Saturday, 18 June 2022 18:06

የኢሃብ ጋላል ስንብት

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(3 votes)

  ግብፅ በኢትዮጵያ መሸነፏ እግር ኳሷ በመጥፎ ደረጃ ላይ መገኘቱን ያመለክታል፡፡ በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ የነበራትን ክብርና ዝና ያኮስሳል- የግብፅ ፓርላማ ተወካይ

            ኢትዮጵያና ግብፅ በ2023 እኤአ ላይ ኮትዲቯር የምታዘጋጀውን 34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለመሳተፍ በሚካሄደው ማጣርያ በአንድ ምድብ ውስጥ መግባታቸው ከጅምሩ አነጋጋሪ ነበር፡፡ በተለይ ባለፉት ሁለት አስር ዓመታት በሁለቱ አገራት መካከል በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙርያ የተፈጠረው የፖለቲካ ውጥረት ወደ እግር ኳሱ ሜዳ ገብቶ ሊንፀባረቅ እንደሚችልም የተለያዩ ሃተታዎች ቀርበዋል፡፡  ወደ የአፍሪካ ዋንጫው ለማለፍ የሚካሄደው የምድብ ማጣርያው ሁለተኛ ዙር ጨዋታ ላይ ሁለቱ አገራት የተገናኙት  አዲስ አበባ ላይ አልነበረም። ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ጨዋታ የማስተናገድ አቅም ያለው ስታድዬም ስላልነበራት የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ባሳለፈው ውሳኔ ጨዋታው እንዲካሄድ የተወሰነው በማሊዋ ከተማ ሊሎንግዌ በሚገኘው ቢንጉ ብሄራዊ ስታድዬም ነበር፡፡
ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያው ሁለቱ ብሄራዊ ቡድኖች ማሊ ላይ ከመገናኘታቸው በፊት  የግብፅ እግር ኳስ ፌደሬሽን፤ የስፖርት ሚኒስትሩና ታላላቅ የአገሪቱ ሚዲያዎች ለኢትዮጵያ ዝቅተኛ ግምት የሰጡባቸው ምክንያቶች ያስገርማሉ፡፡   በዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ደረጃ ላይ ከግብፅ በ108 ደረጃዎች  ዝቅ ብላ 140ኛ ላይ የምትገኘውን ኢትዮጵያን እንደሚገጥሙ በማንቋሸሽ ተናግረዋል ፡፡ ለዓለም አቀፍ እግር ኳስ ጨዋታ የሚመጥን ሜዳ ከሌላቸው 16 የአፍሪካ አገራት አንዷ መሆኗን እየጠቀሱ ተሳልቀዋል፡፡  ግብፅ ከኢትዮጵያ ጋር በእግር ኳስ ያላቸውን የኋላ ታሪክ በመዘርዘርም ያንን ታሪካዊ የበላይነት መቀየር እንደማይቻል በመግለፅም ዝቅተኛ ግምት ሰጥተዋታል፡፡  በማጣርያው ጨዋታ ላይ የግብፅ ቡድን ምንም እንኳን በአስተማማኝ አቋም ላይ መገኘቱን ቢጠራጠሩም ከኢትዮጵያ  ላይ ከፍተኛውን ነጥብ  ለመውሰድ እንደማይቸገር በተለያየ አጋጣሚ እየገለፁም ነበር ፡፡
