Tuesday, 07 June 2022 07:18

የሰላም መንገድ...

Written by  ክቡር መተኪያ ኃይለሚካኤል
Rate this item
(1 Vote)

በኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር ከ1970ዎቹ እስከ 1980ዎቹ ባሉት አመታት በርካታ የሙዚቃ ባንዶች፣ ሁሉም የየራሳቸውን አይረሴ ደማቅ ቀለም በሙዚቃው ታሪክ ላይ አትመው አልፈዋል። የሮሀ ባንድ “የአንበሳውን ድርሻ” ይወስዳል የሚለውን አባባል ብዙዎቹ የሙዚቃ አድማጮችና ባለሙያዎች ይስማሙበታል። ሰላም ስዩም ደግሞ ይሄንን ባንድ ከመሰረቱት ሙዚቀኞች ከዋነኞቹ መካከል አንዱ ነው። ከመመስረትም ባለፈ እንደ ተክሌ ተስፈዝጊ ያሉትን የትግሪኛ ድምጻዊ በማስመጣት፣ የፋይናንስ ምንጭ በማፈላለግ፣ የባንዱ መሪ በመሆን የአስተዳደር ስራን በመስራት አገልግሏል።
ከሀገር ከወጣ ሰላሳ አመት ሞልቶታል። ያለፉትንም ሳምንታት ከፍተኛ የሚዲያ ትኩረት የሳበበት ሳምንታት ነበሩ ብሎ በድፍረት መናገር ይቻላል። ሰላም ከሰላሳ አመታት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ይመጣል ከተባለ በኋላ በፌስቡክ ገጹ ከተለቀቀው የአውሮፕላን ላይ የጉዞ ፎቶግራፍ እስከ ቦሌ አየር ማረፊያ የእነ አብረሀም ወልዴ አቀባበል፣ በኤልያስ መልካ መካነ መቃብር ላይ ካሳረፈው የአበባ ጉንጉን እስከ ለዛ የሽልማት ፕሮግራም ድረስ የሰላሚኖ ጉዞዎችን ሚዲያዎች እግር በእግር እየተከታተሉ ዘግበውታል።እርግጥ ሰላም ስዩም “ከኢትዮጵያ እንደወጣሁ ሶስት አስርት አመታትን በባህር ማዶ እቆያለሁ” ብሎ አላሰበም ነበር። ከሁለት አመታት በፊት እንኳ የራሱ የሙዚቃ ስራዎችን በሙዚቃ መሳሪያ ብቻ አቀናብሮ የሰራበት grace (ጸጋ) አልበሙን በሸራተን አዲስ ሊያስመርቅ አቅዶና እቅዱንም በቫላንታይንስ ቀን እውን ሊያደርግ ከወዳጆቹ ጋር ተማክሮ ሲያበቃ፣ የቫላንታይንስ ቀን ሊከበር የቀሩት ግን 15 ቀናት ብቻ በመሆናቸው የቪዛ፣ የትኬትና ሌሎች የወረቀት ጉዳዮች በዛች የተጣበበች ቀን እንደማያልቁ አውቆ እቅዱን ማሳካት እንዳልቻለ ከብርሀኑ ድጋፌ ጋር በለዛ የራዲዮ ፕሮግራም ላይ ባደረገው ቃለ ምልልስ አሳውቋል።
ሮሀ ባንድ ባንድ ወቅት ባሳተመው በመሳሪያ ብቻ የተቀነባበረ ሙዚቃ ላይ የሰላም ስዩም የጊታር አጨዋወት ነጥሮ የወጣበት ከመሆኑ ባሻገር “ሆዴ መላ መላ” (አስቴር አወቀ)፣ “ትዝ ትዝ ትዝ እያለኝ” ( መሀሙድ አህመድ)፣ “አካሌ” (ኤፍሬም ታምሩ)፣ “እየቆረቆረኝ” (ቴዎድሮስ ታደሰ)፣ “ፍቕረይ ተለመኒ” (ተክለ ተስፋዝጊ) የተሰኙት ሙዚቃዎች በድምጻዊያኑ ይበልጡኑ የታወቁ ቢሆኑም፣ የሙዚቃው ቅንብር ለሙዚቃው ተደማጭነትና ህልው መሆን ወሳኝ ጉዳይ እንደሆነ አሳይቷል:: ለዚህም ለአልበሙ ነብስ ከዘሩበት የሮሀ ባንድ ተጫዋቾች መካከል የሰላም ስዩም ጊታር ጨዋታ አይረሴ ነበር። በሃገራችን የሙዚቃ አድማጭ ዘንድ በመሳሪያ የተቀነባበረ (instrumental) ሙዚቃን እንዲሁም ረቂቅ (classic)ሙዚቃን እንደ አንድ የሙዚቃ ዘውግ ያለመቁጠርና እርስ በርስ አምታትቶ የመግለጽ ችግር በነበረበት ወቅት በአልበም ደረጃ ኢንስትሩመንታል ሙዚቃን ሰርቶ ለአድማጩ ማበርከት በራሱ አስደናቂ ነው::
