Print this page
Saturday, 18 June 2022 17:40

በአዲስ አበባ የዶሮ በሽታ ከፍተኛ ስጋት ፈጥሯል

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(5 votes)

         - እስከአሁን በበሽታው ከ50ሺ በላይ ዶሮዎች ሞተዋል
         - በአቃቂና ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተሞች ስርጭቱ በስፋት ይታያል
         - ህብረተሰቡ የዶሮ ስጋና እንቁላል ከመመገብ እንዲቆጠብ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል
         - ግብርና ሚኒስቴር ወደ ከተማዋ በሚገቡ ዶሮና እንቁላሎች ላይ እገዳ ተጥሏል
                
               በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ተከሰተ የተባለው “ያልታወቀ” የዶሮ በሽታ ለአገሪቱ በተለይም በመዲናዋ አዲስ አበባ ከፍተኛ ስጋት ፈጥሯል። በሽታው  በሰዎች ላይ ስለሚያስከትለው የጤና ችግር ለማወቅ ምርምር እያደረገ መሆኑንም የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት አስታውቋል።
የግብርና ሚኒስቴር ሰኔ 3 ቀን 2014 ዓ.ም  በሰጠው መግለጫመሰረት፤ በዚሁ የዶሮ በሽታ ሳቢያ ከ50 ሺ በላይ ዶሮዎች መሞታቸውንም አስታውቋል። ሚኒስቴር መ/ቤቱ የበሽታው ምንነት ባለመታወቁና በሰዎች ላይ  የሚያስከትለው የጤና ችግር ባመለየቱ ምክንያት ከተለያዩ የክልል ከተሞች ወደ አዲስ አበባ በሚገቡና ከውጪ አገር በሚመጡ እንዲሁም ወደ ውጪ አገር ሊላኩ የተዘጋጁ እንቁላሎች፣ የተፈለፈሉ ጫጩቶችና ዶሮዎች ወደ ከተማው እንዳይገቡ አግዷል። ግብርና ሚኒስቴር በዚሁ የእግድ ደብዳቤው፣ በተለያዩ አካባቢዎች የዶሮ ሞት ክስተት እያጋጠመ በመሆኑ ችግሩ ተጣርቶ መፍትሄ እስከሚሰጥበት ጊዜ ድረስ ገቢና ወጪ ዶሮና የዶሮ ውጤቶች ላይ እግድ ጥሏል። የተጣለውን እግድ ተላልፈው ወደ ከተማዋ ምርቶችን በሚያስገቡ ሰዎች ላይ እርምጃ እንደሚወስድም ገልጿል።
የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት በጉዳዩ ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑንና በሽታው በሰዎች ላይ ሊያደርስ የሚችለውን ጤና ችግር ለማወቅ ናሙና ተወስዶ  ምርምር እየተካሄደ መሆኑን እስከ አሁን ግን በሰዎች ላይ የደረሰ የጤና ችግር አለመገኘቱን አመልክቷል።
የኢትዮጵያ ዶሮ አርቢዎች ማህበር ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ቴዎድሮስ ካሳሁን ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፤ በተከሰተው የዶሮ በሽታ ሳቢያ በዶሮ እርባታ ስራ ላይ ተሰማርተው በሚገኙ የማህበሩ አባላት ላይ የደረሰው ኪሳራ እጅግ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው በሽታው በሰው ላይ ሊያስከትል የሚችለውን የጤና ችግር ለማወቅ የሚደረገው ምርምር በአፋጣኝ ተጠናቆ ወደ ስራው መመለስ እንደሚፈልጉም ተናግረዋል።
በኦሮሚያ ክልልና በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ተሰራጭቷል የተባለው ይኸው የዶሮ በሽታ፤ በቢሾፍቱ ከተማ፣ በአቃቂ ቃሊቲና በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተሞች በስፋት ተሰራጭቶ መታየቱ ተገልጿል።
በሽታው መከሰቱ ከታወቀበት ጊዜ ጀምሮ ከግብርና ሚኒስቴርና ከሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየሰሩ መሆናቸውን ለአልዓይን የገለጹት የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ሃይሉ፤ የዶሮ በሽታው በተከሰተባቸው በቢሾፍቱ አቃቂ ቃሊቲና ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተሞች ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች የዶሮ ስጋና እንቁላል ከመመገብ እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።


Read 11946 times