Sunday, 19 June 2022 00:00

ድል እና እድል!!

Written by  ምትኩ አዲሱ
Rate this item
(0 votes)

 "--በዛሬው ድል ዛሬ መደሰት ተገቢ ቢሆንም፣ የሚያዋጣው፣ ካለፈው ትምህርት ወስዶ ለአዲስ ፍልሚያ መዘጋጀት፣ እርስ በርስ መጠባበቅና አብሮ መጋፈጥ ነው። አዲስ ቀን፣ ሁሌ አዲስ ጅማሬና አዲስ ተስፋ ነው። እንደ ይቅርታ ደጅ፣ ለሚገቡበት ሁሌ ክፍት ነው።--"
          
              ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድናችን ባለፈው ሳምንት ሐሙስ “የማይበገሩ” የፈርዖንን ልጆች እንዴት ድል ሊነሳ ቻለ? ተንባዮች፣ ፈርዖን 1 ለ 0 ያሸንፋል ብለውን ነበር። ይህን ያሉበት ምክንያት አላቸው፦ ሁለቱ ቡድኖች ከ1981 ዓ.ም ጀምሮ 16 ጊዜ ተጋጥመው፣ ኢትዮጵያ 2ቴ ብቻ ስታሸንፍ፣ 3ቱን እኩል ለእኩል በመለያየታቸው ነው።
ያለፈው አልፏል።
ያለፈው ታሪካችን ድሎች ነበሩት፤ ሽንፈቶችም ነበሩት። ሁሌ ድል አይገኝም። ሁሌ ሽንፈት አይሆንም። መውደቅ መነሣት፣ መክበር መዋረድ፣ ማዘን መደሰት የሰው ሁሉ እጣ ነው። ስለ ተሸነፍንበት ብቻ ማሰብና ማውሳት፣ ማመኻኘት፣ ማማረር፣ የዛሬን ከማባከን ወዲያ ፋይዳ የለውም። በዛሬው ድል ዛሬ መደሰት ተገቢ ቢሆንም፣ የሚያዋጣው፣ ካለፈው ትምህርት ወስዶ ለአዲስ ፍልሚያ መዘጋጀት፣ እርስ በርስ መጠባበቅና አብሮ መጋፈጥ ነው። አዲስ ቀን፣ ሁሌ አዲስ ጅማሬና አዲስ ተስፋ ነው። እንደ ይቅርታ ደጅ ለሚገቡበት ሁሌ ክፍት ነው።
አብሮ የተሠለፈ አብሮ መጋፈጥ እንጂ አማራጭ የለውም! አብሮ ለተሠለፈ፣ ጣፋጭ ጣፋጩን ብቻ፤ ከመራራው ይቅርብኝ ማለት የትም አያደርስም። መፍትሔው፣ ለዛሬና ለነገ በማይበጅ ታሪክ ከመታሠር፣ አዲስ ስልት መቀየስ ነው። ምሥጢሩ፣ “አብሮ፣ በጋራ፣ እንደ አንድ” የሚለው ላይ ነው።
ብሔራዊ ቡድናችን፣ የማይበገር የተባለውን ፈርዖንን፣ ባእድ ምድር ላይ ገጥሞ ድል ሊያደርግ እንዴት ቻለ? መልሱ ቀላል ነው፤ ደግሞ መልሱ ከባድ ነው።
11 ተጫዋቾች እንደ 11 ሳይሆኑ፣ እንደ 1 ወጥተው ተፋለሙ። ለሁለቱም ወገን የተመደበው ዘጠና ደቂቃ ነው። ፊሽካዋ እንደ ጌታ ቀን ድንገት ሳትሰማ፣ ስልት አሳምረው ተረባረቡ፤ አጠቁ። በ21ኛዋ ደቂቃ አቡበክር ናስር ተከላካዩን አታልሎ አለፈ፤ አመቻችቶ ለዳዋ ሆቴሳ አቀበለ። ዳዋ በተመቸ ሥፍራ ላይ ነበርና በቀኝ እግሩ የመጀመሪያዋን ግብ አስቆጠረ። በ39ኛዋ ደቂቃ አማኑኤል ገብረሚካኤል እራሱ ከሚሞክር፣ ወደ ግብ ለቀረበው ለሽመልስ አቀበለ፤ ሽመልስ በቀለ ተከላካዩን አልፎ በቀኝ እግሩ ሁለተኛዋን ግብ አስቆጠረ።
