Saturday, 11 June 2022 18:17

የብሔራዊ መግባባትና እርቅ ሂደቱ ለዜጎች ግልጽ መደረግ ይገባዋል ተባለ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(1 Vote)

• እርቅ የሚያስፈልገው በህዝብና ህዝብ መካከል ብቻ ሳይሆን በህዝብና መንግስት መካከልም ጭምር ነው
  • አገራዊ እርቁ እንዲሰምር ነፍጥ ታጣቂ ኃይሎች ነፍጣቸውን አውርደው ለእርቅ መቀመጥ ይገባቸል
   • ዛሬም የጥፋት እጁን ካልሰበሰበ ቡድን ጋር ምን ዓይነት እርቅ እንደሚደረግ አይገባንም
               
             በሀገራችን የተከሰቱ ቅራኔና አለመግባባቶችን በመፍታት ብሔራዊ መግባባትና ሠላምን ያሰፍናል የሚል ተስፋ የተጣለበት ብሔራዊ የምክከር ሂደቱ ለዜጎች ግልጽ መደረግ እንዳለበት የፖለቲካ ምሁራን ተናገሩ፡፡ ባለመግባባት የትጥቅ ትግል እስከማካሄድ የደረሱ ቅራኔዎችን በሽፍንፍን በሚደረግ እርቅና ስምምነት ለመፍታት መሞከሩ ዘላቂነት ያለው ውጤት አያስገኝም ተብሏል፡፡
በአማራ ክልል በደሴና ወልዲያ ከተሞች ያነጋገርናቸው ነዋሪዎችና የፖለቲካ ምሁራን እንደገለጹት፤ አገራዊ እርቁና መግባባቱ መደረግ ያለበት ሁሉም ዜጋ እኩል ተሳትፎ በሚያደርግበትና በሚስማማበት መንገድ ነው፡፡
አገራዊ እርቅና መግባባቱ በህዝብና በህዝብ መካከል ብቻ ሳይሆን በህዝብና በመንግስት መካከል ጭምር ሊሆን ይገባል የሚሉት የፖለቲካ ምሁራኑ፤ በእርቁ ውስጥ መሳተፍ ያለባቸው ተቃዋሚ ሃይሎች፣ ድምጻቸውን ያጠፉት አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያንና የፖለቲካ እስረኞችም ጭምር ናቸው ብለዋል፡፡
 አገራዊ እርቁ እንዲሰምር ነፍጥ የታጠቁ ኃይሎች ነፍጣቸውን አውርደው ለእርቅ መቀመጥ እንዳለባቸው የተናገሩት ምሁራኑ፤ ያለዚያ ግን በአገሪቱ ሠላም ለማስፈን የሚደረገው ጥረት ዘላቂ ውጤት አይኖረውም ብለዋል፡፡
 በአክሱም ዩኒቨርስቲ በፖለቲካል ሳይንስ መምህርነት ለ5 ዓመታት ያገለገሉትና በደሴ ከተማ የሚኖሩት አቶ ምስጋናው ተስፋዬ ለአዲስ አድማስ በሰጡት አስተያየት፤በአሁኑ ወቅት በመንግስትና በህዝቡ መካከል የሚታየው መሻካር ለውጪ ጠላት አመቺ ሁኔታዎችን እየፈጠረ መሆኑን ጠቁመው፣ ከሁሉም በፊት ዋናዎቹ እርቅ የሚያስፈልጋቸው አካላት መንግስትና ህዝብ ናቸው ብለዋል፡፡
ሁላችንም በግልጽ መተማመን ያለብን ጉዳይ በአገራችን የዘር ጥላቻ በሚያስደነግጥ ደረጃ እየተስፋፋ መምጣቱን ነው ያሉት አቶ ምስጋናው፤ በበርካታ የአገሪቱ አካባቢዎች መንግስት የለም ወይ እስከሚባል የሚደርሱ በደሎች በዜጎች ላይ ሲፈፀሙ ይታያል፤ ይህንን ሁኔታም መንግስት በቸልታ የሚያልፈው በመሆኑ ዜጎች በመንግስታቸው ላይ እምነት እንዲያጡ አድርጓቸዋል ብለዋል፡፡
በአገሪቱ ከተራ ብጥብጥ እስከ ህይወት መጥፋት የሚደርሱ ግጭቶች ያልተቀሰቀሱባቸው አካባቢዎች ማግኘት እንደማይቻል የተናገሩት ምሁሩ፤ በተለይም ዩኒቨርስቲዎች ለእንዲህ አይነት ችግሮች ዋነኛ መናኸሪያዎች ሆነው መቆየታቸውን አስታውሰዋል፡፡
ወደ እርቅና አገራዊ መግባባት ከማምራታችን በፊት ለግጭትና ላለመግባባቶቻችን ምክንያት የሆኑ መሰረታዊ ጉዳዮችን በጥንቃቄ መለየት እንደሚያስፈልግ የሚናገሩት አቶ ምስጋናው፤ የግጭት መንስኤዎቻችን ተለይተው ከታወቁ በኋላም በጉዳዩ ላይ ዜጎች በጋራ እንዲመክሩበትና እንዲወያዩበት ሊደረግ እንደሚገባ አስምረውበታል፡፡
