Monday, 20 June 2022 00:00

ሚዛን የያዙ፣ ሰይፍ የታጠቁ።

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(2 votes)

 “የፍትህ እመቤት” ይሏታል። ትርጉሟ ወይም መልዕክቷ፣… እኛ “በሕግ አምላክ” ከምንለው አገላለፅ ጋር ይቀራረባል። እንዲህ ዓይነት ስያሜዎችና ምስሎች፣ አንድ ልዩ ባሕርይ አላቸው። የተማረውንና መሃይሙን ሁሉ ወደ “እኩልነት” ያጠጋጋሉ። እንደ ኪነጥበብ ናቸው።
የፍርድ ቤትና የዳኝነት ሥርዓትን፣ የህግ እና የፍትህ መርሆችን፣… በብዙ ቃላት ተንትነን ለማወቅ ቢከብደን፣… በአጭሩ፣ “በሕግ አምላክ፣ በፍትህ አምላክ” ብለን መናገር አያቅተንም። “የፍትህ እመቤት ትፋረደኝ” ብሎ ስሜቱን ለመግለፅ የሚከብደው ሰው አይኖርም።
ቃል መተንፈስ ላያስፈልግም ይችላል።
“ሚዛን ያንጠለጠለች፣ ሰይፍ የጨበጠች እመቤት” አለችልን። ሐውልቷን አላያችሁም? የፍትህና የሕግ ጉዳይን፣ በብዙ መፃሕፍት ተተንትነው አይጨርሱትም። በእልፍ አዋጆችና አንቀፆች ተዘርዝሮ፣ በምዕተ ዓመታት ተተርኮ አያልቅም። እንኳን የሕግ ሙያተኛ ላልሆነ ሰው ይቅርና፣ ለሕግ አዋቂዎችም ይከብዳል። ቀላል ስራ አይደለም።
ታዲያ፣ ለቁጥር ለስፈር የሚያስቸግረውን የሐተታና የታሪክ ዓይነት በሙሉ ጠቅልለን፣ “በአንድ ትንፋሽ መናገር”፣ ወይም “በአንድ ቅፅበት ማየት” ብንችል አስቡት። ደግሞም እንችላለን። ቢያንስ ቢያንስ እንሞክራለን። “በሕግ አምላክ” እንላለን - በምናባችን አንዳች ሕያው አካል እየቀረፅን፣ በዓይነ ልቦናችን እየተመለከትን እንናገራለን። ሰውም ይገባዋል። ሁሉም ሰው ባይሆንም፣ ብዙዎቹ ይገባቸዋል።
“በሕግ አምላክ” ከተባለ፣ ወይ “ሕግ ይዳኘን” የሚል አቤቱታ ነው። ወይ፣ “ሕግ ፊት እገትርሃለሁ፤ በሕግ ትጠየቃለህ” የሚል ማስጠንቀቂያ ይሆናል። አንዳንዴ ደግሞ፣ እንደ  ተግሳጽና እንደ ቁጣ ነው። “ኧረ በሕግ አምላክ!” ቢላችሁ፣…”ኧረ ዝም በሉ፤ ኧረ በቃ” እንደማለት ነው።
“በሕግ አምላክ”፣… በዘወትር አባባል የሚያስተላልፈው መደበኛው መልዕክት ግን፣ “የሕግ ያለህ! የፍትህ ያለህ” ከሚለው ጥሪ ጋር ይቀራረባል። ለዚህ ጥሪ ምላሽ የሚሰጥ ነው - “የሕግ አምላክ”። በሕግ አምላክ የሚለው አባባል ውስጥ፣ “ሕግ አለ”፤ “ፍትሕ አለ”፤ “ሁሌም ይኖራል”፤ ወይም “መኖር ይገባዋል” የሚል መልዕክት እናገኝበታለን።
