Sunday, 12 June 2022 00:00

ይድረስ ለሼህ ሙሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ

Written by  (ከአብዱራህማን አህመዲን፤ የቀድሞ የፓርላማ አባል)
Rate this item
(1 Vote)

- ክፍል 2:-
                      የሚድሮክ ነገር “ትሻልን ሰድጄ ትብስን አመጣሁ” ሆኖብናል!


            ውድ አንባብያን! ባለፈው ሳምንት በወጣው አዲስ አድማስ ጋዜጣ፣ በዚሁ ርእስ ክፍል አንድ ጽሑፍ ለህትመት መብቃቱ ይታወቃል። ለማስታወስ ያህል፤ ሳምንት በቀረበው ጽሁፍ የሚድሮክ ኢንቨስትመንትና የባለቤቱ የሼህ ሙሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ ለሀገር የነበራቸው አስተዋጽዖ ምን እንደሆነ፣ እንዲሁም እኔ የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ ማን እንደሆንኩና የደረሰብኝ በደል ምን እንደሆነ የሚያስገነዝብ ነበር፡፡
በዚህ በዛሬው በክፍል ሁለት ጽሁፍ ትኩረት የማደርገው በቅድሚያ በአቶ ጀማል ዘመን የተከናወኑ በጎ ጅምሮችን በማውሳት ይሆናል፡፡ በመቀጠልም በእኔን መሰል ግፉአን የሚድሮክ ሰራተኞች ዙሪያ አተኩራለሁ። በአቶ ጀማል አህመድ ፊታውራሪነት የሚዘወረው አዲሱ የሚድሮክ አመራር እኔን ብቻ ሳይሆን ሚድሮክን ለረጅም ዓመታት ያገለገሉ (Memory of MIDROC ሊባሉ የሚችሉ) በርካታዎችን በሁለት መስመር ደብዳቤ እንደ አሮጌ ቁና ወርውሯቸው በረንዳ አዳሪና ለማኝ አድርጓቸዋል፡፡ ይህንን ጽሁፍ እንድጽፍ ዋነኛ ገፊ ምክንያት የሆነኝ በእኔ ላይ የደረሰው በደል ብቻ ሳይሆን በእነዚህ የስራ ባልደረቦቼ ላይ የደረሰው ግፍና መከራ ስለሆነ፤ በዚህ በክፍል ሁለት ጽሁፌ ማሳያ የሚሆኑ መረጃዎችን ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡
ከዚያ በፊት አንድ ማስታወሻ ላቅርብ። ባለፈው ሳምንት የወጣው ጽሑፍ በሶሻል ሚዲያ ሲዘዋወር የተሰጡ አንዳንድ አስተያየቶችን ተመልክቻለሁ፡፡ ለመንደርደሪያ ይሆን ዘንድ ከእነርሱ ብነሳ የተሻለ ነው ብዬ አሰብኩ፡፡ “ባልቻ አባነፍሶ ነኝ” የሚሉ የፌስቡክ አስተያየት ሰጪ እንዲህ ብለዋል፤ “…የሚድሮክ ኢቨስትመንት ግሩፕ ካምፓኒ ሥራ አስኪያጅ አቶ ጀማል፣ በፈለገው መንገድ የሚያዛቸው ወይም እጅ የሚጠመዝዛቸው ግለሰብ እንዳልሆኑና የትኛውም ጥሩ የሚሰራ ሀላፊ ወይም ሰራተኛ በስራው በብቃቱ በታማኝነቱ እንጂ በእምነቱ በብሄሩ በዝምድና በጓደኝነት እንደማያምኑ… ድርጅቱም ቢሆን ከመዘጋት ተርፎ… ብዙ ቢለዮኖች ያተረፈው ባሁኑ ስራ አስፈፃሚ እንጂ ባንተ ዘመን በነበረው ስራ አስፈፃሚ እንዳልሆነ… ሀገር ያወቀው ፀሀይ የሞቀው እውነታ ነው” ብለዋል፡፡
እንዲህ ያለው የፌስቡክ ጨዋታ በወንዝ ልጅነት የተሰጠ አስተያየት ከመሆን የዘለለ ትርጉምም ፋይዳም የለውም፡፡ ባለፈው ሳምንትም እንዴት ወደ ሚድሮክ እንደመጣሁ ገልጨዋለሁ፡፡ ለማንኛውም እኔ ወደ ሚድሮክ የገባሁት በዘርም በሃይማኖትም ሳይሆን ባለኝ እውቀት፣ ልምድና የትምህርት ዝግጅት መሆኑ ግንዛቤ ቢወሰድ መልካም ነው፡፡ በመሰረቱ እኔም አቶ ጀማል ኃላፊነትን ከወሰዱ ወዲህ የተሰራ ስራ የለም አላልኩም፡፡ እንዲያውም ይህንን ጽሑፍ የምጀምረው በአቶ ጀማል የአመራር ዘመን የተሰሩ በጎ ተግባራትን በማውሳት ነው፡፡ የጽሁፌንም ሚዛን ለመጠበቅ የሚጠቅም ስለሆነ ወደዚያው እናምራ…
ክቡር ሆይ!
