Saturday, 06 October 2012 15:33

“ጭምብል የሚያስጥል ዘመን…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(11 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ… መቼም ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… በፊት እኮ…አለ አይደል…ከወዳጅ ጋር ትንሽ ቆይታችሁ ስትገናኙ… “አንቺ እንዴት ነው እንዲህ የጨመርሽው፣ የቄራን ሠንጋ ያለ አዋዜ የዋጥሽ ነው እኮ የሚመስለው? ምን ተገኘ?” “አጅሬ…ያ ተንጠልጥሎ የኦሎምፒክ ባሉን ይመስል የነበረው ሆድ ጠፍቶ ሽንቅጥ አልክ አይደል እንዴ! ማሳጅ ምናምን የምታደርግ ቋሚ ቴራፒስት አገኘህ እንዴ!” ምናምን ይባል ነበር፡፡ (እንደሷ አይነት ካገኘህ ጠቁመንማ! ምናልባት መንትያ እንዳላት…ቂ…ቂ…ቂ…)


ልጄ አሁን ነገርዬው ሁሉ እንዳይገባን፣ እንዳይገባን እየሆነ ነው፡፡ ልክ ነዋ…እንደ ድሮ የሚለዋወጠው ዳሌና ሆድ ብቻ ሳይሆን አፍንጫና ብሬስት እየሆነላችሁ ነው! “እኔ የምለው ይቺ ልጅ አፍንጫ ሲታደል ሳታስፈቅድ ቀርታ የሆነ ‘ትሩ’ ምናምን ነገር አልነበር እንዴ የተሰጣት! ይሄን ልዕልት ዲያናን የመሰለ አፍንጫ ከየት አመጣችው? ነው ወይስ ልጅቷ ራሷ ነች!” ምናምን ልንባባል ነው፡፡
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…በፊት አንድ ግጥም ነበረች፡፡
አፍንጫ ቢገተር እንደ በር እንጨት፣
በመልክ ይበልጡሻል እነጎራዲት፣
ይባል ነበር፡፡ እናላችሁ…ነገርዬው ስር ሰዶ ጎረድ ብለው “የደም ገንቦ…” ምናምን የሚባሉት ሁሉ ‘ኖዝየው’ ሁሉ ቀጥ ካለ ለዘፈን ግጥም እንኳን እነ ጎራዲት ሊጠፉ ነው! ቂ…ቂ…ቂ…
እናላችሁ…“ከሳህ…”፣ “ወፈርክ…”፣ “ዳሌ አወጣሽ…” ምናምን መባባል የሚናፍቀን ጊዜ እንዳይመጣ ፍሩልኝማ፡፡
እናላችሁ ይሄ ፕላስቲክ ሰርጀሪ የሚባል ነገር መጥቶ አፍንጫ እየተገተረ፣ ‘ብሬስት’ ፊኛ እየሆነ ፊት ‘እየተነካካ’…አለ አይደል… አርቲፊሻል ባህሪያችን ሰዉን መግቢያ መውጫ አሳጥቶ አሁን ደግሞ መልኩ ሁሉ አርቲፊሻል እየሆነ…‘ስልጣኔ’ መተንፈሻ እያሳጣን ነው እላችኋለሁ፡፡
ምን ይመስለኛል መሰላችሁ…የሆነ ‘ናሽናል ዲዚዝ’ እየሆነ የመጣ ነገር…ብዙዎቻችን ራሳችንን መሆን እየጠላን ይመስላል፡ “እንደ እነ እንትና…” የሚባለው ነገር በሁሉም ነገር ውስጥ እየገባ እያሽከረከረን ነው፡፡ ልክ ነዋ…ከላይ እስከታች ብዙ ነገር ካያችሁ የራስን ስብእና ቁም ሳጥን ምናምን ውስጥ ቆልፎ የሌላውን አርቲፊሻል ስብእና ያለ ይሉኝታ ማጥለቅ ሆኖላችኋል፤ ጭምብል ማጥለቅ በሉት፡፡
እናላችሁ…የብዙዎቻችን ማንነት ከጭምብል ጀርባ ተደብቋል፡፡
