጋት በመሸጋገሩ “ውሾን ያነሳ ውሾ ነው” ተባብለን በታሪክ ላንግባባ፣ በመጠጥ ብቻ ልንግባባ ተስማምተን ቺርስ ለማለት ብርጭቋችንን አንስተናል፡፡ ልብወለድ፣ ፍልስፍና፣ ግለታሪክ፣ ባህል ነክ ጽሑፎችማ ማን ዞር ብሎ ሊያያቸው? የህትመቶቹ ድርቀት እንደ ጤናማ አካሄድ ቅቡል ሆኖ በመታሰቡ የሞት ሞታቸውን ተጣጥረው አንድ መጽሐፍ የሚያሳትሙ ሰዎች ገዢ አጥተው በስንተኛው ወር ከዋጋው በወረደ ተመን የፒያሳ ጎዳናዎች ላይ ሲሸጡ አይተናል፡፡ የመጽሔቶቹም እድል ፈንታ ከዚህ ፈቀቅ አይልም፡፡ አዳዲስ መጽሔቶች ገበያ ላይ ቀርበው (ይዘትና ጭብጥ ላይ ችግር ሊኖርበት እንደሚችል ታሳቢ ተደርጎ) ገና መንፈቅ ሳይሞላው ከተጫዋችነት ወደ ተመልካችነት ይሸጋገራሉ፡፡
ይህን የታዘበ ሰው ጥያቄ ይጠይቃል፡፡ ለመሆኑ ዛሬ ዛሬ በመዲናችንና በክልል ከተሞች እየተገነቡ ያሉ ግዙፍ ቤተመጻሕፍት የትና መቼ የታተመ የሀገር ውስጥ መጻሕፍት አግኝተው መደርደርያዎቻቸውን ይሞላሉ? ውብ ዘመናዊና ደልቀቅ ያሉት ቤተመጻሕፍት በመጽሐፍ ጠኔ ተይዘው ከዜጎች በሚደረግ እርጥባን እስከ የት ይደርሳሉ? እስከ መቼ ድረስ በልመና እንደሚዘልቅ ባይታወቅም ይህ አካሄዳችን የማስታገሻ መርፌ መወጋት እንጂ ሁነኛ ፍቱን መድሃኒት አለመሆኑን ልቦናችን ያውቀዋል፡፡
"እንኳን ዘንቦብሽ እንዲያውም ጤዛ ነሽ" እንዲል የሀገሬ ሰው፣ እንኳን መጽሐፍ መጽሔትና ጋዜጣ ጠፍቶ ይቅርና ለወትሮውም ቢሆን አወቀ ነቃ በቃ ያልነው ትውልድ ጭምር ጸረ ንባብ ሆኖ በፌስቡክ ቅንጫቢ እውቀት ላይ የሙግት አጀንዳ ፈጥሮ ሀገር ለመበጥበጥ ሲጨቃጨቅ ማየታችን መጻኢው ጊዜያችንን በአጉሊ መነጽር እንድንመለከት ያስገድደናል፡፡
ጋዜጦችና መጽሔቶችን ከተመለከትን ደግሞ ሟርት ይመስል ይሆናል እንጂ ወደ ታሪክነት ሊቀየሩ ደርሰዋል፡፡ ተአምር እኮ ነው! ከመቶ ሚሊየን በላይ ህዝብ ባለበት ሀገር ያሉትን ጋዜጦች ለመቁጠር መሞከር ድፍረት ነው፡፡ የሌለ እንዴት ይቆጠራል ጃል? ለመቁጠርም እኮ ተቆጣሪ ያስፈልጋል አይደል እንዴ?
