Saturday, 25 June 2022 17:46

ብትፈትል አንድ ልቃቂት፣ ብትናገር ያምናውን

Written by 
Rate this item
(5 votes)

  አንድ የኢራቅ ተረት እንዲህ  ይላል፡-
ከዕለታት አንድ ቀን ከሁለት የተለያዩ ሚስቶች ሶስት ወንዶች ልጆች የነበሩት አንድ ሡልጣን ነበር፡፡ አንደኛው ልጁ እንደሱው ዐረብ መልክ ያለው ነው፡፡  ሦስተኛው ልጁ ግን የዐረብ መልክ ያለው ሃበሻ ነው፡፡ እኒህ ወንዶች ልጆች አንድ ቀን ወደ አባታቸው መጥተው “ለምን ሚስት አትፈልግልንም?” አሉና ጠየቁት፡፡ አባትየውም ለሁለቱ ታላላቅ ወንዶች ልጆቹ፤ “ጣራችን ላይ ውጡ፡፡ ቀስታችሁንም ወደፈለጋችሁት አቅጣጫ ወንጭፉት፡፡" አላቸው፡፡
የትልቁ ልጅ ቀስት ተወርውሮ በአንድ አሚር ቤት ጣራ ላይ አረፈ፡፡ (የአሚር ትርጉሙ የአገሪቱ ልዑል እንደማለት ነው) የአሚሩ ሴት ልጅ ሽማግሌ ተላከባትና የቀለበት ሥነ ሥርዓት ተፈፀመ፡፡ ትልቁ ልዑል አገባት፡፡ ቤቱም መጣች፡፡ የሁለተኛው ልዑል  “ቀስት የአዋቂው ቤት ላይ አረፈ” ስለዚህም የአዋቂው ሴት ልጅ ሽማግሌ ተላከባት፡፡ የቀለበት ሥነ ሥርዓቱንም ፈፀሙ፡፡ ባል ቤትም  መጣች፡፡ ሦስተኛውና ሃበሻው ወጣት የአባቱን ቤት ትቶ ሚስቱ ወደምትሆነው ሴት ቤት ሄደ! ብዙ መንገድ ኳተነ፣ ሄደ…ሄደ…. አንድ አንበሳ ጋ እስከሚደርስ ተጓዘ፡፡ ኳተነ፡፡ አንበሳውም፤ “የሰው ልጅ ሆይ! አትፍራ፤ ወደ እኔ  ና" አለው፡፡ "አልጎዳህም ናና እርዳኝ ውለታህን  እከፍላለሁ፤ አይዞህ ናና እርዳኝ" አለው፡፡ "እንደምንም የተጎዳውን እግሬን ብቻ አክመኝ፡፡ ውለታህን እከፍላለሁ” አለው፡፡
ወጣቱ ወደ አንበሳው ቀርቦ እግሩን አየ፡፡ ትልቅ እሾህ ተቀርቅሮበታል፡፡ መንጭቆ ነቀለለት፡፡ አንበሳውም እፎይ አለ፡፡ ከዚያም አንበሳው ልጁን አለው፡-
“ከቆዳዬ ሦስት ፀጉር ነቅለህ ያዝ፡፡ በቸገረህና ችግር በገጠመህ ሰዓት እርስ በእርስ ፀጉሮቹን አስተሻሻቸው” አለው፡፡
አስተሻሻቸው፡፡ ሶስት አገልጋዮች እፊቱ ድቅን አሉና፤ “ምን እንታዘዝህ ጌታዬ?” አሉት።
"አንድ ክንፍ ያላት በቅሎ” አላቸው፡፡
 ወዲያውኑ አንዲት የምታምር በቅሎ ከነመረሻቷ ብቅ አለች፡፡  ያማረ ልብስ ለበሰ ልዑሉ። በቅሎዋን መጭ ብሎ በአየር ላይ ተጉዞ ወደ አቅራቢያ ማረፊያው አረፈ! እዚያም እንደ እረኛ አግኝቶ አንድ በግ ገዛ፡፡  የበጓን ቆዳ ገፈፈና እንደ ዘውድ ጎፈር ራሱ ላይ አደረገው። መላጣም መሰለ፡፡
ሱልጣኑ ቤተ መንግስት ፊት ለፊት መጣ፤ ከዚያ ከአንድ አትክልተኛ ተገናኝቶ መንገድ ጠየቀ፡-
ሦስተኛው ልጅ ግን ፣ የአበሻዋን ልጅ የአበሻ እናቱን ትቶ ቤት ያለው ማረፊያ ቦታ በመፈለግ አቅሙ እስከሚቻለው ድረስ  እስከ መሬት ጠርዝ ተጓዘ! አንድ አንበሳ እስከሚገኝበት ድረስ ተጓዘ! አንበሳውም “ና ቅረበኝ ወንድሜ! ቅረበኝና እርዳኝ፡፡ እኔ አልጎዳህም!” አለው፡፡
በበግ ቆዳ  ተሸሽጎ ወደ ከተማ ገባ! አንድ አትክልተኛ ከሡልጣኑ ቤተ መንግስት አገኘ። "ሥራ ከኔ ጋር እንድትሰራ  ነፃ ሆነህ ልታገለግለኝ ይቻለሃልን?” ሲል ጠየቀው፡፡ እሺ ብሎ አትክልት ውስጥ ሆኖ በልዕልቲቱ መስኮት አኳያ ፀሐይ/ ተመስላ አያት! አንድ ቀን አያት!