ሰላም ከሰላሳ አመታት የባህር ማዶ ቆይታ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በብዙ ህዝብ ፊት የተገለጠው ግንቦት 13 ምሽት 2014 ዓ.ም በግዮን ሆቴል የመናፈሻ ስፍራ በኤፍሬም ታምሩ ኮንሰርት ላይ ነበር። ብዙሀኑ የኤፍሬም ታምሩ አድናቂዎች ይሄን ኮንሰርት በተደበላለቀ ስሜት ነበር ሲጠባበቁት የነበረው። ከጥቂት አመታት በፊት በሚሊኒየም አዳራሽ በብዙ ጉጉት ሲጠበቅ የነበረው ኤፍሬም ታምሩ፣ ጥቂት ሙዚቃዎቹን ብቻ አቅርቦና የታዳሚውን የናፍቆት ጥም ሳይቆርጥ የመውረዱ ትውስታ በብዙሃኑ ህሊና ውስጥ ሳይመላለስ አልቀረም:: በተጨማሪ የኤፍሬም ታምሩ “እንደገና” የሙዚቃ አልበምና የሮሀ ባንድ ዳግም መሰባሰብ (reunion) ላይ በሙዚቃው ቅንብር የተሳተፉ ሰዎችን በአካል የማየት ፍላጎትና በይበልጡን ደግሞ ከሰላሳ አመት የባህር ማዶ ቆይታ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሰውን ሰላም ስዩምን የማየቱ ጉጉት ከፍ ያለ ነበር።
ሰላም ስዩምን በቅርበት የሚያውቁ አንዳንድ ወዳጆቹ እንደሚሉት ከሆነ፤ በዚህ ኮንሰርት ላይ ታስቦ የነበረው መርሀ ግብር፣ ኤፍሬም ታምሩና ሌሎች የባንዱ አባላት የሙዚቃ ስራዎቻቸውን በሚያቀርቡበት ሰአት በድንገት ሰላም ስዩም ከመድረክ ጀርባ ጀምሮና መብራት ጠፍቶ፣ የኤፍሬም ታምሩ ሙዚቃ የሆነውን “በፍቅርሽ መያዜን” የተሰኘውን ታሪካዊት ሙዚቃ መግቢያ (intro) እየተጫወተ መውጣትና ህዝቡን በድንገቴ (surprise) ማስደሰት ነበር። ሆኖም ግን የሰላም ስዩም ጉዳይ ከአሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት ከወሰነበት እለት ጀምሮ እስከ አውሮፕላን ውስጥ ጉዞው እንዲሁም እስከሚሳተፍበት መርሀ ግብር የራዲዮና የቴሌቪዥን ጋዜጠኞች ሲቀባበሉት ስለባጁ፣ ሰርፕራይዝነቱ ቀርቶ በይፋ “በኤፍሬም ታምሩ ኮንሰርት ሰላም ስዩም ይታደማል” ብለው አስተዋወቁ።
ግንቦት 13 ምሽት ሶስት ሰአት ገደማ የጀመረው የኮንሰርቱ ድግስ፣ በወጣቱ የኦሮምኛ ዘፋኝ አንዷለም ጎሳ ካሟሸና በራሄል ጌቱ ክልዔቱ ካለ በኋላ ታዳሚ እየተቁነጠነጠ ሲጠብቀው የነበረው ኤፍሬም ታምሩ ብቅ አለ። መቼም ኤፍሬም በዚያ ዠርጋዳ ቁመናው መድረኩ ላይ ከወዲህ ወዲህ ብሎበት ይቅርና አንዱ ቦታ ላይ እንኳ ቆሞበት አይንን መሙላቱ የታወቀ ነው። ከኤፍሬም ባልተናነሰ ከቁመቱ ከተት፣ ከተክለ ሰውነቱ ደልደል ከጸጉሩ ገባ ያለውና ሁሌም ጊታሩን አንግቦ የሚታየው የሰላም ስዩም ግርማና ሞገስም እንዲሁ በመድረኩ ላይ የረበበበት ሆኖ ታይቷል። በተለይ ኤፍሬም ታምሩ እንደ ወትሮ ልማዱ የባንዱ አባላትን የእያንዳንዳቸውን ስም እየጠራ በሚያስተዋውቅበት የሰርክ ልማዱ፣ የሰላም ስዩምን  ስም እየደጋገመ እየጠራ የታዳሚ ትኩረት ሰላም ላይ እንዲያርፍ አድርጓል። በተለይ ኤፍሬም “አንቺ ካልመሰለሽ” የተሰኘውን ሙዚቃ ሲጫወት “ለሰላም ክብር” እያለና ከሌሎቹ የባንድ ተጫዋቾች ይበልጥ ሲያሞካሸውና ሲያደንቀው ታይቷል።
