Print this page
Saturday, 11 June 2022 18:18

ኢትዮጵያ የበርበራ ወደብ የባለቤትነት ድርሻዋን አጣች

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(3 votes)

  የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል
                                   
    ኢትዮጵያ በርበራ ወደብ ላይ የነበራትን የ19 በመቶ ድርሻ ማጣቷ ተነገረ፡፡ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጉዳዩን እያጣራሁ  ነው ብሏል፡፡


ኢትዮጵያ ከሱማሌ ላንድ ለወሰደችው የ19 በመቶ የበርበራ ወደብ ድርሻ፣ ማሟላት የሚገባትን ጉዳዮች ሳታሟላ በመቅረቷ የባለቤትነት መብቷን  ማጣቷ ተነግሯል። የሶማሌ ላንድ የገንዘብ ሚኒስትር እንዳስታወቁት፤ የኢትዮጵያ መንግስት ማሟላት የሚገባውን የባለቤትነት መስፈርቶች በጊዜው ባለማሟላቱና ለወደብ ግንባታ የሚጠበቅበትን የገንዘብ መዋጮ ለመክፈል ባለመቻሉ የባለቤትነት መብቱን ተነጥቋል ብለዋል፡፡
የበርበራ ወደብ 51 በመቶ ድርሻ በአረብ ኢምሬትስ አለም አቀፍ የሎጀስቲክ ተቋም ዲፒ ወርልድ፣ 30 በመቶ ደግሞ በራሷ በባለቤቱ በሶማሌላንድ የተያዘ ሲሆን ቀሪው 19 በመቶ ደግሞ በኢትዮጵያ ድርሻ ነበር፡፡ ይህንኑ ተከትሎም ኢትዮጵያ መርከቦቿን ማሰማራት ጀምራ ጊቤ የተባለችው የጭነት መርከብ ከወደቡ ጭነት ማራገፏ መገለፁ ይታወሳል ከዚህ በተጨማሪም የወደቡ የመጀመሪያ ዙር ማስፋፊያ የኮንቴይነር ተርሚናል የኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት በተገኙበት ከወራት በፊት በይፋ ተመርቆ ስራ የጀመረ ሲሆን የማስፋፊያ ፕሮጀክቱን 500 ሺህ ኮንቲነሮችን የመያዝ አቅም ያለውና በዓመት 1 ሚ. ኮንቲነሮችን ማስተናገድ የሚችል እንደሆነ ይታወቃል፡፡
አሁን አገሪቱ የወደብ ድርሻዋን እንድታጣ ስለተደረገበት ጉዳይ ምንነት  እያጣራ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አሰታውቋል፡፡
ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር መጨረሻ ከ20 ዓመታት በኋላ ጊቤ መርከብ የመጀመሪያ ጉዞዋን አድርጋ በርበራ ወደብ 11 ሺ 200 ሜትረክ ቶን የፍጆታ ዕቃ ያራገፈች ሲሆን በወሩ ሸበሌ የተባለችው መርከብ ለሁለተኛ ጊዜ ጭነቷን  አራግፋለች በነሐሴ ወር አጋማሽ ደግሞ ጊቤ 15 ሺ ሜትሪክ ቶን ጭነት በ-በርበራ ወደብ ማራገፏ ይታወሳል።

Read 11990 times