አሉ የምንላቸውም ጋዜጦችና መጽሔቶች የሞት ሞታቸውን ሲታገሉ ውሎ አድሮ በሚጨምረው የጥሬ እቃና የማምረቻ ዋጋ ሁለት እርምጃ ወደፊት አንድ እርምጃ ወደ ኋላ እየተጓዙ ይገኛሉ፡፡ ዳሩ አለመታደላችን ሆኖ እንጂ በአሁኑ ጊዜ ቢያንስ በመዲናችን በተለያዩ የሀገር ውስጥ ቋንቋዎች በርካታ የጋዜጣና መጽሔት ህትመቶችን ባገኘን ነበር፡፡ ዳሩ የብሄር ተቆርቋሪነታችንና ወገንተኝነታችን ለልዩነትና ለጭቅጭቅ እንጂ ለእውቀት ማስፋፍያነት ባለመጠቀማችን ጉዳዩን ከመጤፍ ቆጥሮ የመወያያ አጀንዳ ያደረገው አካል የለም፡፡
የሰለጠነው ዓለም ብለን የምናሞካሻቸው ሀገራትም ሆነ ማህበረሰብ የንቃተ ሕሊናቸውና የዳበረ ስርዓታቸው አንደኛው መመዘኛ ከንባብ ጋር ያላቸው ቤተሰባዊነትና መንግስትም ለዘርፉ አንጀት አርስ ድጋፍ ማድረጉ ነው፡፡ የዲሞክራሲ መገንቢያ ስርዓቱ ከእውቀት ካልመጣ በስተቀር በምኞት ብቻ የሚሳካ አይደለም፡፡ የእውቀት ምንጩ ደግሞ ንባብ ነው፡፡ ጭንቅላቱ በንባብ ድርቀት የተመታን ሰው በቅቤ ማለስለስ አይቻልም፡፡ ልቡ በግንዛቤ እጦት የተጣመመን ሰው በምርኩዝ ድጋፍ ማቃናት አይቻልም፡፡ መንፈሱ በአርቆአሳቢነት ያልተገራን ትውልድ በፍል ውሃ እጥበት ማንጻት አይቻልም፡፡ አንጀቱ በፍልስፍና ጠኔ የተራበን ማህበረሰብ በሙክት ሥጋና በቆየ ወይን ማጥገብ አይቻልም፡፡
ወጣ ብለን አካባቢያችንን ብናየው ተአምራዊ የከተማ ለውጥ እያየን ነው፡፡ የዛሬ ሶስት ወር ጭር ያለው ስፍራ ተመልሰን ስናየው ግዙፍ ህንጻዎች በቅለውበት እናገኛለን፡፡ ሰፋፊ መንገዶች ተሰርተዋል፡፡ የሚያሳሱ መዝናኛ ስፍራዎች ተንጣለዋል፡፡ በጥቂት ሀገሮች የሚገኘው 5G የኢንተርኔት ቴክኖሎጂ ራሱን ሞሽሮ አስመርቋል፡፡ ስንጀምራችው የደሃ ቅንጡ ናችሁ ተብለን ያስወረፈን የሃይል ማመንጫ ግድቦች ወደ ሃይል ማመንጨት ተሸጋግሯል። ታዲያ ይህ ሁሉ ለማን ተሰራ ካልን መልሱ ለሰው የሚል ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
ታዲያ ይህ ሁሉ የተሰራለት የሰው ልጅ ቁሳዊ ልማትና እርካታ ሰጥተነው አእምሮው ላይ ካልሰራንለት ምን ዋጋ አለው? አእምሮው የተዛባ ሰው እኮ ጥፋትን ሙያ ያደርጋል፡፡ በውብ ጎዳና ላይ እየሄደ ብረት ነቅሎ ይወስዳል፤ መዝናኛ ስፍራ ገብቶ አበቦችን ይነቅላል፡፡ ኮንደሚኒየም ውስጥ እየኖረ ፍሳሽ ወደ መንገድ ይለቃል፡፡ 5G ኢንተርኔት እየተጠቀመ ብሔርን ከብሔር፣ ሃይማኖትን ከሃይማኖት ያጋጫል። የኃይል ማመንጫ ገመዶችን በጥሶ ጌጣጌጥ ይሰራበታል፤ እናም የሰው ልጅን አእምሮ ልክ እንደ ግንባታው ሁሉ በእውቀትና በመረጃ መገንባት ይጠበቅብናል ማለት ነው፡፡