ሰላም ስዩም (እናቱ፣ መላው ቤተሰቡና ወዳጆቹ  "ሰላሚኖ" እያሉ ነው የሚጠሩት) የተወለደው በአዲስ አበባ ከተማ በ1947 ዓ.ም ነው። ቅድመ አያቶቹ በኢትዮጵያ የመጀመሪያዎቹ የፕሮቴስታንት እምነትን የተቀበሉና ያራምዱ የነበሩ እንደሆነ ሰላም ስዩም ይናገራል፡፡ ይህም ቤተሰብ ሙዚቃን እንደ አንድ አይነተኛ የአምልኮ ስርአት ማከናወኛ መሳሪያ ይጠቀም ስለነበር ለሙዚቃ ያለው አረዳድ ግንዛቤና ፍቅር መነሻው ከዚያው ሊሆን እንደሚችል ይገምታል፡፡ ብዙዎች በተለያየ ሚዲያ ላይ “ሰላሚኖ ትውልደ ኤርትራ ነው” እያሉ በተለያየ ሁኔታ ሲያስተጋቡ ቢደመጡም፣ ከጥቂት ወራት በፊት በሸገር ኤፍኤም ራዲዮ ብርሀኑ ድጋፌ በሚያሰናዳው “የለዛ” ፕሮግራም ላይ ሰላም የተወሰነ አመታት ኤርትራ ውስጥ ይኑር እንጂ ትውልዱ አዲስ አበባ ካዛንቺስ አካባቢ እንደሆነ ተናግሯል።
“በአንድ ወቅት ቀዳማዊ ኃይለስላሴ በመንገድ በሚያልፉበት ሰአት አይነስውር ወላጅ አባቴን ስዩም ወልደማርያምን ያገኙትና ምን እንድናደርግልህ ትፈልጋለህ? ይሉታል። እርሱም “እንደኔ ያሉ አይነ ስውራን በመንገድ ወድቀው ከሚቀሩ የሚማሩበት ተማሪ ቤት እንዲቋቋምላቸው ነው የምፈልገው” ብሎ ይመልስላቸዋል፡፡ ንጉሱም “ሰው ያስባል አምላክ ይፈጽማል” የሚል ቃል ነግረውት ሄዱ። በሄዱም በሶስተኛው ወር ካዛንችስ አካባቢ በአሜሪካዊያን ሚሲዮኖች የሚተዳደር የአይነ ስውራን ተማሪ ቤት መቋቋሙን በመልእክተኛ ነገሩት:: እርሱም ባለቤቱን ይዞ ወደ ካዛንችሷ ተማሪ ቤት ይመጣና በቅጥር ግቢው ውስጥ መኖሪያውን ያደርጋል፡፡ በዚያው ግቢ ውስጥ ነበር እኔም የተወለድኩት”
ከጥቂት አመታት በኋላም ሰላም ወደ አስመራ ተጓዘ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ወላጅ አባቱ በአዲስ አበባ ያቋቋሙትን የአይነ ስውራን ተማሪ ቤት በአስመራ እንዲያቋቁሙ ከቀዳማዊ ኃይለስላሴ መልዕክት ስለደረሳቸው ነበር፡፡ ሰላም አስመራ ከደረሰ በኋላ በቤተሰቡ እንደ ታላቅ ንብረትና ቅርስ የምትታይ፣ ብዙሃኑ እንዲነካ የማይፈቀድለት የነበረችውን ጊታር እንዲነካ ከአባቱ ዘንድ ፍቃድ አገኘ፡፡ በቃ ሰላሚኖና ጊታር “ላልከዳህ ላልከዳሽ” ተባባሉ፡፡ ከጥቂት ጊዜያት በኋላ እዛው በአስመራ እያለ ከጓደኞቹ ጋር አንዲት አነስተኛ የሙዚቃ ባንድ አቋቁሞም ከፍተኛ ዝናንና ተወዳጅነትን አትርፈው ነበር፡፡ ሆኖም ግን በቤተክርስትያን አምላኪዎች ከነበሩ “አንጋፋና ወግ አጥባቂ” ሰዎች ከፍተኛ ተቃውሞ ገጠማቸው።  የባንዱም ህልውና በዚያው አከተመ፡፡ በመቀጠልም እነ ተክሌ ተስፋዝጊ ይጫወቱበት ወደነበረው ወደ ብላክ ሳባ (ቆይቶ ብላክ ሶል ባንድ ወደተባለው) የሙዚቃ ባንድ አመራ፡፡
ግዜው 1960ዎቹ አጋማሽ ተጠግቷል:: ኤርትራ ከቅኝ ገዥዋና ከሞግዚቷ እንግሊዝ ተላቅቃ በፌደሬሽን ወደ ኢትዮጵያ ከተቀላቀለች ወዲህ የተጠበቀው አንድነትና ህብረት ሊመጣ አልቻለም፡፡ እንዲያውም በተለይ በአረብ ሃገራት የሚደጎሙና የኤርትራን መገንጠል የሚያቀነቅኑ ኃይሎች በአንድ ወገን፣ አንድነቱን የሚሰብኩና በንጉሰ ነገስቱ የሚደገፉ ኃይሎች በሌላ ወገን ጎራ ለይተው ሲያደርጉት የነበረው መቃቃር እየተባባሰ ሄዶ ጦር ካማዘዘ ሰንበትበት ብሏል፡፡ የሰላም ስዩም ቤተሰቦችም ይሄን ያልተረጋጋ የፖለቲካ ሁኔታ ጥለው በ1964 ዓ.ም ገደማ ተመልሰው ወደ አዲስ አበባ መጡ። ሰላምም አስመራ ያቋረጠውን የመደበኛ ትምህርት ቀጠለ። የ1967 ለውጥን ተከትሎ የመጣው ደርግ መራሹ መንግስት ወጣቱ ስራ መቀጠር የፈለገ እንደሆነ እንደ ቅድመ ሁኔታ “የእድገት በህብረት ዘመቻ መዝመት አለበት” የሚል ፖሊሲ ይዞ በመምጣቱ የሰላምን የቀለም ትምህርቱን መቀጠልን በጎንም የሙዚቃ ስራ መስራት ፍላጎቱ ላይ እንቅፋት ገጠመው:: ስለዚህ አስጨናቂ ግዜ ምስክርነቱን ሲሰጥ፤ “ከአስመራ ጀምሮ የማውቃቸው ብላክ ሶል የሙዚቃ ባንዶችና ራሱ የሙዚቃ ጥበብ መደበቂያ ሆነኝ” ይላል፡፡