አግቢው፣ ዳዋ ይሁን አማኑኤል፣ አቡበከር ይሁን ሽመልስ ቁምነገሩ ግብ ማስቆጠር ነው! የአንዱ ድል የሁሉም ነው፤ በሁሉም ነው፤ ለሁሉም ነው።
የፈርዖን ልጆች ግራ ተጋቡ፤ ተፍረከረኩ። ስልት ቀይረው አጠቁ። ሰዓቲቱ ግን አልቃለች። ድል ለኢትዮጵያ።
ሜዳና ስታዲየም የሕይወት መድረክ ናቸው። ተጫዋችና እኛ ሁላችን ተዋንያን ነን። ተጫዋችና ቲፎዞን ሁለት ወገን እንደ ሆኑ ማሰብ የተለመደ፣ ግን የተሳሳተ አመለካከት ነው። ሁለቱ አይነጣጠሉም፤ አክንባሎና ምጣድ፣ ተደጋጋፊ ናቸው። ተጫዋችን ነጥሎ አግዝፎ ማሳየት የተለመደ ነው፤ ይህም ስህተት ነው። የሌሎችን ድርሻ ማሳነስ ነው። የገዘፈ ድርሻ አይኖርም ማለት አይቻልም። ምንም ቢገዝፍ ግን ብቻውን፣ የተፈላሚ መቀለጃ ከመሆን አያልፍም። በረኛ ተገትሮ ሥራ ፈትቶ ዋለ አይባልም። በረኛ ባይኖር ውጤቱ፣ በር እንደሌለው ቤት፣ የሥጋት ደጅ መሆን ነው።
ተጫዋች ሲያምጥ ቲፎዞም ያምጣል። ተጫዋች በደስታ ይዘላል፤ ተመልካችም። ድሎቻችን ግን እየዘገዩ፣ እየዘገዩ እንደ መስቀል ወፍ ሆነውብናል። ሰሞኑን ምድረ ሐበሻ የተንጫጫው ለዚህ ነው። ሰላምን ጠብተን አላደግንም። ድል ብርቁ ሆነናል። ያሳየነው ፍንደቃ በጉስቁልናችን ጥልቀትና ስፋት ልክ ነው።
የቲፎዞ ድምጽ ተጫዋች ያበረታል። የተጫዋች ቁመና፣ መለያና ገምባሌው፣ የጠጉር አበጣጠሩ፣ ወደ ግብ ሆ ብሎ መገሥገሡ፣ አታልሎ ማለፉ፣ አነጣጥሮ መተኮሱ፣ በሰማይ ወይ በምድር ኳሲቱን ከአጥቂ እጅ ማስመለሱ መቀማቱ፣ ከኬላው ላይ ተረባርቦ መከሥ ከሡ መመከቱ …
ጊዜ ሲያገኙ ከተጫዋች ላይ ዐይንዎን ነቅለው የተመልካቹን አኳኋን ይከታተሉ። የተመልካች ፊት ማንበብ የማእበል ፊት እንደ ማንበብ ነው።
+ +
ኮቪድ ወረርሺኝ ዘንድሮ ብዙ ትምህርት አስተምሮናል። አንደኛችን ያለ ሌላው አያምርብንም። በድብብቆሽ፣ ለሰላምታ እጅ ለጅ ሳንያያዝ፣ ዐይን ላይን ሳንተያይ አይሆንልንም። አፍ በገበር ተከልሎ ጥርስ እንነካከስ ፈገግ እንበል አይማታብንም።
ቲፎዞ የሌለበት ጭር ያለበት ስታዲየም አይተናል። ተጫዋች ወላጅ እንደ ሞተበት ጸጋ ርቆት ብቻውን ሲራወጥ ተመልክተናል። እንደ ግዞተኛ ከብረት ደጅ ውስጥ ተባራሪ ድምፁ እንደሚያቃስት አውሬ አምልጦ ወደ ሰማይ ሲወጣ አድምጠናል። ቦምብ ካወደመው ከተማ ጋር ተመሳስሎብናል!
