Monday, 13 June 2022 00:00

“የተቀደሰውን ነገር ለውሾች አትስጡ”

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(1 Vote)

 ዋዜማ የተባለ ሬዲዮ ጣቢያ፤ ግብጽ ሱዳንና ኢትዮጵያ በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ጉዳይ በቅርቡ በተባበሩት አረብ ኢምሬት አስተናጋጅነት ለድርድር እንደሚቀመጡ ዘግቧል። ጣቢያው ያገኘውን መረጃ የበለጠ ለማረጋገጥ በኢትዮጵያ በኩል በድርድሩ ተሳታፊ የሆኑ ማብራሪያ ለመጠየቅ ቢሞክርም፣ ተጠያቂዎቹ  ምላሽ ከመስጠት መቆጠባቸውን ጣቢያው አመልክቷል። ጣቢያው ስማቸውን መግለጥ  ያልፈለጉ በጡረታ ላይ የሚገኙ ዲፕሎማት አነጋግሮ “ድርድሩ የሚቀር አይመስለኝም” የሚል  መልስ ሰጥተውታል።
ዲፕሎማቱ ወደዚህ መደምደሚያ የደረሱት የተባበሩት አረብ ኢምሬት መንግሥት በይፋም ሆነ  ይፋ ባልሆነ መንገድ ለኢትዮጵያ መንግስት ሲያደርግ የቆየውን ድጋፍ፣ በኢምሬቱ መሪ በሻህ መሐመድ ቢንዝያድና ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አሕመድ መካከል ያለውን ግንኙነት ከግምት ውስጥ በማስገባት መሆኑን ለመገንዘብ ይቻላል። የየአገራቱ ተወካዮች ወደ አቡዳቢ በተናጠል በመሄድ ውይይት ማድረጋቸውን ዋዜማ መዝገቡን ማውሳትም፣ ሶስቱ አገሮች አቡዳቢ ላይ ለድርድር መቀወጣቸው አይቀርም ወደሚል ድምዳሜ ይወስዳል። ኢትዮጵያና ግብፅ በጉዳዩ ላይ በይፋ የተናገሩት ነገር ባይኖርም ሱዳን የእምሬትን አደራዳሪነት እንደምትቀበል አስቀድማ ማሳወቋ ሳይጠቀስ አይታለፍም። ሱዳን የተቀበለችውን ድርድር ግብፅ ትገፋለች ለማለትም ያስቸግራል።
የእኛ የክረምት ወራት እየተቃረበ በመጣ ቁጥር እያደር አዲስ የሚሆነው የታላቁ የህዳሴ ግድብ ጉዳይ፤ ከሰሞኑ የግብጹን ፕሬዚዳንት አልሲሲንና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸውን  ወደ ዋሽንግተን ተከታትለው እንዲጓዙ አድርጓቸዋል። በራሺያና በዩክሬን ጦርነት፣ ግብፅ አሜሪካ የያዘችውን አቋም እንድትደግፍ ለማድረግ የታላቁ ሕዳሴ ግድብን ጉዳይ እንደ መጨዋቻ ካርድ በሩሲያ ዩክሬን ጦርነት የገለልተኛ አቋም የያዘችው ግብፅ፤ ወደ አሜሪካ ለመጠቅለል በህዳሴ ግድብ የአሜሪካንን ድጋፍ አስቀድማ ማረጋገጥ እንደፈለገች ጠቋሚ ነው-የፕሬዚዳንቷ የዋሽንግተን ጉዞ።
ድንበር ተሻጋሪ ወንዝ ያላት አገር ኢትዮጵያ ብቻ ባትሆንም የታችኞቹ አገሮች እረፍት ነስተው የሚያንገላቷት ደግሞ ኢትዮጵያ ብቻ መሆኗ ረገጥ ተደርጎ መነገር ያለበት እውነት ነው። አሜሪካና ቱርክ፣ ብራዚል፣ ራሺያና ሕንድ ከሌሎች አገሮች ጋር በሚጋሩት ወንዝ ላይ ግድብ ሲሰሩ ማንንም ያላማከሩ ምንም ደግሞ ማንም ሊያደርጋቸው እንዳልተነሳም ይታወቃል። የኢትዮጵያ ፈተናዋ የበዛው ግን እንደ ሌሎች አገሮች ክንደ ብርቱ ባለመሆኗ የተነሳ መሆኑን በግልጽ መገንዘብ ያስፈልጋል።
አበው ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል ይላሉ። ታላቁ የሕዳሴ ግድብ በሱዳንና በግብፅ ላይ የሚያስከትለው የከፋ ጉዳት አለመኖሩን ለማሳወቅ በማሰብ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በሶስቱ አገሮች መካከል ምክክር እንዲደረግ የከፈቱት በር፣ ቀስ በቀስ አድማሱ እየሰፋ መጥቶ- በኢትዮጵያ በኩል የአባይ ወንዝ ባለቤትነት መብትን የማስከበር፤ በግብፅና ሱዳን በኩል ደግሞ ሁለቱ አገሮች እ.ኤ.አ በ1929 እና በ1959 የተዋዋሉትን ውል የማስጠበቅ ያ ውል የሚሰጣቸውን መብትና ጥቅም ማጽናት አድርገውታል። ለአለፉት አስር ዓመታት በሶስቱ አገሮች መካከል የተደረጉት ድርድሮች ይህ ነው የሚባል መሰረታዊ ለውጥ ሳያመጡ በከንቱ የቀሩት ዋና ጉዳያቸው መብት በትክክል ከመትከልና ተገቢ ባይሆንም ጥቅማችንን አሳልፈን አንሰጥም በሚለው ሊላላ የማይችል ትንቅንቅ ጉዳይ መሆኑ እሙን ነው።
