Print this page
Wednesday, 08 June 2022 00:00

ገድለ አጎት ሆ ቺ ሚን

Written by  ስብሐት ገ/እግዚአብሔር
Rate this item
(0 votes)

አሉ አንዳንድ ሰዎች። በቅድሚያ ጀግኖች፣ የሀገራቸው ነጻነት አርበኞች ሆነው ወሳኝ ሚና የሚጫወቱና ጊዜ ሲያልፍ ደሞ ህዝባቸው የሚኮራባቸው አበው ሆነው የሚያልፉ። የአንዳንድ ልዩ ሀገር መብራቶች ናቸው። ካገራቸውም አልፈው ለዓለም ህዝቦች ያበራሉ። (የምንጠቅሳቸው ዓመተ ምህረቶች በፈረንጅ አቆጣጠር ናቸው)
በስመ ፍትህ ወነጻነት ወአብዮት ስለ ጀግናው የቪየትናም ልጅ ስለ ሆ ቺ ሚን እናወርሳለን፡፡ “ቪጥና ለቪየትናማውያን ሳይሆን አይቀርም የሆ ቺ ሚን የኑሮና የትግል መመሪያ። መጀመሪያ ጃፓንን፣ ቀጥሎ ፈረንሳይን፣ ቀጥሎ ደሞ አሜሪካን፣ ተለማምጦ ሳይሆን ተራ በተራ ተዋግቶ ከምድረ ቪየትናም አባረራቸው።
በየተራ ሲያሰናብታቸውም “ቻው ቻው!” አላቸው። በጠራ የቪትናምኛ “ከእንግዲህ በንግድ ልውውጥ ለጋራ ጥቅም ወይም በባህር ልውውጥ ለጋራ ደስታ ብትመለሱ የቪየትናም ሕዝብ በክብር ይቀበላችሏል። እንገዛለን እናስተዳድራለን ብላችሁ እንደማትመለሱ ግን መጪዎች ትውልዶች  ይገነዘቡታል ብዬ አምናለሁ።”
እኔ ነኝ እንጂ እንክል ሆ እንኳ ንግግር አያበዙም፣ ድርጊታቸው ነው ይበልጥ የሚናገረው። በዚያን ወቅት በእንግሊዘኛው ተናጋሪ ዓለም አንክል (አጎት) የሚባሉ አራት ብቻ ናቸው። እነሱም አንክል ጆ የሩሲያው ጆዜፍ ስታሊን፣ አንክል ሆ የቪየተናሙ፣ የቻይናው አንከል ማኦ እና አንክል ሳም ናቸው። አንክል ሳም ግን ሰው አይደለም፤ የዩናይትድ ስቴትስ ኦቭ አሜሪካ መንግስት ነው። አንክል ሳም ቢፈልግ እንኳን የአሜሪካ ለምን የሰማይ መንግስት አይሆንም? የራሱ ጉዳይ! አንክል ሆ ስሜት አይሰጣቸውም። “ቪየትናምን ለቀህ እስከወጣህ ድረስ በፈለግከው ዓለም ንገስ” ሳይሉት አልቀሩም በልባቸው። አቤት አንክል ሳም ደሞ ሲያከብራቸው።
ሀ. ሆ ቺ ሚን ዕድሜ ከ1890-1969 (ማለት ሰባ ዘጠኝ ዓመት)
ለ. የአንክል ሆ የፕሬዚዳንትነት ዘመን  ከ1945-1969 ማለት  ሃያ አራት ዓመት
ሐ. አንክል ሆ የተዋጉበት ዘመን- ሃያ ሰባት ዓመት!
