Saturday, 11 June 2022 18:14

አዲሱ የህክምና መመሪያ ለኤችአይቪ ታማሚዎች ተስፋን ፈንጥቋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

 በኢትዮያና ህንድ ላይ የተሞከረው አዲሱ የህክምና መመሪያ ለኤችአይቪ እና ቀንጭር (አባላዘር) ህሙማን  የተሻለ ተስፋን ፈንጥቋል ተባለ።
የዓለም ጤና ድርጅት ይፋ ያደረገውና በዋናነት በኢትዮጵያና በህንድ በሚገኙ የኤችአይቪ እና የአባላዘር በሽታ ተጠቂዎች ላይ የተሞከረው አዲሱ የኤችአይቪ እና አባላዘር ህሙማን ህክምና መመሪያ፣ ቀድሞ ከነበረው በእጥፍ ያህል የተሻለ መሆኑ በጥናት ተረጋግጧል፡፡
አዲሱ የህክምና ስትራቴጂ በኢትዮጵያ 78 በመቶ ውጤታማነት መጠን እንዳለው መጠየቁንና አሁን ያለው መደበኛ ህክምና ግን ውጤታማነቱ ከ55 በመቶ ያልዘለለ እንደሆነ ያመለከተው ሪፖርቱ፤ በተመሳሳይ በህንድ አዲሱ የህክምና መመሪያ 96 በመቶ ውጤታማ ሲሆን መደበኛው (ነባሩ) 88 በመቶ እንደነበር ጠቁሟል፡፡
በዚህም በኢትዮጵያ እጅግ የተሻለ ውጤት ማምጣቱ የተረጋገጠ ሲሆን ይህ መመሪያ በሁለቱም በሽታዎች የተጠቁ፣ መገለልና መድልኦ የደረሰባቸውንና በገቢ ማጣት እንዲሁም በተደጋጋሚ የበሽታ ማገርሸት የሚሰቃዩትን ታካሚዎች ህይወት በእጅጉ የሚያሻሽል ይሆናል ተብሏል።
በኤችአይቪ የተያዙ ሰዎች በዋናነት በአሸዋ ዝንብ ንክሻ ለሚተላለፈውና የትሮፒካል አካባቢ ሰዎችን ለሚያጠቃው አባላዘር በሽታ የመጋለጥ እድላቸው ከ100 እስከ 2,300 እጥፍ የሚበልጥ ሲሆን ሁለቱ በሽታዎች ሲደራረቡ ለህክምና አስቸጋሪ ሆነው መቆየታቸው ተጠቁሟል።
በኢትዮጵያም በትላልቅ እርሻዎች ውስጥ የሚሰሩና ለአሸዋ ዝንብ ንክሻ የተጋለጡ ወጣት ጊዜያዊ ስደተኛ ሰራተኞች ለተጓዳኝ በሽታ የመጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ መሆኑን ጥናቶች ያመለክታሉ።
አሁን በኢትዮጵያና በህንድ በትግበራ ላይ የሚገኘው የኤችአይቪ እና አባላዘር መደበኛ ህክምና የሊፕሶማል አምፎቴሪሲን ቢ የተሰኙትን ክትባቶች የሚያካትት ሲሆን አዲሱ የህክምና ክትትል ደግሞ የአፍ ውስጥ ህክምና ሜሊተፎሲን እና የሲፕሶማል አምፎቴሪሲን ቢ ጥምረት ነው ተብሏል።
አዲሱ የህክምና መመሪያ በመርፌ የሚሰጡ መድሃኒቶችን መጠቀምን የሚቀንስና ለታካሚዎች የመዳን እድሎችን በእጅጉ የሚጨምር ሲሆን መመሪያው ታካሚዎች መድሃኒት ለማግኘት ይወሰድባቸው የነበረውን 38 ቀን ወደ 14 ቀን አውርዶታልም ተብሏል።
ይህን ጥናት ያከናወኑት ትኩረት የተነፈጉ በሽታዎች ላይ የሚሰራው ዲኤንዲ ኢኒሽየቲቭ፣ አለማቀፉ ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድንና ሌሎችም አጋር ድርጅቶች መሆናቸውን ለአዲስ አድማስ የተላከው መግለጫ ያመለክታል።



Read 11729 times