ወጣቱ ሦስቱን ፀጉሮች አስተባብሮ አሽቶ ልዕልቲቱ ፊት ከች  አለ፡፡ እንዳየችው ወደደችው! ያንን አትክልተኛ ወደሷ ላከው፡፡ "የሆነውን ለንጉሡ ንገር" አለችው!
አትክልተኛው ንጉሱ ዘንድ መቅረብ ስለፈራ አንድ ዘዴ አበጀ፡፡ ሶስት ሀብሀቦች አመጣ። አንድ ጥሬ፣ አንድ መካከለኛ የበሠለ፣አንድ በደንብ የበሰለ! ንጉሱ ተናቅሁ ብለው ተናደዱ! አትክልተኛው ግን የሦስቱን ሀብሀቦች ትርጉም  በማስረዳት እንዲህ አላቸው፡፡
1ኛ ጥሬው ሃብሃብ  የተሰጣት ልጅዎን የምትወደው ወንድ ላይ እንድትወረውረው ይጠይቋት
2ኛ መካከለኛውን ሀብሀብ ለሁለተኛዋ ልጅዎ ይስጧትና ምረጭ በሏት
3ኛውን ሀብሀብ ለሦስተኛዋ ልጅዎ የምትፈልጊው ወንድ ላይ ወርውሪው በሏት አላቸው፡፡
ሦስቱም የንጉሡ ልጆች ሀብሀባቸውን ይዘው አላፊ አግዳሚውን ሲያዩ ቆዩና፤
 ሀ/ ታላቅየዋ የአንድ አሚር ልጅ ላይ ወረወረች
ለ/ ሁለተኛዋ ታላቅ ደግሞ የአዋቂ ልጅ ላይ ወረወረች
ሐ/ ሦስተኛዋ ሳትወረውር ቀረች፡፡ ንጉሡ አስጠርተው፤
“ምነው የኔ  ልጅ፤ የምትፈልጊው ወንድ ላይ ሀብሀብሽን አልወረወርሺም?” አሏት፡፡
ልዕልቲቱም፤
“የሚመርጠኝ ራሱ ይመጣል!” አለቻቸው፡፡
እንዳለችውም አትክልተኛው መጣ።
“ለምን ለምርጫ ከሰዎቹ ጋር አልተለሰለፍክም?” አለችው።
“አንቺ የራስሽ ምርጫ እንዳለሽ እኔም የራሴ ምርጫ አለኝ። ለእኔ ያላትን አላጣትም ብዬ ቆየሁ። የበሰለው ሀብሀብ በእጅሽ እንዳለ ሳውቅ፣የእኔ መሆኑን አመንኩ!” አላት።
“እኔም የምጠብቀው የበሰለውን ሀብሀብ ነበር!; ብላ አቀፈችው። በሣምንቱ ሰርጋቸው ሆነ ይባላል!
*   *   *
ጥሬውን፣ መካከለኛ በሳሉንና፣ ሙክክ ያለውን የአገራችንን ሁኔታ እንወቅ። ምርጫችን ለህልውናችን ወሳኝ ነውና በበረሃ ውስጥ የሚበቅለውን ሀብሀብ የብስለት ደረጃ እንለይ! ሁልጊዜም ውስጡን እንፈትሽ፡፡ አንዳንዱ ሁኔታ ገና ፍፁም ጥሬ ነው! አንዳንዱ ገና ግማሽ መንገድ ላይ ያለ ነው! አንዳንዱ ግን በስሎና ጎምርቶ በሰአቱ እጃችን ካልገባ ያመልጠናል። በአገራችን የለውጥ ሂደት ይሄን ዓይነት ባህሪ አለው!
“ካልተሳፈሩበት፣ቶሎ ተሽቀዳድሞ
ጊዜ ታክሲ አይደለም አይጠብቅም ቆሞ።
እንደሚለው ጥንታዊ አገርኛ ግጥም ነው! ወይም ደግሞ  ናፖሊዮን ቦናፓርት በታሪክ አለ እንደሚባለው፡-
"Place we can recapture Time never!"
