Monday, 13 June 2022 00:00

ለሐሜት መንሾካሾክ ድሮ ቀረ? መረቡ ግን ሰፍቷል።

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ፖለቲከኞች፣ የሕዝብ አገልጋይ ናቸው። “ለሕዝባቸው” እና “ለአገራቸው”፣ አዳዲስ የወሬና የሐሜት እድል መፍጠር ነው - የነገረኛ ፖለቲከኞች ስራ። የሕዝባቸውን የወሬና የሐሜት ፍላጎት ማርካት ነው - አገልጋይነታቸው።
              
                ዘመኑ ፍሬያማ ነው። መወዛገቢያ ጉዳዮችን ወይም ሰበቦችን በየእለቱ ይፈበርክልናል። አዳዲስ ባንጨምርባቸው እንኳ፣ ነባሮቹ የውዝግብ ሰበቦች ከበቂ በላይ ናቸው። ቢሆንም ግን፣ የብዛታቸው ያህል፣ እንደገና ሳይባዙ አይውሉም፤ አያድሩም። እድሜ ለነገረኛ ፖለቲከኞችና ለቆስቋሽ ተናጋሪዎች።
የመወዛገቢያ ዘዴዎችና የማጋጋያ መንገዶችም፣ ለቁጥር ለስፍር ያስቸግራሉ። ፖለቲከኞች የውስጥ ስሜታቸውን በሌላ ተቀናቃኝ ላይ የሚያራግፉበት፣ “ተንፈስ የሚሉበት” ከሆነ ግን፣ የቻሉትን ያህል ውዝግብ ቢፈጥሩ ምን ችግር አለው? ካልተወዛገቡ ማን ያስታውሳቸዋል?
እንዲያውም፣ አንዴ ተነታርከው ከተረጋጉ፤ “ስራቸውን ረስተዋል” ማለት ነው። በየእለቱ የውዝግብ አጀንዳ፣ ከየትም ከየትም ፈልገው ማምጣት አለባቸው። “ለሕዝባቸው” እና “ለአገራቸው”፣ አዳዲስ የወሬና የሐሜት እድል መፍጠር ነው - የነገረኛ ፖለቲከኞች ስራ። የሕዝባቸውን የወሬና የሐሜት ፍላጎት ማርካት ነው - አገልጋይነታቸው።
ብዙዎቹ ፖለቲከኞችና ቆስቋሽ ተናጋሪዎች፣ “ዝነኛና ታዋቂ” ከሆኑ በኋላ፣ እንዳሻቸው ሕዝብን የሚያንጋጉ መሪዎች የሆኑ ይመስላቸዋል። አዎ፣ ያንጋጋሉ። ገደል ያስገባሉ። ነገር ግን፣ የዝናቸውና የታዋቂነታቸው ያህል፣ የአገልጋይነት ሸክማቸው ይጨምራል።
ብዙ ሰው የሚያውቃቸው ዝነኛ ፖለቲከኞች፣ የሕዝብን የሐሜት ፍላጎት በብዛት የማርካት እዳ ይኖርባቸዋል። ለብዙ ሰው የሚዳረስ የወሬና የሐሜት እድል ለመፍጠር፣ በየእለቱ ትኩስ የውዝግብ ርችት ማፈንዳት አለባቸው። እግረ መንገዳቸውን፣ ተቀናቃኛቸውን አንቋሽሸው፣ የውስጣቸውን ተንፍሰው፣ ትንሽ ቢረጋጉ፣ ማንም አይከለክላቸውም። ተረጋግተው ዝም ማለትና አርፈው መቀመጥ ግን አይችሉም።
የንትርካቸው ዋና ጥቅም፣ ለሌሎቻችን የሀሜት እድል የሚፈጥር መሆኑ ላይ ነው። ዝም ለማለት ቢሞክሩ እንኳ፣ እረፍት አንሰጣቸውም። እነሱ ካልተወዛገቡ፣ የሐሜት እድል ይቀርብናል።