በአቶ ጀማል የአመራር ዘመን ከተሰሩ ተግባራት ውስጥ ለማሳያ ይሆን ዘንድ ጠቅለል ያሉና ዋና ዋና ናቸው ብዬ ያሰብኳቸውን ብቻ ለአብነት ያህል ለመጥቀስ እወዳለሁ። በቀዳሚነት የማነሳው አቶ ጀማል ይመሩት የነበረው ሆራይዘን ግሩፕ በ2012 ዓ.ም አጋማሽ አካባቢ የሚድሮክን የአመራር ሁኔታ እንዲሁም የኦፕሬሽንና የፋይናንስ አቋም በባለሙያ ቡድን እንዲጠና በማድረግ የተካሄደው የአወቃቀር ለውጥ፤ ምርትንና ግብይትን የተሳለጠ እንዲሆን ከማድረጉም በላይ የእርሻም ሆነ የኢንዱስትሪ ምርቶች በአጭር የግብይት ሰንሰለት ለተጠቃሚው ለማድረስ ማስቻሉን ማስተዋል ይቻላል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ከሚድሮክ ኩባንያዎች እንዲሁም ከሌሎች አምራቾች የእርሻ ማሳና ፋብሪካ የተመረቱ ምርቶችን በኩዊንስ ሱፐር ማርኬት አማካይነት በተመጣጣኝ ዋጋ ለደንበኞች ለማቅረብ የተደረገው ጥረት በአዲስ አበባ ከተማ በተለይም በተወሰኑ መሰረታዊ ሊባሉ በሚችሉ ምርቶች ላይ የዋጋ መረጋጋት እንዲኖር አስተዋጽዖ ነበረው፡፡ ይህ ሁኔታ እንደ ትልቅ ስኬት የሚታይ ነው፡፡ ምክንያቱም ህዝቡ በሚድሮክ ላይ ከሚያቀርባቸው ቅሬታዎች አንዱ፣ የሚድሮክ ምርቶች ተጠቃሚ መሆን አልቻልንም የሚል በመሆኑ ለዚህ ቅሬታ ምላሽ የሚሰጥ ነው፡፡
ሌላው የአቶ ጀማል በጎ ተግባር ለየኩባንያው ስራ አስኪያጆች የተሰጠው የመወሰን ነፃነት ነው፡፡ እንደሚታወቀው በዶ/ር አረጋ ዘመን የየኩባንያው ሥራ አስኪያጆች በራስ በመተማመን ስሜት ስራቸውን መስራት ትተው በየእለቱ ወደ ዶ/ር አረጋ ቢሮ በመሄድ ከእርሳቸው የሚሰጥን ቡራኬና መመሪያ አንጠልጥለው በመምጣት ያልገባቸውን ስራ ለመስራት፣ ላይ ታች በማለት ሲመናተሉ ይታዩ ነበር፡፡ ዶ/ር አረጋ ኩባንያዎቹን የሚመሩ ዋና ሥራ አስኪያጆችን የሾሙ ቢሆንም፤ “ዋና ሥራ አስኪያጅ” ተብለው የተቀመጡት ሰዎች በስማቸው የንግድ ፈቃድ ከማውጣት የዘለለ የመወሰን ስልጣን አልነበራቸውም፡፡ የእያንዳንዱን ኩባንያ እቅድ የሚያቅዱት፣ ከዘበኛ ጀምሮ ሰራተኛ የሚቀጥሩና የሚያሰናብቱት፣ አቅጣጫ የሚሰጡት፣ ስለ እያንዳንዱ ነገር ውሳኔ የሚወስኑት… ራሳቸው ዶ/ር አረጋ ነበሩ፡፡ በዚህ ረገድ ሌላው በጥቅል የሚታይ የአቶ ጀማል ዘመን ትሩፋት፣ የተለያዩ ኩባንያዎች መሪዎች ስራቸውን ራሳቸውን ችለው እንዲሰሩ አንጻራዊ ነፃነት የተሰጣቸው መሆኑ ነው፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ለሰራተኞች የተደረገው የደመወዝ ማስተካከያም የሚበረታታ ነው፡፡
