Saturday, 18 June 2022 18:27

የጃፓን መንገድ - እንደ ማንቂያ ደወል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)


            "--ጃፓንን ከ25ዐ ዓመታት በላይ እንደ ብረት በጠነከረ መዳፍ ያስተዳደረው የቶኩጋዋ ሥርወ መንግሥት ተገረሰሰ፡፡ በመቃብሩም ላይ ሜጂ (የብርሃን ዘመን) ሲሉ የሰየሙት መንግስት ተመሠረተ፡፡ የጃፓን አዲስ ጉዞ ተጀመረ፡፡ አዲሶቹ “የለውጥ ሃይሎች” ጃፓንን ለመለወጥ የወሰዱት የመጀመሪያ እርምጃ፣ በርዕዮተ ዓለም መነታረክ ሳይኾን በዕድገት ከቀደሙት ምዕራባውያን አገሮች መማርን ነበር፡፡--"
               አያልቅበት አደም                ፈር መያዣ
ከሁለት መቶ ሃምሣ ዓመታት በላይ በመሣፍንትና በጦር አበጋዞች ስትታመስ ለነበረችው ጃፓን ቶኩጋዋ ኤያሱ የተባለ የጦር መሪ ተነሣላት፡፡ በየመንደሩና በየጎጡ  ነፍጥ አንስተው ሲተጋተጉ የነበሩ ጦረኞችን ድል ነስቶ የራሱን ወታደራዊ መንግሥት መሠረተ። የቀደመውን የንጉሥ ሥርዓት ለይስሙላም ቢኾን ወደ መንበሩ መለሰው፡፡ ይኽ ከ250 ዓመታት በላይ የዘለቀው ወታደራዊ የመንግሥት ሥርዓት ሾገን በመባል ይታወቃል፡፡
ይኽ ወታደራዊ ሥርዓት የጃፓንን በር ጠርቅሞ ከሌላው ዓለም ጋር ያላትን ግንኙነት በማቋረጥ ነጠላት፡፡ የአገሩን ሕዝብ በመደብ ለይቶ፣ በሥራም ኾነ በማኀበራዊ ግንኙነት እንዳይተሳሰር ከፋፈለው፡፡ የእያንዳንዱ ጃፓናዊ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ እንኳ በሕግ ተደነገገ፡፡ ጃፓን ውስጥ የነበሩ አውሮጳውያንን ከአገሩ አስወጣ፡፡ የአገሩም ሰው ከጃፓን ውጭ ወደየትም ውልፍት እንዳይል አዘዘ፡፡ ቀደምት መጻተኞች የሰበኩትን ክርስትና አገደ፣ አብያተ ክርስቲያን እሣት በላቸው፡፡ የወቅቱን ሁኔታ  በአጭር ለመግለጽ ከባለቅኔ ከበደ ሚካኤል “ጃፓን እንደምን ሰለጠነች?” ጥቂት እንጥቀስ፤
 “. . . ከእንግዲህ በኋላ ፀሐይ በመሬት ላይ አብርታ እስከምትኖርበት ጊዜ ማንም ሰው ቢኾን ጃፓን አገር ለመግባት አይድፈር . . . ይኽን ዐዋጅ ጥሶ ሲገባ የተገኘ የውጭ አገር ሰው ሁሉ በሞት ይቀጣል፡፡” (ገጽ፤26)
የሰው ልብ በቅጥር አይያዝም
የሰው ልብ፣ የሰው ምኞት ግን አይቀጠርም። በሥፍራ ተለይቶ አገር ድንበር ተበጅቶለት ይቀመጥ እንጂ ሰው ልቡ እግረኛ ነው፡፡ የትም መቸም፡፡ ዘራሰብ ሉላዊ ነው፡፡ ዘመነኞች ስደት በሚል ይበይኑት እንጂ ዕጣ ፈንታ እንዲህም እንዲያም ብሎ ያገናኘዋል፡፡ ሰይፉ መታፈሪያ ፍሬው “ጉልበተኛ የፈጠራት ዓለም” የሚለው ግጥማቸው እንዲህ የሚል ሃሣብ አለው፡-
