Print this page
Saturday, 06 October 2012 15:12

ዘ - ሴክሬት “እውነት”

Written by  ሌኤሊኢሳኧ
Rate this item
(25 votes)

ዘ - ሴክሬት “እውነት”
“ዘ-ሴክሬት” ተብሎ በሀገራችን (ምናልባትም በአለም አቀፉ ደረጃ) በብዙ ኮፒ የተሸጠውን መጽሐፍ አላነበብኩትም፡፡ በብዛት ሲገዙ ሳይ የሚያስፈሩኝ መጽሐፍት አሉ፡፡ ምናልባት ብዛት እና ጥራት እንደማይጣጣሙ ስለማምን ይሆናል፡፡ ምናልባት፤ ብርሐን ውስጥ ጨለማ እንዲገባ የማልሻ “ጨለምተኛ” ስለሆንኩም ሊሆን ይችላል፡፡ ግን ብዛት ጥራትን እንደሚያሸንፈው አውቃለሁ፡፡ የጀርመን ናዚ የሚሰራቸው ታንኮች በጣም ጥራት ነበራቸው፡፡ በአንዱ ጥራት ያለው ታንክ፣ አስር የሩሲያ ታንኮች በፍጥነት ማምረት ይቻላል፡፡ በመቻላቸው፤ ብዛት ጥራትን አሸነፈ፡፡