(“ቦታን ቢያስለቅቁንም ደግመን እንይዘዋለን። ጊዜን ግን በጭራሽ !” እንደ ማለት ነው።)
ኢትዮጵያ ከንጉስ እስከ ፕሬዚዳንት፤ አልፎ ተርፎም ከሊቀ መንበር እስከ ጠቅላይ ሚኒስትር፤ በየዘመኑ አስተናግዳለች። አንዳንዱ ዘለአለማዊነትና ረጅም ዕድሜ የተምታታበት ነው! He mistook longevity for eternity የሚባል አይነት! አንዳንዱ “ይቺ ወንበር አንድ ናት፤ ለስንት ትበቃናለች" የሚል ነው! አንዳንዱ ደግሞ “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” የሚል ነው! አንዳንዱ ደግሞ “ከመታህ ድርግም፣ ከዋሸህ ጥርቅም!” አለ የተባለው አይነት ነው!! ዞሮ ዞሮ ግን “አንተ ብሳና ይሸብታል ወይ?” ቢለው “ለዛፍ ሁሉ ያስተማረው ማን ሆነና ነው?” አለ እንደተባለው ነው!
ብዙዎቹ መሪዎቻችን በዚህም ተባለ በዚያ “የቆቅ ለማዳ የለውም!” የሚለው ተረት የሚገልፃቸው ናቸው-ዛሬም ጭምር! ረዣዥም ዲስኩርና ንግግር እስኪታክተን ያሰማሉ። ለምሳሌ የደርግ መንግስት መሪ የነበሩት ጓድ ሊቀ መንበር፣ አንድ ከሰዓት ሙሉ ሰው ስራ ትቶ ንግግራቸውን እንዲያዳምጥ አድርገዋል! አንድም በካሮት፣ አንድም በበትር (carrot and stick እንዲል መፅሀፉ) የማማለልና የማስፈራራታቸውን ያህል በ”ዴማጎጂ”ም - የህዝብን ስሜት በመቀስቀስም ይጠቀማሉ!
በሀገራችን በተደጋጋሚ የሚሰሙት የፖለቲካል ኢኮኖሚ አጀንዳዎች እጅግ ከመደጋገማቸው የተነሳ በልካችን የተሰፋ የዘወትር ልብስ ይመስላሉ፡- ረሀብ፣ ጦርነት፣ መፈናቀል፣ መልሶ ማቋቋም፣ መንደር ምስረታ፣ ሽግግር፣ ትራንስፎርሜሽን፣ ፀረ ህዝብ፣ ፀረ ልማት፣ የማዳበሪያ እጥረት፣ የዘር እጥረት፣ የመብራትና ውሃ መጥፋት፣ የዋጋ ግሽበት፣ የመዋቅር ለውጥ፣ ሰላም፣ ተሐድሶ፣ መካከለኛ ገቢ፣ የኑሮ ውድነት፣ ድርቅ፣ ቸነፈር፣ የፍትህ መጓደል፣ ሰውን አላግባብ ማሠር፣ የሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብት መጓደልና መነፈግ፣ መደበኛ ስብሰባ፣ ድንገተኛ ስብሰባ ("አሁንስ ህይወት ራሷ የተራዘመ ስብሰባ መሰለችኝ” ነው ያለው በአሉ ግርማ?....)…ምኑ ቅጡ!
"እንደ አፍ የሥራ ካቴና የለም፤ እንደ ጉራ የሹም መቃብር” ያሉት ደራሲ ደህና መጠቅለያ ይሆኑልናል፡፡
የዲሞክራሲ፣ የፕሬስ፣ የተቋም ማበልፀግና የመብት ጥያቄዎች ዛሬም አሯሯጭ (pace maker) እንደፈለጉ ናቸው። አጠቃላዩን የፀጥታ ጥያቄንና የጎረቤት ወረራን እንደ ድግግሞሽ ተግባር ከማየት ይልቅ ለዘለቄታው ምን ይበጀናል ማለትን እንደ አንገብጋቢ ጥያቄ ቢያዩት ደግ ነው! ቢያንስ "ከስንቱ ተቋስለን እንችለዋለን?” ብሎ መጠየቅ  ያባት ነው! “በድብቁ ድርድር ውስጥ እኛም እንሳተፍ” ከሚል አላጋጭ የፓርላማ አባል ልዩ መፍትሔ ባንጠብቅም፣ የፓርላማችንን ዲሞክራሲያዊነት ጥሩ ጅምር ነው ማለትን ማንም አይከለክለንምና! ለዛሬው ዋነኛ መልዕክታችን “ነገር ቢበዛ በአህያ አይጫንም” የሚለውን ነው። የጉዳያችን ቡጥ ግን "ብትፈትል አንድ ልቃቂት፣ ብታወራ ያምናውን" የሚለው ብርቱ ፍሬ ነገር ነው! አፍ ይሰብሰብ፣እጅ ይዘርጋ!

Read 11874 times