በማሊዋ ሊሎንግዌ ከተማ በሚገኘው ቢንጉ ብሄራዊ  ስታድዬም በተደረገው ጨዋታ ላይ ግን ያልተጠበቀው ነገር ተከሰተ። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በመጀመርያው ግማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በተጋጣሚዋ ግብፅ ላይ ከፍተኛ ብልጫ ያሳየበትን አቅም ፈጠረ፡፡ በተለይ የዋልያዎቹ አጥቂ መስመር የፈርኦኖቹን የተከላካይ መስመር በተደጋጋሚ በሚያዋክቡ አጨዋወቶች በመውረር ቆይቶ ፤ ሁለት ጎሎችንም በዳዊት ሁጤሳ እና በአምበሉ ሽመልስ አማካኝነት በግብፅ መረብ ላይ ለማሳረፍ ቻለ፡፡ በሁለተኛውግማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የግብፅ ቡድን የተሻለ የኳስ ቁጥጥር በማሳየት ውጤቱን ለመቀልበስ ቢሞከርም በፍፁም ሊሳካላት አልቻለም፡፡ ጨዋታውም በዋልያዎቹ 2ለ0 አሸናፊነት ተጠናቀቀ፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንም የግብፅ አቻውን ከ33 ዓመታት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ለማሸነፍ በቃ፡፡
ከጨዋታው በኋላ የግብፅ ስፖርት አካላትና ሚዲያዎች ፈርኦኖቹ ባልጠበቁት ሁኔታ በዋልያዎቹ የደረሰባቸውን ሽንፈት ክፉኛ አበሳጫቸው፡፡ ከሁሉ በቅድሚያም ለሽንፈቱ ዋና አሰልጣኙን ኢሃብ ጋላል ተጠያቂ ማድረግ ጀመሩ፡፡ አንዳንዶቹ ሚዲያዎች በዘገባቸው ከዋልያዎቹ ጋር በተደረገው ጨዋታ ላይ ለገጠመው ሽንፈት በተለይ በሁለተኛው ግማሽ ላይ በዝናብ የረጠበው የቢንጉ ብሄራዊ ስታድዬም ሜዳ አለመመቸቱን አማረሩ። ሌሎች ደግሞ የሊቨርፑሉ መሃመድ ሳላህ፤ የአርሰናሉ ማሃመድ ኤሊኒኒና ሌሎች የብሄራዊ ቡድኑ ወሳኝ ተጨዋቾች በጉዳትና በተለያዩ ምክንያቶች በፈርኦኖቹ ስብስብ አለማካተታቸው ፈርኦኖቹን ለውርደት እንዳጋለጣቸው ሀተታ አቀረቡ፡፡
ፈርኦኖቹን በአሰልጣኝነት ከተረከቡ በኋላ  ከኢትዮጵያ ጋር  ሲገናኙ ሁለተኛ ጨዋታቸውን ያደረጉት ኢሃብ ጋላል የደረሰባቸው ሽንፈቱ ሃላፊነታቸውን አጣብቂኝ ውስጥ እንደከተተባቸው ቢገነዘቡም ስራቸውን ለመቀጠል በማሰብ እንደመከላከያ የተለያዩ ምክንያቶችን አቅርበው ነበር፡፡ ከኢትዮጵያ ባደረጉት ጨዋታ ወሳኝ ተጨዋቾቻውን በጉዳት አለማሰለፋቸው፤ አንዳንድ ተጨዋቾችን ከአውሮፓ ክለቦች በወቅቱ ለማሰባሰብ መቸገራቸውና ከግብፅ የስፖርት አስተዳደር የሚገጥማቸው ጣልቃ ገብነት መብዛቱን በመጠቃቀስ ለሚዲያዎች አቤቱታቸውን አሰምተዋል፡፡
