Saturday, 11 June 2022 20:14

ራስን የመሆን ጥበብ!

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 "ለመሆኑ ኢትዮጵያ ማን ናት? ምን ትመስላለች? እንደ ኅብረተ-ሰብዕ እኛ ማን ነን? ማንነታችንን ምን ያህል እናውቃለን? ምን ገጠመን? እንዴት አለፍነው? በገንቢ ጽናትስ ማንነታችንን ይዘን ቀጥለናል ወይ? ራሳችንን እንይ!"

            ይበል አዘጋጅ፡- ተንስኡ ለንባብ፡፡
ይበል አንባቢ፡- በስመ አብ…አቤቱ እውነቱን ግለጥልን፡፡ የሁሉ ፈጣሪ ማስተዋልን ስጠን፡፡
እነሆ፡- የፈጣሪ ባሪያ፣መጻፍ እና ማስነበብ ጀመርኩ፡፡ ዛሬ ላነሳ የወደድሁት ፍሬ ነገርም እጅግ መሠረታዊ እንደሆነ አምናለሁ፡፡
ሀ/ ዓላማዎች
የመጀመሪያው ንዑስ ዓላማ ራስን መሆን ሲባል ብዙ ጊዜ ተዛብቶ ይቀርባልና እርሱን ማስተካከል ነው፡፡ በተለይ በግለሰብ ደረጃ ሲቀርብ፡፡ ራስን መሆን ሲባል ሰባቱ የማንነት መርሆዎች የምንላቸውን በሚጻረር መልኩ ሌሎችን ማዳመጥ ትቶ፣ ራሱን ብቻ እያደመጠ፣ ስሜቱን እና ሐሳቡን ተከትሎ፣ ከመንጋው ቢነጠልም ተነጥሎም፣ ለማንም ስሜት እና ጉዳት ሳይጨነቅ፣ ሥራው ያውጣው ብሎ፣ ለሌላው ግድ አጥቶ፣ በራሱ ህልም ተመስጦ፣ የራስን ኑሮ መኖር የሚመስላቸው እና እንዲህም አድርገው የሚያቀርቡ እና የሚያስተምሩ ብዙዎች ናቸው።  ያው ምዕራባዊ የግለኝነት ትርጉም ነው፡፡  ይህ በፍጹም ስህተት ነው፡፡
ራስን መሆን ማለት እንደ ግለሰብም እንደ ኅብረተ-ሰብዕም ሊታይ የሚችል ሲሆን ላመኑበት መኖርን ወይም ላመኑበት ነገር፣ እሺ ላላመኑበት ነገር እምቢ ማለትን የሚያሳይ ነው፡፡ ፍቅር ፍቅር እያለ በፍቅር እና መረዳዳት እንደማያምን፣ ማኅበራዊ ሆኖ እንዳልተፈጠረ የጫካ አውሬ፣ ያሻን እየሰሩ፣ ምክርን እየጣሉ፣ ትብብርን እየገፉ መኖር ማለት አይደለም፡፡
ራስን መሆን በዋናነት የሚያስፈልገው ባመኑት ለመኖርና ኃላፊነት ለመውሰድ ነው፤ ለሚሰራው ኃላፊነትን የማይወስድ ሰው ቢያጠፋ ለወቀሳ፣ ቢያለማ ለምስጋና አይመችም፤ ምክንያተኛ ይሆናልና፡፡ ለዚህ ነው ብዙ ጊዜ ሥራ መሪዎች (ሥራ አስኪያጆች) ኃላፊነት ለማይወስድ ሰው ኀላፊነት መስጠት የማይወዱት፡፡
ዛሬ እንደ ግለሰብም እንደ ኅብረተሰብም ራሳችንን መሆን አለብን ስል ስለሠራነው እና ስለምንሰራው ሥራ ኃላፊነት እንውሰድ፤ ለማንነታችን ዋጋ እንስጥ፣ እያልኳችሁ ነው። ማንነትን፣ ለማጽናትም ለመለወጥም ማንነትን ከመቀበል ይጀምራልና፡፡
ራስን መቀበል እና መሆን ከሰባቱ የማንነት መርሆዎች አንዱ ነው እንጂ ብቸኛው አይደለም። እነርሱም፡-