እስኪ ከዚህች ወዲህ፤ ከዚያ ወዲያ ብሎ፤
ዛቻ ከፖለቲካ ቀላቅሎ፤
ከለላት እንጂ
አሰመራት
ዓለማችን
መች ድንበር ነበራት
ከመሣፍንትና የጦር አበጋዞች ነፍጥ አስጥሎ፣ የአገሪቱን መግቢያ መውጪያ የከረቸመው የሾገኑ አስተዳደር፣ ከምዕራቡ ዓለም የዕድገት ወሬ የጃፓናውያንን ልብ በቅጥርም ኾነ በነፍጥ መከለል አልቻለም፡፡ በተለይ የባህር ዳርቻ ግዛት አስተዳዳሪዎች የወሬው ነፋስና እነርሱ ያሉበት ኹኔታ ከተራ መንፈሳዊ ቅናት አለፈ፡፡ የአገራቸው መፃዒ ዕድል ያሣስባቸው ጀመር፡፡ በአናቱ ጥቁር ጢሱን እያትጎለጎለ “ጥቁሩ መርከብ” (The Black Ship) ደረሰ፡፡  ይኽን ተከትሎ ከሁለት መቶ ሃምሣ ዓመታት በላይ ተዘግቶ የነበረው በር ተከፈተ፡፡ የመርከቡ ጢስ ለቶኩጋዋ ሥርወ መንግሥት መፍረክረክ፣ ለለውጥ ፈላጊ ወጣቶች ግን የማንቂያ ማጠንት ኾነላቸው፡፡ ዓመጽ ማቀጣጠሉን ገፉበት፡፡ የተፍረከረከውን ነባር ሥርዓት ለማስቀጠል የቆረጡ “ታማኞች” በለውጡ እሣት አቀጣጣዮች ላይ ብረት አነሱ። ብረት ያነሱ በብረት ይጠፉ ዘንድ ተጽፏልና የሾገኑ ሥርዓትና ጭፍሮቹ ማብቂያ ኾነ፡፡
ጃፓንን ከ25ዐ ዓመታት በላይ እንደ ብረት በጠነከረ መዳፍ ያስተዳደረው የቶኩጋዋ ሥርወ መንግሥት ተገረሰሰ፡፡ በመቃብሩም ላይ ሜጂ (የብርሃን ዘመን) ሲሉ የሰየሙት መንግስት ተመሠረተ፡፡ የጃፓን አዲስ ጉዞ ተጀመረ፡፡ አዲሶቹ “የለውጥ ሃይሎች” ጃፓንን ለመለወጥ የወሰዱት የመጀመሪያ እርምጃ፣ በርዕዮተ ዓለም መነታረክ ሳይኾን በዕድገት ከቀደሙት ምዕራባውያን አገሮች መማርን ነበር፡፡
መብሰልሰል  
ከጃፓን መንግሥት በተገኘ የባሕል፤ የቋንቋና የዲፕሎማሲ ስልጠና ለስምንት ወራት ያህል ጃፓን የቆየው ዲፕሎማቱ አሰፋ ማመጫ አርጋው፤ በጃፓን የኢኮኖሚና የዲፕሎማሲ ጉዞ ያደረበትን ምሳጤ በ366 ገፆች ቀንብቦ አቅርቦልናል፤- በ“የጃፓን መንገድ”፡፡ የዓለምን ኢኮኖሚ ከሚመሩት አገሮች አንዷ የኾነችውን የዚህችን ትንሽ አገር ውድቀትና አነሣስ ድርሳናት አገላብጦ፣ የዜና አውታሮችን ዘገባ ፈትሾ ቅልል ባለ ቋንቋ፣ አጠገባችን ኾኖ እንደሚተርክ ሰው እስኪሰማን ድረስ ወጉን ይቀዳልናል፡፡
እውነት እውነት እላችኋላሁ፣ በየምዕራፎቹ እንደ መስታወት የእኛን የእስካሁን የአብዮትም የነውጥም ጉዞ የሚያስታውሱ ተረኮች በርካታ ናቸው፡፡ የፀሐፊው ዋና ቁብ ይኽው ይመስለኛል፡- ቁጭትን መፍጠር፡፡