ሀሳብ አለን…የጠባይ ፕላስቲክ ሰርጀሪ ይጀመርልን፡፡ ልክ ነዋ…አሁን መለወጥ ያለበት አፍንጫና ‘ጉች ጉች ነገርዬ’ ሳይሆን ጠባይ ነው፡፡ መኮረጅ ቢቻል አሪፍ አሪፍ ጠባይ መኮረጅ፡፡
ለምሳሌ መግለጫ ማውጣት የሚሉት ነገር አለላችሁ፡ ብዙ ድርጊቶች በሆነ ጉዳይ ላይ “እንደግፋለን…” “ቁርጠኝነታችንን እንገልጻለን…” ምናምን አይነት መግለጫ የሚያወጡት በራሳቸው እምነት ብቻ ሳይሆን ሌሎቹ ድርጀቶች ስላሉ ነው፡ እናላችሁ…በድርጅት ደረጃ እንኳን ‘ጭምብል’ ማጥለቅ እየተለመደላችሁ ነው፡፡
በጣም የሚገርመኝ ነገር አለ…የሆነ ነገር ሲነገር ድፍን የአገሩ መሥሪያ ቤት መግለጫ ማውጣት አለበት፡፡ ነገሬ ብላችሁ እንደሆነ ለምሳሌ አትሌቶቻችን በሌሊት ሮጠው ሲያሸንፉ ገና ትንፋሻቸውን ሳይሰበስቡ “እንትን መሥሪያ ቤት በአትሌቶቻቸን ድል የተሰማውን ከፍተኛ ደስታ ይገልጻል…” ምናምን የሚል ጽሁፍ መጥቶ ገጭ! የድርጀቱ መብራቶች በሙሉ ጠፍተው፣ ዘቦቹ ኩሼ ብለው… መግለጫው መቼ ተዘጋጅቶ መቼ ተልኮ ደረሰ!
እናላችሁ…ብዙ ቦታ ነገሮች ሁሉ ‘የፕላስቲክ ሰርጀሪ’ አይነት ነገር እየሆኑ ናቸው፡፡ አንድ መሥሪያ ቤት አንድ አዲስ ነገር ከጀመረ…በሳምንቱ ሠላሳና አርባ መሥሪያ ቤት ያንኑ ሲያደርግ ታያላችሁ፡፡
እናላችሁ…አንድ አልለቅ ያለ ባህል አለ…“እነ እንትና ካደረጉት እኛም ማድረግ አለብን፣” አይነት ነገር፡፡
ስሙኝማ…የጭምብል ነገር ካነሳን አይቀር…እንደ ውጪ ዘፋኝና ኳስ ተጫዋቾች…አለ አይደል… ትውልድ ላይ ጫና ያሳደረ ያለ አይመስለኝም፡፡ ለምሳሌ እዚህ አገር በተለያዩ ባህሎች ውስጥ የተለያዩ የጸጉር አሠራሮችና አበጣጠሮች አሉላችሁ፡፡ አንዳንዴ እንደምናየው ‘የረፈደበት ፓትሪዮትነት’ ሳይሆን እውነት እንነጋገር ከተባለ…ምደረ ራፐር አሁን ‘እየሸለለበት’ ያለው የጸጉር አሠራርና አበጣጠር አብዛኛውን በአገራችን በተለያዩ ቦታዎች የሚገኝ ነው፡፡
ኮሚኩ ነገር ግን ምን መሰላችሁ…እስከ አሁን ማንም ከተሜ እነዛን… በዘመኑ ቋንቋ ‘ስታይሎች’ እንኳን ሊጠቀምባቸው ከእነመኖራቸውም አያውቅም፡፡ አሁን ግን… እንግዲህ የጭምብል ዘመንም አይደል…ይሄ የሱሪውን ቀበቶ ጭኑ አጋማሽ ሊያደርሰው ምንም ያልቀረው ‘ትኩስ ኃይል’ የውጪ ዘፋኞችንና ኳስ ተጫዋቾችን እየኮረጀ ለስንት ዘመን የነበሩንን በሚመስሉ አሠራሮችና አበጣጠሮች እየተምነሸነሸባቸው ነው፡፡ የጭምብል ዘመን ነዋ!
ኮሚክ ነገር እኮ ነው…አሁን ንቅሳት ለእኛ ምኑ ነው አዲስ ነገር፡፡ እንደውም እኛ ሳህን ድንችና ጮርናቄ ስለበላን የስልጣኔን በትረ መንግሥት የጨበጥን የሚመስለን ከተሜዎች የተነቀሱ እንትናዬዎችን ስናይ “ኒቂሴ” “ተነቦ የማያልቅ ጋዜጣ!” ምናምን እያልን ስንሳለቅ አልነበር! አሁን ታዲያ ምን አዲስ ነገር ተፈጠረና ነው ነገርዬው መነቀስ ወይም ሞት አይነት የመሰለው! የጭምብል ዘመን ነዋ!