“ዘ - ሴክሬት” የጠራ ፍልስፍናም፣ መንፈሳዊ ዶክትሪንም ….የጠራ ሳይንስም አይደለም፡፡ ኳንተም ሜካኒክስ የሚመስል፣ “ቋንጣ” ሆኖ ያልከረመ፣ ያልደረቀ ነገር ነው፤ ለእኔ፡፡ ይኼንን መጽሐፍ ለማንበብ የቡርዧ መንፈሴ ስላልፈቀደ በአስረጂ ፊልም መልክ አግኝቼ ተመለከትኩት፡፡ አንድ ሰአት ከግማሽ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ፡፡
ሚስጥር ተብሎ የቀረበው ሃሳብ በአጭሩ እንደሚከተለው ነው:- “መልካም ወይንም Positive ምኞትን ወደ ህዋ ስትለቅ… ህዋው ለጠየቅኸው ነገር መልሱን ይሰጥሃል” ይላል ሚስጥሩ፤ በአንድ አረፍተ ነገር ተጠቅልሎ ሲቀርብ፡፡
በመቀጠል:- “ህዋ ማለት ከአላዲን ምትሀተኛ ፋኖስ ውስጥ እንደሚወጣው ጂኒ ነው” ይላል፡፡ “ጂኒው ያዘዝከውን የተመኘኸውን ይፈጽማል፡፡ Your wish is my command እያለ…”
ምኞት እንዴት በአንድ በኩል ገብቶ በሌላ በኩል ተግባር እንደሚሆን ለመግለጽ የሚያገለግላቸው ያ የፈረደበት ኳንተም ቲዎሪ ነው፡፡ ሞገድ (Wave) ቁስ አካል (Particle) ይሆናል እና ተገላቢጦሽ የሚለው መሰረታዊ “የቋንጣ” (ኳንተም በ’ኔ አማርኛ) እሳቤ ማለቴ ነው፡፡
ስለዚህ ምኞት ሞገድ ከሆነ ተግባር ሆኖ የሚመጣው ደግሞ ቁስ ሆነ ነው ነገሩ፡፡ “የፀሎት መልስ” ከማለት የተለየች አይደለችም፡፡ በዲጂታል ዘመን የተፈጠረች “ከስተማይዜሽን” ከመሆኗ በስተቀር፡፡
ያም ሆነ ይህ፤ እንደ ሀሳብነቱ ተቀብዬው ከሀሳቤ ጋር ለማስማማት ስጥር ከረምኩ፡፡ በተለይ ከራሴ የህይወት ተሞክሮ ጋር ይጣጣም እንደሆን መመልከት ጀመርኩ፡፡
እኔ እስከማውቀው ድረስ፤ የደሞዝ ቀን በእርግጠኝነት ነገ ወይ ከነገ ወዲያ ይሆናል ብዬ ምኞቴን በተመኘሁ ጊዜያት ሁሉ ደሞዝ ሁለት ሳምንት ይዘገያል፡፡
በአንድ ስፍራ ላይ የቀጠርኩት ሰው በሰአት ይደርሳል ብዬ በተመኘሁ ጊዜ ሁሉ ተበሳጭቼ ሳልመለስ ቀርቼ አላውቅም፡፡ ጥሩ ሰው እንዲገጥመኝ በጠበቅሁበት አጋጣሚ ጥሩ የሚመስል መጥፎ ነው የሚገጥመኝ፡፡ …አሁን፤ የእውነት፤ የጳጳሱን ወይንም የጠ/ሚሩን ሞት ማን ተመኝቶ ያውቃል፡፡ ያልተመኘነው ነው የሚደርሰው፡፡
በየአዲሱ አመት መግቢያ ስኬታማ እንድንሆን፣ የኑሮ ውድነቱ እንዲቀንስልን፣ ደስተኛ እንድንሆን፣ ሰላም እና ጤና እንዲሰፍን ሳንመኝ ቀርተን አናውቅም፡፡ እና ምንድነው ነገሩ? ምንድነው ይህ “ዘ-ሴክሬት” የተባለ መጽሐፍም ሆነ ፊልም የሚለኝ፡፡ የሚፈልገውን ነገር የማያውቅ ሰው መቼም የለም፡፡ የሚፈልገውን ነገር ቁጭ ብሎ መመኘት ብቻ ሳይሆን የተመኘው ነገር እንዲሳካ መንገድ ከማመቻቸት ቦዝኖ የሚያውቅ ሰው…በሀገር ቤቴ ውስጥ አይቼ አላውቅም፡፡ እንዲያውም፤ እውነቱን ልናገር:- ብዙ ጊዜ ተስፋ ስቆርጥ ወይንም ልቆርጥ ስል ነው ተስፋ መተኪያ የሆነ ነገር የሚጥመኝ፡፡ አልከፈል ያለው የሚከፈለኝ፣ አልታይ ያለኝ የሚያየኝ፡፡
ምናልባት “ሚስጥሩ” ለኛ ሀገር የሚሰራው በተገላቢጦሽ ይሆን እንዴ?
..የእኛ አንድ አይን ጠፍቶ የጐረቤታችን ሁለት አይን እንዲጠፋ ስንመኝ
…ይሆን እኛ ባለሁለት እይታ፣ ጐረቤታችን ባለ አራት የሚሆንልን?
ስለ ሞገድ እያወራን ከሆነ፤ ፈረንጅ የምኞት ሞገዱን የሚያስወነጭፍበት ጂኦግራፊያዊ ቦታ ከምድር ወገብ የራቀ በመሆኑ… መልካም ሲመኝ መልካም እንደሚገጥመው ሊያምን ይችላል፡፡ እኛ በራሳችን መንገድ ነው ምኞታችን የሚሰራው ብንልስ?...ፖዘቲቭ ሞገድ ፖዘቲቩን ይገፋል ይሉናል ምዕራባዊያን፡፡ በሌላ የእውቀት ዘርፍ በኩል ደግሞ!
መልካም ሃሳብ እየተመኘን፤ መልካሙ ምኞታችን ተሳክቶ ሊያሳካን ወደኛ ሲገሰግስ መልካም ሆነን ከቆየነው… ተመሳሳዩ ሞገዶች ይገፋፉና እንደተራራ መልካሙ መልካም ሳይገጥመው ይቀራሉ፡፡ ይህ ነው የአገር ቤት “ምስጢራችን” ፍቺ፡፡ ለማንኛውም ግን “የዘ-ሴክሬት” ምስጢር ለእኔ ባይገባኝም ብዙሀኑ ገብቶት ገዝቶታል፡፡ ከጥራት ብዛት ይበልጣል፡፡

 

Read 34330 times Last modified on Saturday, 06 October 2012 15:20