ጃፓን ላለፈችበት መከራ ሁሉ መንስኤው ልጓም ያልተበጀለት ብሔርተኝነት ይመስለኛል። መዳኛዋ ደግሞ ሽንፈትን ተቀብሎ ከመሰበር ይልቅ በአዲስ አቅጣጫ በአዲስ መንገድ፣ እንደ አገር አንድ ልብ፣ አንድ ሃሣብ ይዛ መነሣቷ ነው፡፡ ከሁለት ምዕት ዓመት በላይ አገሪቱን ዘግቶ ያቆያት ሥርወ መንግሥት እንደተቀየረ፤ አብዮተኞቹ ቀጣይ ሥራቸው አገራቸውን እንደምን አበልጽገው ከሃያላን ተርታ ማሰለፍ እንጂ በርዕዮተ ዓለም ጎራ ለይቶ መተጋተግ አልነበረም፡፡ እኒያ የጃፓንን የብርሃን ዘመን ማሾ የለኮሱ ቀደምት እንደምን በአንድ ልብ ተነስተው አገሪቱን ሃያል እንዳደረጓት አሰፋ ከሰው አውግቶ፣ ከማዕምራን ጠይቆ እና ድርሣናት ፈትሾ ነው መብሰልሰሉን የሚያካፍለን፡፡
‘. . . ለኔ ብለህ ስማ’    
የአሰፋ ትረካ ስሜትን የሚበረብር ነው። መጽሐፉ ከገጽ ገጽ በተነበበ ቁጥር፣ የእኛን የእስከዛሬ ጉዞና አሁናችንን እንድንጠይቅ፣ የት ጋ እንደጎደልን ውስጣችንን እንድንበረብር ይጎተጉታል፡፡ ለምን በመፈክርና ቃላት በማሽሞንሞን ላይ ተቸንክረን ቀረን? የጃፓን መንገድ እንዲህ ውስጥን ይሞግታል፡፡
“. . . የቀድሞው መንግሥት በአመጽ ተወግዶ የሜጂ ንጉሣዊ መንግሥት ወደ ሥልጣን ሲመጣ፣ ጃፓን ድሃ እና ኋላቀር አገር ነበረች፡፡ [..] እናም አገሪቱን ከኋላቀርነት ፈጥኖ ለማውጣት ለለውጡ መበዎቹ ከሌሎች የሠለጠኑ አገራት ልምድ መቅሰም ወሳኝ ጉዳይ ኾነ፡፡ [. . .] ለዚሁ ዓላማ ሥልጣን የጨበጡት ወጣቶቹ የለውጥ መሪዎች፣ በታሪክ “ኢዋኩራ ሚሽን” በመባል የሚታወቀውን የልዑካን ቡድን አዘጋጁ” (ገጽ 46-47)
በወቅቱ እንደተነገረን የኢትዮጵያ አብዮት በግብታዊነት ከፈነዳ በኋላ እና ከግማሽ ምዕት ዓመት መንበራቸው ንጉሡን ከገረሰሰ በኋላ ምን  ተፈጠረ? አንድ ጥራዝ የሶሻሊዝምን ፍልስፍና ያነበቡ ወጣት ተማሪዎች ጎራ ለይተው መተጋተግ ጀመሩ፡፡ ስልጣኑን የጨበጠው ወታደር በበኩሉ፤ "ተማሪ አርፎ ትምህርቱን ይማር፡፡ በዚህ ግርግር ይህች አገር እንደ እንቁላል ከእጃችን ወድቃ እምቦጭ ማለት የለባትም" አለና ጠብመንጃውን አቀባበለ፡፡ ያኔ የተጀመረ መናቆር አንድ ደርዝ ሳይበጅለት የትውልድ ዕድሜ እየበላ ቀጥሏል፡፡
አገር ከርዕዮት ዓለም በላይ ናት፡፡ አገር ልብ በሚያሞቅ ዘፈን፣ ነፋስ በሚነሰንሰው የሰንደቅ ዓላማ ዳንስ፣ ገድሎ በመሞት ብቻ አትበየንም፡፡ አገር በሁሉ ስምም ራዕይ የጋራ ምሰሶና ካስማ፣ ሁሉን አቅፋ የምታኖር የትናንት አደራ፣ የነገ ስም የዛሬ ማረፊያ ናት፡፡ እንጂ ለ”ከእኔ በላይ ለአሣር” በሚል የምትሰዋ በግ፣ ጭዳ የምትኾን ዶሮ አይደለችም፡፡
