Saturday, 18 June 2022 17:48

"የራሷ ሲያርርባት የሰው ታማስላለች!"

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

  ከሃያ ዓመታት በፊት የሚከተለውን ተረት ተርከነው ነበር። ሆኖም ከዚያ በባሰ ሁኔታ ውስጥ የምትገኘው አገራችን ደግመን እንድንለው አድርጋናለች!
ከዕለታት አንድ ቀን ሁለት ያገር ቤት ወንድና ሴት፣ ዕድሜያቸው ከገፋ በኋላ ተገናኝተው፣ በባልና ሚስትነት አብረው መኖር ጀመሩ። ባልየው ሁሌ የመከፋት ምልክት ይታይበት ነበርና ሚስቲቱ ሁሌ ትጨነቅ ነበር።
አንድ ቀን ግን፤
“ባሌ ወዳጄ፣ እንኳን ደስ አለን” አለችው
“ምን ተገኘ?” አላት።
“የወር አበባዬ ከቀረ ሦስት ወር አለፈ”
“እንዴት?” አለ በድንጋጤ።
“እርጉዝ ነኝ!”
“አዬ ጉድ! ሌላ መከራ!” አለና አቀረቀረ።
“ለምን ሌላ መከራ አልክ?” ብላ ጠየቀችው።
“ተይኝ ባክሽ። የደረሰብኝን መከራ ሁሌ ልነግርሽ አስብና ተመልሶ ይመጣ እየመሰለኝ ደንግጬ እተወዋለሁ።;
“ባክህ ስለመከራህ ልወቅ” ብላ ወተወተችውና አወጋት፡-
“ባገራችን በሽታ ገብቶ ብዙ ሰው አለቀና የመንደሩ ጥቂት ሰዎች ተረፍን። ከተረፍነውም ጉልበት የነበረኝ እኔ ብቻ ነበርኩኝ። ሰው ሁሉ አልቆ ቀባሪ በታጣበት ሰዓት አባትና እናቴ በአንድ ቀን ልዩነት ተከታትለው ሞቱ። ቤታችንን ዘግቼ መቃብር ስቆፍር ዋልኩና ሁለቱንም ባንድ ጉድጓድ ልቀብር በቅድሚያ ያባቴን አስክሬን ወስጄ መቃብሩን አድርሼ የናቴን ላመጣ ተመለስኩ። የእናቴን አስክሬን አውሬ በልቶት ራስ-ቅሏን ብቻ አገኘሁ። አዝኜ ወደ አባቴ ስሄድ እሱንም አውሬ በልቶታል። አንዳቸውንም ሳላድን ቀረሁ። ሌትና ቀን ይሄው ሰቀቀኑ አልለቅ ብሎኝ  አለቅሳለሁ!;
 እሷም፤
“ከኔ የባሰ መከራ የደረሰበት ያለ አይመስለኝም ነበር።; አለችው።
“ያንቺስ ምን ነበር?” ሲል ጠየቃት።
“እኔ ባሌና ሶስት ልጆቼ ረሀብ ገባና ተሰደድን። ዝናብ ዘነበ- ሀይለኛ። ባሌ ሶስቱን ልጆች ተራ በተራ አመላልሶ እኔን ሊወስድ ሲመጣ ጎርፍ በጣም ሞላና ወሰደው። ብቻዬን ቀረሁ። እንግዲህ የቀረኝ ይሄ ሆዴ ውስጥ ያለው ፅንስ ነው።;
“አይዞሽ! የባሰ አታምጣ በይ! ልጅሽን ይባርክልሽ። ያለፈውን ረስተን ለነገ እንኑር!” አላት ይባላል።
***
ረሀብ፣ ድርቅና ጦርነት ዛሬም ያልተለያት አገራችን፣ የህዝቧን ጽናትና የመንግስቷን ጥንካሬ ትማጸናለች። በሄደች ቁጥር መንገዱ ይረዝምባታል። በዙሪያዋ ያሉት ጎረቤቶቿ ሁሉ ዐይናቸው በእሷ ላይ እንደቀላ ነው። ደግነቱ ዘንድሮ ቢያንስ ስፖርቱ እየካሣት ነው- ሳይደግስ አይጣላም!
የአንድ አገር ዲፕሎማሲ ከሽርሽር ባለፈ ሊታሰብ ይገባዋል። የአገር መሪ ክብር፣ የአገርና ህዝብ ክብር መሆኑን አለመዘንጋት ሀላፊነትን መወጣት ነው። መከራ ሲደራረብ ተስፋችን፣ የልብ ጽናትና ሀሞትን መራር ማድረግ ይጠይቃል።
የፖለቲካው ሁኔታ ሲጠነክር፤ መቼም ቢሆን-
“ነገሩ አልሆን  ብሎ፣ ሁኔታው ሲጠጥር
ጠጣሩ እንዲላላ፣ የላላውን ወጥር።;
ማለትን እንመርጣለን - እንደ ገሞራው። ጠጣሩ እንዲላላ ግን የእኛን መጠጠር ይጠይቃል። ለዚህ ደግሞ የንቃተ ህሊናችን መዳበር እጅግ ወሳኝ ነው። የንቃተ ህሊናችን መዳበር የሚመጣው አንድም ከዕውቀት፣ አንድም በኑሮ ከመብሰል ነው! አንድም በፊደል ´ዋ´ ብሎ፣ አንድም በኑሮው ዋ! ብሎ እንደተባለው ነው።
ገጣሚው፤
ዋ!
እግረ-ቀጭን ብጤ፣ ጭንቅላተ- ክብ
ፊደል ናት፣ ሆሄ ናት፤ እንደሌላ ራብ
መች ያጣዋል እሱ፣ ፊደል የቆጠረ
´ዋ´! ብሎ ከቀረ፣ ዋ! ብሎ የኖረ!!
ያለው ወዶ አይደለም፡፡ መጠንቀቅና ማስጠንቀቅ ደግ ነው። በምንጓዝበት የለውጥ ጎዳና ከጎረቤት አገሮች ጋር ካለን ግንኙነት ጋር ዲፕሎማሲያዊ መጣጣም እንጂ በጦርነት እጅ የሚያስጠመዝዝ ሁኔታ ውስጥ የሚከትተን መሆን የለበትም። ለዚህም  የአገር ወዳዶችን ምክር ማዳመጥ በጣም ወሳኝ ነው። የአገር ውስጥ ችግራችንን ለመፍታት መትጋትን ቅድሚያ እንስጥ እንጂ ለጎረቤት አገር ድግስ ላይ-ታች የምንል ከሆነ፣” የራሷ ሲያርርባት የሰው ታማስላለች” የሚለው ተረት አስፈጻሚዎች ሆንን ማለት ነው!
ከዚህ አባዜ ይሰውረን።

Read 12270 times