ማንነትህን ዕወቅ፣
ማንነትህን ተቀበል፣ (ራስህን ሁን፣)
ማንነትህን አጥራ፣ ገንባ፣
ማንነትህን ለአንድነት እና ለጋራ ስም ብለህ ካልሆነ በቀር አጽንተህ ያዝ ፣
በንግግርህ ማንነትህን በጨዋ ግልጥነት ግለጥ፣
ማንነትህን በሥነ-ምግባር፣ በሥራ ግለጥ፣ (ራስህን ሁን፣)
የማንነትህን ዕውቀት ለውሳኔዎችህ በግብአትነት ተጠቀምበት፤ የሚሉ ናቸው።
ማንነትን ስለማጥራት ማውራት የማይመቸው ምዕራባዊው የሥነ-ልቦና አስተምህሮና ማንነትን ስለ አንድነት ሲሉ መሰዋት የሚለው ቃል እንደ ሬት የሚመራቸው የዘውጌ ፖለቲካ አቀንቃኞች፣ በልዩ ልዩ ስልት የማንነት አጠባና የአዕምሮ አጠባ እያካሄዱብን ነው፤ አንድነታችንን እየሸረሸሩ ነው፤ ባህላችንን እያጠፉ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ እና የመንፈስ ልጁ ጢሞቴዎስ ናዝራዊ በመሆን እና በመገረዝ የማንነትን ዋጋ እንደከፈሉ ወደው አያስተውሉም፡፡
ስለዚህ ወቅቱ ራሳችንን ስለመሆን እና ራሳችን ስለመቀበል አጥብቀን ልናስብ፣ አጥብቀን ልንወያይ የሚገባን ጊዜ ነው፡፡ አንድ ሰው ወይም አንድ ኅብረተ-ሰብዕ ራሱን ሲሆን ለራሱ ያለውን ዋጋ እና ክቡርነት ይገልጣል፤ ራስን ከባዕዳን እና ከጠላት አሳንሶ ማየትን አባቶቻችን አላስተማሩንም፡፡
ነፍስን ጠልቶ፣ሕይወትን ተጠይፎም አይሆንም፡፡ ነፍስን ወዶ፣ ለሥጋ ሳስቶም አይሆንም፡፡ ወንጌል “ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ይጥላት” ሲል “ይጉዳት” ማለቱ ነው፡፡ የሚጎዳውም ነፍሱን ሊያድን ነው። አብርሃም ልጁን እስከ መሰዋት የታዘዘው እግዚአብሔር እንደሚያስነሳለት እና ዳግም እንደሚያገኘው ስላመነ ነበር፡፡ የቃሉ ሐሳብ፣ ሰው መከራ መቀበል ግዴታው ከሆነ መከራን ይቀበል፤ ራሱን ይጉዳ፤ ለወንድሙ ይሙት፤ ማለቱ እንጂ፣ መከራን በገዛ እጃችን እንድንጎትተው አይደለም። ጸሎታችን ወደ ፈተና አታግባን ነው፤ ጥረታችንም ችግርን መፍታትና ማቃለል ነው፡፡ ነገር ግን ስደቱ፣ መስቀሉ ልናልፈው የማንችል ሆኖ ከመጣ ስለ ነፍሳችሁ ተጎዱ፤ ነው፡፡
እንደ እውነቱ ከሆነ ከራሳችንም ከሰውም የምንስማማው ራሳችንን ስንሆን፣ ባመንበት ስንኖር እና ወጥ ጠባይ ሲኖረን ነው፡፡ ራስን መሆን ከጸጸት ያድናል፤ የአእምሮ ሰላም ይሰጣል፤ ምነው ያመንኩትን ሠርቼ ቢሆን ከሚል ጸጸት ያድናል፡፡ የዘመናችን ምስቅልቅሎሾች ለማንነት ግጭት እንዳይዳርጉንም ይረዳናል፡፡
ሌላው ራስን መሆን እና አለመሆን መክሊትን የመጣል እና ያለመጣል ጉዳይ በመሆኑ፣ እንደሚገባ ባንይዘው እና እንደሚገባ ባንጠቀምበት፣ በአምላክም በታሪክም ተጠያቂ ያደርገናል ብዬ አምናለሁ።
