Saturday, 25 June 2022 18:15

ማዕድን ሚኒስቴር 513 ሚ. ዶላር የውጪ ምንዛሬ አግኝቻለሁ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

 የ972 ኩባንያዎችን ፈቃድ መሰረዙንም
                                  
            ማዕድን ሚኒስቴር ባለፉት 11 ወራት ብቻ 513.9 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ማግኘቱን አስታወቀ። የተገኘው የውጪ ምንዛሬ ከቡና ከተገኘው የዶላር መጠን በሁለተኛነት ደረጃ የሚያሰልፈው መሆኑም ታውቋል።
የማዕድን ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ ታከለ ኡማ ባለፈው ረቡዕ በጽ/ቤታቸው ለጋዜጠኞች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ  ነው ይህን ያስታወቁት።
ሚኒስትሩ አክለውም በማዕድን ምርመራ፣ ምርትና ኤክስፖርት ዘርፉ ፈቃድ ወስደው በህጉና በውሉ መሰረት ወደ ስራ ያልገቡ፣ ገብተውም ህገ-ወጥ ሥራ (ማዕድንን በኮንትሮባንድ መሸጥን ጨምሮ) ሲሰሩ የነበሩና አገር ልታገኝ የሚገባትን ጥቅም ያሳጡ 972 ኩባንያዎችን ፈቃድ የሚኒስቴር መ/ቤቱ መሰረዙንም ገልጸዋል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ኢትዮጵያና ህዝቦቿ ከማዕድንና ከተፈጥሮ ሀብታቸው የሚገባቸውን ያህል ጥቅም እንዲያገኙ የተለያዩ የሪፎርም ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ያብራሩት አቶ ታከለ፤ አሁንም የተለያዩ ሀገራዊና አካባቢያዊ ፈታኝ ሁኔታዎችን ተቋቁሞ በላቀ ትጋት እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በዚህም ምክንያት የወጪ ንግድ ማእድናትን በስፋት፣ በጥራትና በአይነት እንዲመረቱ በማድረግ በአገራዊ የውጪ ምንዛሬ ግኝት ላይ እየተገባደደ ባለው የበጀት ዓመት ሁለተኛው ከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ ያስገኘ ዘርፍ ለማድረግ ተችሏል ብለዋል።
የማዕድን ዘርፍ ብዙ ተዋናዮች ያሉበት በመሆኑ ለውጤታማነቱም ከፍተኛ ትስስርና የጋራ ስራን ይጠይቃል ያሉት ሚኒስትሩ፣ በህጋዊ መንገድ ሰርተው ራሳቸውንም ጠቅመው ኢትዮጵያም ከዘርፉ ማግኘት ያለባትን ጥቅም እንድታገኝ የሚያደርጉ ኩባንያዎችና ግለሰቦች እንዳሉ ሁሉ የማዕድን ሀብትን በህገ-ወጥ መንገድ መጠቀምን አማራጫቸው ያደረጉ ኩባንያዎችና  ግለሰቦችም እንዳሉ በተደረገ የመስክ ክትትል መረጋገጡንም ጠቁመዋል፡፡
በዚህም መሰረት በተለያየ የማዕድን ኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደው በገቡበት ውል ስምምነትና ባጸደቁት የስራ ፕሮግራም መሰረት ስራቸውን ያላከናወኑ የተለያዩ ባለፈቃዶች ላይ አስፈላጊውን ህጋዊና አስተዳደራዊ ሂደት በማሟላት እንዲሁም ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመወያየት፣ ሚኒስቴሩ ህዝብን በሚጎዳ ተግባር ውስጥ ያገኛቸውን የተለያዩ ፈቃዶች እንዲቋረጡ ወስኗል ብለዋል፡፡
