Print this page
Saturday, 25 June 2022 18:34

የሠላም ዋጋው ሥንት ነው?

Written by  ልጅ አቤኑ (አቤንኤዘር ጀምበሩ)
Rate this item
(1 Vote)

  ሠላም በህግ በፀደቀ ቻርተር ወይም በቃልኪዳን ሰነዶች ላይ ሳይሆን በሰዎች ልቦናና ጭንቅላት ላይ ነው ፀንቶ የሚኖረው ይላሉ፤ የአሜሪካው 35ኛ ፕሬዚዳንት ጆን ኤፍ ኬኔዲ፡፡
ምሁሩ የፖለቲካ ሰውና የነፃነት ታጋይ የነበሩት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ከኢሳት ቴሌቪዥን ጋር በ2008 ዓ.ም. ባደረጉት ቃለምልልስ፤ በ1950ዎቹ በአሜሪካ ያደረጉትን የመጀመሪያ ጉዞና በአይናቸው እማኝነት ያረጋገጡበትን የጥቁር አሜሪካውያን ሰቆቃና በደል፣ የነጮችን የተወሳሰበ ጥላቻ ሰንሰለት ሲመለከቱ ነጭ አሜሪካውያን በዚያ ደረጃ የጥቁር ጥላቻ ይኖራቸዋል ብለው በጭራሽ አስበው እንደማያውቁ ይናገራሉ፡፡ ነጭ ሬስቶራንቶች ሲገቡ አስተናጋጆቹ ያደነቃፋቸው እየመሰሉ ሾርባ ይደፉባቸውና በዛው ጥለው እንዲወጡ የሚያደርጉበት ዘዴ ነበራቸው ይላሉ፤ በትዝታ ወደ ኋላ እየነጎዱ፡፡
በዚህ ልቡ የተነካው የወቅቱ ወጣት መስፍን፣ የዘር መድሎውን ልክ ለማወቅ ከዋሽንግተን ተነስቶ ደቡባዊውን የአሜሪካ ክፍል በአውቶብስ ጉዞ ለማዳረስና የነገሩን ደረጃ ለመገምገም ተነሳ፡፡ ምንም እንኳን በወቅቱ ከአንድ ግዛት ወደ ሌላ ግዛት የሚወጡ የትራንስፖርት ሰጪ ሀገር አቀፍ የትራንስፖርት መገልገያዎች ላይ የዘር ልዩነት እንዳይደረግ በፌዴራል መንግሥቱ የተወሰነበት ጊዜ ቢሆንም፣ ወጣቱ መስፍን ትኬት ወደቆረጠበት አውቶብስ ሲገባ ነጮቹ በሙሉ ወደ ፊተኛው ረድፍ ወንበር ተቀምጠው፣ ጥቁሮቹ የኋለኛውን የአውቶብስ ረድፍ ይዘው ይመለከታል፡፡ ልበ ሙሉው ወጣት መስፍን ወልደማርያም ግን የቀለም አምሳያዎቹ ጋር ሄዶ ከመቀመጥ ይልቅ አንድ ቆንጆ ነጭ ወጣት እንስት ያለችበት ወንበር አጠገብ ሄዶ ይቀመጣል፡፡ በነገሩ ጥቁሩም ነጩም የአውቶብስ ተሳፋሪዎች ይገረማሉ፡፡ አጠገቡ የተቀመጠችው ወጣት እንስትም በብስጭት ትቁነጠነጣለች፣ መስፍን ግን ሁኔታውን ከምንም ሳይቆጥር ጉዞውን ይቀጥላል። ማልዶ የተነሳው አውቶብስ ለቁርስ ዌስትቨርጂኒያ ላይ ጉዞውን ይገታል፡፡ አሁንም ነጮቹ ለብቻ ጥቆሮቹ ለብቻ ወደተለያየ አቅጣጫ ለቁርስ ይጓዛሉ፡፡ ወጣቱ መስፍን አሁንም ነጮች ወደሚስተናገዱበት ሬስቶራንት በድፍረት ይሄዳል፡፡ የሬስቶራንቱን ዙሪያ ገባ ተመለከተ፤ አዎ ጥቁር አይስተናገድበትም የሚል ምልክት በየትኛውም አቅጣጫ አላየም፡፡ ወጣቱ መስፍን ቀጥ ብሎ ወደ ሬስቶራንቱ በመግባት በነጮቹ መሃል አልፎ ለመስተናገድ ወንበር ይይዛል፤ አሁንም አይኖች ሁሉ በጥቁሩ ወጣት ላይ ያነጣጥራሉ፤ ተመጋቢውና ሰራተኛው ሁሉ መስፍንን በጥሞና መመልከት ይጀምራሉ፡፡