ወይም ደግሞ፣ ሕግንና ፍትህን፣ በአካል እንድትላበስ የተቀረፀችውን ምስል ማየት ይቻላል።  “የፍትህ ያለህ! የፍትህ ያለሽ! ብሎ ለሚጮህ ሰው፤ “የፍትሕ እመቤትን” እንዲመለከት እንጠቁመዋለን። እንደ መጽናኛም፣ እንደ ማበታቻም ነው። ፍትህ ሲዛባ ወይም ሲጓደል፣ “ፍትህ የለም፣ ፍትህ የውሸት ነው” ብሎ ተስፋ እንዳይቆርጥ፣ “የሕግ አምላክን” ያስታውሳል። አንገቱን ቀና አድርጎ፣ የፍትሕ እመቤትን ሐውልት ያያል።
ጥሩ ዘዴ ነው። የሐተታ ሸክምን ያቃልላል። የትረካ ጊዜን ለማሳጠር ይጠቅማል። “የስንፍና ዘዴ፣ የመታከት ውጤት” እንዳይሆኑ እስከተጠነቀቅን ድረስ፣ ምናባዊ ምስሎችና ስያሜዎች ሐውልቶችና ምልክቶች የግድ ያስፈልጋሉ። ሀሳቦችን በአካል እንደማየት ቁጠሯቸው።
የስነ-ምግባር መርሆዎችንና የጀግንነት ገፅታዎችን የሚተነትን ትምህርትን አስቡና፣ ከዚያ በኋላ ከድርሰት ጋር አነፃፅሩት። ኪነጥበብ፣ ሀሳቦችንና ሐተታዎችን ሳይተነትን፣ ሁሉንም አቀናብሮ፣ ሕይወት ይዘራባቸዋል፤ በአካል ያሳያችኋል።
“ጀግንነትና ፅናት ማለት”፣… እያለ አይተነትንም፤ አይዘረዝርም። ጀግንነትን በአካል፣ “እከሌ”… “እከሊት”… ብሎ ያሳያችኋል - ጀግናውንና ጀግኒትን። ፅናትንም፣ በአካል ያገኛችሁት እስኪመስላችሁ ድረስ፣ ሕይወት አልብሶ ያቀርብላችኋል - በውጣ ውረድ ውስጥ ሲጓዝ ያሳያችኋል።
በሃሳብ  ለማስረዳት ሳይሆን፣ ሃሳብን በእውን ከፊታችሁ አምጥቶ ያገናኛችኋል። በአካል ያስተዋውቃችኋል። ልክ እንደዚያው፣ ጽናትን በሃሳብ ሳይሆን በተግባር፣ ጀግኖች በሚያስጨንቅ አጣብቂኝ ውስጥ አስገብቶ፣ ተስፋ በሚያስቆርጥ መከራ ስር፣ የሞት ሞታቸውን ሲታገሉ፣… እዚያው በቦታው ተገኝታችሁ፣ በሰቀቀንና በተስፋ መጨረሻቸውን ለማወቅ፣ ልባችሁ እያንጠለጠለ ያስጨንቃችኋል።
ጥረው ግረው በማይሻግሩት ዓይነት አዘቅት፣በረመጥ የመከበብና የመንገብገብ ስቃይ መሃል፣ በሞት ሽረት ትርምስ ውስጥ ሲሟሟቱ፣… በአንድ በኩል፣ በበደል ላይ ግፍ ሲጨመርባቸው፣ ወይም በሌላ በኩል፣ በደልን በፍትህ ሲሽሩ፣… በአካል በእውን ያሳያል (ድርሰት፣ ትያትር፣ ፊልም፣ ድራማ)። በአካል ከጀግኖች ጋር ያስተዋውቀናል። የጀግንነትን ውጣ ውረድና የጽናት ፍልሚያውን በእውን ያስቃኘናል።
ጀግኖች ሃሳቦች አይደሉም። ስም ያላቸው ሰዎች ናቸው - ባለታሪኮች። ምናባዊ ምስሎች ናቸው፤ ግን ሊጨበጡ ሊዳሰሱ የሚችሉ።
የኪነጥበብ ስራዎች፣ የተግባር ምክሮችን አይተርኩም። የተግባር ሕይወትንና ሕልውናን፣ በግልቢያ ወይም በእንፉቅቅ ያሳያሉ እንጂ።