መ. አንክል ሆ ፈረንሳይን በተዋጉበት በስምንቱ ዓመት ውስጥ ሁለት ጊዜ ሕጋዊ የሆነ የሞት ሰርቲፊኬት ተፈርሞላቸዋል። ወይም “ሆ ቺ ሚን የተባለ ግለሰብ በዚህ ቀን በዚህ ስፍራ መሞቱን አረጋግጣለሁ” ይላሉ ሕጋዊው ፈረንሳዊ ሀኪም። “እፎይ ግልግል!  ሸይጣን ሞተልን” ይላሉ የፈረንሳይ መንግስት።
አንክል ሆ ታዲያ ለተወሰነ ጊዜ ተሰውረው ይሰነባብቱና፣ ጊዜው ልክ አሁን ነው ብለው በሚገምቱበት ሰዓት፣ ተታኩሰውም ተጋድለውም ጉድ ካፈሉ በኋላ “ኢሮ! አልሞትኩም! ውሸቴን ነው!” ይላል። እኛ ነን እንጂ አንክል ሆ እንኳ ፉከራ አላስፈለጋቸውም።
ሠ. ሳይሞቱ መሞት ብቻም አይደለም አንክል ሆ የሚችሉት። አንድ ቦታ እያሉ የሌሉ መምሰሉንም ያውቁበታል። ብዙ ጊዜ ለሞት የሚጋለጡት ታጋይ ጓዶች´ኮ አንዳንዴ የመዝናናት ስሜት ይመጣባቸዋል። በእንዲህ አይነቱ ሰዓት አንክል ሆ ተሰብስበው ቆመው በሚያወሩት ጓዶች አጠገብ ያልፋሉ። ከጓዶቹ የሚያዩዋቸው አይጠፉም፤ አያውቋቸውም እንጂ!
አንክል ሆ ደሞ መልክም ልብስም አልለወጡም። ገፋ ቢል ቦላሌያቸውን ወደ ላይ አጠፍ፣ ትከሻቸውን ጎበጥ አድርገው ይሆናል። በቂ ነው። እልፍ ካሉ በኋላ መለሰ ሲሉ ታዲያ ጓዶቹ ዓይናቸው ይከፈትና ይገረማሉ፣ ይስቃሉ። አይ አንክል ሆ!
ረ. ለመሆኑ እኔና አንክል ሆ ቋንቋችን አይመሳሰል፣ ሀይማኖታችን አይተዋወቅ፣ ባገሮቻችን መሀል የስንትና ስንት ሺ ኪሎ ሜትር  ርቀት ያራርቀናል፣  እሳቸው ለነጻነት መዋጋት ጽድቃቸው፣ እኔ ውጊያ የሚሉትን አላውቀውም በወሬ ነው እንጂ። እንዲያው እንዴት ተገናኝተን ነው እኔ ስለሳቸው ስጽፍላቸው ኩራት ጭምር የሚሰማኝ? ከላይ እንዳልኩት አንዳንድ ልዩ ጀግና ላገሩ ልጆች ከመሆኑም አልፎ ተርፎ ለባዕዳኖች ጭምር ጀግናው ይሆናል። የሰው ልጅ መሆን በቂ ነው ለእንዲህ ዓይቶቹ…
..ሆ ቺ ሚን ወጣት እያለ ቪየትናም የፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ነበረች። ወጣቱ የፈረንሳይ መርከብ ውስጥ ሥራ ያዘ። ያ ሲበቃው ለንደን ከተማ ሲደርስ ከመርከቡ ተሰናብቶ አንድ ሆቴል ውስጥ ተቀጠረ።
አንደኛው የዓለም ጦርነት ሊያልቅ ሲል ሆ ቺ ሚን ወደ ፈረንሳይ ተሻገረና የሶሻሊስት ፓርቲ አባል ሆነ። ቀጥሎ የፈረንሳይ ኮሚኒስት ፓርቲ መስራች አባል ሆነ። ጊዜው ሲደርስ ሆ ቺ ሚን አብዮታዊ ዘዴዎችን ለማጥናት ወደ ሶቭየት ህብረት ገሰገሰ። እዚያ ደርሶ ከመቼው የኮሚኒስት ኢንተርናሽናል (ኮሚንተርን Comintern) አባል እንደሆነ እንጃ፣ ወደ አሥራ ዘጠኝ መቶ ሃያዎቹ ማለቂያ አካባቢ ላይ ወደ ምሥራቅ እስያ ተመደበ።