የኩባንያዎችን አትራፊነት በተመለከተ የተሰራውም ስራ በበጎነት የሚነሳ ነው። ቀደም ባሉት ዓመታት በዶ/ር አረጋ ስር የነበሩ ኩባንያዎችን ዓመታዊ የአፈጻጸም ሪፖርት ስንመለከት፣ ከሃያ ስድስቱ ኩባንያዎች ብዙዎቹ መዘጋት የሚገባቸው አክሳሪዎች ነበሩ። አንዳንዶቹ በሚሊዮን የሚቆጠር የባንክ ብድር እንዳለባቸውም እንሰማ ነበር፡፡ እነዚያን ኩባንያዎች አቶ ጀማል ከተረከቧቸው በኋላ በርካታ ለውጦች ታይተዋል፡፡ እንደ ኤልፎራ ያሉ በካፒታል ድጎማ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ፣ ለኪሳራ የተዳረጉ ኩባንያዎች ዛሬ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ትርፍ ማስመዝገባቸውን እየሰማን ነው፡፡
በአቶ ጀማል ዘመን እነዚህና ሌሎችም መለስተኛ የሆኑ በበጎነት የሚጠቀሱ ጥቅል ስኬቶች የተመዘገቡ ቢሆንም በርካታ ጉድለቶችና ድክመቶች እንዳሉበት መላው በሚድሮክ ግሩፕ የሚሰራ ሰራተኛ የሚያውቀው ሀቅ ነው፡፡ እነዚህንም ደካማ ጎኖችና ከላይ የተጠቀሱትም በጎ ተግባራት ሊሳኩ የቻሉበትን ምክንያት እንደሚከተለው በአጭር በአጭሩ ለማሳየት እሞክራለሁ፡፡
በሌሎች ሰራተኞች ላይ የደረሰ በደል
ክቡር ሆይ!
በዶ/ር አረጋ ይመሩ የነበሩ ኩባንያዎችን አቶ ጀማል ከተረከቡበት ጊዜ ጀምሮ አቶ ጀማል በሰጡት ግልጽ የሆነ መመሪያ መሰረት አሁን በየኩባንያው ያለው የሚድሮክ አመራር በዶ/ር አረጋ ዘመን የተቀጠሩ ሰራተኞችን የማባረር ግብ አስቀምጦ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡ በዚህም የማባረር ዘመቻ ብዙ እኔን መሰል ሰዎች በግፍ ተሰናብተዋል፡፡ ነገሩ የደረሰው በእኔ ላይ ብቻም አይደለም፡፡ እኔ ብቻ ብሆን ኖሮ ይህንን ጽሁፍ ለማዘጋጀት ጊዜየንም ጉልበቴንም አላባክንም ነበር። ብዙዎች ተጎድተዋል። በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰራተኞች ተባረዋል፡፡ በመባረራቸው በርካታ ቤተሰብ ተበትኗል። በረንዳ አዳሪ ሆኗል። ስራ አጥተው ብቻቸውን እያወሩ በየጎዳናው ሲንከራተቱ የሞቱ አሉ፡፡ ለማሳያ ይሆን ዘንድ ከሦስት ኩባንያዎች ብቻ የተባረሩ አንድ ከፍተኛ ኃላፊ፣ አንድ ከመካከለኛ ደረጃ እና አንድ ከበታች ሰራተኛ በምሳሌነት ላቅርብ፡፡