ለ/ ችግሮች
ገንቢ ጽናት የሚለው ቃል ገንቢ ያልሆነ ጽናትም እንዳለ የሚጠቁም ሲሆን፣ ለለውጥ አለመቸኮልንም፣ ለለውጥ አለመለገምንም ያሳያል፡፡ ለመሆኑ ኢትዮጵያ ማን ናት? ምን ትመስላለች? እንደ ኅብረተ-ሰብዕ እኛ ማን ነን? ማንነታችንን ምን ያህል እናውቃለን? ምን ገጠመን? እንዴት አለፍነው? በገንቢ ጽናትስ ማንነታችንን ይዘን ቀጥለናል ወይ? ራሳችንን እንይ! ጥያቄዎቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡
ማንነታችንን ዕናውቀዋለን? (እንደ ግለሰብም እንደ ኅብረተ-ሰብዕም)
ካወቅነውስ ማንነታችንን ተቀብለነዋል? መልካምም ቢሆን መጥፎ ኃላፊነት ወስደናል?
ማንነታችንን አጥርተናል? ገንብተናል? ወይስ ይብስ አቆሽሸናል?
ለአንድነት እና ለጋራ ስማችን ስንልስ ማንነታችንን እና ልማዳችንን እየሰዋን ነው?
ማንነታችንን በጨዋ ግልጥነት ነው የምንገልጠው? ወይስ ይሉኝታ ቢስ ግልጥነት ያጠቃናል?
ማንነታችንስ ያለው አንደበታችን ላይ ብቻ ነው? ወይስ በሥራ እንገልጠዋለን?
“ማንነታችን፣ እንዲህ ነው፤ እናውቀዋለን።” ብለን ዘጋነው? ወይስ ለውሳኔዎቻችን እንጠቀምበታለን?
ነጻነት አምሳሉ አፈወርቅ የተባሉ ጸሐፊ ሰሞኑን በአዲስ አድማስ ጋዜጣ በጻፉት ጽሑፍ እንዳሉት፤ “ትውልዱ ግብረገብነት የለውም፤ እንደ ሃይማኖተኛ ሕዝብ እየኖርን አይደለም፤ እንደ ባህላችን እና ሥርዓታችን ልከኛ አልሆንም፤ ሀገር ወዳድነታችን እየቀዘቀዘ ነው፤ ማህበራዊ ትስስራችን ላልቷል፤ ወገናዊ ስሜታችን በግለኝነት ተቀይሯል፤ አጉል ባህል ተጣብቶናል፤… የሚሉ ትችቶች ይሰነዘራሉ።” ብለዋል። አዎ በሚያሳዝን ሁኔታ ባህለ ማንነታችን እየተሸረሸረ ነው፡፡ ይገርማል! ጸሐፊው የምጽፈውን አስቀድመው አውቀው ለእርዳታ የጻፉልኝ ይመስላል፤ ይህ ችግራችን ነው፡፡
ዛሬ ባማረው እና በጸናው በኢትዮጵያዊ መልካችን፣ ከአባቶቻችን በተረከብነው ማንነት እና ባህል እንዳንኖር የሚያደርጉ ብዙ ነፋሳቶች እና ግፊቶች እያስተናገድን የምንገኝበት ጊዜ ነው፡፡ ከለውጡ በኋላ ብዙ ነገሮች ቢሻሻሉም እኛን የማይመስሉ መገናኛ ብዙኃን ዛሬም አሉ፡፡ ለምሳሌ እንደ ቃና ያሉ፡፡ የጠላት ፕሮፓጋንዳም ቀጥሏል፡፡ ዛሬም አለባበሳችን እና የኑሮ ዘዬአችን ባህለ- ማንነታችንን አይመስልም፡፡
በወንጌል ስም ዓለማዊ ወንጌሎች፣ በሳይንስ ስም ሐሰተኛ ሳይንሶች፣ በፍቅር ስም የጅልነት ስብከቶች፣ በእውነት ስም የድራማ እና የማኖ መረጃዎች ተጽእኖ እያደረጉብን ነው፤ ከማንነታችሁ ውጡ እያሉን ነው፡፡