ደግሞስ፣ ከስብሰባ አዳራሽና ከመግለጫ የማይሻገር ንትርክ፣ ከአንድ ንግግር ወይም ከአንድ ፅሁፍ በላይ አልፎ የማይሄድ አተካራ፣ ተጨማሪ እዳና ሸክም የማያስከትል ውዝግብ ቢኖር፤ ምን ችግር አለው? በልኩ እስከተያዘ፣ መረን እስካልተለቀቀ ድረስ፣ የሕዝብን የወሬ ፍላጎጽ ሊያረካ፣ የሐሜትን ጥም የሚያስታግስ ማብረጃና ማርከሻ ሊሆን ይችላል - የፖለቲካ ውዝግብና ንትርክ።
መቼም፣ ከጥንታዊ ሐሜት ሳይሻል አይቀርም። ጎረቤታሞችን ከሚያጣላ የሰፈር ሐሜት ይልቅ፣ በየሳምንቱ የሚናፈስ የፖለቲካ ወሬና ውዝግብ አይሻልም? በእርግጥ፣ የፖለቲካ ወሬና ንትርክ፣ እንደማንኛውም ነገር፣ ከልኩ ከዘለለ፣ አገርን የሚያጣላ ክፉ ጥፋት ማስከተሉ አይቀርም። የጥላቻ ንትርክ ይቅርና፣ የጓደኝነት ጨዋታም፣ ከመጠን ካለፈ፣ መጨረሻው አያምርም።
የመጠጥ ቤት ቆይታቸውን፣ ተመልከቱ። አጭር የጨዋታ ጊዜ፣ ጥሩ ነው። ዘና የሚሉበት ሊሆን ይችላል። የመጠጥ ቤት ቆይታቸው፣ ገና ቀትር ላይ የሚጀምር ከሆነ ግን፣ ጨዋታ ያልቅባቸዋል። እስከ አመሻሽ ሲረዝም፣ እስከ እኩለ ሌሊት ሲያዘግም፣ ከዚያም አልፎ ሲጎተት፣… ዘና ያለ ጨዋታ ከየት ይመጣል?
የሚያዝናና የጓደኝነት ጨዋታ ምናልባት ለአንድ ለሁለት ሰዓት ሊቆይ ይችላል። ከዚህ በላይ ግን፣ አይዘልቅም።
ዘና ያለ ረዥም ጊዜ፣ በቀላሉ አይገኝም። አዝናኝ ሙያተኛ አገልጋይ ያስፈልገዋል። ስፖርት፣ የሙዚቃ ኮንሰርት፣ ትያትር፣ ሰርከስ፣ ፊልም፣ ኮሜዲ፣… በምርጥ ጥበበኛ፣ በጎበዝ ሙያተኛ ተሰርቶ ሲቀርብ፣ መንፈስን የሚያድስ አስደሳችና መሳጭ መዝናኛ ይሆናል።
ይሄም ቢሆን ግን፣ ከልክ ካለፈ፣ አለቅጥ ከረዘመ፣ ከመጠን በላይ ከበዛ፣…. መዝናኛ መሆኑ ይቀራል። ይሠለቻል፤ ቋቅ ይላል። የሕይወትን መንፈስ ከማደስ ይልቅ፣ ሕይወትን ያዛባል። እንቅልፍ ያሳጣል፤ የኑሮና የስራ ዑደትን ያቃውሳል።
በጥበበኞችና በሙያተኞች የተሰናዳ የመዝናኛ ድግስ፣ ብርቅ እና ድንቅ ቢሆንም፣ በልኩ ስንቋደሰው እንጂ፣ ከጠዋት እስከ ምሽት፣ ከማታ እስከ ማለዳ፣ መዋያ ማደሪያችን እንዲሆንልን ብንመኝ ወይም ብንሞክር፣ መዝናኛነቱን እናበላሸዋለን።
ከጓደኛ፣ ከስራ ባልደረባ፣… ከድሮ የትምህርት ቤት ወይም የሰፈር ሰው ጋር፣… ዘና ብሎ መጨዋወትስ? ለተወሰነ ሰዓት ዘና ሊያደርግ ይችላል።
