Saturday, 25 June 2022 18:10

750 ሚ. ብር የፈጀው ቲኬ ሆቴልና ሪዞርት ዛሬ ይመረቃል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

ግንባታው  13 ዓመታትን የፈጀውና 750 ሚ. ብር ወጪ የተደረገበት ቢሾፍቱ ቲኬ ሆቴልና ሪዞርት ዛሬ ከረፋዱ 4፡00 ጀምሮ ይመረቃል። በቢሾፍቱ ሀይቅ ዳር የተገነባውና ባለ አምስት ኮከብ  ደረጃ እንዳለው የተነገረለት “ቢሾፍቱ ቲኬ ሆቴልና ሪዞርት”፤ ከሌሎቹ ሆቴልና ሪዞርቶች የሚለይበት በርካታ መሰረተ ልማቶች እንዳሉት የቲኬ ኢንተርናሽናል ቢዝስና የቢሾፍቱ ቲኬ ሆቴልና ሪዞርት ባለቤት አቶ ጠና ከበደ ሰሞኑን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል።
የሆቴሉ ዋና ስራ አስያጅ አቶ ታሪኩ ተስፋዬ በበኩላቸው፤ ቢሾፍቱ ቲኬ ሆቴልና ሪዞርት ከ78 በላይ የተለያየ ደረጃ ያላቸው የመኝታ ክፍሎች፣ ከ25-800 ሰዎች የሚያስተናግዱ 6 የስብሰባ አዳራሾች፣ ከሆቴሉ እስከ ሃይቁ የሚወስድ 450 ደረጃዎች፣ ሳውና፣ ስቲም፣ ጂም፣ ሬስቶራንቶችና በአጠቃላይ አንድ ባለ አምስት ኮከብ ሆቴል ሊያሟላው የሚገባውን መሰረተ ልማት በበቂ ሁኔታ ማሟላቱን አብራርተዋል።
የቢሾፍቱ ሆቴልና ሪዞርት የሴልስና ማርኬቲንግ ክፍል ሃላፊ አቶ ዘበነ ኩራባቸው እንደገለጹት፤ ሆቴሉና ሪዞርቱን ለየት ከሚያደርጉት ነገሮች አንዱ ህንጻው እጅግ ዘመናዊ በሆኑ ቁሳቁሶች ከመገንባቱም ባሻገር ፈሳሽና ደረቅ ቆሻሻን የሚለይ እንዲሁም ጥቅም ላይ የዋለውን ውሃ መልሶ በማከም ጥቅም ላይ የሚያውል “ዋተር ትሪትመንት” የተሰኘ ቴክኖሎጂ የተገጠመለት  በመሆኑ አካባቢ ላይ የሚያደርሰው አንድም የብክለት ችግር አይኖርም።
አቶ ዘነበ አክውለም ሆቴሉ በአሁኑ ወቅት ከ100 በላይ ሰራተኞችን የቀጠረ ሲሆን 99 በመቶው የቢሾፍቱ ከተማ ነዋሪዎች እንደሆኑ ገልጸው፤ ሆቴሉ በሙሉ አቅሙ ስራ ሲጀምር  የሰራተኞቹን ቁጥር ወደ 200 ያሳድጋል ብለዋል።
ባለፉት 13 ዓመታት በግንባታው ሂደት በርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች የስራ እድል ተፈጥሮላቸው መቆየቱንም ነው አቶ ዘበነ ያብራሩት።
በሌላ በኩል፤ በሆቴልና ሪዞርት የምርቃት ሥነ-ስርዓት ላይ የባለሀብቶቹ አቶ ጠና ከበደና የባለቤታቸው ተስፋነሽ አሰፋ 52ኛ የጋብቻ በዓል የሚከበር ሲሆን ይህም ምርቃቱን የተለየና ታሪካዊ ያደርገዋል ተብሏል። በስነስርዓቱ ላይ የፌደራል መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት የኦሮሚያ ክልል ስራ ሃላፊዎች፣ የቢሾፍቱ ከተማ አመራሮችና ጥሪ የተደረገላቸው እግዶች እንደሚገኙም ታውቋል።


Read 644 times