ለጋሽ ሀገራት እጃችንን ለመጠምዘዝ ግፊት ያደርጋሉ፤ የተገዙ ባንዳዎች ፕሮፓጋንዳ ይነዛሉ፤ በመልካሙ እንዳንጸና፣ በአጉሉ እንድንቀጥል የሚፈልጉ እና ከለውጥ የሚገድቡ እንክርዳድ ባህሎች ያሰሩት የኅብረተ-ሰብዕ ክፍል እና ግፊትም አለ፤ ጭፍን ደጋፊዎችም ሳይገባቸው የሚደግፉ ክፍሎችም ከጥቅሙ ጉዳቱ ሊያመዝን ይችላልና ችግሮቻችን ናቸው፡፡
ሐ/ መፍትሔዎች
እስቲ በመጀመሪያ የሚከተሉትን ጽንሰ ሀሳቦች እንመልከት፡፡ በፍልስፍናው ዓለም ከሚዳሰሱ እና ምላሽ ከሚፈለግላቸው ሥነ-ማኅበረሰባዊ ጥያቄዎች ሁለቱ የሚከተሉት ናቸው፤ ሃይማኖትን እና ፖለቲካን አንድ ነጥብ ላይ ያገናኙ ጥያቄዎች ናቸው፡፡
1ኛ/ ከምንም በበለጠ ለዓለም የሚያሻት ፈዋሽ ክኒን ምንድን ነው? ሃይማኖትና መንፈሳዊነት? ብልህነትን እና ክሂልን የታጠቁ መሪዎች? አነስተኛ ህግጋት እና ደንቦች? ወይስ ምን?
2ኛ/ የአንድ ማኅበረሰብ ጥሩነት የሚመዘነው በየትኞቹ መስፈርቶች ተለክቶ ነው? በሀብት በንብረቱ? ደሀ ዜጎቹን በሚይዝበት መንገድ? በደረጀ ባህሉ እና ኪነ-ጥበቡ? በነዋሪዎች መካከል የእርስ በእርስ መስተጋብሮች በሚፋፉበት ሂደት? ወይስ በምን? የሚሉ ናቸው፡፡
ለሁለቱ ጥያቄዎች ሊሆኑ የሚገቡት ምላሾች፣ ብቁ መንፈሳዊ መሪ እና የመንፈሳዊነት ባህል የሚሉት ናቸው፡፡ የመንፈሳዊነት ባህል ያልኩት ያው ሳይንሱ ግብረገባዊ ባህል የሚለውን ነው፡፡ ማለትም ግብረገባዊነት የሚጸናው በሃይማኖትና በመንፈሳዊነት ነው በሚለው እምነት በመደገፍ ጭምር ማለት ነው፡፡
የአንድ ማኀበረሰብ ጥሩነት የሚለካው በኅብረተሰቡ ውስጥ ባለው ግብረገባዊ ባህል አማካኝነት ነው፡፡ ይህን ሳይንሱም ስለተቀበለው ክርክር የሚኖር አይመስለኝም። ለዓለም የሚያሻት ፈዋሽ ክኒን ብቁ መንፈሳዊ መሪ ነው፤ የሚለው ላይ ግን ጥያቄዎች ሊነሱ ይችሉ ይሆናል፡፡
አስተዋይ የሆነ አንባቢ እንዲሁም የሶሻሊዝምን ሃይማኖት ጠልነት እና ዲሞክራሲ አልባነት፣ የካፒታሊዝምን ስግብግብነት እና ዓለማዊነት (ሴኩላርነት) ያስከተሏቸውን ሰብዕናዊ ውድቀቶች የተረዳ ሰው አባባሌን እንደሚረዳ እና እንደሚደግፍ እርግጠኛ ነኝ፡፡
የሥነ- ልቦናው ሳይንስም በግለሰብ ደረጃ እያንዳንዱ ሰው ሊወስደው የሚገባው ክትባት ሥነ-ምግባራዊነት እና ግብረገብነት እንደሆነ አስቀምጧል፡፡ እኛስ እነዚህን መድሀኒቶች አግኝተናል ወይ?  ለነዚህ መሰረታዊ ነገሮች መፈጠር እና መዳበር ምን ማድረግ ይገባናል? ሳይንሱ ያዘዘውን መድኃኒት ማለትም ግብረገብነትን የያዘው ባህላችንን ለማስቀጠል ምን ማድረግ ይገባናል?