ሰዓቱ ከረዘመ ግን፣ ከእለት እለትም ከተደጋገመ፤ ወሬውና ጨዋታው፣ ጣዕም ያጣል፤ ቀለሙ ይለቅቃል። በየቀኑ ተመሳሳይ ትዝታዎችን እየመላለሱ መተረክ፣ አንድ ሁለት ቀልድ እያፈራረቁ መደጋገም፣… ለስንት ጊዜ ይታገሱታል? ያሰለቻል። የተረብ ጭምጭምታዎች፣ ከዚያም የብሽሽቅ ፍንጥርጣሪዎች የሚበረክቱት ይሄኔ ነው።
ዘና ያለ መንፈስ ውስጥ ሆነው ሲጨዋወቱ የነበሩ ጓደኞች፣ ከዚህም ከዚህም፣ የተረብ ብልጭታ የብሽሽቅ ሽውታ ቢያጋጥማቸው፤ ለጊዜው ቦታ አይሰጡትም። የመዝናናት መንፈስ፣ ወደ አሰልቺ ችኮ መንፈስ ሲለወጥ ግን፣ ሌላ አማራጭ አይኖራቸውም። የተረብና የብሽሽቅ ፍንጥርጣሪዎችን መወራወር ይጀምራሉ። ወይም በሙግትና በፉክክር ስሜት ይጠመዳሉ። ብዙ ሳይቆዩ ቅሬታና ቂም፣ እልህና ጥላቻ ውስጥ ይገባሉ።
ከዚህ ይልቅ፣… በጊዜ ተዝናንተው፣ ልኩን ጠብቀው በመልካም መንፈስ ወደ የኑሯቸው፣ ወደ የስራቸው ተሰነባብተው ቢለያዩ ይሻላቸው ነበር። ብዙ ሰዎች ግን አያስችላቸውም። ለግማሽ ሰዓት ከልብ ከተዝናኑ፣ ሌላ ግማሽ ሰዓት መጨመር ያሰኛቸዋል። ጨዋታቸውን፣ እስከ እኩለ ሌሊት ማራዘም፣ በየእለቱም እየደጋገሙ አዘውትረው መዝናናት የሚችሉ ይመስላቸዋል። ደግሞም ይሞክራሉ።
ዘወትርና በረዥሙ ለመዝናናት እየተመኙ፣ በየቀኑ እየደጋገሙ ይደዋወላሉ። ቀጠሮና ግብዣ ያበዛሉ። ሳያወሩ ሳይገናኙ መዋል ያቅታቸዋል። ነገር ግን፣ አለምክንያት አለልክ በጣም የተቀራረቡ ሰዎች፣ ብዙም አይሰነብቱም። ብዙዎቹ፣ በጊዜ ይወጣላቸዋል፤ ይበርድላቸዋል። በሰላም ወደ “ኖርማል” ይመለሳሉ። ርቀታቸውን ይጠብቃሉ። እድለኞች ናቸው።
አንዳንዶቹ ግን፣ ክፉኛ ይጣላሉ። በቀልድና በጨዋታ ሲዝናኑ ቆይተው፣ ጊዜው ሲረዝም፣ ወደ ተረብና ብሽሽቅ ተንሸራትተው፤ አካባቢውን የሚረብሽ አምባጓሮና የቀለጠ ፀብ ለመፍጠር ጊዜ አይፈጅባቸውም።
አንዳንዶቹ ግን፣ ሌላ ዘዴ ይኖራቸዋል። እንደማንኛውም ሰው፤ ዘና የሚያደርግ ጨዋታ ያልቅባቸዋል። ነገር ግን ጨዋታ ሲደርቅባቸው፤ እርስ በርስ ተረብ ከመወራወር ይልቅ፣ በቦታው የሌሉ ሰዎችን እያነሱ ያወራሉ። “ሐሜት” የሚሉት ነው።
ያው፣ የሐሜት ግዛት ታውቁታላችሁ። ከጎረቤታሞች፣ ከጓደኞችና ከዘመዳሞች አያልፍም - ነባሩ የሐሜት ግዛት።
በአገሩ በሰፈሩ የሌለ፣ የማያውቁት ሰው ላይ፣ ለዓመት ለሁለት ዓመት ያላዩት የካቻምና እንግዳ ላይ፣… ምን ማውራት ይቻላል? በየእለቱ የምናገኘው የቅርብ ሰው ላይ፣ ለሐሜት ሰበብ የሚሆን፣ ለወሬ የሚበቃ እለታሚ ገጠመኝ ብንፈልግ አናጣም። የውሸት ወሬ ለመፍጠርም ላያስቸግር ይችላል።
