Tuesday, 07 June 2022 06:59

ነሀሴ፤ ሌላኛው ጭንቀት ያልተለመደ ዶፍ ፍለጋና ኩርፊያ ነሐሴ 1-13 ቅዳሜ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 ዛሬም የፈራሁት ወይም ማታ ለራሴ ስጠይቅ የነበረውን ምላሽ ያገኘሁት ይመስል ሌሊት አልመጡም ብዬ አሁንም ለራሴ ምላሽ ሰጠሁ፡፡
ቁርስ ከበላን በኋላ በቤቱ ጀርባ ምጣድ ልለኩስ ዞሬ ስለነበር ጋሽ በላይ ሲሄድ አልነገረኝ ወይም አላየሁትም፡፡ ወደ ቤት ስገባ ድምፁ ጠፋብኝ፡፡ “ዳጉሮ በላይ፤ ሴት እህት በላይ” ይል ነበር፡፡ አሁን አላለም፡፡ ሀያትን “ጋሽ በላይሳ?” ብዬ ስጠይቃት “ሞባይሌን ቻርጅ” ላድርግ ብሎ ወጣ” አለችኝ፡፡ ተረጋጋሁ፡፡ ከዚያስ ሰዓት የለም፤ ብጠይቅ ማን ይመልስልኝ፡፡ ስወጣ ስገባ ሃያት ወደነ ሰአዳ ቤት ሄዳ ስትመለስ 6፡30 ነው አለችኝ፡፡ “ይህ ሰው ቀረ፣ ምን አደረጉት? ሰብስበው ገደሉት፣ መንገድ ላይ አረዱት፣አፈኑት…”  ስንቱን አሰብኩት፡፡ ከድርን ስልክ ቻርጅ የሚደረግበት ቦታ ሂድና ፈልግ፣ ገነትንና ሀያትን ስልክ ከሚደወልበት ቦታ  ሆስፒታሉ አካባቢ ሂዱና ፈልጉ ብዬ ላኳቸው፡፡ ጨነቀኝ፡፡ ጥሩ ነገር አልታይሽ አለኝ፡፡ ለፈንታዋ ከእነ አብዱቀድር ቤት ሄዶ ይሆን አልኩና ልሄድ ተዘጋጅቼ “ቤቱን እያየሽ” ብዬ ዞር ስል ጋሽ በላይ “ቢሮዬ ተገንጥሎ ተሰብሮ” እያለ ሲመጣ አየሁት፡፡ እርጎዬ “በላይ ደምሌ ምንም አይሆንም፤ይመጣል ብየሽ የለ!”
አለችኝ፤ በሚጣፍጠው በተለመደ  የአነጋገር ዘይቤዋ! ቢሆንም በጣም ተናደድኩ፡፡ ተከታትለው እነሃያት መጡ፡፡
 ሀያትና ገነት “ሆስፒታሉ እንደ ዲቃላ ወንዝ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ መስሏል፤አንዲት ሴት “ስኳር አለብኝ፣ ያለኝ መድሀኒት ለነገ ሰኞ ብቻ ናት፣በአገኝ ብዬ ነበር” ብላ እየፈለገች አገኘናት” እያሉ እያወሩ መጡ፡፡ ቦታ አልሰጠኋቸውም፡፡
“ምሳ?” እንብላ ሲሉ
“ከድር ይምጣ” አልኩ፡፡
እሱ ደግሞ ቀረ፡፡
ሀሳቤ ወደሱ ነጎደ፡፡ “ምን ይሻላል?” አልኩ፡፡
ምሳ ቀርቦ “ብይ” ሲሉኝ፤
“ከድር ይምጣ” ብዬ እንደውሻ ኩርትምት ብዬ ተጠቅልዬ ተኛሁ፡፡ ወዲያው ሀያት “ከድር መጣ” ስትል ሰማሁና ውስጤን ደስ አለው፡፡ እሱም “ባታ ነው፣ከድር ነው ቀኑ(ቅዳሜ ነው)፣ ቡና ይፈላ” አለ፡፡
እኔ ቡና አልጠጣም ብዬ ተኛሁ፡፡
ደህና አደርን፡፡
ነሀሴ 2-2013 እሁድ
 ከበላይ ጋር ከተማ ብዬ ሄድሁ፡፡ በየጠጅ  ቤቱ ሰው ሞልቷል፡፡ ይበላል፣ይጠጣል፡፡ ስንመለስ የባቄላ በቆልት በሰናፍጭ በ “ቴክአዊይ” ይዤ ወደ ቤት መጣን፡፡ ከሀያት ጋር በላን። ከድር ሲመጣም በላን፡፡ አዲስ ነገር የለም። የተለመደ ወሬ ስለሆነ ማውራት ነው። “እኛ ከቤት ሳንወጣ ይሄን ሁሉ ወሬ ሳያወራን ወደ ከተማ መጠጥ ቤት ያሉት ስንት ያወሩ ይሆን?” አልኩ፡፡
ሆስፒታሉ የከብት መዋያ ሆነ!