ባህላችን እና የግብረገብ መርሀችን መንፈሳዊ ነው፡፡ ዞር ዞር ብለን ዙሪያችንን እንመልከት። ኢትዮጵያውያን እምነት የለሽ አይደለንም፤ ራስ ወዳድም አይደለንም፤ ኢትዮጵያውያን ሥርዓተ-ወጥ አይደሉም፤ ግብዝም አይደሉም፤ ወስላታ እና ቀበጥባጣም አይደሉም፤ ልበ ጭለማም አይደሉም፣ ከጀግንነት የራቁ የፍርሃት እስረኛም አይደሉም፡፡ ኢትዮጵያውያን ከፈሪሃ-እግዚአብሔር አይወጡም። በምንም ልኬት የግብረገብ ባህላችን ሃይማኖተኛ እና መንፈሳዊ ነው፡፡
ስለዚህ የባህላችንን መንፈሳዊነት ይበልጥ ለመረዳት፣ የኢትዮጵያዊነት እሴቶችን ማየት በቂ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ስንልም ግብረገባዊ የጋራ ባህላችንን ነው፡፡ ግብረገባዊ የጋራ ባህላችን የፈጠረው የጋራ ሥነ-ልቦና እና የጋራ ሰብዕና ማለታችን ነው፡፡
መቼም የኢትዮጵያ ቤተ-ክርስቲያንን እና መስጊድን ገብተው ሳያጠኑ፣ መንፈሳዊ እና ቁሳዊ ቅርሶቻችንን እና እሴቶቻችንን ሳይቃኙና ሳያስተውሉ፣ ኢትዮጵያን ዐውቃታለሁ ማለት ዘበት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ያሉ ሃይማኖትን የማይቀበሉ ሶሻሊስቶችን፣ ሊብራል ኑሮን እና ሴኩላሪዝምን የሚያቀነቅኑ ፖለቲከኞችን፣ ሌሎችም ያልተጠቀሱ አንድ አንድ የማኅበረሰብ ክፍሎችን፣ አንድ የሚያመሳስላቸው ጉዳይ ቢኖር ኢትዮጵያን ዐለማወቃቸው ነው፡፡ ብዙዎቻችን ኢትዮጵያን ዐናውቃትም፡፡
ኢትዮጵያን ዐውቀናትስ ቢሆን ይህ ሁሉ ውጥንቅጥ በሀገራችን ባልተከሰተ ነበር። ዐውቀናትስ ቢሆን ‹‹ሃይማኖት ብቻ መንፈሳዊ፣ መንግስት ዓለማዊ›› ባላልን ነበር። ከባለስልጣናትም መካከል ሃይማኖተኞች እና መንፈሳዊያን ሊገኙ አይችሉምን? ሊባል የሚገባው ‹‹ሃይማኖት ሰማያዊ፣ መንግስት ምድራዊ ነው፤›› ነው። ይህም ቢሆን አብዛኛው ትኩረታቸውን ያሳያል እንጂ ሃይማኖት ምድራዊው ጉዳይ፣ መንግስትም መንፈሳዊው እና ሃይማኖታዊው ጉዳይ ፈጽሞ አይመለከታቸውም፤ ማለት አይደለም፡፡
ከላይ እንደተመለከትነው የባህል ጉዳይ ይህን ያህል ወሳኝ ከሆነ፣ ለምን የባህል ጉዳይ አያሳስበንም? ኢትዮጵያዊ ጨዋነት እና ግብረገብነት የጋራ ባህላችን ከሆነስ ለምን የግብረ ገብነት ጉዳይ አይበልጥብንም? ለምንስ ራሳችንን አንሆንም? ለምንስ ከባህላችን ለመውጣት እንወራጫለን?