ሰላሚኖ አምባሳደር ሲኒማ ህንጻ ስር የነበረውን ቬነስ የምሽት ክለብን ለታላቅ ሙዚቀኛነት የታጨበት ስፍራ እንደሆነ ይናገራል:: ከዚያም አልፎ ወደ ታላቅ ሙዚቀኛነት መጓዝ የጀመረበትን የአይቤክስ ባንድ አባላትን ማግኘት የጀመረበት እንደሆን ይመሰክራል፡፡ ሰላም የወደፊቱን ታላቅ የሙዚቀኝነት ጉዞውን ለመጀመር ያበቃውን አይቤክስ ባንድን አንድ ብሎ እርካቡን ረገጠ፡፡
የ1967 ዓ.ም የመንግስት ለውጥ ለበርካታ የውጭ ሃገር ሙዚቀኞች አመቺ አልነበረም።  እንደ አንድሪው ዊልሰንና ዚንጎን ለመሳሰሉ ሙዚቀኞች መኮብለልም ምክንያት ሆነ። በአይቤክስ ባንድ ውስጥ የተፈጠረውን ክፍተት እነ ሰላም ስዩም በጊታር፣ ኃይለማርያም በኪቦርድ፣ ግርማ ጭብሳ፣ መሃሙድ አህመድንና አሊ ቢራን በድምጻዊነት በማካተቱና ፍጹም ለውጥ በማምጣቱ፣ ሰላም ይህንን አዲሱን የአይቤክስ መዋቅር “አይቤክስ ቁጥር ሁለት ባንድ” በማለት ይጠራዋል፡፡
ሰላም ወደ አይቤክስ ባንድ የተቀላቀለበት ሁኔታ በአጋጣሚ ሳይሆን ችሎታው ታይቶና ተመርምሮ ነው:: ቬኑስ ክለብ ጊታር እየተጫወተ በነበረበት በአንደኛው ምሽት፣ ዚምባብዌያዊው አንድሪው ዊልሰን ለአይቤክስ ባንድ የሚመጥን ሁነኛ የጊታር ተጫዋች ለመመልመል በክለቡ ባልኮኒ ላይ ተሰይሟል። ሰላም የጊታር ጨዋታው ላይ ተመስጦ የገባ የወጣውን ባይመለከትም  አንድሪው ዊልሰን ግን ሰላምን በሚገባ አይቶና መዝኖ ጨርሶ ነበር፡፡ ሰላም ይሄንን ጉዳይ ያወቀው እነ ጆቫኒ ሪኮ ከቀናት በኋላ ደውለው በአንድሪው ዊልሰን አማካይነት መታጨቱንና ለዚህም ክብር ሊሰማው እንደሚገባ ሲነግሩት ነው፡፡
በሃገራችን ከተሰሩና ዛሬም ድረስ ከሚደመጡ  የአይቤክስ ባንድ አሻራዎች መኻከል ጎላ ያለውና እንደ ብርሀኑ ድጋፌ አባባል ደግሞ “በኢትዮጵያ የሙዚቃ አልበም ህትመት ታሪክ የመጀመሪያው ዲጂታል (የሲዲ) ህትመት” እንደሆነ የሚነገርለት ይኸው መሀሙድ አህመድና እነሰላሚኖ የነበሩበት አይቤክስ ባንድ ያሳተሙት የሙዚቃ አልበም ነው።
አይቤክስ ባንድ የሰላም ስራዎች የተሟሹበት፣ የወጣትነት ዘመኑን ያሳለፈበት፣ በርካታ የሙዚቃ እውቀቶችን የቀሰመበት ቢሆንም፣ በብዙ ወጀቦች ከወዲህ ወዲያ ሲወዘወዝ ከረመ። በተለይ ጆቫኒ ሪኮና እርሱ የዩንቨርስቲ ተማሪዎች መሆናቸው በባንዱ አባላት ዘንድ በቅንነት አልታየላቸውም። በሌላ በኩል ደግሞ በወቅቱ የፖለቲካ ውጥረት ሳቢያ አንዳንድ  አባላት ከሀገር ለቅቀው ለመውጣት አጋጣሚዎችን መጠባበቅ ጀምረዋል። በድንገት የዋልያስ ባንድ ሳክስፎኒስት ሞገስ ሃብቴ ወደ ውጭ ሀገር የመሄድ ፍላጎትና ዋልያስ ባንድ አሜሪካ ሀገር ኮንሰርት ለመስራት እድል ማግኘቱ፣ ከዳህላክ ባንድ ሳክስፎኒስቱ ከዳህላክ ባንድ እንዲሁም መራሄ ድምጻዊ መሀሙድ አህመድን ከአይቤክስ ባንድ ለማዘዋወር በለስ ሲቀናቸው፣ አይቤክስ ባንድ ውስጥ ከፍተኛ ክፍተት ፈጠረ። “በዚህም ጊዜ እኔ ጆቫኒና ፍቃደ አምደመስቀል ብቻ ቀረን” ይላል፤ ሰላም ስዩም ትውስታውን ሲናገር።