ከከፍተኛ አመራር የዴይላይትን ጉዳይ እንጥቀስ… ሣሙኤል አረጋይ ይባላል። ሲቀጠር ወጣት መሃንዲስ ነበር፡፡ የተቀጠረው በዋናው መ/ቤት በፕሮጄክት መሐንዲስነት ነበር። በአልፋልፋ ፕሮጄክት ከውጭ ከመጡ መሐንዲሶች ጋር በመስራት ሙያውን በማዳበሩ በኤልፎራ ዋና ቢሮ የቴክኒክ ክፍል ተዛወረ፡፡ በዚያም የተሻለ ስራ በመስራቱ ወደ ዴይላይት ኩባንያ ተዛውሮ የቴክኒክ ክፍል ስራ አስኪያጅ ሆነ፡፡ ከዓመታት በኋላ የዴይላይት ዋና ስራ አስኪያጅ ሆኖ በተሾመ የአንድ ወር ደመወዝ እንኳ ሳይበላ ዶ/ር አረጋ ተነስተው አቶ ጀማል ተሾሙ። ትንሽ ጊዜ እንደሰራ ሳሙኤል የዓመት ፈቃድ ውጣ ተባለ፡፡ ምክንያቱ ሳይነገረው በዚያው ተባረሃል ተባለ። ከ10 ዓመት በላይ ከሰራበት ሚድሮክ ምንም ዓይነት ጥቅማ ጥቅም ሳይሰጠው በዚያው ወጥቶ እንዲቀር ተደርጓል፡፡ የሁዳ ሪል እስቴትን እንጨምር፡፡ የሁዳ ሪል ስቴት ስራ አስኪያጅ የነበረውና የወልዲያን ስታድየም የገነባው ወጣት መሀንዲስ ዮናስ ብርሃነ፣ እቢሮው ቁጭ እንዳለ የግል ንብረቱን እንኳ ሳያነሳ፣ “የመኪናና የቢሮ ቁልፍ ቁጭ አድርግ” ብለው በእግሩ ነው ከግቢው ያስወጡት...
ወደ መካከለኛ ማኔጅመንት በመሄድ ከኤልፎራ የአቶ ቢንያም ዘነበን ጉዳይ እናንሳ፡፡ ቢንያም እድሜው በ30ዎቹ መጨረሻ አካባቢ ነው፡፡ በእርሻና ቢዝነስ ማኔጅመንት ተምሯል። በሙያው ተወዳድሮ በኤልፎራ የተቀጠረው የዛሬ 10 ዓመት ገደማ ሲሆን፤ ሐዋሳ አጠገብ በሚገኘው የሻሎ እርሻ የአልፋአልፋን መኖና አትክልት በስፕሪንክለርና ድሪፕ (ጠብታ) የመስኖ ውሃ ለማልማት ነበር የተቀጠረው። አልፋልፋን በ25 ሄክታርና አትክልት 25 ሄክታር መሬት ላይ በሙከራ መልክ ጀመረው። አልፋልፋ ለሀገራችን ብዙ የማይታወቅ ቢሆንም ቢንያም አቅሙንና ችሎታውን ተጠቅሞ ባሳየው ጥረት በሀዋሳ ከተማ አካባቢ ለወተትና የወተት ተዋጽዖ አምራቾች ያመረተውን መኖ በማቅረብ አልፋልፋን አስተዋውቋል፡፡ የመኖውን ምርታማነት ለማሳደግም ችሏል፡፡ በዚህም ጥረቱ የሻሎ እና የመልጌ ወንዶ እርሻዎች ስራ አስኪያጅ ለመሆን በቅቷል፡፡
ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ በአካባቢው በነበረው የወጣቶች እንቅስቃሴ ቢንያም የሻሎ እና የመልጌ ወንዶ እርሻዎች እንዳይወረሩ ከፍተኛ ጥረት አድርጓል፡፡ በዚህም ወቅት ጥይት ተተኩሶበታል፣ በሽጉጥ አስፈራርተውታል፣ መኪናውን ለማቃጠል ተሞክሯል፣… ሁሉንም ተቋቁሞ የኩባንያውን መሬት ከወረራ አድኗል። የአቶ ጀማል ማኔጅመንት ከመጣ ወዲህም 3,000 ሄክታር መሬት ላይ የተለያየ የአገዳና የቅባት እህሎች እንዲሁም የተለያዩ አትክልቶች እንዲለሙ በማድረግ፣ ጠንክሮ ሰርቶ በማሰራት ባስገኘው ውጤት ኤልፎራም አቶ ቢንያምም የፌዴራል ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር፣ የግብርና ሚኒስቴር ሀላፊዎችና ባሉበትና አቶ ጀማል ራሱ በተገኘበት ከዞንና ወረዳ ኢንቨስትመንት የእውቅና ሽልማት ተሰጥቷቸዋል፡፡ ኤልፎራም ቢንያም ላስገኘው ውጤት የደመወዝ ማሻሻያና የ10 ሺህ ብር የቤት አበል በየወሩ እንዲከፈለው ተደርጓል፡፡
በዚህ ሽልማት የተበረታታው ቢንያም ስራውን እየሰራ ሳለ ከአዲስ አበባ ዋና መስሪያ ቤት አዳዲስ ሰዎች እየተቀጠሩ ይላኩ ጀመር። ችግሩ መቀጠራቸው አልነበረም። አዲሶቹ በከፍተኛ ደመወዝ ሲቀጠሩ እርሻው ላይ ለረጅም ዓመታት የሰሩ ነባር ሰራተኞች በተመሳሳይ ስራ መደብ ላይ እየሰሩ ደመወዛቸው ከነሱ በታች እንዲሆን በመደረጉ በሰራተኛው መሀል ልዩነት ፈጠረ። “ይህ እንዲስተካከል ብጠይቅ ሰሚ ጠፋ፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ስራችንን በተገቢው ህጋዊ መንገድ እንዳንሰራ እንቅፋቱ በዛ፡፡ ሰውን በውጤት ከመመዘን ይልቅ የቤተሰብ ሽፋን ተጀመረ” ይላል ቢንያም፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ “የኤልፎራ ስራ አስኪያጅ መጣና የሐዋሳውን የእኔን ማኔጅመንት ሰበሰበን፡፡ ምን ምን ችግሮች እንዳጋጠሙህ ተናገር ስባል ከአዲስ አበባ እየቀጠራችሁ የምትልኳቸው ሰዎች “እኔ የዋና ስራ አስኪያጁ የሚስቱ ወንድም ነኝ፣ እኔ የአስተዳደሩ ወንድም ነኝ፣ እኔ የእከሌ ዘመድ ነኝ…” እያሉ ስራ አይሰሩም፡፡ በዚያ ላይ በአዲሶቹና በነባሩ ሰራተኛ መካከል የተፈጠረው የደመወዝ ልዩነት ስራ ሊያሰራ አልቻለም… በማለት እዚያው ስብሰባ ላይ ተናገርኩ፡፡ ዋና ስራ አስኪያጁ በዚህ ደስተኛ አልሆነም፡፡ “እኛ ከምናባርርህ ራስህ መልቀቂያ አቅርብ አለኝ” አስር ዓመት ያገለገልኩበት የስራ ልምድ ማስረጃ እንዳይበላሽብኝ በመፍራት 2 መስመር ጽፌ መልቀቂያ አቀረብኩኝ፡፡ አስር ዓመት ከፍተኛ መስዋዕትነት የከፈልኩበትን መ/ቤት ለፈጣሪ ሰጥቼ ወጣሁ፡፡ ጥቅማ ጥቅሜን እንዲሁም ሌላ ስራ እንዳልፈልግም የስራ ልምዴን ሳይሰጡኝ እነሆ ስድስት ወራት ተቆጠሩ…” ይላል ቢንያም፡፡