በባህላችን ውስጥ እንክርዳድ ባህሎች እንዳሉ እኔም እገነዘባለሁ፡፡ ነገር ግን የጨዋ ግልጥነት ሳይሆን ይሉኝታ ቢስ ግልጥነት እንደሚያጠቃን ሁሉ ፈረንጅ ጣሉ ያለንን ለመጣል፣ ያዙ ያለንን ለመያዝ የምንሽቀዳደም አንዳንዶች አለን። ማድረግ ያለብን አንድ መፍትሄ በገንቢ ጽናት እሴታችን መቆም ነው፡፡ ገንቢ ጽናት ገንቢ ካልሆነ ጽናት የሚለየው የሚቆመው በእውነት ነው፤ ሰውን አይቶ አይደለም፡ለውጥ የሚያደርገው እውነትና መልካም መስሎት የያዘው አቋም ሐሰት እና መልካም ያልሆነ፣ መጥፎ ሆኖ ሲያገኘው ነው፡፡ በዚህ ላይ፣ ደጋግሞ መመርመር፣ ለለውጥ አለመቸኮል እና፣ ለለውጥ አለመለገምም ያስፈልጋል፡፡
እርግጥ ነው በግራኝ አህመድ ጦርነት ጊዜ እና በሁለተኛው የኢጣሊያ ጦርነት ጊዜ ከገጠሙን ድንጋጤዎች የተነሳ (ማለትም ካልጠበቅናቸው የቴክኖሎጂ መሳሪያዎች የተነሳ) ቴክኖሎጂን ለማወቅ እና ለመጠቀም ካደረብን ጉጉት የተነሳ በራችንን ሥልጣኔ ለተባሉ ሥነ-ርዕዮቶች ሁሉ (ፍልስፍናዎች ሁሉ) በመክፈታችን፣ ባዕድ አስተሳሰቦች እና ባህሎች ሰርገው ሊገቡብን ችለዋል፡፡ ዛሬ ዛሬ ግን ችግሩ ኢትዮጵያን ዐለማወቅ እና የተዛባ የበታችነት ስሜት ይመስለኛል፡፡ ነገር ግን “ትውልዱ፣ኢትዮጵያ ውስጥ ሰው ሆኜ ከምኖር አሜሪካ ሀገር ኮባ ሆኜ ብፈጠር ይሻለኛል፤ የሚል ነው” የሚለው አባባል ግን በጣም የተጋነነ፣ የጠላት ፕሮፓጋንዳ እና የጥቂት ባንዳዎች ቃል ነው፡፡
ኢትዮጵያ የገጠሟትን ጠላቶች ሁሉ እያሸነፈች በድል ተጉዛ፣ እዚህ የደረሰች እና በታሪክ ክብሯን ከፍ አድርገው የኖሩ ጀግኖች ልጆች የሞሏት ሀገር ናት፡፡ ንጥቂያ በተለይም የሉዐላዊነት ንጥቂያ ክፉ ኃጢአት እና ተኩላነት ስለሆነ አባቶቻችን አብረው ዘምተው ታግለውታል፤ እኛም እንታገለዋለን።
ለልዕለ ንጥቂያ ዘመቻውም ሆነ ለሌሎች አስተምህሮታዊ ችግሮች ተጠያቂው፣ አስተዳደጉ በት/ቤት የተበላሸበት እና በጥድፊያ እና በውክቢያ የሚኖረው የምዕራቡ ሀገራት ሕዝብ አይደለም፡፡ ኪነ-ጥበቡንም ድርሰቱንም ትምህርቱንም ገበያ መር ያደረጉት እና ለብዙኀኑ እና ለጉዳተኛው ሳይሆን ለጥቂት ከበርቴዎች የቆሙት፣ ገበያው የሚፈልገውን እንጂ፣ ገንዘብ እና ትርፍ ለሚያስገኘው እንጂ፣ እውነትን መናገር የሚቸግራቸው፣ እረኛ መሆን ሲገባቸው ራስ ወዳድ ተኩላ የሆኑበት የአመራሩ ክፍሎች ናቸው፡፡ ማለትም የፖሊሲ መሪዎች (ፖለቲከኞቹ)፣ የሐሳብ መሪዎች (ፈላስፎቹ)፣ የዕውቀት መሪዎች (አስተማሪዎቹ)፣የኪ-ነጥበብ ሰዎች ወዘተ… ናቸው፡፡  
