Saturday, 18 June 2022 17:29

አገራዊ ምክክሩ ከድርድሩ ሊቀድም ይገባል ተባለ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(4 votes)

 "አገራዊ ምክክሩ በመካከላችን ያለውን ጥላቻና ያልጠራ ስሜት ያክማል"
                    
            በመንግስትና በህውኃት ታጣቂ ሀይሎች መካከል ሊደረግ ታስቧል ከተባለው ድርድር በፊት አገራዊ ምክክሩ ሊቀድም እንደሚገባውና መንግስት በወሳኝ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ከዜጎች ጋር መክሮ ውሳኔ  ማሳለፍ እንዳለበት ተገለጸ። ታሪክ፣ ህገ-መንግስትና ሰንደቅ ዓላማ ከዜጎች ጋር ግልጽ ውይይትና ምክክር ሊደረግባቸው ከሚገቡ አገራዊ  ጉዳዮች መካከል ዋነኞቹ ናቸው ተብሏል።
የብሔራዊ እርቅና አገራዊ መግባባት አስፈላጊነትና ጥቅም ላይ ሰፊ ጥናት ያካሄዱት የፖለቲካ ምሁሩ ዶ/ር ሰለሞን ተስፋዬ ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፤ አገራዊ መግባባትና ምክክሩ ኢትዮጵያ የተጋፈጠቻቸው  ዘርፈ ብዙ ችግሮች ተባብሰው ወደ ከባድ ቀውስ እንዳትገባ በማድረግ፣ መፍትሄዎችን  በሰላማዊ መንገድ ለማበጀት ያስችላል ብለዋል።
ሁሉንም ተሳታፊ የሚያደርግ አገራዊ ምክክርና ብሔራዊ እርቅ፣ ጦርና የጦር ታሪኮችን ለማስቀረት የሚያስችል ብቸኛው መንገድ ነው ያሉት  ምሁሩ፤ በግለሰቦች መካከል ያለውን ጥላቻና ያልጠራ ስሜት ለማከምም ያገለግላል ብለዋል፡፡
በብሔር ግጭትና ንትርክ፣ በድርቅና በጦርነት መከራዋን እያየች ባለች አገር ከብሔራዊ እርቅና አገራዊ ምክክር ልናስቀድመው የሚገባን ጉዳይ አይኖርም ያሉት የፖለቲካ ምሁሩ፤ እንደ ታሪክ ሰንደቅ ዓላማና ህገ-መንግስትን በመሳሰሉ እጅግ መሰረታዊ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ያሉትን ልዩነቶች ለማጥበብ ህዝባዊና አገራዊ ምክክሮች ማድረጉ እጅግ አስፈላጊ ነው ብለዋል።
አገራዊ ምክሩ በልሂቃንና በፖለቲከኞች መካከል ብቻ የሚደረግ መሆን የለበትም የሚሉት  ዶ/ር ሰለሞን፤ በብዙ መሰረታዊ ጉዳዮች በዜጎች መካከል የተፈጠሩ ቅራኔዎች እያደጉና እየሰፉ ሄደው ሀገር ወደማፍረስ ደረጃ እየደረሱ መሆኑን ጠቅሰው፤ በእነዚህ መሰረታዊ ቅራኔዎች ላይ ሁሉም ህብረተሰብ በጋራ ሊመክርና  ቅራኔዎቹን በሰላማዊ መንገድ ሊፈታ እንደሚገባም አብራርተዋል።
#ከህውሓትም ይሁን ከማንኛውም ሰላም ፈላጊ ወገን ጋር የምንፈልገው ሰላም ነው። የሚቻል ከሆነ ለሰላም መቆም ችግር የለውም። ይህን ማለት ግን በድብቅ ድርድር እናደርጋለን ማለት አይደለም።; በማለት ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ሰሞኑን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያደረጉትን ንግግር ተከትሎ የህውሓት ኃይሎች ለድርድር ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡
ህወሓት በኬኒያ መንግስት አሸማጋይነት በሚካሄድ ድርድር ላይ ለመሳተፍ ዝግጁ መሆኑን በገለጸበትና በዶ/ር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል ተፈርሞ በተሰራጨው ደብዳቤ፤ ቡድኑ ከዚህ በፊት ለድርድር ያቀረባቸው ቅድመ ሁኔታዎች አለመካተታቸው  ታውቋል።
ዘላቂነት ያለው ሰላም እውን ለማድረግና በአገራዊ ምክክሩ ሁሉም ወገን አሸናፊ ሆኖ የሚወጣበት ሁኔታ ለመፍጠር ከድርድሩ በፊት ምክክሩ ሊቀድም እንደሚገባ ምሁሩ አስረግጠው ይናገራሉ፡፡  
በወልዲያ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህሩ አቶ ሲሳያስ ታምሩ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ለዓመታት የዘለቁና ብዙ ዋጋ ያስከፈሉ ለቅራኔና  ግጭቶች መነሻ የሆኑ ጉዳዮች ስላሉ በነዚህ ጉዳዮች ላይ በጥልቀት ተወያይቶ አገራዊ መግባባት ሊፈጥር የሚችል መፍትሄ ማበጀት ያስፈልጋል ይላሉ፡፡  በኢትዮጵያ ውስጥ በተሳሳተ የታሪክ ትርክት፣ በሀገረ መንግስት ግንባታ ሂደትና በወደፊት ፍላጎቶች ላይ ሰፊ ቅራኔዎች መኖራቸውን አመልክተው፤ እነዚህ ቅራኔዎች ባልተፈቱበትና ዜጎች በመሰረታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ አቋም ባልያዙበት ሁኔታ ድርድር ለማድረግ መሞከር አደገኛ ውጤት ይኖረዋል ብለዋል።
በኢትዮጵያ መፃዒ ዕድል ላይ ለመወሰን ብሔራዊ መግባባትና አገራዊ ምክክር ማድረግ ወሳኝነት ያለው ጉዳይ ነው ያሉት የፖለቲካል ሳይንስ መምህሩ፤ ለዚህም መንግስት የታሪክ ምሁራንና የማህበረሰብ አንቂዎች የየበኩላቸውን ሚና ሊጫወቱ ይገባልም ብለዋል፡፡




Read 11594 times