ኢትዮጵያ በቅንነት ከግብጽና ከሱዳን ጋር የጀመረችው ድርድር፣ ለናይል ተፋሰስ ትብብር ትሰጥ የነበረውን ትኩረት እንድትቀንስ አደረጋት። በአንፃሩ ግብፅ ከኮንጎ፣ ከታንዛንያ፣ ከኬንያ ወዘተ የተፋሰሱ አገሮች ጋር ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቷን ለማጠናከር ጊዜ ሰጣት። ቀስ በቀስም የናይል ተፋሰስ የትብብር ስምምነት ድጋፍ አግኝቶ፣ ሕጋዊ ሰነድ ከመሆን ይልቅ ሣር እየበቀለበት ሄደ። ከዚህ አንፃር በኢምሬት አስተናጋጅነት ይካሄዳል ተብሎ በሚታሰበው ድርድርም የባሰ ሊመጣ እንደሚችል በድፍረት ለመናገር ያግዛል።
በወቅቱ የአፍሪካ ህበረት ሊቀመንበር በነበሩት በአልጀሪያው ፕሬዚዳንት አንነሳሽነት የተጀመረው የ3ቱ አገራት፡- ግብጽ ሱዳና ኢትዮጵያ በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ የሚያደርጉት ድርድር፣ ችግሩ የአፍሪካ ጉዳይ እንዲሆን እድል አስገኝቷል። የዛሬ ሁለት ዓመት በግብፅ ጠያቂነት ወደ ዋሽንግተን ያቀናው ድርድሩ፣ ኢትዮጵያ አሜሪካ ያዘጋጀችውን አድላዊ ውል አልፈርም ብላ ስትወጣ፣ ግብፅና ሱዳን ረግጠውት ወደ ሄዱት መድረክ የተመለሱት። በግብፅና ሱዳን ጠያቂነት የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት ተደጋጋሚ ስብሰባ አድርጎ፣ የግብጾች ፍላጎት ሳይሳካ የቀረው ሩሲያና ሌሎች አገሮች ኢትዮጵያን ስለ ደገፉ ብቻ ሳይሆን “የአፍሪካን ችግር አፍሪካውያን ለመፍታት ይችላሉ” የሚል ተቀባይነት ያለው ሀሳብ በመኖሩ ነው። ድርድሩ በአቡዳቢ እንዲካሄድ ማድረግ ደግሞ ያለጥርጥር ኢትዮጵያ ይህን መተማመኛዋን እንድታጣ ያደርጋታል።
ሌላው አሳሳቢው ጉዳይ የአቡዳቢ የገለልተኛነት መሆን አቡዳቢ የአረብ ሊግ አባል አገር ናት፡ ሊጉ ግብፅ በአነጠሰች ቁጥር የሚሰበሰብ፣ ግብፅ ያቀረበችለትን አጀንዳ እንዳለ ተቀብሎ በማስተጋባት የሚታወቅ ነው። አቡዳቢ ከዚህ ትርቃለች ተብሎ አይታሰብም። በሱዳን ሰፊ የአርሻ ልማት የመጀመር እቅድ ያላት አቡዳቢ፣ ከዮርዳስና ከግብፅ ጋር በመተባበር፣ የግብፁን ቶሸካ ግድ በመጠቀም ሰፊ የእጓርሽ ልማት ለማካሄድ ማቀዷም እየተዘገበ ነው። በብዙ ድር ከግብፅ ጋር የተሳሰረችው አቡዳቢ፤ በኢትዮጵያ ጥቀሞች ጉዳይ ለኢትዮጵያ ታማኝ ዳኛ መሆን ትችላለች ወይ? ብሎ መጠየቅም ይገባል።
ይህ ድርድር እንደታሰበው በሶስቱ አገሮች መካከል የሚፈለገውን ስምምነት ባያመጣ፣ ጉዳዩን ወደነበረበት ወደ አፍሪካ ህብረት አደረዳሪነት መመለስ ይቻላል?
ግብፅና ሱዳን እንደለመዱት በተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት የህዳሴ ግድብን ሙሌት አጀንዳ ቢያደርጉት መመከት የሚያስችል እድል አለ? እጅግ ያሳስባል።
ታላቁ መጽሀፍ፤ “የተቀደሰውን ነገር ለውሾች አትስጡ ይላል። ለመንግስት የሚቀለው ምንጊዜም ስምምነት በማይገኝበት የግብፅና ሱዳን በድርድር ከመጠመድ ይልቅ አንደ አምናና ሃችአምና አንድም አይነት አስገዳጅ ውል ሳይፈርም፣ የህዳሴውን ግድብ መሙላት ነው። ግብፅና ሱዳን ሰማይ ደመና በያዘ ቁጥር ያዙኝ ልቀቁኝ የሚሉት ለመስማማት ሳይሆን የግድቡን የሥራ ጊዜ ለማባከን መሆኑም ሊገለጥልን ይገባል።

Read 9852 times