ምስክርነትም የሚጸናው በሦስት ስለሆነ ወደ ዝቅተኛ የስራ መደብ እንውረድና አንድ ምሳሌ ላቅርብ፡፡ … አንድ ቀን እቢሮዬ ቁጭ እንዳልኩ በማላውቀው ስልክ ተደወለልኝ። አነሳሁት፡፡ ከወዲያኛው ጫፍ የእንባ ሳግ የተናነቃት ሴት ሰላምታ አቀረበችልኝ፡፡ “ማን ልበል” አልኳት፡፡ “አንተ አታውቀኝም፡፡ እኔ አውቅሃለሁ። የዶ/ር አረጋ የእህታቸው ልጅ ነኝ… “እከሊት” እባላለሁ፡፡ በ… ኩባንያ ነው የምሰራው…” እያለች ራሷን በማስተዋወቅ የደረሰባትን በደል ነገረቺኝ፡፡ የዚያች እህት በደል ሲጠቃለል፤ የዶ/ር አረጋ ይርዳው ዘመድ በመሆኗ ሰበብ እየተፈለገ ከስቶር ክለርክነት ስራዋ ልትባረር መሆኑን ነው የነገረቺኝ፡፡ ይህቺ ሴት በዶ/ር አረጋ ዘመን የስቶር ክለርክ ከመሆን የዘለለ ዶ/ር አረጋ ዘወር ብለውም አይተዋት አያውቁም፡፡ የእህታቸው ልጅ ብትሆንም የተደረገላት ልዩ ነገር አልነበረም። ዶ/ር አረጋ ቤት እንኳ ሄዳ አታውቅም፡፡ በቂመኛው በአዲሱ አመራር ደግሞ የዶ/ር አረጋ ዘመድ በመሆኗ የተባራሪነት ቀስት ተነጣጠረባት። አረጋግቼ ስልኬን ዘጋሁ፡፡ አሁን በምን ሁኔታ ላይ እንዳለች አላውቅም። ተመሳሳይ ማስፈራራቶች በተለያየ ኩባንያ ውስጥ በሚሰሩ ሰዎች ላይ መድረሱን ሰምቻለሁ፡፡
ክቡር ሆይ!
“ነገር ቢበዛ በአህያ አይጫንም” እንዲሉ አበው፣ ለበረካ ካለው ይኸው በቃል። በአጠቃላይ አቶ ጀማል የሚድሮክን ስልጣን ከጨበጠበት እለት ጀምሮ ባለፈው አንድ ዓመት ከኤልፎራ፣ ከዴይላይት፣ ከሚድሮክ ጎልድ፣ ከአንሊሚትድ ፓኬጂንግ፣ ከማኔጅመንት ሊደርሺፕ አገልግሎት፣ ከዋንዛ፣ ከትረስት፣ ከኩዊንስ፣... እና ከሌሎችም ኩባንያዎች በሺዎች የሚቆጠሩ ሰራተኞች ተባረዋል። የሚገርመው ነገር “በዘመቻ ጥረግ” የሚባረሩት ቀደም ሲል ዶ/ር አረጋ ይመሯቸው በነበሩ ኩባንያዎች ይሰሩ የነበሩ ሰራተኞች መሆናቸው ነው። አቶ ጀማል ይመሯቸው በነበሩ በአግሪ ሴፍት እና በሆራይዘን ግሩፕ ይሰሩ የነበሩ ሰራተኞች ዶ/ር አረጋ ይመሯቸው ወደነበሩ ኩባንያዎች በሹመት ከመዛወራቸው ውጪ መባረራቸውን አልሰማሁም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ እነዚህን የሚባረሩ ሰራተኞች እንዲተኩ እየተደረጉ ያሉት ከቀድሞው ሜቴክ እና ከስኳር ኮርፖሬሽን በመጡ ሰዎች መሆኑ፤ አቶ ጀማል የማንን ኔትዎርክ እያጠናከሩ እንደሆነ ሌላው አጠያያቂ ነገር ነው፡፡
