Saturday, 18 June 2022 20:41

‹‹እኔ ሙዚቀኛ ነኝ›› (ከባዶ ላይ መዝገን ፪)

Written by  ያዕቆብ ብርሃኑ
Rate this item
(1 Vote)

 መለኮቱ ወይ ማንኛውም ሰው ድንገት የሆነ ቦታ አስቁሞ፤ ‹‹ይሄን ሁሉ ዘመን ምን ስታደርግ ነበር?›› ብሎ ቢጠይቀኝ እላለሁ...
‹‹እንደ እብዶች ጉባዔ በታወከች ከተማ፣ ሀገር፣ ዓለም መሃል ነፍሴን የማስጠልልባት የሆነች የፅሞና ጥጋት ሳስስ ነበር፡፡››
በእርግጥ ይህ ሀሰሳ ትርጉም ያለው፣ ሊኖሩለትስ የሚገባ ግብ ይሁን አይሁን አላውቅም፡፡ ግን በዘመኔ ሙሉ ከዚህ የሚልቅ ዓላማ ነበረኝ ለማለት አልችልም፡፡
መጀመሪያ በዚህች ግራ ገብ ከተማ መሃል መሸሸጊያ ሳጣ ወደ ተተው መካነ መቃብሮች፣ ወደ ፈራረሱ መንደሮች፣ ወደ ተራሮች እና ቆሻሻ መጣያ ቦታዎች ሁሉ ሳይቀር በማቅናት ጽሞናዬን ሙጥኝ አልኳት፡፡ ለዚህም መዳፈሬ ከአራት ዓመታት በፊት ከሞት አፋፍ የሚያደርስ የሰይፍ ጉብኝት ገጥሞኛል፡፡ ዛሬም ግን በስለት ጠርዝ ላይ እየተረማመድኩ በጀብደኝነት ብፈልጋትስ ስንኳ እርፍት የምትጨበጥ አልሆነችም፡፡ ሽሽቱ የእኔ ብቻ አልነበረማ፡፡ የኪነት ዛር ሲሰፍርብህ ጽላቱን ይሸከም ዘንድ እንደተመረጠው ዲያቆን (ምናልባት ካህን ወይ መነኩሴ) መሆን ነው አየህ፡፡ መማለል መለማመንህ ለሁሉም ነው፡፡ ጠዓርህ የመሰሎችህ ሰብዓዊያን፣ በአጠቃላይ የመላው ስነፍጥረት ሁሉ ጉዳይ እንጂ ያንተ ብቻ አይደለም! ...
አንተ የሌሎች ነገር የሚገድህ ከሆንህ ዘመንህ ደግሞ ሸክምህን ለማክበድ የተመቸ ይመስላል። ‹Francis August Schaeffer› የተሰኘ ኢቫንጀሊስት ፈላስፋ ‹‹escape from reason›› በተሰኘ መጽሐፉ የሳርትረን ኤግዚስተሻል ዕሳቤ መነሻ አድርጎ ሲጽፍ እንዲህ አለ...
‹‹በአመክንዮአዊ አረዳድ ስታየው ዓለም አብዲናጎ (absurd) ነው፡፡ አንተ ለነጻ ፈቃድህ ተጥለሃል፡፡ ማን መሆንህን ለማረጋገጥ፣ ምናልባት ለመለየት ነጻ ፈቃድህን እንደመሰለህ ትተገብራለህ፡፡ ለምሳሌ በዶፍ ዝናብ መሃል መኪና እየነዳህ ከፊት ለፊትህ ዝናብ የሚያኳትነው ምስኪን አየህ እንበል፡፡ መኪናህን አቁመህ ልትሸኘው በር ከፈትክለት፡፡ ሰውየው ባንተ ፊት ማንም፣ ሁኔታውም ኢምንት ነው፡፡ ግን ነጻ ፈቃድህ ይሄንን እንድታደርግ ዕድል ሰጥቶሃል፡፡ ችግሩ ምን መሰለህ? ነጻ ፈቃድ ምንም የሚገራውም ሆነ የሚዳኘው አመክንዮ የለውም፡፡ እናም በመሰለህ መልኩ ምንም ብታደርግ ልዩነት አያመጣም፡፡ እኩል ነው፡፡ እንበልና ሰውየውን በመሸኘት ፋንታ በኃይል እየነዳህ የጎርፍ ውኃ ከላይ እስከ ታች አከናንበኸው ወይም ገጭተኸው ብትሄድም ትችላለህ፡፡ ነጻ ፈቃድ አለህ፡፡ የምልህ ገባህን? በል እንግዲያውስ ይህን ለመሰለ ተስፋ አስቆራጭ ዕጣ ተላልፎ ለተሰጠው ዘመናዊው የሰው ልጅ አልቅስለት፡፡››
አየህ አንተ ባልቀሰቀስከው ምንም ባላዋጣህበት ጦርነት ሁሉንም ነገርህን ታጣለህ። ዕጣፋንታህ አብዛኛው በሌሎች ዕጅ ነው፡፡
