Saturday, 18 June 2022 17:29

ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ዝንጀሮዎች ሰዎች ላይ ጥቃት እየፈፀሙ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

 ከ8 ሚ. በላይ ሰዎች ለምግብ እጥረት ተጋልጠዋል
                                   
            ድርቅና የምግብ እጥረት በተከሰተባቸው የአገሪቱ አካባቢዎች ዝንጀሮዎች በሰዎችና ህጻናትና ከብቶች ላይ ጥቃት እየፈጸሙ መሆኑን “(ሴቭ ዘ ቺልድረን)”  ሰሞኑን ባወጣው ሪፖርት ጠቁሟል፡፡
በተለይ በምስራቅና በደቡብ ምስራቅ ኢትዮጵያ የተከሰተው ድርቅ፣ የዱር እንስሳትን መደበኛ ባህሪይ እየቀየረው መጥቷል ያለው ሪፖርቱ፤ ዝንጀሮዎችና ሌሎች እንስሳት መኖሪያ ቤት ድረስ በመምጣት መተናኮል ጀምረዋል ብላል፡፡ በተለይ ዝንጀሮዎች ህፃናትን ጫካ ውስጥ ሲያገኙ ጥቃት በመፈፀም የያዙትን ነገር እንደሚቀሟቸው ጠቁሟል፡፡
በምስራቅና ደቡብ ምስራቅ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት 185 ሺህ ያህል ህጻናት ለከፋ የምግብ እጥረት መጋለጣቸውን ያስታወቀው የህጻና አድን ድርጅት ሪፖርት፤ ህጻናት ተገቢውን እርዳታ እያገኙ አለመሆኑንና ለተለያዩ የጤና እክሎች መጋለጣቸውን አመልክቷል፡፡
የምግብ እጥረቱ ከዩክሬን  ጦርነት፣ ድርቁ ከመቀጠሉና፤ ከብር የመግዛት አቅም ከመዳከሙ ጋር ተያይዞም ቀጣይነት እንዳይኖረው ስጋቱን የገለፀው ድርጅቱ በዚህም በዋናነት አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ በእጅጉ እንደሚጎዳ ነው ያመለከተው፡፡
በአሁኑ ወቅት አብዛኞቹ አርብቶ አደሮች ከብቶቻቸው በድርቁ ምክንያት እንደሞቱባቸው የሚገልፀው ሪፖርቱ፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በረሃብ አፋፍ ላይ ይገኛሉ ብሏል፡፡
በርካቶች የቤት እንስሶቻቸው ከሞቱባቸው በኋላ ከአካባቢው እየተሰደዱ መሆኑን የሚያትተው ሪፖርቱ፤ ይህም በሌሎች አካባቢዎች ጫና እየፈጠረ ነው ብሏል፡፡
“የሴቭ ዘ ቺልድረን” ባልደረቦች በጉዞ ላይ አግኝተው ያጋገሯቸው የ40 ዓመቱ  አርብቶ አደር አቶ አህመድ ሲሆኑ የ7 ልጆች አባት ሲሆኑ ከቀያቸው ተፈናቅለው ምግብ ፍለጋ እየተንከራተቱ መሆናቸው ገልጸዋል፡፡
“ልጆቼን እንዴት አድርጌ መመገብ እንዳለብኝ  አላውቅም፣ ዝናቡ የለም ሳሩ ደርቋል። ፍየሎቼና  በጎቼ በሙሉ አልቀውብኛል፤ ታዲያ እዚህ ተቀምጬ ምን እሠራለሁ?” ሲሉ በተስፋ መቁረጥ ስሜት የጠየቁት  አቶ አህመድ፤ የልጆቻቸውን ህይወት ለማቆየት ምግብ ይገኝበታል ብለው ወዳሰቡት አካባቢ መሰደዱን እንደመረጡ ነው የተናገሩት፡፡
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ 8.1 ሚሊዮን ሰዎች በድርቅ ምክንያት ለምግብ እጥረት የተጋለጡ ሲሆን እነዚህን ጨምሮ 30 ሚሊዮን ሰዎችም የእርዳታ ጥገኛ መሆናቸውን የህጻናት አድን ድርጅቱ ሪፖርት ያመለክታል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ 12 ሚሊዮኑ ህጻናት መሆናቸው ታውቋል፡፡ በአየር ጠባይ ለውጥ ምክንያት ኢትዮጵያ ፣ሶማሊያና ኬንያ የገጠማቸው ድርቅ በአጠቃላይ 23 ሚሊዮን ሰዎችን ያጠቃ ሲሆን 5.8 ሚሊዮን ህጻናትም ለከፋ የምግብ እጥረት ተጋልጠዋል ብሏል ሪፖርቱ፡፡
በአሁኑ ወቅት በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ግጭትና ጦርነት ተከትሎ፤ የተከሰተው መፈናቀልና  በሁሉም ወገኖች ዘንድ ትኩረት ማግኘቱን የሚጠቁመው ሪፖርቱ፤ በደቡብ ምስራቅና በምስራቁ  የአገሪቱ አካባቢዎችያለው ድርቅ እንዲሁም ግጭትን ተከትሎ እየተፈጠሩ ያሉ ሰብአዊ ቀውሶች ግን በእጅጉ ትኩረት እንደተነፈጋቸው አመልክቷል አመልክቷል፡፡




Read 11429 times