በ1930 ሆ ቺ ሚን ኢንዶቻይኒዝ ኮሙኒስት ፓርቲን መሰረተ።
በ1930ዎቹ ሆ ቺ ሚን ሲመቸው በሶቭየት ህብረት፣ ሲመቸው በቻይና እንዳሰኘው ይኖር ነበር። ከሁሉ አክርሮ የሚያሰኘው ደሞ አገሩን ከማንም ቅኝ ገዢ ነጻ ማውጣት ሆነ። ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሲነሳ ጊዜ፣ ሆ ቺ ሚን በጠራ ሩስኪኛ፣ በጠራ ቻይንኛ እንዲሁም በቪየትናምኛ “ጠራችኝ አገሬ!” አለና ወደ ቪየትናም ተመለሰ።
በ1941 ሆ ቺ ሚን “ቪት ሚን” የተባለውን  የሀገር ወዳድ ተዋጊዎች ማህበር መሰረተ። የጃፓንን ወራሪ የጦር ኃይሎች ለአራት ዓመት ከተዋጉዋቸው በኋላ አስወጧቸውና ሲያበቁ፣ በሴፕቴምበር 2 ቀን 1945 እ.ኤ.አ ሆ ቺ ሚን ነጻይቱን የቪየትናም ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መመስረት አወጀ። ከእንግዲህማ አንክል ሆ ሰሜን ቪየትናምን ነፃ አውጡ እንጂ ከተማዋ ሳይጎን የሆነችው የደቡብ ቪየትናም ገዢዎች ግን አንክል ሳምን የሙጥኝ ብለው በሰላም ለመኖር እየሞከሩ ነበር፡፡ ዳሩ ምን ዋጋ አለው? በደቡብ ቪየትናም ውስጥ ቪየት ኮንግ የተባሉ የነጻነት አርበኞች ተነሱ። ዕድሜ ለአንክል ሆ፣ ሰሜን ቪየትናም አስራ አምስት አመት ሙሉ ከቪየት ኮንግ  ጎን ተሰልፋ አንክል ሳምን “ያንኪ ጎ ሆም!” (ያንኪ አገርህ ግባ) ብለው አባረሩት?
ለሁለት ተከፍላ የነበረችው ቪየትናም በ1976 ዓመተ ምህረት ተመልሳ ተዋሃደች።
ይህን አጭር ገድል ለመቋጨት (እልባት ለመስጠት)) ወደ ፓሪስ እንጓዛለን። አንክል ሆ ይኖሩበት የነበረው ቤት ታሪካዊ ቦታ በመሆኑ፣ እና የቱሪስቶች መስህብ ስለሆነ፣ በእብነ በረድ “ሆቺ ሚን እዚህ ይኖር ነበር” ተብሎ ተጽፏል፤ በወርቅ ቀለም።
አንዲት ልዩ አይነት ወፍ አለች። የጎጆዋን ሳሮች የምትሸምናቸው በምራቅዋ እያጣበቀቻቸው ነው። ይህን ጎጆ የፈላ ውሃ ውስጥ ሲጨምሩት ወደር የሌለው ሾርባ ይወጣዋል። ይህን ሾርባ የሚያቀርብ ምግብ ቤት ፓሪስ ውስጥ አንድ ብቻ ነው። ይህን ልዩ ሾርባ ለመቋደስ ሃያ አራት ሰዓት አስቀድሞ ማዘዝ ያስፈልጋል።
አንክል ሆ ከሁሉ ይበልጥ የሚወዱት የምግብ ዓይነት ይህ ልዩ ሾርባ ነበር። (ፈረንሳይና ቻይና “ጣት የሚያስቆረጥሙ” የምግብ ዓይነቶች ሲፈጥሩ እንደ ጉድ ነው ይባልላቸዋል)።
ከአዘጋጁ፡- ከጋሽ ስብሃት ምርጥ ወጎች ለማስታወስ ያህል በሰኔ 2 ቀን 1993 ዓ.ም የአዲስ አድማስ ዕትም ላይ ለንባብ የበቃውን ፅሁፍ ነው እነሆ በረከት ያልናችሁ


Read 6923 times