ነሀሴ 3-2013 ሰኞ
ገበያ ሄጄ ጤፍ ልገዛ ተነሳሁ፡፡ ጋሽ በላይ በመጀመሪያ እነ ሲቲና ጋር ስልክ ልደውል ሲል እኔም አዲስ አበባ የምትገኘው እህቴ ፈንትሽ ጋር መደወል አለብኝ ብዬ አብሬ በአየር ማረፊያው በሆስፒታሉ በስተደቡብ ባለው ቦታ ሄድን፡፡ አውነትም ሆስፒታል የከብት፣ የአህያ፣ የፍየል መዋያ ሆኗል፡፡ ከዚህ ፍራሽ የሌላቸው አልጋዎች፣ ከዚያ ዊልቸር፡፡ በየቦታው የመድሀኒት ወረቀቶች ተበታትነው፣ ሸልፎች፡፡ ምን የሌለ አለ፡፡ የተወሰደው ተወስዶ የቀረው ተበታትኖ ይታያል፡፡
እውነት ነው፣የኛ ህዝብ ነገ የምንገለገልበትን፣ የምንታከምበትን በአግባቡ ሊጠብቅ አልቻለም። ዘርፎ ለዘራፊ ሰጠው፡፡ መቼም የሚጠገን አይመስልም፡፡ ቢጠገን እንኳን ብዙ ዋጋ ያስከፍላል ይመስለኛል፡፡ በዚህ ባልመጣሁ አልኩ፡፡ ያላስተዋልኳቸው በዕድሜ የእኔ እኩያ የምትሆን ሴት ሁለት የብረት ቱቦ ይዛ ፍየል እየቀረበች መጣች። ተገረምኩ፡፡ ይህን አሳልፌ ኔትወርክ ካለበት ቆሜ  ዞር ስል ባጃጅ ይዘው በመሄድ የተረፈውን መድሐኒት ይሁን ሌላ ይጭኑ ነበር፡፡ ምነው በተጠጋው አልኩ፡፡ ከ150-200 ሜትር እርቅ ነበር፡፡ ኔትወርክ ስለሌለ ከዋጃ፣ከአላማጣ ለመደወል የመጡ ነበሩ፡፡ ከዚህ የጠፋው የወልዲያው ስለተቆረጠ ነው ይላሉ፡፡ ብቻ ተመለስን፡፡ ገበያም ሳልሄድ ቀረሁ፡፡ ጋሽ በላይ እንደሰመረለት አይደለም፤ ደሞ መጥቶበታል አልኩ፡፡
ሀያት፣ ከገነት ጋር  ገበያ ሄዳ ቶሎ ተመለሱ፡፡
“ምነው?” ስላት፣
“ታጋዮቹ አሉ፣ዳርዳሩን መሳሪያ ይዘዋል እና ችግር የተነሳ እንደሁ ብለን ቲማቲም፣ወይራ፣ቃሪያ እንደነገሩ ገዝተን ተመለስን” አለችኝ፡፡ እንኳንም በደህና ተመለሱ፡፡ በላይና አፊያ ስልክ ከተገኘ እንሞክር ብለው ወጥተዋል፡፡ ይቅናቸው!! አሁንም ኔትወርክ ሳያገኙ ተመለሱ፡፡ በነገራችን ወደ ቆቦ ከተመለስኩበት ቀን እስከዛሬ ድረስ “ዝሆንና አውራ ዶሮ” ፣ “መቅረዝ” ፣ “የመጨረሻዋ ቅጠል”፣ “ጥቁር ድንጋይ”፣ “ዣንቶዣራ” ፣ “መርበብት” ፣    “እምቢታ” የተሰኙ መፅሐፎች ያነበብኩኝ ሲሆን፣ አሁን ደግሞ “ፅጌረዳ የሚል እያነበብኩኝ ነው፡፡ የቤቱ ሰው በሙሉ ያነባል፡፡ ከቤት መዋል እንዴት ይጨንቃል፡፡ ለማንኛውም ወደ እነ እርጎዬ (ጎረቤት) ወጣ አልኩ፤ አዲስ የሰሙት ወሬ ካለ ብዬ፡፡ እንዳሰብኩትም ወልዲያ ሄደው የነበሩት ጎረቤቶቻችን ከወልዲያ በቃሊም ሮቢት ገብተው እንደመጡ ነገሩኝ፡፡ ወልዲያም ተይዟል አሉ ብለው ሲነግሩኝ፣ የሄደው ሁሉ “ተመለሱ ወደ ሀገራችሁ” ብለዋል ሲባል፣ እኔም አፋፍ እያለሁ “ቆቦ ሰላም ነው፣ ወደ ሀገርሽ ብትሄጂ ጥሩ ነው” ብለው የነገሩኝን አስታወስኩና ወደ ቤቴ ተመለስኩ፡፡
በላይ “ሌላ ኔትወርክ ካለበት” ብሎ ሄደ፡፡ ሳይሳካለት ቀረ። እንዳኮረፈ ነው፡፡
 በሠላም መሸ፡፡
ተኛን፣ አልሀምዱሊላህ፡፡
ነሀሴ 4- 5/2013 ማክሰኞ -ዕሮብ
ጠዋት እንጀራ ለቁርስ የሚሆን ዳቦ ጋግሬ ከጋሽ በላይና ከድር  ጋር ገበያ ሄድን፡፡ የደመቀ ገበያ ሆኗል፡፡
እንጨቱ፣ ክኩ፣ ጤፉ፣ ማንጎ፣ ሽንኩርቱ፣ ቲማቲሙ፣ ገብሱ፣ ….ሁሉም…ጫማው፣ ልብሱ፣ ወዲው ሳይቀርብ ሞልቷል፡፡ ጤፍ ነጩን 60 ብር፣ 55 ብር ይላሉ፡፡ እነ ሰርገኛ ጤፍ በ50 ብርና 52 ብር ገዛሁ፡፡ አተር ክክትልቁ 140፣ደቃቁ 100 ብር ይላሉ፡፡ ሁለት ጣሳ ደቅቆ እንጨት በ400 ብር፣ ክኩን በ200፣ ጨው በ40 ብር ገዝተን ጀምበር ስታዘቀዝቅ ወደ ቤታችን ልንመለስ ስንል የማውቃቸውን የሥራ ባልደረቦቼን አገኘኋቸው፡፡
“ቆቦ ያለሁት እኔ ብቻ አይደለሁም” እያልኳቸው ሰላም ተባብለን፣ ወዲያውኑ ተለያየን፡፡ እርስ በእርሳችን ስላልተማመንንን፣ መጠራጠር ነግሶ ስለነበረ ቆመን የልባችንን አውጥተን ማውራት አልቻልንም፡፡
ከቤታችንም በደህና ገባን፡፡
ሀየሎም ሞላ ከወልዲያ ወደ ቆቦ እንደተመለሰ ሰማሁ፡፡ ሃየሎም የራያ ቆቦ ወረዳ የፋይናንስና የግዢ ባለሞያ ሲሆን ቤተኛችን ነው፡፡ ከቤታችን አይጠፋም፡፡ በግርግሩ ምክንያት አድራሻው ጠፍቶብን ተጨንቀን ነበር፡፡
አልሃምዱሊላህ፡፡
የዛሬው ቀን የተባረከች ነች፡፡ ወልዲያ ካለ ምንም የጥይት ድምጽ እንደተያዘች፣ባንቺአየሁ ከወልዲያ  ዶሮ ግብር በእግራቸው፣ከዶሮ ግብር በባጃጅ ሁለት ሁለት መቶ ብር ከፍለው ቆቦ መግባቷን፣ መንገድ ላይ ብስኩት እየሰጧቸው “አይዟችሁ” እያሉ እንደሸኟቸው” ነገረችኝ የጎረቤታችን ሚስት የሞገስንም ልጆቿን ይዛ መጣች፡፡ ሀሉም እየገቡ እንደሆነ ከአነጋገሯ ተረድቻለሁ፡፡ የአብይ መግለጫን ሰምታ “ቦሩ ሜዳ እንገኛለን” አለች፣ በጆሮዬ ነው የሰማሁት ብላ….አወራችን ደጋግማ…አየ ባንቺ…
“የሼህ ሁሴን ጅብሪል ትንቢት እየደረሰ ይሆን? አልኩ፡፡”
በደህና ያሳድረን፡፡
የሌሊቱ ነገር አይነሳ፡፡ የአላህ ቁጣ ያልተለመደ ዓይነት ብልጭታ፣ኤሌክትሪክ ኮንታክት ሲያደርግ ብልጭ ድርግም እንደሚለው፡፡ ይሄ አይን አያስገልጥም፡፡ ደግሞ ጉርምርምታው። ስንጥቅጥቅ ብሎ መጮኽ፣እንደ ነሺዳ ጉርምርምታው ረጅም ነው፡፡
ያ አላህ! ሰው ይገናኛል የሚል ተስፋ አልነበረኘም፡፡ አላህ ግን  የወደደውን አደረገ፡፡  የመጣውን መለሰልንና ደህና አድረን ተገናኘን፡፡
(“የባየሽ ማስታወሻ” ከሚለው መጽሐፍ የተቀነጨበ)

Read 1201 times