Saturday, 18 June 2022 20:39

‘ለምሳ ሦስት ቁርጥ፣ ለእራት ሦስት ቁርጥ...’

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(3 votes)

 "--አንድ የሆነ እቃ ሊገዛ ሄዶ ከጥቂት ቀናት በፊት ስምንት መቶ ብር የነበረው ዋጋ በአንድ ጊዜ ሁለት ሺህ ስምንት መቶ ብር የሆነበት ወዳጃችን ቢቸግረው “ዝም ነው እንጂ ሌላ ምን ማድረግ ይቻላል!” ነው ያለው፡፡ እናላችሁ... ገና ከአሁኑ በየቦታው በዚህም በዛም እቃ ላይ እየጨማመሩላችሁ ነው፡፡ አሁን እየጨመሩባቸው ያሉ እቃዎችና አገልግሎቶች ላይ በሐምሌ ደግሞ ሲቆልሉበት ይታያችሁማ!--"
                 
             እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እኔ የምለው...ስለ ኑሮ መወደድ ስናወራ ስንት ዘመን እንደሆነ ጥናት ይደረግልንማ። ልክ ነዋ... ስለሆነ ነገር ስናነሳ...አለ አይደል... “ያኔ ስለ ኑሮ መወደድ ማውራት ከመጀመራችን በፊት...” እያልን እንድንጠቅስ ያግዘናላ! ስሙኛማ...እንዲህማ እንደ ወገብ እንትን ተጣብቆብን ከዕለታት አንድ ቀን (“ዋንስ አፖን ኤ ታይም” እንዲል ‘ፈረንጅ’) ወደዛ ለማሽቀንጠር ዕድሉን ያገኘን ጊዜ፣ የምንወረውረው እርቀት እነኚህ እኛን እየሰለሉ ለእነ እንትና ሹክ የሚሉባቸው ሳተላይቶች እንኳን አይደርሱበትም፡፡ (እግረ መንገድ ለግንዛቤ ያህል...መሀመድ አሊ ወይም ካስየስ ክሌይ “የጉልበት ግማሹ አፍ ነው፣” ይል ነበር አሉ!)
እናላችሁ...አብዛኛውን ጊዜ  የኑሮ መወደድን የምናውቀው ያው ሸመታ ስንወጣ ነው እንጂ ቀድመን ምን እናውቅና! ያለችንን ፈረንካ ይዘን ‘ለሸመታ’ ደንበኛችን እንትና ሱቅ እንሄዳለን። (ስሙኝማ... እንግዲህ ጨዋታም አይደል...አሁን አሁንማ ለስንትና ስንት ዘመን ደንበኛ ብላችሁ ስትመላለሱበት የነበረው ባለሱቅ ሁሉ፣ ልክ እንደ አንዳንዶቻችን ጠባይ፣ በአንድ ጊዜ ጥምዝዝ ብሎ ቁጭ! ቀደም ሲል  ከሆነ እቃ ላይ አምስት ብርም፣ አስር ብርም ይቀንስላችሁ የነበረው ሰው አሁን “እኔ ለጂ ፕላስ ስሪና ለቪ ኤይት ምን ያንሰኛል!” ብሎ እንደሁ እንጃ፣ “ገበያው ነው፣” ብሎ ጀርባውን ያዞርባችኋል፡፡
“ጌታው እንዴት ነህ?”
እንደ ሌላው ጊዜ ቢሆን ሰላምታው ገና ከአፋችሁ ወጥቶ ሳያልቅ ተጠምጥሞ ሊመጨምጫችሁ ምንም አይቀረው፡፡ ገና ምን ለመግዛት እንደመጣችሁ እንኳን ሳያውቅ “እዚህ ድረስ መልፋት አያስፈልግም ነበር እኮ፡፡ እኔ እቤት ድረስ አመጣው ነበር፣” ምናምን ይላል። ይሄ እንግዲህ አሁን ከታሪክ ማስታወሻ አይነት ነገር እየሆነ የመጣ ነው፡፡ እናማ... ሰላምታችሁን በራስ እንቅስቃሴ ይመልስላችኋል፡፡ እግረ መንገድ...“ሦስቴ እንዴት ዋላችሁ አንዱ ለነገር ነው፣” የሚለውን አባባል ችላ ብሎ በአንዴ አስራ ሦስት ጊዜ ሰላም ይላችሁ የነበረው ሰው ድንገት ወደ ራስ ማወዛወዝ ከገባ በቃ ነገር አለ ማለት ነው፡፡ ወይ ወንበር አግኝቷል፣ ወይ ገንዘብ አግኝቷል ወይ ብቻ የፋይቭ ሚሊዮኗን መኪና ገዝቷል ማለት ነው፡፡ እናማ ራሱን አወዛወዘ ማለት...አለ አይደል...“ወደ እኩዮችህ ሂድ!” እንደማለት ነው፡፡ (ሰዋችን እኮ ስንቱን እንደቻለ እኛና አንድዬ ነን የምናውቀው፡፡)
“እስቲ ባለ አምስት ሊትሩን ዘይት ስጠኝ።”
“አንድ ሺህ ሁለት መቶ ብር ነው፡፡”
እንደሚያውቃችሁና ደንበኛው እንደሆናችሁ ሳይሆን ልክ ከሌላ አካባቢ የመጣ ለአገሩ እንግዳ፣ ለሰዉ ባዳ አይነት ነው የሚያስመስላችሁ፡፡
“ምን! አንድ ሺህ ሁለት መቶ ነው ያልከኝ! ምን ያልኩ መስሎህ ነው? ባለ አምስት ሊትሩን ዘይት ነው እኮ ያልኩህ፡፡”
“ሰማሁ፤ አንድ ሺሀ ሁለት መቶ ሆኗል፡፡”
“ትናንትና አምስት መቶ ዘጠና ብር አልነበረም እንዴ!”
