Print this page
Saturday, 25 June 2022 18:06

መንግስት የዜጎችን በህይወት የመኖር ተፈጥሯዊ መብት እንዲያስከብር ፓርቲዎች ጠየቁ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

 - “ከጥቃቱ የተረፉ ዜጎችን ደህንነት አስተማማኝ ማድረግ ይገባል”-ኦፌኮ-
      -መንግስት ለሚረግፉ ዜጎች ህይወት ተጠያቂ ነው”- ኢዜማ-
      - “መንግስት ዜጎችን መጠበቅ ቢያቅተው፣ ቢያንስ ከማዘናጋት ይቆጠብ”-እናት -ፓርቲ
                   
           ከጊዜ ወደ ጊዜ በዜጎች ላይ ማንነትን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶችና የጅምላ ጭፍጨፋዎች መባባስ በእጅጉ እንዳሳሰባቸው የገለፁ የተቃዋሚ ፓርቲዎች፤ መንግስት የዜጎችን በህይወት የመኖር ተፈጥሯዊ መብት እንዲያስከብር ጠየቁ።
በወለጋ በአማራ ተወላጆች ላይ ሰኔ 11 ቀን 2014 ዓ.ም የተፈጸመውን የጅምላ ግድያ በመግለጫቸው በጽኑ ያወገዙት የፖለቲካ ፓርቲዎቹ፤ መንግስት የዜጎችን ደህንነት የማስጠበቅ ዝቅተኛውን ሃላፊነቱን እየተወጣ አይደለም ሲሉ ክፉኛ ወቅሰዋል።
በየጊዜው በዜጎች ላይ እየጠፈፀሙ ያሉትን ጭፍጨፋዎች  በመግለጫው ያወገዘው ኢዜማ፤ እንዲህ አይነት ጭፍጨፋዎች እንዳይፈጠሩ አስቀድሞ መስራት ያለበት መንግስት፤ “ለሚረግፉ ዜጎች ህይወት ተጠያቂ ነው” ብሏል።
የመንግስት ተቀዳሚ ተግባሩ የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ መሆኑን ያስታወሰው ኢዜማ፤ በተለይ በዚህ ወቅት መንግስት የዜጎችን ደህንነት የማስጠበቅ ስራውን በጥንቃቄ እንዲወጣ ጥሪ አቅርቧል።
ህዝብን በሚያሸብሩና የበርካቶችን ነፍስ በሚቀጥፉ ሃይሎች ላይ በማያዳግም መንገድና ተመልሰው ለህብረተሰቡ የደህንነት ስጋት መሆን በማይችሉበት ደረጃ በከፍተኛ ጥንቃቄ እርምጃ መወሰድ እንዳለበትም ኢዜማ አሳስቧል።
“መንግስት ዜጎችን መጠበቅ ቢያቅተው እንኳን ቢያንስ  ከማዘናጋት ይቆጠብ” ሲል በመግለጫው ያሳሰበው  እናት ፓርቲ፤ “ባለፉት አራት አመታት የታየውን ያህል በኢትዮጵያ ውስጥ በሰላማዊ ሰዎች  ላይ የበዛ ግፍ ደርሶ አያውቅም” ብሏል።
መንግስት ለዚህ መሰሉ የዜጎች ጥቃትና ጭፍጨፋ ተጠያቂ የሚያደርገውን አሸባሪ ቡድን በየጊዜው “ደምስሼዋለሁ፣ በአካባቢው የለም” የሚሉ ፕሮፓጋንዳዎችን እያሰራጨ  ዜጎችን ከማዘናጋት እንዲቆጠብ አሳስቧል-ፓርቲው።
በወለጋ ከሰሞኑ የተፈጠረውን ጨምሮ ከዚህ ቀደም የተፈጸሙ ጭፍጨፋዎች በሙሉ የዘር ፍጅት (ጄኖሳይድ) ነው ብሎ እንደሚምንም ፓርቲው በመግለጫው አስታውቋል።
ይህ “የዘር ፍጅት” ይቆም ዘንድም መንግስት መሰረታዊ የእርምት እርምጃዎች ሊወስድ እንደሚገባ ያስገነዘበው እናት ፓርቲ፤ የዘር ፍጅቱን የፈፀሙ ሁሉ ለፍርድ እንዲቀርቡ፣ የአካባቢው ባለስልጣናት ከሃላፊነታቸው ተነስተው በህግ ተጠያቂ እንዲደረጉ፣ በምትካቸውም የሰው ነፍስ ግድ በሚላቸው፣ አንደበታቸው በታረመና ከጥላቻ በጸዱ አመራሮች እዲሾሙ ጥሪ አቅርቧል።
በተጨማሪም ብሄራዊ የሃዘን ቀን እንዲታወጅ፤ ህዝቡ ራሱን በያለበት ተደራጅቶ እንዲከላከል መንግስትም ከአዘናጊ መግለጫዎችና ፕሮፓጋንዳዎች እንዲቆጠብ ጥሪ አቅርቧል እናት።
የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) በበኩሉ፤ “በአማራ ህዝብ ላይ እየተፈጸመ ላለው የዘር ማጥፋ ወንጀል መንግስት ሙሉ ሃላፊነቱን ሊወስድ ይገባል”ብሏል።