አለመግባባቶችን አስወግዶ ግጭቶችን ለማስቀረት ብሔራዊ እርቅ ማውረዱ ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ መሆኑን የጠቆሙት ሌላው የፖለቲካ ምሁር ዶ/ር ታደሰ አይተነው፤ በብሔራዊ ደረጃ ውይይት ከመደረጉ በፊት ግን ህዝቡ በየአካባቢውና በየቀዬው በጉዳዩ ላይ እንዲመክርበትና  ሃሳብ እንዲሰጥበት ሊደረግ ይገባል ብለዋል፡፡ በየአካባቢው ባሉ አደረጃጀቶች ማህበረሰቡ እየተገናኘ እንዲወያይና በባህላዊ መንገድ፣ በሃይማኖት አባቶችና በአገር ሽማግሌዎች ግጭትና አለመግባባቶችን ለመፍታት የሚችልበትን መድረክ ማመቻት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
#ብሔራዊ መግባባትና እርቅ ለማድረግ ሞክረው ያልተሳካላቸው አገራትን ልምድ ስንመለከት ለውድቀታቸው መነሻ ምክንያቱ በሂደቱ ላይ የሚነሱ የግልፀኝነት ጥያቄዎች ናቸው፡፡ ስለዚህም ኮሚሽኑም ሆነ መንግስት ሂደቱን በየጊዜው ግልጽ ማድረግና በጉዳዩ ላይ ህዝቡን ማሳተፍ ይኖርባቸዋል፡፡; ብለዋል፤ ምሁሩ፡፡
የፖለቲካ ምሁሩም አክለው፤ ”በዋና ዋና ችግሮች ላይ የጋራ ስምምነትና መግባባት ላይ መድረስ ከተቻለ ባለፉት ዓመታት በአገሪቷ የተፈፀሙ ወንጀሎች ዳግም እንዳይፈጸሙ ዋና ወንጀል ፈጻሚዎችን ለህግ በማቅረብ ፍርድ እንዲያገኙ በማድረግ እንዲሁም ለተበዳዮችም ካሳ በመክፈልና ይቅርታ በመጠየቅ እርቀ ሰላም ማውረድ ይቻላል፡፡; ብለዋል፡፡
 በዚህ መንገድም ከግጭትና ከጦርነት አዙሪት በመውጣት ሁሉም ዜጋ በእኩልነት የሚኖርባት ሀገር ለመገንባት እንደሚቻል ጽኑ እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡
በደሴ ከተማ ቧንቧውሃ ቀበሌ ውስጥ ነዋሪ የሆኑት አቶ ካሳሁን አበጋዝና አቶ ደረጀ አስፋው በበኩላቸው፤ የህወኃት ታጣቂ ሃይሎች በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ላይ የፈፀሟቸው እጅግ ዘግናኝና አሰቃቂ ወንጀሎች ከህብረተሰቡ ህሊና ውስጥ ባልጠፋበትና ቁስሉ ባልሻረበት ሁኔታ እርቅና ሠላም እንፍጠር መባሉ እንዳሳዘናቸው ተናግረዋል፡፡
 ከልብ የሆነ እርቅና ሠላም ለመፍጠር አጥፊዎቹ በህግ አግባብ ተጠያቂ ሊሆኑና ተበዳይ ወገኖችም ሊካሱ ይገባል ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ፤ ቂምና ቁርሾ ይዞ የሚደረግ እርቅ ዘላቂነት የለውም ብለዋል፡፡
የዘር ጥላቻ የሰውን ህሊና ከሚሰውሩ እንደሁም የሰው ልጅ የመጨረሻ አውሬነት አፍጥጦ እንዲወጣ ከሚያደርጉ ክፉ ድርጊቶች መካከል አንዱ ነው ያሉት አቶ ካሣሁን፤ ይህንን ሰይጣናዊና  አውሬያዊ ተግባር በገዛ ወገኖቹ ላይ እንዲፈፅም ያስገደደውን የዘር ጥላቻ ሁሉም ወገን  ሊያስወግድ ይገባል ብለዋል፡፡  
#የህወኃት ታጣቂ ሃይሎች ለዳግም ጥፋትና ውድመት እየተንቀሳቀሱ ባሉበት በአሁኑ ወቅት ሊደረግ የታሰበው አገራዊ መግባባትና እርቅ በቅጡ ሊጤን ይገባዋል; ሲሉም አቶ ካሣሁን በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡

Read 10595 times Last modified on Saturday, 11 June 2022 19:45