የትናንት የህትመት ዋጋን ስንኮንን ከርመን የተሻለ ቅናሽ የሚደረግበት ቀን ይመጣል ብለን ባንጠብቅም እንኳ ቢያንስ ቢያንስ ባለበት ይቀጥላል ብለን ተስፋ ስናደርግ አሁን የተከሰተው ጭማሪ ግን ትልቅ ህመም የሚፈጥር ነው፡፡ የአሁኑ የ70% ጭማሪ ዋጋ እኮ ለውይይትም ለድርድርም የሚመች አይመስልም፡፡ እንደ ብርቅዬ የዱር እንስሳ በቁጥር እያነሱ የመጡትን የህትመት ውጤቶች ነገ ነበሩ ብለን ለማውራትና መልካቸውን ለማየት ወደ ወመዝክር እንዳንሄድ ትልቅ ስጋት አለኝ፡፡
አንድ የህትመት ውጤት እጃችን ላይ ሲገባ ቀለል ያሉ ወረቀቶችን አንድ ጋር ጠርዞ ቢሆንም ዋጋውን ስናሰላው ግን ጀርባ የሚያጎብጥ ወጪ መደረጉን ለማወቅ የድርጅቶቹን የአመት ሂሳብ መዝገብ መመልከት አይጠበቅብንም፡፡ ለአንድ መጽሐፍ ጋዜጣና መጽሔት ህትመት ሲባል ደመወዝ የሚከፈላቸው ባለሙያዎች፣ የገቢ ግብር፣ የህንፃ ኪራይ፣ የመስርያ ቁሳቁስ፣ ውድ የማሳተሚያ ዋጋ ተደማምሮ እኛ እጅ ሲገባ የሚሸጥበት ተመን ከወጪው ጋር ሲነጻጸር ጎልያድን ከዳዊት ጋር በአንድ ሚዛን የመመዘን ያህል ነው ልዩነቱ፡፡ ህትመቶቹ ገበያ ላይ ውለውም እንኳ በታተሙበት ቁጥር ልክ ቢሸጡ እሰየው ነበር፡፡ ነገሩ የተገላቢጦሽ ነው፡፡ ለገበያ ቀርቦ ሳይሸጥ ቀርቶ ወደ አሳታሚው የሚመለሱ ሺ ቅጂዎች አሉ፡፡
የህትመት ውጤት ዋጋ መናር ከውስጥ አቅማችን ማነስ ብቻ ሳይሆን ከዓለም ገበያ መቀያየርም ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በዚያ ላይ የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ዳፋው በስንዴ እጦት ብቻ እንዲህ በቀላሉ የሚተወን አይደለም። ገና ያልተላቀቅነው የኮሮና ወረርሽኝ ዳፈው የዋዛ አይደለም፡፡ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደሚባለው፣ የሀገር ውስጥ ጦርነትም የራሱን አስተዋጽኦ ማድረጉ ሃላል ነው፡፡
ለሁሉም ነገር መንግስትን ተጠያቂ ማድረጉ ፍርደገምድልነት ቢሆንም መንግስት መጠየቅ ባለበት አንኳር ጉዳይ ግን መጠየቃችን ሀገር ወዳድነታችንን ያሳያል፡፡ መንግስትን መደገፍ በሚገባን ልክ እንደምንደግፈው ሁሉ ክፍተት ስናይ ክፍተቱን በቀናነት ማሳየት ደግሞ የዜግነትም የሰውነትም ግዴታችን ነው፡፡ ለዚህ ነው ምንጩ እየደረቀ ያለውን የህትመት ውጤት ለመታደግ ወደ መንግስት ለመጮህ የተገደድነው፡፡