በቅርበት የማያውቁት የሩቅ ሰው ላይ ግን፣ ሐሜት መፍጠርና ማውራት ያስቸግራል። የሩቅ ሰው ላይ፣ የቱንም ያህል ብናወራ፣ ሰሚ አናገኝም። የማይታወቅ ሰው ላይ የሐሜት ጥልፍ ስንሰራ ብንውል፤ ከንቱ ልፋት ነው። ዓለምን ሁሉ “ጉድ ነው! አጃኢብ ነው!” የሚያሰኝ ካልሆነ በቀር፣ የአድማጮችን ጆሮ መማረክ አንችልም።
ሐሜታችን፣ በቅርብ የምናውቀው ሰው ላይ ካልሆነ፣ አድማጮችን ለሐሜት ሱታፌ አይጋብዝም፤ ለሐሜት ድግስ የበኩላቸውን እንዲያበረክቱ አያነሳሳም።
ያው፤ የተቀራረቡ ሰዎች መካከል ነው፤ ሐሜት የሚኖረው። ቅርበትና ጓደኝነት ሲኖር፣ በየቀኑ አዳዲስ ወሬዎችን ለመልቀምና ለመቃረም ይመቻል። ትውውቅ ሲጨምር፣ መረጃ እየተቀባበሉ ለማፍተልተልና ለመሸመን፣ አቆንጅቶና በቅመም አሳብዶ ለማውራት የሚጠቅሙ አዳዲስ ገጠመኞች በየቀኑ ይፈጠራሉ። በጎረቤቶች፣ በጓደኞችና በስራ ባልደረባዎች መካከል፣ ለሃሜትና ለውሸት ወሬ የሚያስቸኩሉ የሚያስጎመጁ ሰበቦች እልፍ አእላፍ ናቸው።
አንድ ግቢ ውስጥ የሚኖሩ ወይም ዘወትር የሚገናኙ ዘመዳሞችንም መታዘብ ትችላላችሁ። በጣም ጥበበኞችና ጥንቁቅ ካልሆኑ በቀር፤ የእለት ተእለት ቅርበታቸው ያህል፤ ሐሜታቸው ይበዛል፤ ፀባቸው ይበረታል።
ከሐሜት አስደናቂ ባህሪያት መካከል አንዱ፣ እዚያው በዚው፣ የልብ ለልብ ቅርርብን የሚያጸና ጓደኝነትን የሚያደምቅና የሚያሟሙቅ መምሰሉ ነው። ልዩ የጓደኝነት ስሜትን፣ ከሌሎች የሚበልጥ የቤተኝነት መንፈስን ያላብሳል። ተቀራርበው ሐሜት ሲያወሩ፣ “የሚተማመኑ ምስጢረኞች” የመሆን ስሜትን ይፈጥርላቸዋል።
አበበ እና ከበደ፣ ነባር ጓደኝነታቸውን የሚያሟሙቁ ይመስላቸዋል - ሌላ ጓደኛቸውን በማማት፤ በቀለ ላይ በማንሾካሾክ።
ግን ደግሞ፤ ሐሜት፣ ጓደኝትን የሚያሞቅ ቢመስልም፤ ከዚሁ ጎን ለጎን፣ መተማመንን የሚያሟሟ፣ መከባበርን የሚያሳሳ፤ ጓደኝትን የሚያሟሽሽ ባህሪይ አለው።
በቀለ እና ከበደ፣ የሐሜት እድል ካገኙ፣ ተመራጩ ኢላማቸው፣ “የጋራ ጓደኛቸው አበበ” እንጂ፣ ሌላ ሰው አይሆንም። ነባሩ ጓደኛቸው አበበ፣ ይህን ያውቃል። ለጊዜው በቦታው ከሌለ፣ የሐሜት መሸመኛ እንደሚሆንላቸው አይጠፋውም። እሱ ራሱ ጓደኞቹን ያማል። ጓደኞቹም እሱን እንደሚያሙት ይገባዋል። ሰው ሲያማ ለኔ ብለህ ስማ ይባል የለ!