አቶ ጀማል ከላይ የተገለጹትንና መሰል በጎ ቁም ነገሮችን ያከናወኑ ቢሆንም፣ በተለይም ከምርታማነት ጋር ተያይዘው የተገኙት ውጤቶች የአቶ ጀማል የአመራር ብቃት ያመጣቸው ተደርገው የሚወሰዱ አይደሉም። እዚህ ላይ መነሳት የሚገባው መሰረታዊ ጥያቄ “ተጨማሪ የፋይናንስ ድጋፍ (Capital Injection) ሳይደረግ እነዚህ የምርታማነት ለውጦች እንዴት ሊመዘገቡ ቻሉ?” የሚለው ነው፡፡ ቀደም ባሉት ዓመታት ሰራተኛው እንዳይሰራ ነፃነቱን አጥቶ፣ በተማከለ አሰራር እግር ተወርች ተቀፍድዶ ነበር፡፡ ይህ እንዲነሳለት ተደጋጋሚ ጥያቄ ያቀርብ ነበር፡፡ ብዙዎቻችን የውስጥ ትግልም እናደርግ ነበር፡፡ አሁንም እንደ ኤልፎራ ባሉ እርሻዎች መሬቱ ሳይለወጥ ኩባንያውን ለተሸላሚነት ያበቃው ሰራተኛው “ከሰራሁ አገኛለሁ” በሚል በለውጥ መንፈስ በመንቀሳቀሱ ነው እንጂ አቶ ጀማል የተለየ ተዓምር ስለፈጠሩ አለመሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡
አበው “ጅብ ያነክስ እስኪነክስ” እንዲሉ፣ አቶ ጀማል የሚድሮክን ኦፕሬሽንና ፋይናንስ በባለሙያ አስጠንቶ ለእርስዎ በማቅረብ የአወቃቀር ለውጥ ፕሮፖዛል ያቀረበው እውነተኛ ጥልቅ ተሃድሶ በማድረግ የሰራተኛውንና የድርጅቶቹን የረጅም ጊዜ ጥያቄ ለመመለስ ሳይሆን፣ እነ ዶ/ር አረጋን ከስልጣን ለማስነሳት 7 ዓመታት የፈጀ ትግል ከግቡ በማድረስ በሚድሮክ ላይ ለመንገስ መሆኑ የገባን፣ አቶ ጀማል የእነ ዶ/ር አረጋን አሻራ የማጥፋት እርምጃዎች ሲወስዱና በእነ ዶ/ር አረጋ ዘመን የተቀጠሩ ሰራተኞችን አንድ በአንድ ማባረር ሲጀምሩ ነው፡፡
ከላይ የጠቀስኳትን የዶ/ር አረጋን የእህት ልጅ ለምን ሊያባርሯት እንደፈለጉ አቶ ሁሴን አህመድ የተባሉ (አሁን ምክትል ሲኢኦ ሆነዋል) በስልክ ሳናግራቸው፤ “አብዱራህማን እኔ ነገሩን አቀዝቅዤ ይዤው ነው እንጂ አቶ ጀማል እኮ በእነ ዶ/ር አረጋ የተቀጠሩ ሰራተኞችን በሙሉ ጠርገህ አስወጣ ነው ያለኝ” አሉኝ፡፡ ይህንን ጠርጎ የማባረር ዘመቻ በተመለከተ አቶ ጀማል በአንድ ስብሰባ ላይ ሲናገሩ የሰማሁትን ልጨምር፡፡ በአንድ ስብሰባ የኤልፎራ ዋና ስራ አስኪያጅ የነበሩ ሰው፤ “የኤልፎራ የሰው ኃይል አስር በመቶ (10%) በአዲስ ተቀይሯል…” የሚል ሪፖርት ያቀርባሉ፡፡ አቶ ጀማልም፤ “ሰባ በመቶ (70%) ሳትቀይር ነው ይሄን ስራ ሰራሁ ብለህ ሪፖርት የምታቀርበው?” ብለው እንደገሰጿቸው አስታውሳለሁ፡፡
ክቡር ሆይ!