“በቃ ጨምሯል፡፡” (የአንዳንድ ነጋዴዎች እብሪትማ... ከእናንተ ጋርማ ገና የምናወራርደው ‘ማትስ’ አለን!)
ታዲያላችሁ...ድሮ ሱቅ ከደረስን በኋላ ስንሳቀቅ የነበረው አሁን ግን ለወጥ ብሏል። ልክ ነዋ...ያለችንን ብር ቋጥረን ይዘን ሄደን ከመሳቀቃችን በፊት አሁን...አለ አይደል... ልክ እንደ ቅድሚያ ክፍያ አገልግሎት... ‘ቅድሚያ መሳቀቅን’ እየተለማመድን ነዋ! ለምን ይዋሻል... “ይሄ ሐምሌ መጥቶ ምን ያደርጉን ይሆን?” እያልን እንደሆነ መዝገብ ላይ ይስፈርልንማ! መቼም መገረም የሚሉትን ነገር ለምደነው “የሚገርም ነገር እኮ ነው!” ማለት ቀንሰን እንጂ የሚያስገርም ነገርማ መአት አለ፡፡
አንድ የሆነ እቃ ሊገዛ ሄዶ ከጥቂት ቀናት በፊት ስምንት መቶ ብር የነበረው ዋጋ በአንድ ጊዜ ሁለት ሺህ ስምንት መቶ ብር የሆነበት ወዳጃችን ቢቸግረው “ዝም ነው እንጂ ሌላ ምን ማድረግ ይቻላል!” ነው ያለው። እናላችሁ... ገና ከአሁኑ በየቦታው በዚህም በዛም እቃ ላይ እየጨማመሩላችሁ ነው፡፡ አሁን እየጨመሩባቸው ያሉ እቃዎችና አገልግሎቶች ላይ በሐምሌ ደግሞ ሲቆልሉበት ይታያችሁማ! (እነ እንትና “እስቲ ሻይ ግዛልኝ፣” የምትሉትን ነገር ካልተዋችሁኝ በቀጠሯችን ዕለት ከቤት ሻይ በፔርሙስ ይዤ እንደምመጣ እንድታውቁት ነው፡፡ መጠጫ ብርጭቆ ከእናንተ፡፡ ‘ስትራክቸራል አድጀስትመንት’ ይሏችኋል እንዲህ ነው፡፡ ቂ...ቂ...ቂ...)
የምር ግን እንግዲህ ጨዋታም አይደል፣ ያው ነገርዬው “የማይቀርልህን እንግዳ አጥብቀህ ሳመው፣” ስለሆነ ከአሁኑ በየአቅማችን መዘጋጀቱ ሳይሻል አይቀርም። ያው እንግዲህ አባወራና እማወራ ይቀመጣሉ... ‘ስትራቴጂና እቅድ’ ለመንደፍ። (ስሙኝማ... ለጨዋታው ያህል... ይቺ አባባል የሆነ ዜማ ያላት ነገር አትመስልም! ልክ ነዋ ‘ስትራቴጂና እቅድ’ የተዘጋጀለት ነገር አሪፍ መሆን አለበታ! ያው መጨረሻ ላይ “ድንቄም ስትራቴጂና እቅድ” ብለን አጨብጨበን ብንቀርም ማለት ነው፡፡)
እናላችሁ... እሱና እሷ ውይይት ይጀምራሉ፡፡
“እንደምታውቂው ኑሮ ጣራ ነክቷል፡፡ ሁሉም ነገር ከባድ እየሆነ ነው፡፡”
“ምን ኑሮ ብቻ የእኔም ደም ብዛትና ስኳር ጣራ ነክቷል፡፡”
“ከመቼ ወዲህ ነው ደግሞ ደም ብዛትና ስኳር የመጣብሽ?”