የግብፅ ብሄራዊ ቡድን በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን 2ለ0 መሸነፉ  በአገሪቱ እግር ኳስ ፖለቲካ የተለያዩ አካላት የነበራቸውን እሰጥ አገባ አክሮታል፡፡ ከኢትዮጵያ ጋር ካደረገችው ጨዋታ ከ4 ቀናት በኋላ ግብፅ ከደቡብ ኮርያ ጋር የወዳጅነት ጨዋታ ለማድረግ ወደሲዮል ከተማ ተጓዘች፡፡ ‹‹ሳምሶን›› በሚል ቅፅል ስያሜ የሚጠራው የደቡብ ኮርያ ብሄራዊ ቡድን በወዳጅነት ጨዋታው የግብፅ አቻውን 4ለ1 ለማሸነፍ በቃ፡፡ ፈርኦኖቹ ላይ በድጋሚ የደረሰው ሽንፈት በእንጥልጥል የነበሩትን ውዝግቦች ይባሱኑ አቀጣጠላቸው፡፡  የግብፅ እግር ኳስ ፌደሬሽን፤ የግብፅ ስፖርት ሚኒስትርና የግብፅ ፓርላማን የሚወክሉ ከፍተኛ ባለስልጣኖች ለሽንፈቶቹ ምክንያት ያሏቸውን አጀንዳዎች ማራገብ ጀመሩ።  በግብፅ ፖለቲካ ከፍተኛ ተፅኖ የሚፈጥሩ ትልልቅ ሚዲያዎችም ሽንፈቶቹ በአገሪቱ እግር ኳስ ታይቶ የማይታወቅ ቀውስ መፈጠሩን ያመለክታል በሚል አቋማቸው ዋና አሰልጣኝ ኢሃብ ጋላል እንዲባረሩ በይፋ ጥሪ እንዳይሰሙም አደረጋቸው፡፡
በነገራችን ላይ የግብፅ እግር ኳስ በውዝግብ አጀንዳዎች መተራመስ የጀመረው ከኢሃብ ጋላል ሽንፈቶች በፊት ነበር፡፡ ፖርቱጋላዊው አሰልጣኝ ካርሎስ ኬሮዠ የፈርኦኖቹ ዋና አሰልጣኝ በነበሩበት ወቅት ያጋጠሙት ሁኔታዎች ብዙዎችን አካላት ሲያነታርካቸው ቆይቷል፡፡ በመጀመርያ በካሜሮን በተካሄደው 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ በኬሮዠ የሚመራው የግብፅ ብሄራዊ ቡድን በፍፃሜ ጨዋታ ላይ በሴኔጋል አቻው ተሸንፎ የዋንጫው ድል አመለጠው፡፡ ብዙም ሳይቆይ ደግሞ በኳታር ለሚካሄደው 22ኛው የዓለም ዋንጫ ለማለፍ በአፍሪካ ዞን በተደረገው ጥሎ ማለፍ ፈርኦኖቹ በድጋሚ የቴራንጋ አንበሶች በሚባለው የሴኔጋል ቡድን ተረቱ ፡፡ በአፍሪካ እግር ኳስ ከፍተኛውን ስኬት ያስመዘገበችው  ግብፅ የአፍሪካ ዋንጫ ድል ስላመለጣትና በአረቡ ዓለም ለመጀመርያ ጊዜ የሚካሄደው የዓለም ዋንጫ ስለቀረባት ሁሉንም ግብፃዊያን ከዳር እስከዳር ያበሳጨ ነበር፡፡ የግብፅ እግር ኳስ ፌደሬሽንም ከነዚህ ሁኔታዎች በመነሳት ፖርቱጋላዊው ካርሎስ ኬሮዠ  የነበራቸውን ኮንትራት በአዲስ ውል እንደማያድስ በመግለፅ ከሃላፊነቱ አነሳቸው፡፡ የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ  አዲስ ዋና አሰልጣኝ ሊቀጥር ሲወስንም የመጀመርያ ትኩረቱ በአገር ውስጥ የሚሰሩ አሰልጣኞችን ለሃላፊነቱ እንደሚያወዳድር በመጠቆም ነበር፡፡ ይህን ተከትሎም የመጀመርያው ምርጫ ለመሆን የበቁት ደግሞ ኢሃብ ጋላል ነበሩ፡፡ በግብፅ እንዲሁም በአፍሪካ የክለብና የብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝነት በነበራቸው ሰፊ ልምድ ፤ እንዲሁም ከፌደሬሽኑ አስተዳደር የነበራቸው ቅርበት ብቸኛው እጩ አድርጓቸዋል፡፡ ኢሃብ ጋላል