ኢትዮጵያ ካወቋት እጅግ የምታኮራ ሀገር ናት፤ ራሳችንን መሆን አለብን፤ የራሳችንን ችግር በራሳችን ጸጋ ለመፍታት የምንጥር መሆን አለብን፤ ከወዳጅ ሀገራትም ጋር አብረን መሥራት አለብን፡፡ እኛን ከሚመስሉ ሀገራት ጋር በመተባበር ጭምር።  ራስን ለመሆንም ቁርጠኝነትን ማሳየት ይፈለግብናል፡፡
ሀገራችን ከጥንት አንስቶ ምድረ-ኩሽ፣ ኢትዮጵያ፣ ሀገረ-ሀበሻ፣ አቢሲኒያ ወዘተ… በሚሉ መጠሪያዎች እንደምትጠራ ይታወቃል። ኢትዮጵያ የሚለው መጠሪያ “ኢትዮጵግዮን” ወይም በሱባ “እንቅዮጳዝዮን” ከሚለው ቃል የመጣ እና “የግዮን ወርቅ” የሚል ትርጉም እንዳለው የሚናገሩ ጸሐፍት ብቅ ብለዋል። የቃሉ አመጣጥም “ኢትዮጵ” ከተባለ ንጉስ እንደሆነ ብዙዎች ያምናሉ፡፡ ኢትዮጵያ እንደ አንዳንዶች የ5 ሺህ፣ እንደ አንዳንዶች የ4 ሺህ፣ እንደ ሌሎች ደግሞ የ3 ሺህ ዓመት ታሪክ ያላት ጥንታዊት ሀገር ነች፡፡ ቀደምትነቷ ራሱ አንድ የኩራት ምንጭ ነው። የመጀመሪያው የምድሪቱ ነዋሪዎች የካም ነገድ ኩሻውያን ሲሆኑ ሀገሪቷንም ምድረ ኩሽ አሰኝተዋታል። በኋላም የሴም ነገዶች (አግአዛውያን)ተቀላቅለዋል፤ ማለትም እንደ ብዙ ታሪክ ጸሐፊዎች እምነት፡፡
አሁን ኢትዮጵያ ልዩ ልዩ ቋንቋን የሚናገሩ የብዙ ልሳነ-ህዝብ፣ የብዙ-ልሳነ ነገዶች (ብሔረሰቦች)፣ ልዩ ልዩ እምነትን ይዘው በመቻቻል እና በወንድማማችነት የሚኖሩ የበርካታ ሃይማኖቶች እና ማኅበረ-ሰቦች እናት ነች፡፡ ኢትዮጵያ በቅዱሳት መጻሕፍት ስሟ በተደጋጋሚ በክብር የተወሳ፣ በአምላክ የተመረጠች እና የተመሰገነች ሀገር ናት፡፡ ከነዚህም መካከል፡-
“ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች፡፡”
“ነብር ዥንጉርጉርነቱን፣ ኢትዮጵያዊ መልኩን ሊለውጥ ይችላልን?”
“እናንት እስራኤላውያን እናንተ ለኔ እንደ ኢትዮጵያውያን አይደላችሁምን?”