ድርሰቶችና ድራማዎች፣ ደረጃቸውና ቅኝታቸው ቢለያዩም፣ ሃሳብን በአካል የሚሳዩና የሚስጨበጭቡ የፈጠራ ምስሎች ናቸው ማለት ይቻላል። የሆነ ሃሳብን ለመረዳት ወይም ለመግለፅ ስትፈልጉ፣ አእምሮን ቦግ የሚያደርግ ጥሩ ምሳሌ ብታገኙ እንዴት ነው? ጥሩ ማሳያ የሚሆን ምሳሌ፣ ከድርሰት እናገኛለን። በአርአያነት የሚጠቀሱ የሰው (የገፀ ባህሪ) ምሳሌ፣ ወይም የተግባር (የትረካ) ምሳሌ፣ ሃያል ጉልበት አላቸው። ሀሳቦችን አግዝፈውና አጥርተው ያሳዩናልና። የጀግኖች ዓለምና ውሎ ውስጥ ገብተን የመኖር፣ የዓይን ምስክርም የመሆን ያህል ነው - ኪነጥበብ።
የሃይማኖት ትረካ ውስጥ የምናውቃቸውን ምሳሌዎች አስታውሱ። “እንደ ወጣቱ ዳዊት” ብለን መናገር እንችላለን። ለምን? የጀግንነት ሃሳብን፣ በአንድ ጀግና አርአያት ለማሳየት።
“ከግዙፉ ከጎልያድ ጋር የተፋጠጠበት የዳዊት ፍልሚያ!” ብለንም ትረካውን እንደ ምሳሌ እናነሳለን። የጀግንነት ሕይወትን በተግባር ለመቃኘት ማለት ነው።
የጎልያድ ግዙፍነትንና ሃያልነትን አስቡት። አንድም ሰው ሊቋቋመው አልቻለም። ሊፋለሙት የደፈሩ ሃያል ጦረኞች፣ ወኔያቸው አስደናቂ ቢሆንም፣ ከጎልያድ ጋር ሲነጻጸሩ፣ እንደ ጠጠር እንደትንኝ ናቸው። አጠገቡ አያደርሳቸው። አፍታ አያቆያቸውም። ገና ከሩቅ ይጨፈልቃቸዋል። አንጠልጥሎ ይሰብራቸዋል። ሃያል ጦረኞች አይችሉትም። አይሞክሩትም።
ቁመቱ ስድስት ክንድ ከአንድ ስንዝር ነው ይላል - ትረካው። ሦስት ሜትር ወይም ከዚያ በላይ ማለት ነው። በግዝፈቱ ላይ ሃያልነቱ፤… በእጁ የያዘው ጦር፣ ከ8 ኪ.ግራም በላይ ይመዝናል። ከነሀስ የተሰራ ቆብ (ቁር) አድርጓል። ከአንገት እስከ ደረቱም፣ ከነሀስ የተሰራ መከላከያ ጥሩር ለብሷል። የጥሩሩ ክብደት 70 ኪ.ግራም እንደሆነ በትረካው ተገልጿል። ሃያልነቱ የግዙፍነቱ ያህል ነው።
ምን ይሄ  ብቻ? ጦረኝነት፣ ለጎልያድ፣ ከልጅቱ ጀምሮ ያደገበት ሙያው ነው።
ዳዊት ግን ጦረኛ አይደለም። መከላከያ ጥሩር ለብሶ አያውቅም፤ ጋሻና ጦር መታጠቅ አልለመደም።
የበጎች እረኛ ነው። በእርግጥ፣ ብርቱ ወጣት ነው። በጣም ግዙፍ ባይሆንም፣ ጠንካራ ነው። በጎቹን ለአውሬ አሳልፎ አይሰጥም። ከአንበሳ ጋርም ቢሆን ይታገላል። በጎቹን ከአንበሳ መንጋጋ ያስጥላል። አንሳን በክርኑ ያሸንፋል። ቢሆንም ግን፣…