“በምንም ተዓምር ሰራተኛ አይባረር” የሚል ገልቱ አመለካከት የለኝም፡፡ ይሁን እንጂ ሰራተኛ “ጠርገህ አውጣ” በሚል ዘመቻ ሊባረር አይገባውም፡፡ የአፄ ኃ/ስላሴ ቢሮክራሲ በደርግ፣ የደርግ ቢሮክራሲ በኢህአዴግ፣… እየተጠረገ እንደወጣውና ሀገሪቱን ትልቅ ዋጋ እንዳስከፈላት ሁሉ፤ በሚድሮክ አዲስ ሥራ አስፈጻሚ (ሲኢኦ) በተሾመ ቁጥር እንደ መንግስት መስሪያ ቤት ቢሮክራሲው ሊታመስና ሰራተኛው ሊንገላታ አይገባውም፡፡
ሰራተኛ የሚባረረው በህግ መሰረት መሆን አለበት፡፡ እዚህ ላይ ትልቁ ችግር በሚድሮክ ውስጥ ኩባንያ የሚመሩ የማኔጅመንት አባላት የሚመሩበትም ሆነ የሚተዳደሩበት ህግና መመሪያ የሌለ መሆኑ ነው፡፡ አሁን በየኩባንያው የተገኙትን ለውጦች ያመጡት አቶ ጀማል ሳይሆኑ በየኩባንያው ያሉ የማኔጅመንት አባላት ሌት ተቀን ጠንክረው ስለሰሩና ለሰራተኛው ምቹ ሁኔታ ፈጥረው እንዲሰራ ስላደረጉት ነው። እነዚህ የማኔጅመንት አባላት አንዲት ስህተት ሲገኝባቸው ያለ ምንም ካሳና የስራ መፈለጊያ በሁለት መስመር ደብዳቤ ተባረሃል ማለት፣ ከህግም ከሞራልም አኳያ ተገቢ ነው ብዬ አላምንም፡፡
የአቶ ጀማል የሚድሮክ አስተዳደር፤ በተለይም ለማኔጅመንቱ (በኮርፖሬት ደረጃም ይሁን በየኩባንያው ደረጃ) “ትሻልን ሰድጄ ትብስን አመጣሁ” እንዲሉ ሆኖበታል። በመሆኑም የሚድሮክ የበላይ አመራርና ሊቀ መንበራችን የሆኑት ሼህ ሙሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ አላህ ረጅም እድሜ ሰጥቷቸው፣ ወደ እናት ሀገራቸው መጥተው አንድ ቀን ከኩባንያዎቻቸው ማኔጅመንት አባላትና ሰራተኞች ጋር እየበሉና እየጠቱ እንደሚመካከሩ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ እስከዚያው ድረስ እኔ በበኩሌ ሚድሮክን ዘላለማዊ ተቋም ለማድረግ ምን ምን መደረግ እንዳለበት ያለኝን አስተያየት በቀጣይ የማቀርብ ይሆናል፡፡
ክቡር ሆይ!
በዚህ በዛሬው መጣጥፍ እስከ አሁን ያየነው በሰራተኞች ላይ የደረሰውን በደል ነው፡፡ ቀጥሎ ደግሞ በኢንቨስትመንቱ ላይ የደረሰውን ጉዳት አለፍ አለፍ እያልን እናያለን፡፡ ቀደም ባሉት ዓመታት ዶ/ር አረጋ በሚመሯቸው ኩባንያዎች ብቻ ሳይሆን አቶ ጀማል ይመሯቸው በነበሩ ፕሮጄክቶችም በሚወስዷቸው ያልተጠኑና ከህግ አንጻር ያልታዩ እርምጃዎች ምክንያት አንዳንድ ፕሮጄክቶች ወይ መክነዋል አሊያም ቁሞ-ቀር ሆነዋል፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠር ብር ባክኗል፡፡
የሳዑዲ ስታር ፕሮጄክት እንዳልሆኑ መሆንና የገጠመውን ውድቀት ለማካካስ፣ ከቀረጥ ነፃ የገባን ትራክተር በማከራየት በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ብር የመንግስት እዳ፣ የሸገር ዳቦ ፕሮጄክት ኪሳራና ዱቄት በመሸጥ ኪሳራን ለማካካስ የተደረገው ስህተትን በስህተት የማረም መንገድ፣… የመሳሰሉትን የአቶ ጀማል አመራር የፈጠራቸውን የሚድሮክን ውድቀቶች አንድ በአንድ እያነሳን እናያለን። በመጨረሻም ምክረ ሃሳቦችን አቀርባለሁ። (የጽሁፌ የመጨረሻው ክፍል 3 ሣምንት ይቀጥላል)
የምንጊዜም አክባሪዎ!
አብዱራህማን አህመዲን፤
ኢሜይል፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ
የኮሙኒኬሽንና ፕሮሞሽን ኮርፖሬት ዳይሬክተር (የነበርኩ)

Read 3685 times