የአይቤክስ ባንድን ህልውና ማስቀጠል እንደማይቻላቸው የተረዱት ጆቫኒና ሰላም፣ ከባለሀብቱ አቤሴሎም ይህደጉ ባገኙት የአርባ ሺህ ብር ብድር የተወሰኑ የሙዚቃ መሳሪያዎችን ገዝተውና ከዳህላክ ባንድ ኪቦርዲስት ዳዊት ይፍሩን እንዲሁም ተሾመ ወልዴንና ኩኩ ሰብስቤን በማካተት በይፋ ሮሀ ባንድን መሰረቱ። የመጀመሪያዎቹ የሮሃ ባንድ አባላት:-
ሰላም ስዩም (ሊድ ጊታር)
ዳዊት ይፍሩ (ኪቦርድ)
ጆቫኒ ሪኮ (ቤዝ ጊታር)
ተክሌ ተስፋዝጊ ድምጻዊ(ድራም ተጫዋት)
ፍቃደ አምደ መስቀል (ቴነር ሳክስፎን)
ሌቮን ፎንዳቺ (እንግሊዝኛ ሙዚቃ)
ነበሩ። ከዚህ በኋላ ሌሎች በርካታ ድምጻዊያን፣ የሳክስፎን ተጫዋቾች፣ የድራም ተጫዋቾች ተሳትፈዋል። (በተለይ ሙሉቀን መለሰ አስደናቂ የድራም ተጫዋች እንደነበርና ሮሀ ባንድ ባቀናበረው የኩኩ ሰብስቤ የመጀመሪያ የሙዚቃ አልበሟ ላይ እንደተሳተፈ ይነገራል።)
“ሮሃ ባንድ ምን ያህል ሙዚቃዎችን አቀናበረ?” የሚለው ጥያቄ እስከዛሬ ድረስ ሁሉንም የሚያስማማ ምላሽ አላገኘም። አንዳንዶች 250 ካሴቶችና ከ2500 በላይ ሙዚቃዎችን ሮሃ ባንድ ሰርቷል ይላሉ:: ቁጥሩ በውል የታወቀ ባይሆንም የማይካደው ግን በኢትዮጵያ የሙዚቃ ሰማይ ላይ ተግ ብለው ከበሩ ከቴዎድሮስ ታደሰ እስከ ኩኩ ሰብስቤ፣ ከኤፍሬም ታምሩ እስከ ሃመልማል አባተ፣ ከተሾመ ወልዴ እስከ መሃሙድ አህመድ፣ ከጸሃዬ ዮሃንስ እስከ አረጋኸኝ ወራሽ፣ ከኤልያስ ተባባል እስከ ንዋይ ደበበ፣ ከኬኔዲ መንገሻ እስከ ሂሩት በቀለ ሮሃ ባንድ ሙዚቃቸውን ያቀናበረላቸው ድምጻዊያን ናቸው::
የብዙዎቹን የ70ዎቹና የ80ዎቹ ትዝታ ሙዚቃዎችን ያቀናበረው ሮሃ ባንድ፣ ባልተጠበቀ ሁኔታ ህልውናው ከሰመ:: ወደ ግል ስራ የሚሄደው ወደ ግል ስራው ሲሄድ፣ እነ ሰላም ስዩም ደግሞ ከሃገር ወጡ:: እነ ጆቫኒ ሪኮ በተለያየ ጊዜ ከሃገረ አሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ ቢመላለሱም፣ ሰላም ስዩም ግን ላለፉት ሰላሳ አመታት የኢትዮጵያን ምድር ሳይረግጥ ቆየ:: ሰላምን ከዚያ በኋላ የምናገኘው አልፎ አልፎ ብቅ እያለ በሚታደምባቸው መድረኮች ወይም ለእርሱ ክብር በተዘጋጁ ፕሮግራሞችና ሽልማቶች እንዲሁም በማህበራዊ ትስስር ድረገጹ ብቻ ነበር::
ሰላሚኖን በአንድ ወቅት በማህበራዊ ትስስር ድረ ገጽ መነጋገሪያ አድርጎት የነበረው የታሪካዊ ጊታሩ ጉዳይ ነበር:: ኑሮውን በሃገረ አሜሪካ ያደረገው ሰላም ስዩም ኢትዮጵያ እያለ ታላላቅ ሙዚቃዎችን የሰራባት፣የብዙ ታዋቂ ድምጻዊያንን ሙዚቃ ያጀበባትና በዛን ግዜ “የአንድ አውቶሞቢል ዋጋ ያህል ያወጣበትን” የ1979 GIBSON ES-335 TD - SUNBURST ከፊል አኩስቲክ ሊድ ጊታር ከጠፋበት ቦታ መልሶ ለማግኘት የተደረገውን አሰሳ “የአርኪዎሎጂ ፍለጋ” ይለዋል:: ይህ ጊታር ከውጭ ሃገር የሙዚቃ መሳሪያ ማስገባት ብርቅ በነበረበት በ1970 ዎቹ አመታት የመሸጫ ዋጋውን እጥፍ ከፍሎ ያስመጣው ጊታር ነበር:: በአንድ ጎዶሎ ቀን ከአንድ ስለመሳሪያው ዋጋ ከማያውቅ ግድየለሽ ሾፌር