Saturday, 11 June 2022 18:41

“አንድ... አምስት መቶ ብር ይኖርሀል?”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)

"ስሙኝማ... እግረ መንገድ የሆነ ነገር ትዝ ብሎኝ ነው፡፡ በቀደም በሀምሌ የሚደረገው የነዳጅ ጭማሪ ለኑሮ መወደድ ሰበብ ሊሆን አይችልም የሚል ነገር ሰማን ልበል! እንደው እንዲህ በሥራ ተወጥረን ያስቸግረናል አትበሉኝና ምን ማለት እንደሆነ የሚያስረዳኝ ባገኝ፡፡ የምር...በቃ ወጣቶቹ እንደሚሉት ‘ጦጣ’ ሆንን እኮ! እናም ምን መሰላችሁ... የፖለቲካ ተንታኞች ምናምን እስቲ ለጊዜው ‘የወንድ በር’ ልቀቁና ይቺ፣ ይቺ ነገር ትተንተንልን፡፡--"
       


             እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ...አንድ ወዳጅ ምርር ብሎት እንዲህ አለ... “ምን አይነት ሰው ጠላሁ መሰላችሁ፣ ብድር የሚጠይቀኝ!” (ወዳጄ... በቃ ቃል አቀባያችን አድርገንሀል፡፡ እኛ እኮ እንዲህ አይነቱን ነገር በሆዳችን አምቀን የቆየነው ብንናገር የፍረጃ ዘመን ስለሆነ ወይ ከሩስያ፣ ወይ ከዩክሬይን ጋር ይደለድሉናል ብለን ነው ጭጭ ያልነው! ቂ...ቂ...ቂ...) እናላችሁ... ወዳጃችን እንደው ሰው ዓይን ላይ ሲጥለው...አለ አይደል.... ፊቱም፣ ጠጉሩም ምኑም ምናምኑም በለጭለጭ ስለሚል ያለው፣ የተረፈው ይመስላቸዋል መሰለኝ፡፡ መቼም እዚህ ሀገር ላይ ላዩን ምን መምሰል፣ እንዴት ወዛ፣ እንዴት በለጭለጭ ማለት እንዳለበት ላወቀ የውስጡን በቃ... እንደተቆለፈ ቤት “መግባት ክልክል ነው” አይነት ለማድረግ ቀላል ሳይሆን አይቀርም፡፡
እናማ...ብልጭልጭነት ሁልጊዜም ‘ሁሉም ምቹ፣ ሁሉም ዝግጁ’ ነው ማለት አይደለም። ምክንያቱም በባዶ ሆድ፣ ወዛ ያለ ነገር ካገኘ ሰባተኛ ወሩን ባለፈ ሆድ፣ በለጭለጭ ማለት የሳይንስ ፍርድ ገና ባይታወቅም፣ ከመመቸት የተለየ  ነገር ሳይኖረው አይቀርም፡፡ ስሙኝማ...እንግዲህ ጨዋታም አይደል... በሆኑ መአት ጉዳዮች ድብት ብሏችሁ እዚህ ዓለም ላይ ምን ልትሠሩ እንደመጣችሁ ‘ዴንጀረስ’ ፍልስፍና ጀምራችሁ (‘የዘፈን ዳር ዳሩ’ እንዲሉ) መሬት፣ መሬት እያላችሁ ስትሄዱ ድንገት መጥቶ አንተ “እንዴት ነው ያማረብህ!” የሚል ሰው ቆሽትና የ‘ኪድኒ’ ቦታችሁን አይለዋውጥባችሁም! ደግሞላችሁ... እዚህም እዛም ‘መቀላቀል’ ስለሚችልበት ሳይሆን አይቀርም ‘ቤስት ፍሬንድ’ የሚላቸው ብዙ ናቸው፡፡ (የምር እኮ ለአንዳንዶቻችን ከመደበኛ ጓደኞች ይልቅ ‘ቤስት ፍሬንዶች’ ሳይበዙብን አይቀርም! ቂ...ቂ...ቂ...) እናላችሁ...እንግዲህ እዚህ ላይ ‘ቱ ፕላስ ቱ ማለት ነው፡፡ ልክ ነዋ...ያው ‘ቤስት ፍሬንድ’ በበዛ ቁጥር  ‘ፌቨር፣’ ብድር ምናምን ጠያቂም ሊበዛ ይችላል! ስሙኝማ...በፊት እኮ
“ቤስት ፍሬንዴ ነች፡፡”
“ቤስት ፍሬንዶች ከመሆናችን የተነሳ በቃ ወንድማማቾች በለን፣” አይነት ነገር መባባል እኮ...አለ አይደል...“እንዴት አይነት አሪፍ ጠባይ ቢኖራት/ቢኖረው ነው እንዲህ አይነት ቤስት ፍሬንዶች ያሏት/ያሉት?” ይባል ነበር፡፡
“ስሚ፣ ያቺ ሁልጊዜ አብረሻት የማያት ልጅ ዘመድሽ ነች እንዴ?”