አዎ መንግስት እየተበደለም ቢሆን ለሀገር ጥቅም የሚያስገኝ ነው ብሎ ካመነበት ጉዳቱን ታግሶ ሸክሙን ይሸከማል፤ ጉዳዩ ለብዙ ወጪ የሚዳርግም ቢሆን የጠቃሚነቱን ድርሻ አስልቶ ከበጣም መጥፎው መጥፎውን በመምረጥ ለዜጎቹ አእምሮ ሲል የሚከፈለውን ሁሉ ከፍሎ የህትመት ውጤቶችን ማገዝ ይገባዋል፡፡ ነገሩ እኛ ለማኞች መንግስት ተለማኝ የመሆን ጉዳይ አይደለም፡፡ ሀገርን የማስቀጠል፤ ትውልድን የመታደግ ጉዳይ ነው፡፡
የህትመት ውጤቶች ላይ የተጨመረው ዋጋ ውድ መሆኑ ብቻ ሳይሆን አንድም ባለሙያዎችን ከዘርፉ ያስወጣል፤ አንድም ትውልዱን ወደ እወቀተ ቢስነትና እንስሳዊ ባሕርይ ይወስደዋል፤ አንድም በመረጃ ክፍተት በሚፈጠር ዝንፈት በማህበረሰቡ ውስጥ በቀላሉ ሊስተካከሉ የሚችሉ ችግሮችን በወቅቱ ለማረም እንዳይቻል የእንቅፋት ድንጋይ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ዙርያ ጥምጥም መሄድ አያስፈልግም፡፡ መንግስት ዘርፉ በቁሙ እየሞተ መሆኑን ተረድቶ ድጋፍ ያድርግ። ውጫዊውን የዋጋ ጫና ማስቀረት ባይችልም ቅሉ ዘርፉ ላይ ለሚገኙ አካላት የሀገር ውስጥ ድጎማ ያድርግ። የሚከፍሉትን ታክስ ይቀንስ፡፡ የንባብ ባህልን ለማዳበር የሚያስችሉ መድረኮችን ይፍጠር፡፡ የህትመት ዋጋ ላይ ተመጣጣኝ ቅናሽ ያድርግ።
ትውልዱ ግብረገብነት የለውም፣ እንደ አማኝ ህዝብ እየኖርን አይደለም፣ እንደ ባህላችንና ስርዓታችን ልከኛ አልሆንም፣ ሀገር ወዳድነታችን እየቀዘቀዘ ነው፣ ማህበራዊ ትስስራችን ላልቷል፣ ወገናዊ ስሜታችን በግለኝነት ተቀይሯል፣ አጉል ባህል ተጣብቶናል የሚሉትን ትችቶች ማረቅና ማረም የምንችለው የህትመት ውጤቶችን በማቅረብ፣ ዘርፉን በመደገፍ፣ ባለሙያዎቹን በማበረታታት፣ አንባቢያንን በማብዛት ጭምር መሆኑ ታውቆ የስብሰባ አጀንዳችን ገጽ አንድ ላይ መጻፍ ያለበት አንገብጋቢ ርእስ መሆን አለበት እላለሁ፡፡
ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል ብለን በድፍረት የምንናገረው ንባብ ጠማማን ያቃናል፤ ጥላቻን ያከስማል፤ ንቃተ ህሊናን ያዳብራል፤ ትውልድን ይሞርዳል፤ የውይይት ልቦችን ያበዛል፤ መማማርን ያጠነክራል፤ ተስፋን ያጭራል፤ መከራን ያሻግራል፤ አዲስ እሳቤን ያጎለብታል፤ የጎለበተውን ያሳድጋል፤ እኔ ከማለት ይልቅ እኛ ወደሚል ከፍታ ያወጣል፤ የመንግስትን ሀሳብ ለህዝብ ያደርሳል፤ የህዝብን አስተያየት ወደ መንግስት ያሻግራል፡፡ በዚሁ ሁሉ ትስስር ውስጥ አትራፊ የምትሆነው ሀገራችን ናት ብዬ አምናለሁ፡፡ ሻሎም!



Read 2437 times