መኪና ላይ ጊታሩ ወድቆ ተሰበረ:: እንደ አጋጣሚ በዛችው ተመሳሳይ ሞዴል ሌላ መንታ ጊታር ገዝቶ አስቀምጦ የነበረው ሰላም መደበኛ የባንድ ስራውን በአዲሷ ጊታር እያከናወነ አሮጌዋን ጊታር እንዲያድስለት ለኤሌክትራ ሙዚቃ ቤት ባለቤት ለአቶ ተሾመ ጸጋዬ ሰጥቶ ድንገት ከሃገር እንደወጣ ይቀራል:: የዚህችን ጊታር ታሪካዊነት የሚያውቀው ሰላም ስዩም ግን በጆቫኒ ሪኮ አማካይነት ከብዙ አታካች ፍለጋ በኋላ እጅግ ተጎድታና ተጎሳቁላ ካለችበት አፈላልጎ አገኛት:: ከጥቂት ጊዜያት በፊት ዮሐንስ ጦና በፌስቡክ ገጹ ስለዚህቹ ታሪካዊ ጊታር መታደስ ጽፎ ሰላም ስዩምንና የቀደሙ ስራዎቹን ዳግም እንዲታወሱ ማድረጉን ብርሃኑ ድጋፌ በለዛ የራዲዮ ፕሮግራሙ ላይ አስታውሶ፣ ሰላሚኖም ለዮሐንስ ጦና ከፍ ያለ ምስጋና አቅርቦለታል::
ሰላምን ባለፉት ሰላሳ አመታት (በጥቂቱም ቢሆን) ለህዝብ ታይቷል ለማለት የሚያስችለው በ2019 (እ.ኤ.አ) ከአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ በጋዜጠኛ ጽዮን ግርማ ጠያቂነት ከጆቫኒ ሪኮ ጋር ሆነው ባደረጉት ቃለ ምልልስና ፋና ቲቪ ጆቫኒ ሪኮን እንግዳ አድርጎ አቅርቦ በነበረበት ፕሮግራም ላይ ለጥቂት ደቂቃዎች ስለጆቫኒ ሪኮ በሰጠው ምስክርነት  ነበር:: እነዚህ አልፎ አልፎ ብቅ የሚልባቸው አጋጣሚዎችና የቀደመ ተወዳጅነቱ ተደማምረው ነበር ከሰላሳ አመት በኋላ ይታደምበታል የተባለው የሂልተን ሆቴሉ ፕሮግራም በናፍቆት የተጠበቀው::
ሰላሳ አመት በናፍቆት የጠበቀው አድናቂ ሰላምን በአካል የሂልተን ሆቴል መድረክ ላይ ሊመለከተው ቀኑ ደረሰ:: አንጋፋው ሂልተን ሆቴል እንግዶቹን ለመቀበል ከብዙ ቀናት ጀምሮ ሽር ብትኑን ተያይዞታል፡፡አንጋፋና ወጣት ድምጻዊያን፣ የሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋቾች፣ካሜራ ማኖች፣ ዳይሬክተሮች፣ የፊልም ተዋንያን፣ ጋዜጠኞች ፕሮዲውሰሮች ብቻ አከሌ ቀረ እስከማይባል ድረስ በሂልተን ሆቴል የመናፈሻ ስፍራ የተጣለው ድንኳን ከጥግ እስከ ጥግ ሞልቶ ሲጠበቅ የነበረው የለዛ ሽልማት ፕሮግራም ከምሽቱ ሁለት ሰአት ላይ ጀመረ። “የአመቱ ነጠላ ዜማ”፣ “የአመቱ አዲስ ድምጻዊ”፣ “የአመቱ ተከታታይ ፊልም” እና ሌሎቹንም ዘርፎች ላይ የተመረጡ ሰዎች እንደተሸለሙ ቀጣዩ ተሸላሚ ሰላም ስዩም ሆነ። ከዚህ ቀደም እነ መሀሙድ አህመድንና ተሾመ ምትኩን የመሳሰሉ አንጋፋ የሙዚቃ ሰዎችን የሸለመው የለዛ “የህይወት ዘመን” ሽልማት ዘርፍ ዘንድሮ ተሸላሚ አድርጎ የመረጠው የሮሀ ባንዱን የጊታር ተጫዋች ሰላም ስዩምን ነበር። በአዘጋጆቹ አማካይነት ሽልማቱን እንዲያበረክት የተመረጠው ደግሞ አንጋፋው ድምጻዊ መሀሙድ አህመድ ነው። መሀሙድ ለሰላም ስዩም ሽልማቱን ካበረከተ በኋላ በሰጠው ምስክርነት፤ “ከክብር ዘበኛ የሙዚቃ ባንድ አስወጥተው ወደ አይቤክስ ባንድ ያስገቡኝና የተሻለ ኑሮ እንድኖር የረዱኝ ሮሀ ባንዶች ናቸው” ብሏል።