የስታዲየም መቀመጫ በአካል በሌለ ቲፎዞ ምስል ተሞልቶ አይተናል። በመንፈስ፣ ለተፋላሚ የሞራል ድጋፍ ቢሆነው ሞክረናል። በቤት በቡና ቤት በቲቪ መስኮት ባዶ ስታዲየም ማየት፤ መኖሪያችንን ከርቸሌ አስመስሎብናል።
በየስታዲየም ዙሪያ ሰማይ ያካከሉ ቲቪዎችን ደቅነናል። ከየመኪናው ተቀምጠን መመልከትና ድጋፍ መስጠት ሞክረናል። እንደ ጥንቱ ሊሆን ግን ከቶ አልቻለም። ተጫዋች ደጅ  ተዘግቶበት፣ የደጋፊ ድምጽ በቲዊተር እየሰማ፣ ለካስ ብቻዬን አይደለሁም ብሎናል!
ከላይ እንዳልኩት፣ ማሸነፍ ቀላል ነው። ማሸነፍ መተያየት ነው፣ መቀራረብ ነው፤ ያለ ቃል መግባባት ነው። ማሸነፍ፣ መቀባበል፣ አንድነት ማጥቃትና አንድነት መከላከል ነው። ትንሽ እድል ቢጤም አይጠፋም። እድል ባንድ ጎኑ ድል ነው። ድል እና እድል በአብዛኛው ስንዝር ለቀደመ፣ ስንዝር ለዘገየ ነው።
ማሸነፍ ቀላል ብቻ አይደለም፤ ከባድም ነው። ከባድ የሆነው እንዴት ነው? ከባድ የሆነው ቀላሉን ነገር ባለማድረግ ነው!
+ + +
ከእንግዲህ ድልን እንዴት ማስቀጠል ይቻላል? ድልን ማስቀጠል የሚቻለው፣ በመቀባበል፣ በመመካከር፣
በመከባበር፣ በመደማመጥ ነው። ቀላሉን አድርጎ እንደ ታሰበው ድል ባይገኝ እንኳ፣ ድል ነው! አንድ ዓላማ ላነገበ ሁሌ ድል ነው። ድል ደግሞ ባለፈው ብቻ መኩራራት ሳይሆን፣ ለሚቀጥለው መዘጋጀትን የሩቁን ማሰብን ይጨምራል። በአንፃሩ፣ ቀላሉን ሳያደርግ ድል፣ ከሽንፈት አይሻልም!
አያሸንፍም የተባለው ብሔራዊ ቡድናችን እንዴት ሊያሸንፍ ቻለ? ጥያቄው ይኸ ነው። አንድ ነገር ግልጽ ይሁንልን፦ 11 ተጫዋች፣ እያንዳንዱ የግሉን ኳስ እንደሚያነጥር ሆኖ ቢሠለፍ፣ የየራሱን ግብ ቢተክል፣ ዓላማ የለሽነቱ ይፋ ይወጣል። መሳቂያ መሳለቂያ ይሆናል። ውብ የሆነው ነገር፣ አስቀያሚ ጫጫታና ትርምስ ብቻ ይሆናል። ይኸ ወገን ፍፃሜው አያምርም፤ ከመነሻው ተሸንፏል። ድል ለፈርዖን! ይተረትበታል።Read 11350 times