ዶክተር እጓለ ገብረዮሐንስ ‹ብፁዓን ንጹሓነ ልብ›› በተሰኘ መጽሐፋቸው፣ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት በአውሮፓ በተለይም በጀርመን በርሊን ስለደረሰው ቀውስ አጭር ነገር ከትበዋል። በዚያን ዘመን እርሳቸው ለትምህርት አውሮፓ ነበሩ፡፡ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ሕብረት ጥሪን ተቀብለው በበርሊን ቤቶቻቸው በጦርነቱ ምክንያት የወደሙባቸውን ችግረኞች መኖሪያ ለመስራት ወደዚያው ተጓዙ፡፡ ቤቶቹ ተጠናቀው ርክክቡ ሲደረግ ባለንብረቱ በቤቱ ደጃፍ ለተሰበሰበው ሰው አጭር ንግግር አደረጉ። እኒህ ግለሰብ የተናገሩት ሀሳብ ነፍስን ለመንዘር አቅም አለው፡፡
‹‹ቤትስ እንደገና ተሰራ የተቀረው እንዴት ይሁን? ሕንጻዎች ብቻ አይደለም የፈረሱት፣ ብዙ ነገር እንዳልነበር ሆኗል፡፡ የሕልውናችን መሰረት ተናግቷል፡፡ የመንፈሳችን የአስተሳሰባችን መዋቅሮች ተናውጠዋል፡፡ የሕይወታችን ዓላማ የተስፋችን ጨረር አይታየኝም፡፡ ጥቁር ደመና ሸፍኖታል፡፡ ከዚህ የሐዘን ሸለቆ እንዴት እንወጣ ይሆን? አቅመ ቢሶች ሆነናል፡፡ ጉልበታችን በከንቱ ተበትኖ ባክኖ የሰውነት ፍርስራሾች ነን።››
ጦርነቶች ድልድዮችን ብቻ አይደለም የሚያሳጡን... የሕዝቦች መስተጋብሮችን፣ አብሮ የመኖር ልምምዶችንም ጭምር  እንጂ… ድልድዮች መንገዶች ይጠገናሉ። አብሮ የመኖር ሰንሰለቶችን መጠገን ግን ትውልዶችን፣ መቶ ዘመናትን ይፈልጋል። ሊያውም በብልሆች እጅ ከተያዘ...
አንተ በነፍስህ የምታስሳት ይሄን መሰል ሰው የመሆን መቃተት ካለችህ ይህቺ እውነታ ከፈረሰው ሰፈር ጽሞናህ አልፋ እስከ መቃብር ጉድጓድህ የምታሳድድህ መራራ ሀቅህ ናት። ምልዓተ ዓለሙን የሚያስተዳድረው ኃይል (መለኮት በለው ተፈጥሮ) ደግሞ ያንተ ዘይት ሺህ ቢገባ፣ በነጻ ቢታደል ኬር የለውም፡፡ ስድስት ሚሊዮን አይሁድ፤ ብዙ ሺህ ብሔር ብሔረሰብ ተላልቆ ቢያድር ግድ የሚሰጠው አይመስልም። ምክንያቱም እልቂት፣ እጥረት፣ የኑሮ ውድነት፣ የእርስበእርስ ጦርነት ጂኒጃንካ ያንተ እኩይ ግኝት እንጂ የሱ ‹ዳይሜንሽኖች› አይደሉም፡፡
አሁንም የጦርነት ወሬ ልነግርህ ነው፡፡ ሱዛን ኬይን ‹The hidden power of sad music and rainy days› በተሰኘ ቴድቶክ ላይ የቀረበ ንግግሯ ስለአንድ የቦስንያ የሙዚቃ ባለሙያ የተናገረችው ታሪክ አስደንቆኛል፡፡ በ1992 እ.ኤ.አ አቆጣጠር በዩጎዝላቪያ ጦርነት ሙዚቀኛው ቬድራን ስማይሎቪች የሚያገለግልባት ከተማ ሳራጄቮ በከበባ ውስጥ ወደቀች፡፡ በዚህች ከተማ ውስጥ አንድ ማለዳ ለዳቦ ወረፋ የተሰለፉ 22 ሰዎች ተገደሉ፡፡ ስማይሎቪች ለዳቦ ወረፋ ተሰልፈው የተሰው ምስኪኖችን ለማሰብ ለ22 ቀናት በተከታታይ ጎዳና ላይ ፕላስቲክ ወንበር ላይ ተቀምጦ የስናይፐር ጥይት በአናቱ ላይ እየተራወጠ ቼሎውን ተጫወተ፡፡
ስማይሎቪችም አለ...