ሰላም ስዩም መካከለኛ ቁመቱና ደልደል ባለ ሰውነቱ ላይ ልክክ ብሎ ውበት ያጎናጸፈውን ውብ ነጭ ኮት በቀይ የቢራቢሮ ክራቫትና ጥቁር ሱሪ ከጥቁር ቆዳ ጫማ ጋር ለብሷል። ጸጉሩ በጥቂቱ ወደ ኋላ ከመሸሹ በቀር የዛሬ አርባ አመት በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የምናውቀው የጺም አቆራረጡና ከእድሜው አንድ አመት እንኳ ያልጨመረ እስኪመስል ድረስ ከነጥንካሬውና ከነግርማው በመድረኩ ይታያል። በተለያዩ አጋጣሚዎች እንደታየው ሁሉ ሰላም የእድሜ ዘመን ሽልማቱን ከመሀሙድ አህመድ እጅ ከመቀበሉ በፊት የናፍቆት ሰላምታቸው በሆነው በመተቃቀፍ መሃል ሰላም እንባውን በእጆቹ ሲጠርግ በመድረኩ ላይ ታይቷል። አብረውት ለረዥም አመታት በሮሀ ባንድ የቆዩት ጆቫኒ ሪኮና ዳዊት ይፍሩም ወደ መድረኩ መጥተው በሞቀ ሰላምታና መተቃቀፍ ለሰላም ያላቸውን ፍቅርና ክብር አሳይተዋል። ከዚያም በተሰጠችው አጭር የንግግር ሰአት አዘጋጁ ብርሀኑ ድጋፌን፣ የቀጥታ ስርጭት አሰራጭ የነበረውን የባላገሩ ቲቪ ባለቤት አብረሀም ወልዴን፣ አባቱን አቶ ስዩም ወልደማርያምን፣ እናቱን ወይዘሮ ጽርሀነማርያምን ጨምሮ ታናሽ እህቱን እየሩሳሌምን፣ ለአርባ ሁለት አመታት አብራው በትዳር የቆየችውን ክብርት ባለቤቱን ብዙነሽ ኃይሉን፣ አርባ ስምንት የሙዚቃ አመታት አብረውት ያሳለፉትን አይቤክስና ሮሀ ባንድን፣ መሀሙድ አህመድን (በሰላሚኖ አጠራር መሀሙድዬ) ጆቫኒ ሪኮንና ዳዊት ይፍሩን አመስግኗል፡፡
ከጥቂት አመታት በፊት ተሾመ ምትኩ የህይወት ዘመን ተሸላሚ ተደርጎ ሲመረጥ ኢትዮጵያ መጥቶ ሽልማቱን ባለመቀበሉ ምክንያት በተፈጠረ ቁጭት ሰላም ስዩም አዲስ አበባ እንዲመጣና እንዲሸለም ማድረጋቸውን የለዛ ሽልማት ፕሮግራም መሪዋ ጋዜጠኛ ክብሬ ተስፋዬ ተናግራለች:: በዚሁም መሰረት ሰላም ስዩም የህይወት ዘመን ሽልማቱን ከተወዳጁና አንጋፋው ድምጻዊ መሀሙድ አህመድ እጅ ተቀብሏል።
ሰላም እድሜው ስድስት አስርቶችን አልፎ እንኳ ብቃቱና ችሎታው አብረውት ናቸው። በተለይ በለዛ የሽልማት ምሽትና በኤፍሬም ታምሩ ኮንሰርት ላይ የተመለከቱት ሰዎች እጅግ ያስደመማቸው ቀዳሚ ጉዳይ የጊታር አጨዋወቱ ነው፡፡ በኤፍሬም ታምሩ በየሙዚቃዎቹ መሀል ላይ የሰላምን ሶሎ የጊታር ጨዋታ (ሌሎች የሙዚቃ መሳሪያና የዘፋኙ ድምጽ ተቀንሶ በጉልህ የጊታር ጨዋታ የምትደመጥበት ቦታ) ላስተዋለ እንዲሁም በለዛ የሽልማት ፕሮግራም ላይ  በህይወት ለሌሉ የሀገራችን ሙዚቀኞች መታሰቢያ ይሆን ዘንድ በአንድ ወቅት በአሜሪካ ያሉ የሙዚቃ ቡድኖች “see you again” በሚል ርዕስ የተጫወቱትን ኢንስትሩመንታል ከሙዚቀኛ ኪሩቤል ተስፋዬ ጋር በመሆን የተጫወቱትን ለታደመ ሰው አበው “እያደር እንደ ዋይን” ይሉት ሰው እርሱ ሰላም ስዩም ነው ማለቱ አይቀርም ።
ከሮሀ ባንድ መበተንና የባንዱ የሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋቾች በየፊናቸው መጓዝና በተለይ ከሰላም ስዩም ላለፉት ሰላሳ አመታት ከአይን ርቆ መቆየት በላይ የሙዚቃ አድማጩን የጎዳው “ስሁት የሆነው የሮሀ ባንድ ቅንብር ትርክት” ነው። ያ ትርክት “የሮሃ ባንድ ቅንብር ሁሉ የኪቦርድ ተጫዋቹ ዳዊት ይፍሩ ብቻ እንደሆነ አድርጎ ያልተገባ ክሬዲት የመስጠት ትርክት” ነው፡፡ ይሄም በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ በተደጋጋሚ የሚነገር ግን ፍጹም የተሳሳተ መደምደሚያ ነው። ይህ በተደጋጋሚ በየሚዲያው የሚስተጋባ የተሳሳተ ገለጻ መሰረታዊ የሆነውን የሮሀ ባንድ የሙዚቃ ቅንብር ባህል ካለማወቅ የመጣ እንደሆነ ስለ ባንዱ ጥናት ያደረጉ የሙዚቃ ባለሙያዎችና የባንዱ አባላት ጭምር ይናገራሉ። እርግጥ ዳዊት ይፍሩ ለቁጥር የበዙ ሙዚቃዎች ቅንብር ላይ የአንበሳውን ድርሻ የሚወስድ ቢሆንም፣ ሰላም ስዩም ጆቫኒ ሪኮና ሌሎቹም የሮሀ ባንድ የሙዚቃ አባላት የእያንዳንዱ የሙዚቃ መሳሪያ የትኛውን ድምጽ ማሰማት እንዳለበት ድምጻዊው የቱ ጋር መግባት የቱ ጋርስ መውጣት እንደሚገባው፣ የሳክስፎኑ ሚና የጊታሩ የኪቦርዱ የድራሙና የሌሎች መሳሪያዎች ድርሻ እንዴት መሆን እንዳለበት በየበኩላቸው አስተዋጽኦ ያደርጉ እንደነበረና ለሙዚቃው ቅንብር ተዋጽኦ እንደነበራቸው ይናገራሉ። ሌላው ቀርቶ የግጥምና የዜማ ደራሲው አበበ መለሰ በአንድ ወቅት በሸገር ኤፍኤም ራዲዮ የጨዋታ ፕሮግራም ላይ በሰጠው ቃለ ምልልስ ላይ እንደተናገረው፤ የብሩህ ተስፋ እሸት የስብስብ ሙዚቃ አልበም ላይ ከኤፍሬም ታምሩ ጎዳናዬ ዜማ ድርሰት ባሻገር የቅንብር ሀሳብና በሙዚቃው መሀል ላይ ያለውን የኪቦርድ ሶሎ ድምጽ አስተዋጽኦ አድርጓል። ይህ ሁሉ የሚያሳየው የሮሀ ባንድ የሙዚቃ ቅንብር ባህል ከሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋቾቹ አልፎ እንደ አበበ መለሰ ወዳሉ ወደ ዜማ እና ግጥም ደራሲዎች ጭምር እንደሚሸጋገር ነው፡፡ (እንዲያውም አንዳንዶች ምናልባትም ስለ ሙዚቃ ጥልቅ እውቀት አላቸው የሚባሉ እንደ ሙሉቀን መለሰ ያሉት ድምጻዊያንም ለቅንብሩ ሀሳብ ይሰጡ ነበር ይላሉ)። ሌላው ይቅርና በሮሃ ባንድ የሚቀናበሩ ቅንብሮች ላይ ለማቀናበሪያ ከሚከፈለው ክፍያ ላይ ሶስት ሺህ ብር ተቀንሶ ለጆቫኒ ሪኮ፣ ለዳዊት ይፍሩና ለሰላም ስዩም የሚከፈል መሆኑ የሚያሳየው የሮሃ ባንድ ቅንብር እንደ ዛሬው ዘመን አቀናባሪ ተብሎ እንደሚጻፈውና ክሬዲት እንደሚወሰድበት ሳይሆን ለሙሉ ባንዱ የሚሰጥ ክሬዲት አነሰ ቢባል እንኳ እነ ጆቫኒ ሪኮ፣ ሰላም ስዩምና ዳዊት ይፍሩ በጋራ የሚጋሩት ስያሜ ነበር ለማለት ያስችላል፡፡
 በአንድ ወቅት በተካሄደ የቁንጅና ውድድር ሶስተኛ የወጣችውን ብዙነሽ ኃይሉን አግብቶ አርባ ሶስት አመት የቆየው ሰላሚኖ፤ አራት ልጆችና ሁለት የልጅ ልጆችን አፍርቷል። በዩንቨርሲቲ ትምህርት ላይ ሳለ ያጠናውን የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃን በተመለከተ ከሰራው ጥናት (Origin and development of “zemenawi” ethiopian music )ተነስቶ ትልቅ መጽሐፍ ጽፎ እያጠናቀቀ እንደሆነ ይናገራል። በአንድ ወቅት ኤልያስ መልካ ስለ ሙዚቃዊ ህይወቱ ሲናገር፤ የሰላም ስዩምን የጊታር አጨዋወት ስልት ኮፒ ለማድረግ በመሞከር ሙዚቃዊ ህይወቱን እንዳነጸ ለጋዜጠኛው አጫውቶታል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሰላም ስዩም ስለ ኤልያስ ችሎታና ስነምግባር አንስቶ አይጠግብም፡፡ ከኤልያስ ጋር ያለ አንድ ቀን በስልክ አውርተው እንደማያውቁ የሚናገረው ሰላም፤ “እርሱ እኔን ከሚያደንቀው መቶ እጥፍ እኔ እርሱን አደንቀዋለሁ” ነበር ምላሹ።


Read 1626 times