ጎልያድን መፋለም ያስፈራል። በጎልያድ እጅ ውስጥ ከገባ አለቀለት። ጥሩር ሊያለብሱት፣ ሰይፍ ሊያስታጥቁት ሞክረዋል። ግን፣ ያልለመደው ትጥቅ፣ ከጥቅሙ ጉዳቱ ይበልጣል። በወጉ ለመንቀሳቀስም ከበደው። ከልምምድ ጋር፣ የጦርነት ትጥቅ ጠቃሚ ቢሆንም፣ ለጊዜው ግን፣ ሸክሙ ብሷል። ያለበሱትን ያስጨበጡትን ትጥቅ መለሰላቸው።
በጎቹን ለመጠበቅ እንደሚያደርገው፣ በእረኛ አለባበስ ወይም ያለልብስ፣ ጎልያድን ለመፋለም ተዘጋጀ። ወንጭፉን ጨበጠ። ከወንዝ ዳር፣ አምስት ድቡልቡል ጠጠሮችን መርጦ ያዘ። ፍልሚያው ያስፈራል። ቢሆንም ግን፣ ዳዊት፣ የራሱን ችሎታና ብቃት ያውቃል። የጦር የጎራዴ ችሎታ የለውም። ወንጭፍ ግን በእጁ ነው። ችሎታውን አውቋል። የአቅሙን ያህል ችሎታውን ተጠቅሞ ለመፋለም ተዘጋጅቷል።
ከአማራጮቹ ሁሉ፣ የሚሻለውን መንገድ መርጧል። እንዲያ ባላደረግኩ ኖሮ፣ እንዲያ ባላደገርኩ ኖሮ… ብሎ የሚጸጸትበት ነገር የለም።
ከዚህ በኋላ በሙሉ ሃሳብ፣ በሙሉ አቅም፣ በሙሉ ልብና በሙሉ መንፈስ መፋለም ነው የሚያዋጣው። ጦርና ጎራዴ አልያዘም። ወንጭፍና ጠጠር እንጂ።
ቢሳካም ባይሳካም፣… እንዲሳካ የሚፋለምበት ጊዜ ደርሷል።
በሙሉ ነፍሱ፣ ራሱን ለፍልሚያው ሰጥቷል። ሁለመናውን፣ መላ አቅሙንና ችሎታውን፣ “በአንዲት ጠጠር ውስጥ በብርቱ አምቆ”፣ ወደ ጎልያድ አስወነጨፈ። ጠጠሯ ወደ ጎልያድ በረረች። ከአይኖቹ መሃል፤ ግንባሩን በረቀሰችው። እንደ ግዙፍ አለት ተገንድሶ ሲወድቅ ይታያችሁ።
ለጦርነት ታጥቆ በማያውቅ ወጣት፣ እፍኝ በማትሞላ ጠጠር፣… ምን ሊፈጠር ይችላል?  ጎልያድ፣ “ምንም!” ብሎ እንደሚመልስ፣ ቅንጣት አያጠራጥርም።
ግንባሩ ላይ ሕመም ተሰምቶታል? መብረቅ የመሰለ የራስ ምታት መሆን አለበት። ሌላ ምን ሊሆን ይችላል? “ምን ሆኜ ነው እግሮቼ የተብረከረኩብኝ?”... ነገሩ ወዲያው ላይገባው ይችላል።
ጎልያድ ከወደቀ በኋላ፣ የዳዊትን ድል አድራጊነት የሚያሳዩ ሐውልቶች በጥበበኞች ተሰርተዋል። ሚካኤላጄሎ የሰራው የዳዊት ምስል ግን፣ በፍልሚያ ዝግጅቱ ወቅት፣ “ያቺን ቀውጢ ሰዓት”፣ ዘላለማዊ ያደረገ፣ የጥበብ ስራ ነው።
የጀግንት፣ የወኔ፣ የብቃት፣ የብልሃት፣ የጽናት፣ የአላማ”… ሃሳቦችን በአንድነት አዋህደን እንደማየት ነው - ሐውልቱን መመልከት። ጀግንነትን እንደ አእምሮ ሃሳብ ሳይሆን፣ ጀግንነትን እንደ ሕያው አካልን በእውን እንደመመልከት ነው - የዳዊትን ስም ስናነሳ፣ ፍልሚያውን ስንተርክ።