ጃፓን እንዲህ ነው ያደገችው፡፡ ለዘመናት ዘግቶና ጠርንፎ የያዘ የሾገኑ አገዛዝ ተገረሰሰ ብለው የተነሱ ወጣት አብዮተኞች፤ ለሌላ ትግል መነሻ እርሾ አልኾኑም፤ የተነሱበትን ዓላማ ከተነሱለት ሕዝብ ጋር ተገበሩት እንጂ፡፡
‘ሰው ጥሩ አንድ ሰው’
የሰውን ልጅ የሕይወት ትልም በአንድም በሌላ መልኩ የሚቀይረው የአንድ አሳቢ (አፈንጋጭ) ሃሣብ ነው፡፡ ሃሣቡ ግን መሬት የረገጠ፣ የሰው ልብ የሚገዛ፣ መሬት የሚወርድ፣ ውጤቱ የሚገለጥ ነው፡፡ የማኀበረሰቡ ሕይወት እና አስተሳሰብ ላይ በጎ ተጽዕኖ የሚያሣድር አንድ ሰው አገር ያነቃል፡፡ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የምናየው ፋኩዛዋ ዩኪቺ እንደዚያው ነው፡፡
መደምደሚያ
ፀሐፊው የጃፓንን ማኀበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዞ ቀለል አድርጎ በሚነበብ መልኩ አቅርቧል፡፡ ስለ ጃፓን የእርስ በርስ ጦርነት፣ በቅኝ ገዢነት ያደረገችው ጦርነት ስላስከፈላት ዋጋ፣ በሁለቱ የዓለም ጦርነቶች ስለደረሰባት የሰውና የቁስ ውድመት፣ በሽንፈት ከመሰበር እንደምን መንቃት እንደሚቻል፤ ስለ ይቅርታ፣ እንደ አገር በአንድ ርዕይ እንደምን መነሣት እንደሚቻል፣ የሥራ ባሕልን በማኀበረሰብ ውስጥ ስለ ማስረፅ እጅግ በአስደማሚ ሁኔታ አስነብቦናል፡፡ ብቸኛዋ በአቶሚክ ቦምብ የተመታች አገር ከዚያ ውድመት እንዴት እንዳንሰራራችና ከተረጂነት ወጥታ ወደ ቁጥር አንድ የልማት ትብበርና እርዳታ ሰጪነት እንደተቀየረች ያሣያል፡፡  
በመጽሐፉ ውስጥ ከንባብ አንፃር አጽንኦት ለመስጠት በማሰብ አንዳንድ ምዕራፎች መግቢያ ላይ ቀድሞ የተነገረ ታሪክ ይደገማል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ “ወረድ ብለን እንደምናየው”፣ “በሌላ ቦታ በሰፊው እንደምናየው” የሚሉ አገላለፆች አንባቢውን ከንባቡ ፍሰት የሚያናጥቡ በመኾናቸው በቀጣይ ሕትመት ቢስተካከሉ ተመራጭ ይመስለኛል፡፡ በተረፈ ፀሐፊው የካበተ ልምድ እንዳለው ዲፕሎማት፣ የጃፓንን ጉዞ በንስር ዓይን መርምረው ይኽን ሥራ ማበርከታቸው በእጅጉ የሚያስመሰግናቸው ነው፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢ-ሜይል አድራሻው፡ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡


Read 1638 times