“እየመጣ ነው፡፡”
“በምን ታውቂያለሽ? የሚሰማሽ የተለየ ህመም አለ እንዴ?”
“በቃ ቀልቤ ሲነግረኝስ! አሁን የጀመርከውን ቀጥል፡፡”
“አሁን ያለንበትን ሁኔታ ለአንቺ አልነግርሽም። እንደምንም እየተፍጨረጨርንም ቢሆን እዚህ ደርሰናል። እያዳመጥሽኝ ነው?”
“አይ ማካሪና እየዘፈንኩ ነው፡፡”
“ለምንድነው በሌለ ነገር ቱግ የምትዪው! እኔ አሁን ምን ክፉ ነገር ተናገርኩ?”
“እጄን አጣምሬ ዓይኔን አፍጥጬ እየሰማሁ ጭራሽ እያዳመጥሽ ነው ወይ ትለኛለህ! ምነው ደንቆሮ ሆናለች አሉህ እንዴ!”
“እሺ ይቅርታ፡፡ ያው እንደሰማሽው በሐምሌ የነዳጅ ዋጋ ሲጨምር የኑሮ ጫናው መብዛቱ አይቀርም፡፡ ነገሮች አሁን ካለው ከባድ ነው የሚሆኑብን፡፡”
“እና...”
“እናማ ከአሁኑ ወጪያችንን በምን መልክ ማስተካከል እንዳለብን ማሰብ አለብን፡፡ ማለቴ አንዳንድ ነገሮችን ወይ መቀነስ ወይ ጭርሱን መተው አለብን፡፡ ለምሳሌ...”
“ለምሳሌ ምን?”
“ለምሳሌ ሥጋ መቀነስ አለብን፡፡”
ይህን ጊዜ እማወራዋ ወላ ኩል፣ ወላ ፋውንዴሽን ወላ ምናምኑ ሀምሳ ከመቶ እስኪለቅ በሳቅ ፍርስ ትላለች፡፡ እንደውም ትን ብሏት ጎሮሮዋን በውሀ ነው ያባበለችው።
“የጉድ ሀገር አለች ያቺ አክስቴ፡፡ ምን ግርም ይልሻል አትለኝም! የእኔ ባል ዘንድሮ እንዴት አይነት ተጫዋች ሆነሀል እባክህ! ለምን ኮሜድያን ሆነህ ኑሮ መደጎሚያ ትንሽ ተጨማሪ ገንዘብ አታመጣልንም!”
“አሁን ይሄ እንዲሀ ያስቃል! ሥጋ እንቀንስ ማለት ምኑ ነው የሚያስቀው?”
“የሚያስቀውማ የእኔ ውድ ባል ምን መሰለህ...እንኳን ሆዳችን ዓይናችን እንኳን ያልለመደብንን ነገር ምኑን ነው ከምን የምንቀንሰው! ንገረኛ! በዓመት አንድ ጊዜ ቤት ከምታመጣት ግማሽ መደብ የሥጋ ቅርጫ ቅንጥብጣቢ ላይ ነው የምንቀንሰው? ስማኝ የእኔ ኮሜዲያን ባል፤ እኔ ህልም መፍታት ስለማልችልበት ህልምህን አትንገረኝ፡፡ እሺ ሌላ ደግሞ ምን እንቀንስ?”
“ለምሳሌ እንጀራ እንዳለ ትሪው ላይ ከሚዘረጋ ይልቅ አንዷ እንጀራ አስር አስር ቦታ እየተቆረጠች ለምሳ ሦስት፣ ለእራት....እንዴት ነው የምታዪኝ?”
“ምን ላድርግ የእኔ ውዱ ባለቤቴ! ሰጋሁኝ፣ በጣም ሰጋሁኝ፡፡”
“ለምኑ?”
“ምቀኞች ምን አይነት እጸ ፋሪስ አቀመሱብኝ ብዬ ነዋ! አሁን እንደው ባልጠፋ ሰው በአንተ ይቀናል?”
“አንቺ ሁልጊዜ ነገሮችን እንደቀልድ...”
“አንተ ነህ እንጂ! እየቀለድክ ያለኸው፤ አንተ ነህ እንጂ! እንጀራ ስለመቆራጠጥ ከምታወራ እየቆራረጥክ የትም፣ ለማንም ስለምትበትነው ገንዘብ ብታወራ አይሻልም! ምነው እሷ አትሰማም ብለህ ነው እንዴ?”
“ምን ለማለት ፈልገሽ ነው?”
ቀጣዩን ክፍል በስፍራው የሚገኙ ሹክ ባዮቻችን ሹክ ሲሉን እንመለስበታለን፡፡ ቂ...ቂ...ቂ...
ስሙኛማ ‘ለምሳ ሦስት ቁርጥ፣ ለእራት ሦስት ቁርጥ...’ የምትለዋ ሀይለኛ ወጪ ቆጣቢ ነገር አትመስላችሁም!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 1839 times