‹‹በተፋፋመ ጦርነት መሃል መንገድ ላይ ሙዚቃን በመጫወቴ አብደሃል ወይ ትሉኛላችሁ? ከተማዋን ከበው የሚደበድቡትን ስለምን ስለማበዳቸው አትጠይቋቸውም?››
በዚያች ከተማ ውስጥ ብቻ ከ15 ሺህ በላይ ሰዎች ተጨፈጨፉ፡፡ከወራት በኋላ ጦርነቱን ሽሽት ከተበተነው አርባ ሺህ በላይ ሙስሊም፣ ካቶሊክና የምስራቃዊ ኦርቶዶክስ ክርስትና አማኝ ህዝብ ጋር በጫካ ውስጥ ተጉዞ ሲወጣ የቢቢሲ ዘጋቢ አለን ሊትል፣ አንድ መንገድ ያጎሳቆለው አዛውንት አገኘ፡፡ አለን ሊትል ይሄን ሰው ጠየቀው፤
‹‹ይቅርታ አድርግልኝና አንተ ሙስሊም ነህ ወይስ ክሮአት(የክሮሻ ተወላጅ)?››
አዛውንቱ ሰው ምንም ሳያመነታ መለሰ...
‹‹እኔ ሙዚቀኛ ነኝ፡፡››
ልክ እንደዚህ ሰው ሁሉ እኔም ማነህ ባሉኝ ጊዜ ሁሉ፣ ‹የጽሞናው አሳሽ ነኝ› ማለት ይከጅለኛል፡፡
ሰው ሰውነትን ለመገንባት የሄደበት መንገድ የተሳሳተ እንደነበር አስባለሁ፡፡ ምድር የእብዶች ጉባዔ ሆናለች፡፡ ዓለምን የአመጻ ቤተሙከራ አድርገዋታል፡፡ ቀደም ባለው ጊዜ በቅዱሳቱና ተረታቱ መጻሕፍት እንደተነገረን በዚህ የአመጽ ግብር አማልክት ሳይቀር ተሳታፊ ነበሩ፡፡ በጥንቱ ዘመናት ሰዎች ጠንካራ ህብረትና መተባበር እንዲመሰርቱ ብሎም ትንንሽ ግዛቶችና ሀገራት እንዲፈጠሩ ጦርነቶች ሚና እንደነበራቸው ይነገራል፡፡ ምናልባት ዘመኑ ‹Age of forming› ስለነበር ይሄን ፈቅዶ ይሆናል፡፡ አሁን ግን ዘመኑ የመበስበስ፣ የመፈራረስ ‹Age of decadence› በመሆኑ በጦርነት የምትፈራርስ እንጂ የምትገነባ ሀገር አትኖርም፡፡
ዛሬ በርሊንና ሳራጄቮ ከተሞች አስከፊውን ጊዜ ረስተውታል፡፡ ሆኖም የሰው ልጆች የሸክሙን ትከሻ ቀየርን እንጂ ሕመሙ አልቀረልንም፡፡ ዛሬም ከኢትዮጵያ እስከ የመንና ዩክሬን የሰው ልጆች ምኑንም በማያውቁት፣እነሱ ባላስነሱት ጦርነት በእሳት ላንቃ ይለበለባሉ። ዛሬም በምንኖርባት ምድር በኢትዮጵያችን ይሄው የጥርጣሬ ደመና ክቡድ እንደሆነ አለ፡፡
ይህ ሁሉ በብቻ ዓለሜ እንደ ትንኝ እየተራወጠ የሚያናጥበኝ ሰው የመሆን ጥያቄዬ ነው፡፡ ለመሆኑ ጸጥታውን ስክነቱን ብትይዘው ምን ታደርገዋለህ? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡ ግን ጸጥታው ይይዘኛል እንጂ ልይዘውስ ይቻለኛልን? በፍጹም! በምን አቅሜ! ጽሞናው እኮ መለኮቱ ራሱ ነው፡፡ እሱ እንደ ውቅያኖስ ሲሆን እኔ እንደ ጠብታዋ ነኝ፡፡ ቢሆንም የጽሞናው አዳኝ ነኝ፡፡ ወደዚያው መሄድ እፈልጋለሁ፡፡ ነፍሴን የማስጠልልባት የፀጥታ ጥጋት እስካገኝ፣ ብናኝ ፍናኝ አንዳች ሆኜ እስክከስም፣ ወደ ምንም መሄድ ያምረኛል፡፡


Read 388 times