“የትኛዋን ነው የምትዪኝ?”
“ያቺ እንኳን ኤን.ጂ.ኦ. መአት ገንዘብ ይከፈላታል የምትባለው፡፡”
“ውይ እስከዛሬ አላውቅም እንዳትዪኝ!”
“ምኑን?”
“እሷማ፣ ቤስት ፍሬንዴ ነች እኮ!”
“አትዪኝም!”
ኮሚክ እኮ ነው፡፡ ኤን.ጂ.ኦ. የምትሠራ ብዙ ብር የሚከፈላት ‘ቤስት ፍሬንድ’ ማግኘት እኮ ራሱ የሆነ ሜዳሊያ የሚያሸልም ነገር ነበር የሚመስለው፡፡ (እነ እንትና...እንደው አፕዴት ብታደርጉኝ ብዬ ነው...  አሁንም ኤን.ጂ.ኦ. አካባቢ ‘እንደ ያኔው’ ፍሪድጅ፣ ሶፋ፣ ስቶቭ ምናምን በሽ ነው እንዴ!...አይ ሲባል ስንሰማ ስለነበር ነው!) እናላችሁ... ብዙ ጊዜ...አለ አይደል... እንደ እኛ አይነቱን ‘ተራ ሰው’ ጫማ አስጠርጎ ሦስት ብር ከሀምሳ ክፍል ሲባል “ሦስት ብር ከአርባ አምስት ነው፣” ብሎ ‘ሰርድ ወርልድ ዋር’ ለማስነሳት ዳር ዳር የሚለውን ሳይሆን... አለ አይደል... ስሙን ተከትሎ የሆነ ‘ለወሬ የሚመች’ ተቀጥላ ያለው ሰው፣ ‘ቤስት ፍሬንድ’ መሆን በራሱ እኮ ዋጋ ነበረው፡፡ የምር!
“አታውቅም እንዴ፣ እሱ እኮ የእንትና የልብ ጓደኛ ነው፡፡”
“እንትና ድምጻዊው?”
“አዎ፡፡”
“አትለኝም!”
እናማ... እንደዚህ ነበር ለማለት ነው፡፡ ግንማ... ምን መሰላችሁ...እንዲህ አይነቱ ነገር ለሁሉም ይሠራል ማለት አይደለም፡፡ አሀ....ነገርን እያጠሩ መሄድ ያስፈልጋላ!
“እንትና እኮ ቤስት ፍሬንዷ ነው፡፡”
“እኮ...እንትና ይሄ ጋዜጠኛው?”
“አዎ፡፡”
“አፈር በበላሁ! ምኑን ጉድ ጣለባት?” ቂ...ቂ...ቂ...
እናላችሁ... ያ ብድር ጠያቂዎች ያስጠሉት ወዳጃችን ምን ያድርግ ብላችሁ ነው፡፡ እንደው ሳይንሱ ወይም ሳይንስ የሚመስለው ነገር (‘እውቀት’ የበዛበት ዘመን ነው ብለን ነው፣) ገና ማረጋገጥ ያለበት ጉዳይ ቢሆንም በአስራ አምስት ቀን አንዴ ተጋብዞ ሳይሆን ከፍሎ ማኪያቶ መጠጣት የሎተሪ እጣ አይነት የሆነበትን ምስኪን... “ወር ላይ የምመልስልህ አንድ አምስት መቶ ብር ልታበድረኝ ትችላለህ?” የሚል ሰው...አለ አይደል... ጭንቄው አካባቢ ትንሽ ‘ኦፍ ሳይድ’ የገባበት ‘ስስ ብልት’ ልትኖር ትችላለች፡፡ ይሄኔ ነው “የሪፈሪ ያለህ አትሉም ወይ፣” ማለት፡፡
“ብድር ጩቤ አይደለም” የምትል ነገር ነበረች... ያኔ መበደር በማይፈራበት (ብዙም ጊዜ ብልጥነት በነበረበት) አበዳሪም እዚህም አዛም በማይጠፋበት ዘመን፡፡ “ስማ ባልከው በሁለት ሳምንት ውስጥ ካልመለስክልኝ እኔና አንተ ተቆራረጥን ማለት ነው፡፡” በመንፈቅም፣ በዓመትም ቢመለስ ችግር የለም፡፡ ዋናው መመለሱ ነው፡፡ (እንትና የዛሬ ሀያ ዓመት የወሰድሽውን ያን መጽሀፍ በቃ አስቀረሽው ማለት ነው! ስሚ አሁን የምፈልገው ለንባብ ምናምን አይደለም፡፡ ‘ለኢንሹራንስነት’ ነው። ልክ ነዋ ኑሮ ጫናዋ እየበዛ ስትሄድ መጽሀፍ መግዣ ትርፍ ገንዘብ ላለው ወዳጅ... አለ አይደል...ፍቅር ይደርጅም፣ አይደርጅም ‘እጅ በእጅ’ ልትተላለፍ ትችላለቻ! አሀ...እዛም ሼልፍ ላይ፣ እዚህም ሼልፍ ላይ!)