መንግስት በዜጎች ላይ የሚፈጸማን በደልና ጭፍጨፋ በአፋጣኝና ዘላቂ በሆነ መልኩ እንዲያስቆም የጠየቀው ፓርቲው፤ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በአማራ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን የዘር ማጥፋት ወንጀል በግልጽ እንዲያወግዝ፣ በአማራ ህዝብ ላይ የተፈጸሙ “የዘር ፍጅቶች” በገለልተኛ አለማቀፍ አካላት ተጣርተው ወንጀለኞች ለህግ እንዲቀርቡ ይደረግ ዘንድ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችና ሌሎች አለማቀፍ ተቋማ ግፊት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል።
በአማራ ህዝብ ላይ በተለያዩ አካባቢዎች ሲፈጸም የኖረውና እየተፈጸመ ያለው ጭፍጨፋ እንደ ተፈጥሯዊና  መደበኛ ክስተት እየተወሰደ ነው ያለው የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) በበኩሉ፤ “በፌደራሉም ጥቃቱ እየተፈጸመባቸው በሚገኙ ክልሎች መንግስታት እርምጃዎችን ለመውሰድና ጥቃቱን በዘለቄታው ለመከላከልም ሆነ ለማስቆም ፍቃደኝነትና ዝግጁነት የሌላቸው በመሆኑ ያለማቋረጥና በመደበኛ ሁኔታ እየተከናወነ ያለውን የንጹሃን ጭፍጨፋና ጥቃት ማስቆም አልተቻለም” ብሏል።
በዚህ መሃል ማቆሚያ ያጣው ጥቃት መዘዙ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን መትረፉ እንደማይቀር ያሳሰበው አብን፤ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ድርጊቱን እንዲያወግዙና ከንጹሃን ጎን እንዲቆሙ ጥሪ አቅርቧል።
መንግስት የዜጎችን ሰላምና ደህንነት የማስጠበቅ ሃላፊነቱን እንዲወጣና አጥፊዎችን ለፍትህ እንዲያቀርብ፣ ጥቃቱ በተፈጸመባቸው አካባቢዎች ከሞት የተረፉ ነዋሪዎች አሁን በከፍተኛ ስጋት ውስጥ የሚገኙ ስለሆነ አፋጣኝ ህይወት አድን ድጋፍ እንዲያደርግላቸውና ለተጎጂዎችና ቤተሰቦቻቸው አስቸኳይ ሰብአዊ እርዳታ እንዲቀርብላቸው የጠየቀው አብን ፤መንግስት  ለጥቃት ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ነዋሪ የሆኑ ዜጎችን በማደራጀት፣ በማስታጠቅና አመራር በመስጠት ከመሰል ጥቃቶች ራሳቸውን የሚከላከሉበት አስቻይ ሁኔታ እንዲፈጥር እንዲሁም በዘላቂነት ችግሩን ለመፍታት መዋቅራዊና ስርአት ሰራሽ ሽግግር እንዲደረግ መክሯል።
“የንጹሃን ዜጎቻችንን ደህንነት ማስጠበቅ የመንግስት ሃላፊነት ነው” ያለው የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ)፤  ካለፉት ሶስት ዓመታት ወዲህ በኦሮሚያም ሆነ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች እየተካሄዱ ያሉ ጦርነቶችና ግጭቶች ለንጹሃን ዜጎች ሞት፣ ስቃይና መፈናቀል ምክንያት መሆናቸውን ጠቁሟል።
ሰኔ 11 ቀን 2014 በወለጋ በተፈጸመው የጅምላ ግድያ በአብዛኛው ሴቶችና ህጻናት መገደላቸውን የጠቀሰው ኦፌኮ፤ መንግስትና የኦሮሞ ነጻነት ጦር እርስ በእርስ መወነጃጀላቸውን በመግለጫው ይልጻል። በሌላ በኩል፤ በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን እንቶሊ በሚባል ስፍራ ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ ከመኪና ላይ እየወረዱ ግድያ መፈጸሙን፣ በጋምቤላም ሰዎች በአደባባይ  መረሸናቸውን በመጥቀስ፣ እነዚህን ጨምሮ ባለፉት 3 ዓመታት የተፈጸሙ መሰል ግድያዎችና ጥቃዎች በገለልተኛ አካል እንዲጣሩና አጥፊዎች ለህግ እንዲቀርቡ ጠይቋል።
በአሁኑ ወቅት ከጥቃት የተረፉ ዜጎች ተገቢው ትኩረት እንዲሰጣቸው፤ የማረጋጋትና መልሶ የማቋቋም እንዲሁም ደህንነታቸውን አስተማማኝ የማድረግ ስራ እንዲሰራም ኦፌኮ ጥሪውን አቅርቧል።



Read 11566 times