በሚያገኙት ከፍተኛ የደሞዝ ክፍያ በአፍሪካ እግር ኳስ ስማቸው የሚጠቀሱ ግብፃዊው  ነበሩ፡፡ የግብፅ ብሄራዊ ቡድን ከመረከባቸው በፊት ፒራሚድ በተባለው የአገሪቱ ክለብ ዋና አሰልጣኝነት ሲሰሩ  በወርሃዊ ደሞዛቸው እስከ60ሺ ዶላር የሚከፈላቸው ነበሩ፡፡ በእግር ኳስ ተጨዋችነት ወደ ስፖርቱ የገቡት ኢሃብ በፈርኦኖቹ ሃላፊነት ከመሾማቸው በፊት ባለፉት 7 ዓመታት በተለያዩ የግብፅ ክለቦች በሃላፊነት ቆይተዋል። በዋና አሰልጣኝነት ከመሯቸው የግብፅ ክለቦች መካከልም ኤል ማካሳ፤ ኢኤንፒፒአይ፤ ዛማሌክና ኤልማስሪ ይገኙበታል፡፡ ኢሃብ ጋላል ከሁለት ወራት በፊት ሃላፊነቱን ሲረከቡ ግብፅን በ2025 ለሚደረገው 34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የማብቃት ሃላፊነት ተሰጥቷቸዋል። የግብፅ እግር ኳስ ፌደሬሽን የስራ አስፈፃሚ አባላት በአሰልጣኙ ቅጥር የደረሱበት ውሳኔ ከስፖርት ሚኒስትርና ከአገሪቱ ሚዲያዎች ነቀፋ ቢሰነዘርበትም ዋና አሰልጣኙ በአገሪቱ የእግር ኳስ ፖለቲካ ውስጥ የነበራቸው ተሰሚነት ሁኔታዎች ተድበስብሰው እንዲቆዩ አድርጓቸዋል፡፡ በአፍሪካ ዋንጫው የምድብ ማጣርያ የመጀመርያ ጨዋታ ጊኒን 1ለ0 በሆነ ጠባብ ውጤት ሲያሸንፉ ከአየቅጣጫው የሚደርስባቸው ትችት እየጨመረ ቢመጣም ኢሃብ ጋላል ከኢትዮጵያ ጋር የሚያደርጉትን ጨዋታ ድል በማድረግ ስራቸውን ለመቀጠል ተስፋ አድርገው ነበር፡፡ ይሁንና ሁለተኛውን የምድብ ጨዋታ ከኢትዮጵያ ጋር ሲያደርጉ 2ለ0 ለመሸነፍ ግድ ሆነባቸው፡፡ በዋና አሰልጣኝነት የተደረገላቸው ቅጥርን አስመልክቶ  ተድበስብሶ የነበረው ውዝግብ ክፉኛ አገረሸባቸው፡፡ በተለይ የግብፅ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት የሆኑት ጋማል አላለም ትችታቸውን ለማቅረብ ማንም አልቀደማቸውም፡፡ በቀጥታ የቲቪ ስርጭት በሰጡት መግለጫ ላይ አስተዳደራቸው በፈርኦኖቹ የአሰልጣኝነት መንበር ላይ ፕሮፌሽናል ደረጃ ያለው የውጭ አገር አሰልጣኝ ለመቅጠር የስራ ልምዶችን እየፈተሸ መሆኑን አስታወቁ፡፡ በተጨማሪ አስተያየታቸውም ፌደሬሽኑ በሃላፊነት የነበሩትን አሰልጣኝ የማባረር ሃሳብ እንደሌለው በመጥቀስ ሌላ ምርጥ አሰልጣኝ ለብሄራዊ ቡድኑ በማፈላለግ አማራጭ ሁኔታዎችን ማጤን ሃላፊነቱ እንደሆነም አያይዘው ተናገሩ፡፡ የግብፅ እግር ኳስ ፌደሬሽን በያዙት ሃላፊነት ላይ ሌላ አሰልጣኝ ለመሾም እየተሯሯጠ መሆኑን የተገነዘቡት ኢሃብ ጋላል ምላሽ ለመስጠት አልቦዘኑም፡፡ በጉዳዩ ላይ ከሚዲያዎች የቀረበላቸውን ጥያቄዎች በመንተራስ በሰጡት አፀፋዊ ምላሽ ብሄራዊ ቡድኑን ለውጤታማነት የሚያበቃ ስትራቴጂን ለመንደፍ በቂ ጊዜ እንደሚያስፈልጋቸው፤ ወሳኝ ተጨዋቾቻቸው ከጉዳት ተመልሰው ቡድኑን እስኪቀላቀሉ መታገስ እንደሚገባና በተለያዩ የአውሮፓ ክለቦች የሚገኙ ተጨዋቾችን በመሰብሰብ ፌደሬሽኑ እንዲያግዛቸው ተማፅነዋል፡፡