“ኢትዮጵያ የእውነት እና የፍትህ ሀገር ናት…ኢትዮጵያውያን ካልነኳችሁ አትንኳቸው።” የሚሉ ቃላቶች ይገኙበታል፡፡
ኢትዮጵያ እግዚአብሔርን የምታምን የሥልጡን ሃይማኖቶች ባለቤት ነች። የልጆቿ ገጸ መልክ፣  የአምልኮ መልኳና የቅድስናዋ መልክ ሳይለወጥ እንደምትኖር ተመስክሮላትና ከተመረጡት የአብርሃም ልጆች ከእስራኤላውያን ተካክላ እና ልቃም ስትመሰገን እናገኛታለን፡፡  ኢትዮጵያውያን በተክለ ሰውነታቸው፣ እግዚአብሔርን በመምሰላቸው እና በጽድቅ አኗኗራቸው  በታሪክ ሲደነቁ እናገኛለን፡፡
ኢትዮጵያውያን በመልካቸው ጠይም ዓሳ መሳዮች ወይም ቀይ ቡርቱካን መሳዮች ወይም ጥቁር ኑግ መሳዮች ናቸው፡፡ ከዚህም ጋር “ኢትዮጵያ የሚለው ቃል ከግሪክ የመጣ እና ትርጉሙም የተቃጠለ ፊት ማለት ነው፤ የሚለው ስህተት ነው፡፡” የሚሉ ግኝቶች እየወጡ ነው፡፡
ሌላውን የኢትዮጵያውያንን ገጽታ በሚመለከት የታሪክ ድርሳናት አጥጋቢ መረጃ እና ትንታኔ ባያቀርቡም (ብዙ ልንማርበት ስንችል ዕድሉን ባናገኝም) ገና ያልተፈተሹ እና ያልተጠኑ በርካታ የጥንታውያን መጻሕፍት (ድርሳናት) ክምችት መኖሩ እና የተመዘበሩም እንዳሉ እርግጥ ነው። ኢትዮጵያ የማንነቷ መገለጫዎች የሆኑ የሚያኮሩ ጥንታውያን ቅርሶች ባለቤት ነች። ከነዚህም ውስጥ የአክሱም ሐውልት፣ የላሊበላ ፍልፍል አብያተ-ክርስቲያን፣ የፋሲል ግንብ፣ የጀጎል ግንብ፣ የሶፍ ዑመር ዋሻ እና የጥያ ትክል ድንጋዮች ወዘተ… ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ የጀግኖች ሀገር በመሆኗ ለየትኛውም ኃይል ሳትንበረከክ እና ቀኝ ሳትገዛ ነጻነቷን ጠብቃ ለብዙ ሺህ ዘመናት የዘለቀች ታሪካዊት ሀገር ናት፡፡ ከዚህም በላይ ኢትዮጵያ የራሷ ፊደል፣ የራሷ ዜማ እና የራሷ መንፈሳዊ ባህል ያላት የጥንታዊ ስልጣኔ ባለቤት ናት። ስለዚህ ከታሪካችን እና ከባህላችን ጋር በርሷ ስም የእኛ ስም፣ በእኛ ስም የርሷ ስም እንደሚነሳ ዐውቀን፣ እጣ ፈንታ እና መክሊታችን በሆነችው ሀገራችን መደሰት እና መኩራት እንዲሁም ራሳችንን መሆን አለብን፡፡
ችግርም ካለ ኃላፊነቱን በጋራ እንውሰድ እና እንጀምር፡፡ ችግር ፈጣሪም የችግር ሰለባም መሆን ሳይሆን ችግር ፈቺ የመፍትሔ አካል ለመሆን እንጣር፡፡ ይህ ሁሉ እንደ ግለሰብም እንደ ኅብረተሰብም ራስን በመሆን መጀመርን የሚጠይቅ ነው፡፡
ይቀጥላል…
ይበል ደራሲ፡- ሰላም ለእናንተ ይሁን፡፡
ይበል አንባቢ፡- እንደ ቃልህ ይሁንልን፡፡Read 3973 times