“የፍትህ እመቤት”፣ ወይም “በሕግ አምላክ” ስንልም፣ ምስልና ሐውልታቸውን ስናይም፤ የዚያኑ ያህል ሕግንና ፍትህን እንደ ሕያው አካል ፊት ለፊት በእውን እንደመመልከት ሊሆንልን ይችላል።
በእርግጥ፣ ምስሎችና ምልክቶች፣ ከሀሳብ ጥራትና ከግንዛቤ ጥልቀት ጋር ሲሆኑ ነው፤ ትርጉማቸው የሚደምቀው፤ የመልዕክታቸው ጉልበት የሚበረታው።
ሚካኤልአንጀሎ የቀረፀው የዳዊት ምስል፣ ይህን ይመሰክራል። ወጣቱ፣ ለአስፈሪ ፍልሚያ ነው የተዘጋጀው። የፍልሚያው አደገኝነት አልጠፋውም።
ስሜቱን መቆጣጠር ስለቻለ፤ አቋቋሙ ዘና ያለ ይመስላል። ግን፣ ሙሉ ትኩረቱን ለፍልሚያው አነጣጥሮ፣ ሌላ ሌላውን ሁሉ ወደ ጀርባ አቆይቶ፣ ኢላማውን ብቻ ወደፊት አስቀድሞ፣ ጠጠሩንና ኢላማውን የሚያገናኝ፣ “እስከጫፍ ድረስ የተቃኘ መንፈስ” ነው - አቋቋሙ።
ለመስፈንጠር እንደሚያጓራ ብርቱ ሞተር ነው። ቆሞ ነው የሚታየው። ሞተሩ ግን ተነስቷል። እርጋታው፣ እንደሚያስገመግም ነጎድጓድ ነው። ፀጥታው፣ ከመብረቅ በፊት እንዳለው ዝምታ ነው - የእሳት አለንጋ ከመወናጨፉ በፊት እንዳለው የሰማይ ዝምተኛ ቁጣ።    
ስንቱን የጀግንነት፣ የወኔ፣ የፅናት ሃሳቦችን፣… በአንድ ምስል ውስጥ ከነሕይወታቸው ማሳየት እንደሚችል ስታስቡት ነው፣ የኪነጥበብ ሃያልነት የሚያስደንቃችሁ።።
“ከጀግንነት ጋር ድንፋታን ሳይሆን ቁትጥብነትን በአካል ማየት” ቀላል ነው? የዳዊትን ታሪክ ተከትላችሁ መታዘብ ትችላላችሁ።
ጀግናው ዳዊት፣ የኋላ ኋላ፣ ሃያል ጦረኛና ተዋጊ ሆኗል። ብዙ ጦርነቶችን አካሂዷል። መከራዎችን ተቋቁሞ፣ ትላልቅ ገድሎችን ፈጽሟል። ድሎችን አስመዝግቧል።
ምንም እንኳ፣ ከጀግንነት ጋር፣ ቁጥብነትን፣ አስተዋይነትንና መልካም ስብዕናን ያዋሃደ ሰው ቢሆንም፤ ስህተት መስራቱ አልቀረም። የአንድ ንፁህ ሰው ሕይወት አጥፍቷል - በክህደትና በተንኮል። ከባድ ጥፋት ነው።
እንዲህ አይነት ጥፋት ባይፈጽም እንኳ፣ የፍልሚያና የጦርነት ጣጣ ማምለጫ የለውም።
ዳዊት፣ “ቤተ-መቅደስ” ለመገንባት፣ ትልቅ ምኞት ነበረው። የግንባታ ወጥኑን ሲጀምር ግን፤ አልተሳካለትም። ለምን? የጦርነት ጣጣ ነው።
ያው፣ በብዙ ጦርነት፣ ብዙ ደም መፋሰስ ይኖራል።
“ብዙ ደም የተፋሰሰ ሰው”፤ ቤተመቅደስ መገንባት አይገነባም ተብሎ ተነገረው። ጦርነት ሲበዛ፣ ከመልካም ሰብዕና ውስጥ፣ እጅግ የሚያጎድለው የሚያጠፋው ነገር አለ። ዳዊት እንኳ ከዚህ አላመለጠም።
ሚዛንናን እና የሰይፍ ነገርስ? ማለቴ የፍትሕ እመቤቷ ያዘችው ሚዛንና ሰይፍ?



Read 9757 times