ታዲያ፣ ሐሜትም ልክ አለው። ለጊዜው የሚያዝናና የሚያቀራርብ ቢመስልም። ዞሮ ዞሮ ማሰልቸቱ፣ ውሎ አድሮ ጸብ መፍጠሩ አይቀርም። ግን ለተወሰነ ጊዜ ያቆያል። ሐሜት መጨረሻው አያምርም። ለምን እንደሆነ ታውቃላችሁ።
የቅርብ ሰው ነው፣ ዋናው የሐሜት ርዕስ። ጓደኛቸው፣ ጎረቤታቸው፣ የስራ ባልደረባቸው ላይ ነው፣ ሐሜት የሚተረትሩት። ለጊዜው፣ በድብቅ እየተዘረጋ፣ እየተቋረጠ፣ እየተቀጠለ፣ የሐሜት አውታር እርባታ ይጦፋል። ግን፤ የወሬ መስመሮች ተጠላልፈው ሲወሳሰቡ፤ “Short-Circuit” ይፈጠራል። እሳት ይጫራል - ጓደኞቻችን ጎረቤታሞችን የሚያፋጅ የጸብ እሳት ይሆንባቸዋል።
ደግነቱ፣ ዛሬ ዛሬ፣ የድሮ ዓይነት ሃሜት ትንሽ ተቀይሯል።
እዚያው በዚያው፣ ቅርብ ለቅርብ፣ ተቆላልፎ የተተበተበ፣ ውስብስብ የሐሜት መረብ፣ ዛሬ ሰፍቷል፤ ግን ሳስቷል።
የዛሬ ሐሜት፣ የግድ የጓደኛ የጎረቤት ሐሜት መሆን የለበትም። የሐሜት ተፈጥሮ ስለተቀየረ አይደለም። “ሐሜት” ከተባለ፣ የምናውቃቸው ሰዎች ላይ መሆን አለበት። ይሄ የሐሜት ባሕርይ አልተቀረም። ዛሬ ዛሬ ግን፣ የቅርባችን ያልሆኑ፣ ብዙ የምናውቃቸው ዝነኛ ሰዎች አሉልን። የፓርቲ መሪዎችና ፖለቲከኞች ላይ፣ ታዋቂና ዝነኛ ሰዎች ላይ፣ የፌስቡክ የዩቱብ ፊቶች ላይ፣ የእግር ኳስ ኮከቦችና አርቲስቶች ላይ፣… ወሬ መቀባበልና ሐሜት መተርተር ይቻላል።
አንደኛ ነገር፣ አዋቂ ወይም መረጃ ፈላጊ የመምሰል ጉዳይ ነው። በእርግጥም፣ ሐሜት ማለት፣ “የወሬ ጥማትን በየእለቱ የማርካት ሩጫ ነው” ልንለው እንችላለን። ወይም ደግሞ፣ “እውነትን ፍለጋ” ብለን አሳምረን ልንሰይመው እንችላለን። “የማወቅ ጉጉት” ብለን ብንጠራውስ?
ከዚህ የበለጠ ሌላ ቁም ነገር አለ። እንዲያውም፣ የወሬ ወይም የመረጃ ጉዳይ አይደለም - “ዋናው የሐሜት ጉልበት”።
ዳኛና ፈራጅ የመሆን ስልጣን ይሰጣል - ሐሜት።
“የጥፋትና የልማት፣ የጥቃትና የጉዳት የክፋትና የደግነት”… መርማሪና አጣሪ፣ ዳኛና ፈራጅ የመሆን ስሜትን የመፍጠር የሐሜት ባህርይ ነው - ትልቁ የሐሜት ማራኪነትና ጉልበት።
“ሰምተሃል? ሰምተሻል?”… እያሉ ወሬ ለማቀበል ይጣደፋሉ - “መረጃ የመስጠትና የማዛመት፣ የማሳበቅና የማሳወቅ ጉጉት” ልንለው እንችላለን።
“ምን ተፈጠረ?... ከዚያስ?... ኧረ ተው? ወይ ጉድ! ኧረ ተይ፣… እኔ አላምንም!” እያሉ፣ ለወሬ ይስገበገባሉ።
“መረጃ የማሰባሰብ ጥረት፣ ብርቱ የማወቅ ጉጉት” ይመስላል።
ዋናው ቁምነገር ግን፣ ከዚህ በኋላ ነው የሚመጣው። ዋናው እርካታ ያለው፣ ፍርጃው ላይ ነው።  
“በጣም ያናድዳል። አሁን ይሄ ሰው ነው? ሲያዩትማ ሰው ይመስላል።” ብላ ትፈርዳለች።
“በጣም ያሳዝናል። ይህች እባብ። እኔ ደግሞ ደህና ሰው መስላኝ!...” ብሎ ይፈርዳል።
እንዲህ አይነት ፍርጃ ላይ ለመድረስ ነው የሐሜት ሁሉ ሩጫ። ዳኛና ፈራጅ የመሆን ጥማት፣ በጣም ሃይለኛ ነው።


Read 9789 times