Saturday, 25 June 2022 18:00

የኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብታዊ እድገት በበርካታ ተግዳሮቶች እየተፈተነ ነው ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

 የኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት ውስጣዊና ውጫዊ ተግዳሮቶች በእጅጉ እየናጡት እንደሚገኝ የጠቆመው አለማቀፉ የገንዘብ ተቋም መፍትሄው አፋጣኝ መዋቅራዊ ማሻሻያ መሆኑን አመልክቷል።
በ2021/22 የኢትዮጵያ አማካይ አመታዊ እድገት 3.8 በመቶ እንደሚሆን የተነበየው ተቋሙ፤ ይህም በሸቀጦች ዋጋ ንረትና በውጭ ምንዛሬ እጥረቶች የታጀበ ጤናማ ያልሆነ እድገት መሆኑንም አመልክቷል፡፡
በአሁን ወቅት የኢትዮጵያን የምጣኔ ሀብት እድገት በእጅጉ እየተገዳደሩት ከሚገኙ ጉዳዮች መካከል በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ጦርነት፣ በተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰቱ  ግጭቶች፣ አነስተኛ የግብርና ምርት፣ የውጭ እርዳታዎችና  ድጋፎች መቀነስ እንዲሁም ድርቅ  በአለማቀፍ ደረጃ ደግሞ የዩክሬን ሩሲያ ጦርነትና የነዳጅ ዋጋ መናር ዋነኞቹ መሆናቸው ተጠቁመዋል።
በዩክሬን ያለው ጦርነት በኢትዮጵያ በነዳጅ፣ በምግብና በማዳበሪያ ዋጋ ላይ ቀጥተኛ ተጽዕኖ ማሳደሩን ያመለከተው የአይኤምኤፍ ሪፖርት፤ አብዛኞቹ መሰረታዊ ሸቀጦችም በጥቂት ወራት ውስጥ በእጥፍና ከእጥፍ በላይ የሆነ የዋጋ ጭማሪ ማሳየታቸውን ጠቁሟል።
በአሁን ወቅትም ሃገሪቱ በመጠባበቂያነት የያዘቻቸውን ምርቶችና የተለያዩ ግብአቶች  በመጠቀም ላይ እንደምትገኝ የሚገልፀው ሪፖርቱ፤ ይህም አገሪቱ የከፋ ሁኔታ ላይ እንደምትገኝ አመላካች ነው ብሏል፡፡
ከምግብና ምግብ ነክ ሸቀጦች በተጨማሪ የተለያዩ ፍጆታዎች ላይ የሚስተዋለው የዋጋ ንረትም ከፍተኛ መሆኑን የሚገልፀው ሪፖርቱ፤ ለሃገሪቱ የመሰረተ ልማት እድገት ወሳኝ የሆኑ የግንባታ ቁሳቁሶች ግብአቶች ዋጋም መናሩን ነው የጠቆመው፡፡
 በተለያዩ ተግዳሮቶች ክፉኛ እየተናጠ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት ከችግር ለማውጣት መንግስት መጠነ ሰፊ መዋቅራዊ ማሻሻያዎችን እንዲያደርግ፣ ሃገራዊ ምርትን ለመጨመር በሚያግዙ ተግባራት ላይ እንዲያተኩሩ እንዲሁም በዋናነት ለሃገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ስብራት መንስኤ የሆነውን ጦርነትና ግጭትን በአፋጣኝ እንዲያስቆም ሲል ተቋሙ ምክረ ሃሳቡን አቅርቧል።

Read 1065 times