ደግሞ አለችላችሁ፣ “ወይ አበዳሪ ወይ ተበዳሪ ቀድሞ ይሰናበታል፣” የምትል ነገር አለች፡፡ እንደው አበዳሪው አመም ካደረገው ተበዳሪ ያው አንደኛውን ‘ባይ፣ ባይ’ ካለ “ብድሬ ቀረልኝ፣” ብሎ ያስባል ማለት ለአፍ ቢከብድም፣ በተለይ በዚህኛው ዘመን እንደዛ የሚያስብ መአት ሰው ባይኖር ነው፡፡ እናላችሁ... አንዳንድ ጊዜ እኛም ስንጠይቅ...አለ አይደል...ሌላውን ያበሳጨዋል፤ ይከፋዋል ምን ይለዋል ብሎ ነገር የለም፡፡ በቃ ዝርግፍ ነው፡፡
ስሙኝማ... እግረ መንገድ የሆነ ነገር ትዝ ብሎኝ ነው፡፡ በቀደም በሀምሌ የሚደረገው የነዳጅ ጭማሪ ለኑሮ መወደድ ሰበብ ሊሆን አይችልም የሚል ነገር ሰማን ልበል! እንደው እንዲህ በሥራ ተወጥረን ያስቸግረናል አትበሉኝና ምን ማለት እንደሆነ የሚያስረዳኝ ባገኝ፡፡ የምር...በቃ ወጣቶቹ እንደሚሉት ‘ጦጣ’ ሆንን እኮ! እናም ምን መሰላችሁ... የፖለቲካ ተንታኞች ምናምን እስቲ ለጊዜው ‘የወንድ በር’ ልቀቁና ይቺ፣ ይቺ ነገር ትተንተንልን፡፡ አንድ ብር ተምናምንና ሁለት ብር ሲጨመር ሁሉም ነገር ሰማይ ሊነካ በሚደርስባት ሀገር ይሄ ነገር ትንሽ አይከብድም! ዘይት... ዘይት እንኳን ስንት ማስጠንቀቂያ ሲሰጥባት፣ ስንት ሲባልባት፣ ስንት “ወዮላችሁ!” ሲዘንብባት  ሺህና ዘጠኝ መቶ ምናምን ላይ ተንጠልጥላ ማን እኔ ነኝ ያለ ምን አደረጋት!
ደግሞላችሁ... ጭማሪው ከሌላ ጊዜ ላቅ ያለ ነው እየተባለ እንዴት ነው ለኑሮ መወደድ ምክንያት ሊሆን የማይችለው? ያልገባን ወይ ሊገባን የማይችል ከሆነም በሚገባን ቋንቋ የሚያስረዳን ብናገኝ፣ ይቺን ሀያ ምናምን ቀን ቁርጣችንን አውቀን እንከርማለን፡፡
ስሙኝማ...እግረ መንገድ የሆነ ነገር ለመጥቀስ ያህል በየመሥሪያ ቤቶችና በዝቅተኛም፣ በመካከለኛም፣ ሆነ በከፍተኛ የስልጣን ወንበር ላይ ባሉ ግለሰቦች የሚሰጡ መግለጫዎች ችኩልነት ባይኖርባቸውና ነገን ቢያስቡ አሪፍ ይሆን ነበር፡፡
ምክንያቱም በአነጋገር ግዴለሽነት ወይም በአተረጓጎም መዘበራረቅ ግራ መጋባት ሊፈጠር ይችላላ! ለምሳሌ ከሳምንታት በፊት “የመጨረሻው የኮቪድ ታማሚ ከሆስፒታል ወጣ፣” ተብሎ እንደ ሰበር ዜና ተነግሮ ነበር። ይህ ነገር በህዝብ መሀል የፈጠረው ስሜት ቀላል አልነበረም፡፡ ብዙዎች...አለ አይደል... በቃ በሚጥሚጣም ይሁን በበርበሬ ኮቪድ እንዳበቃለት አይነት አድርገው ነበር የተረጎሙት፡፡ ሰዉ እኮ እንደ ጉድ ነው ማስክ ማድረጉን የተወው! አሁን ደግሞ በየቀኑ በኮቪድ ሳቢያ ሆስፒታል የሚገቡ ዜጎቻችን ቁጥር እየጨመረ እንደሆነ እየተነገረን ነው። እባካችሁ... ለ‘ሰበር ዜናውም፣’ ለምኑም ጥንቃቄ!
እናማ... “አንድ... አምስት መቶ ብር ይኖርሀል?” የምትሉ ወዳጆቻችን ስለ እናት ኪስ ብቻ ሳይሆን ስለእኛም ቆሽት አስቡልንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 424 times