እናላችሁ…እንደዛ ‘የመሰልጠንና የኋላ ቀርነት ቀይ መስመር’ አድርገን ስንዘባበትበት የነበረውን ንቅሳት… አይደለም ክንድና ምናምን ላይ ከእነመፈጠራቸው የባዮሎጂ አስተማሪዎች እንኳን ግራ የሚጋቡባቸው የሰውነት ክፍሎች ላይ ሁሉ እየተነቀስን አይደል! ቂ…ቂ…ቂ… (እመኑኝ…አንዳንድ እንትናዬዎቻችን ይነቀሱባቸዋል ተብሎ ካስተማማኝ ምንጮች የሰማናቸውን የሰውነት ክፍሎች ‘ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ’ ቂ…ቂ…ቂ… ሹክ ብንል “ከእንዲህስ እንዲህ አይነት ነገር የሚሠራባት አገር ላይ ለአንድ ተጨማሪ ደቂቃ አልቀመጥም…” አስብሎ ለሂማልያ የእግር ጉዞ ስንቅ የሚያስቋጥር ነው፡፡ እንደገና እመኑኝ…እዚህ አገር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተስፋፉ የመጡ አንዳንድ ‘የጓዳና የመጋረጃ ጀርባ’ ልምዶች ለማመን ማስቸገር ብቻ ሳይሆን ነገና ተነገ ወዲያ ምን ይመጣ ይሆን አስብሎ ስጋት ውስጥ የሚከት ነው፡፡) ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… ስለ ዘንድሮ የጸጉር ስታይሎች ካነሳን አይቀር… አንዳንዶቹ ላይ የሚታየው የሆነ ‘ጸጉር ሲቀወጥ’ አይነት ነገር ግርም ይላችኋል፡፡ የአንዳንዱ ጸጉር እኮ ሱናሚ ረብሾት የሄደና ገና ‘መልሶ ማልማት’ ያልጎበኘው የኢንዶኔዥያ ሠፈር ይመስላል፡፡ ግማሹ ደግሞ ዳዋ የመታው ሰብል ይመስል ተቦዳድሶ፣ ተቦዳድሶ እንደ አዲስ አበባ መንገዶች ‘የሚጥፈው’ እየጠበቀ ያለ ይመስላል፡፡
እኔ የምለው፣ እንግዲህ ጨዋታም አይደል…የሰውን ነገር ስለመፈለግ ካወራን አይቀር ይቺን ስሙኝማ…የሆኑ መለፋለፍ የሚወዱ ባልና ሚስት ሆዬ ጎረቤቶች ወሬያቸውን እንዳይሰሙባቸው ሬድዮ ይገዙላችኋል፡፡ ታዲያ እስከ ጥግ ድረስ ይከፍቱታል፡፡
ከትንሽ ቀናት በኋላ ግን ሚስትየዋ መነጫነጭ ትጀምራለች፡፡ ይሄኔ ግራ የገባው አባወራ ሀዬ “ምን ሆነሽ ነው የምትነጫነጪው?” ይላታል፡፡ ምን አለ መሰላችሁ…“ሬድዮው እንዲህ እየለፈለፈ ጎረቤቶች የሚያወሩትን እንዴት አድርጌ ልስማ!” አሪፍ አይደል!
አሁን ለምሳሌ ሠርግ ላይ ሰዉን ሁሉ ‘ዘቅዝቆ እስከ መጨረሻዋ ሶልዲ የሚያራግፈው’ አጉል ሌሎች ያደረጉትን ካላደረግን አይነት… ፈረንጅ እንደሚለው… ‘በሌሎች ቆዳ ውስጥ’ የመግባት አይነት አባዜ ነው፡፡ በሌለ ‘ፈረንካ’ ያላቸውና የተረፋቸው ያደረጉትን ካላደረግንማ ምኑን ደገስነው አይነት ሰውን የመምስል አባዜ ሙሽሮችን ከሞላ አዳራሽ ወደ ወና ማብሰያ ቤት እየከተታቸው ነው፡፡
እግረ መንገዴን…ስለ ሠርግ ካነሳን አይቀር… አንዱ ተናጋሪ ምን አለ መሰላችሁ፡፡
በድሮ ጊዜ የጋብቻ ቀለበቶች ወፍራም ነበሩ፡፡ አሁን ግን አቅጥነዋቸዋል፡፡ ምክንያቱም ለምን መሰላችሁ…ትዳሩም ብዙ ስለማይቆይ!
ብቻ ጭምብል የሚያስጥል ዘመን ያምጣልንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

 

Read 4258 times Last modified on Saturday, 06 October 2012 15:43