በተለያዩ የግብፅ ሚዲያዎች የቀረቡ ዘገባዎችን በመመርመር መገንዘብ የሚቻለው ለዋና አሰልጣኝ ኢሃብ ጋላል ከሃላፊነት መሰናበት ዋንኛው ምክንያት ፈርኦኖቹ 2ለ0 በሆነ ውጤት በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን መሸነፋቸው ነው፡፡ ለዚህም አንድ የግብፅ ፓርላማ ተመራጭ የሰጡትን አስተያየት መጥቀስ ይበቃል፡፡ ግብፅ በኢትዮጵያ መሸነፏ እግር ኳሷ በመጥፎ ደረጃ  ላይ መገኘቱን እንደሚያመለክት፤ በአፍሪካ እና በዓለም ደረጃ የነበራትን ክብርና ዝና እንደሚያኮስስ የፓርላማ ተመራጩ ተናግረዋል፡፡ የአገሪቱ የስፖርት ሚኒስትርም የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ኢሃብ ጋላልን በዋና አሰልጣኝነት በመምረጥ  ላከናወነው ቅጥር ማብራሪያ እንዲሰጥ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ የፃፈው ዋልያዎቹ በፈርኦኖቹ ላይ ያስመዘገቡትን ድል ተከትሎ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ያልተጠበቀው ሽንፈት ከደረሰባቸው በኋላ ይህን ሁሉ ተቃውሞ እየታዘቡ የቆዩት ዋና አሰልጣኝ ኢሃብ ጋላል ደቡብ ኮርያ ላይ 4ለ1 በሆነ ውጤት ሲሸነፉ በከፍተኛ ተስፋ መቁረጥ ውስጥ ገብተው በመልበሻ ክፍል ውስጥ ተጨዋቾቹን በይፋ ሁሉ እስከመሰናበት ደርሰዋል፡፡
በመጨረሻም የግብፅ እግር ኳስ ፌደሬሽን ዋና አሰልጣኙን ከስራቸው ለማሰናበት የወሰነው ከትናንት በስቲያ ነው፡፡ ከደቡብ ኮርያ ጋር በተደረገው የወዳጅነት ጨዋታ ለአሰልጣኙ ስንብት የመጨረሻው ሰበብ ቢሆንም ፈርኦኖቹ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከፍተኛ ብልጫ ተወስዶባቸው መሸነፋቸው ለመባረራቸው ዋናው ምክንያት መሆኑን የሚዲያ ዘገባዎች ያመለክታሉ፡፡  የአሰልጣኙን ስንብት አስመልክቶ የግብፅ እግር ኳስ ፌደሬሽን የቦርድ አባል ሀዜም ኢማም በጋዜጣዊ መግለጫ ሲናገሩ ዋና አሰልጣኙ በሃላፊነት በቆዩባቸው 2 ወራት ያጋጠሙት ደካማ ውጤቶች ስንብታቸውን እንዳፋጠነው አብራርተዋል፡፡  በአንዳንድ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ የሰራውን የተከበረ ሰው አሰልጣኝ ኢሃብ ጋላልን ማመስገን እንደሚፈልጉና ይቅርታ እንደሚጠይቁ የገለፁት የፌደሬሽኑ ሃላፊ፤ ውጫዊው ግፊት በጣም ስለበዛ በብሄራዊ ቡድኑ ዙርያ ባለው ሃላፊነት ያሉት ሁኔታዎች ቢቀየሩ የተሻለ እንደሚሆን አምነንበታልም ብለዋል፡፡


Read 32732 times