በመሆኑም በማዕድናት ፍለጋ ተሰማርተው ለረጅም ዓመታት በገቡት ውልና ባጸደቁት የስራ መርሃ ግብር መሰረት ሥራዎቻቸውን ያላከናወኑ በመሆኑ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከክልሎችና ከባለድርሻ አካላት በየወቅቱ አስፈላጊ ድጋፍ ቢደረግላቸውም በፋይናንስ፣ በቴክኒካዊና በሌሎች ችግሮች ምክንያት በሚጠበቅባቸው መልኩ ወደ ልማት መግባት ባለመቻላቸው፣ በዚህም የሀገርን የልማት ውጥን በማሰናከላቸው 116 የማዕድን ምርመራ ፈቃዶችን መሰረዙን አስታውቋል፡፡
በሌላ  በኩል፤ የማዕድን ምርት ፈቃድ  ወስደው በገቡት ውል መሰረት ወደ ምርት ያልገቡ 6 ኩባንያዎችን ፈቃድ የሰረዘው መስሪያ ቤቱ፣ከወርቅ ማዕድናት ውጪ ያሉ ሌሎች ማዕድናት ወደ ውጪ ለመላክ የብቃት ማረጋገጫ፣ የምስክር ወረቀትና ፈቃድ የተሰጣቸው ነገር ግን የወሰዱትን ፈቃድ ሽፋን በማድረግ ህገወጥ የማዕድናት ግብይት (የኮንትሮባንድ ንግድ)ውስጥ በመሳተፍ መንግስት ከማዕድናት ምርት ሽያጭ ማግኘት የሚገባውን የሀገር ውስጥ ገቢ ያሳጡ፣ ከዚያም ባሻገር የያዙትን የኤክስፖርት ፈቃድ በውላቸው መሰረት በህጋዊ መንገድ ያልሰሩ፣ ፈቃዳቸውን ለህገ ወጥ የማዕድናት ዝውውር ያዋሉና የመንግስትን የስራ ፈቃድ ለግል ጥቅማቸው ማካበቻነት በማዋል ከማዕድናት  የውጭ ገበያ መገኘት የነበረበትን ሀገራዊ የውጭ ምንዛሬ ግኝት ያሳጡ 850 የማዕድን ላኪ ፈቃዶችን በድምሩ 972 የማዕድን ምርመራ፣ ምርትና ኤክስፖርት ፈቃድ የወሰዱ ኩባንያዎችን ፈቃድ መሰረዙን አቶ ታከለ ጨምረው ገልፀዋል፡፡
የዚህ ሁሉ ኩባንያ ፈቃድ ሲሰረዝ ከየሀገራቱ ጋር ያለው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዳይሻክር ምን ዓይነት ጥንቃቄ ተደርጓል? ኩባያዎቹ ፈቃዳቸው ሲሰረዝ የሚከፈላቸው ካሳ አለ ወይ? ከኮንስትራክሽን ጋር በተያያዘ የሲሚንቶ ዋጋ መናርና ጭራሽ ከገበያ መጥፋት እንዴት ይታያል? በሚል ከጋዜጠኞች ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ሚኒስትሩ ሲመልሱ፣ አንደኛ ሚኒስቴሩ ፈቃድ ከመሰረዙ በፊት በርካታ  የማግባባት የድጋፍና መሰል ሂደቶችን ከመጓዙም በላይ ከየኤምባሲዎቻቸው ጋር መወያየቱን ፣ሁለተኛ አብዛኞቹ ኩባንያዎች ይዘው መምጣት የሚገባቸውን የውጭ ምንዛሬ ጨምሮ ምንም ይዘው ስላልመጡ መንግስት የሚከፍለው ካሳ አለመኖሩን ገልጸዋል። ሲሚንቶ በተመለከተም 120 ሚሊዮን ህዝብ ባለበት አገር የሲሚኒቶ ዋጋ ናረ ጨመረ የሚል ጥያቄ መሆን እንደሌለበት ጠቁመው ከህዝቡ 50 በመቶው  የግድ  ሲሚንቶ እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል፡፡
ይህም ማለት ቢያንስ 50 ሚሊዮን ኩንታል ሲሚንቶ በዓመት ያስፈልጋል ያሉት አቶ ታከለ አሁን በሀገር ውስጥ እያመረትን ያለነው 5 ሚሊዮን ኩንታል በመሆኑ አቅርቦቱና ፍላጎቱ  ፈፅሞ ባለመመጣኑ ይህን ለማስተካከል ዘርፈ ብዙ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን አብራርተዋል ሚኒስትሩ አክለውም፤ በማዕድን ዘርፉ ላይ ቀደም ሲል አሳሪና የማያፈናፍኑ ህጎችና መመሪያዎች እንደነበሩ ጠቁመው አሁን ላይ እነዚህን አሳሪና ውስብስብ ህግና መመሪያዎች እያሻሻልንና እንዲያሰሩ እያደረግን በመሆኑ ብዙ ነገር ግን ምንም የማይፈይዱ ኩባንያዎችን እያስወጣን ጥቂት ግን ጥራትና ሀቀኝነት ያላቸውን ኩባንያዎች በማስገባት ሀገር ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን እንድታገኝ ሌት ተቀን እየሰራን ነው ብለዋል፡፡

Read 597 times