በዚህ መሃል አንድ ነጭ አስተናጋጅ ወደ መስፍን ቀርባ ምን ለማዘዝ እንደፈለገ ትጠይቀዋለች፤ ለመመገብ የፈለገውንም ይነግራታል፡፡ የመስተንግዶ ሠራተኛዋም የፈለገውን እንደምታመጣ ገልጻለት፣ ነገር ግን መስተንግዶውን ለማቅረብ አንድ ቅድመ ሁኔታ ታስቀምጣለች፡፡ ይኸውም በተቀመጠበት ቦታ ላይ መስተናገድ እንደማይችል በማስረዳት፣ ለብቻው የሚመገብበትን ጓዳ ታሳየዋለች፡፡ መስፍን በምላሹ የተቀመጠበት ቦታ ስለተስማማው ወደ ሌላ ክፍል መሄድ እንደማይፈልግ በልበ ሙሉነት ይነግራታል፤ የተወሰነ ጭቅጭቅ ይፈጠራል፡፡ በመጨረሻም የመስተንግዶ ባለሙያዋ ነገሩን እሷም እንደማታምንበት ጠቁማ፤ ነገር ግን የሬስቶራንቱ መመሪያና አሰራር እንደሆነ ትነግረዋለች፡፡ በዚህ ቅር የተሰኘው መስፍንም ሬስቶራንቱን ጥሎ ወጣ። እስከ ጉዞው ማጠናቀቂያም ለአምስት ቀን ያህል ወተት ብቻ እየጠጣ፣ ነገሩን እየቃኘ ነፍሱን ያቆያል፡፡
ታዲያ በአሜሪካ ሳለ በሌላ ጊዜ ያገኛቸው ነጭ የቤተ-ክርስቲያን ቄስ፣ በቤተ-ክርስቲያናቸው ንግግር እንዲያደርግ ይጋብዙታል፡፡ በአትሮንሱ ላይ ለንግግር የተሰየመው ትንታጉ ወጣት መስፍን፣ በጥሩ እንግሊዝኛ ዘረኝነታቸውን በፅኑ እንደሚያወግዘው ይነግራቸዋል፡፡ #በእናንተ ዘረኝነት ምግብ እንኳን በአግባቡ መመገብ እስኪያቅተኝ ድረስ ተፈትኛለሁ; ብሎ ተቃርኖውን ይገልፃል፡፡ ድርጊታቸው አስከፊም አስነዋሪም እንደሆነ አስረግጦ ይናገራል፡፡
 ይሄ የመስፍን ንግግር ከነማርቲን ሉተር ኪንግ ንቅናቄ አመታት በፊት የተደረገ፣ ምናልባትም ጥቁሮቹ ፀረ-ዘር መድሎን ተደራጅተው መታገል ከመጀመራቸው በፊት የቀረበ የመጀመሪያው የአሜሪካ የፀረ-መድሎ ንቅናቄ ንግግር ሳይሆን አይቀርም፡፡
 በመስፍን የእንግሊዘኛ ችሎታም የንግግር ይዘትም የተገረሙት ነጮቹ፣ ነገሩ በባህል ሲወራረድ የመጣ እንደሆነ ገልጸውለት፤ እነርሱም እንደማይቀበሉት ይነግሩታል። እንደውም ለጥቁሩ የማህበረሰብ ክፍል በቤተ - ክርስቲያናቸው መዋጮዎችን እንደሚያደርጉም ይጠቅሱለታል። ከጊዜያት በኋላ ግን መስፍን የነገሩን ጥልቀት የተመለከተበት አጋጣሚ ተፈጠረ፡፡ ለጥቁሮቹ መዋጮ የሚያደርገው የነጮቹ ቤተ-ክርስቲያን፣ ጥቁር ምክትል ፓስተር ይመደብላቸዋል፤ ይሄን ጊዜ የቤተ-ክርስቲያኑ ነጭ ምዕመናን ነገሩን በጥብቅ ተቃወሙ፡፡ ይሄ የሥልጣኔን፣ የዲሞክራሲንና የአስተሳሰብን ልክ ያየበት አጋጣሚ እንደነበር መስፍን ያስታውሳል፡፡  
ነገሩን ወደ 60 ዓመት ገደማ ወደ ኋላ ተመልሰው የሚያስታውሱት ፕ/ር መስፍን፤ “አሜሪካኖች አሁን ላይ ተመንጥቀዋል” ሲሉ በጊዜ ሂደት በአገረ አሜሪካ  የመጣውን ልዩነት ይመሰክራሉ፡፡ “ጥቁር አንገቱን ደፍቶ ነበር የሚኖረው፣ እንደ ዛሬ ደረቱን ገልብጦ አይሄድም፤ ዛሬ ሁኔታው ሌላ ነው፣ ሄደዋል በጣም አድገዋል፤ተሻሽለዋል፤ ነገር ግን ዘረኝነቱ ሙሉ ለሙሉ የሚታጠብ ስላልሆነ የተወሰነ ርዝራዥ አለ” ይላሉ። አሜሪካኖቹ ጥቁር ፕሬዚዳንት እስከ መምረጥ የሄዱበትን፣ የተደማመጡበትንና ለትውልድ የሚተርፍ ታሪክ የሰሩበትን አስደማሚ ሂደት በማድነቅ ይጠቅሳሉ፡፡
ታዲያ የአሜሪካኖቹን እመርታ እያስታወሱ፣ ኢትዮጵያ በዚህ ሁሉ ጊዜ ውስጥ አንድ ስንዝር ፈቀቅ እንዳላለች በድፍረት ይገልጻሉ፤ በቁጭት ስሜት፡፡ ኧረ እንደውም ከነበረችበት ማማ ቁልቁል ወርዳለችም ይላሉ፤ ፕሮፌሰሩ፡፡ በእርግጥም ኢትዮጵያውያን ከነበርንበት የመከባበርና የአብሮነት ልዕልና ወርደናል የሚያስብሉ ብዙ ምልክቶች እያስተዋልን ነው፡፡ አሁንማ ለይቶልን ወደ አውሬነቱ ደረጃ እየወረድን ነው፡፡ በአንድ ጀንበር በመቶዎች የሚቆጠሩ ንጹሃን ዜጎችን በጥይት ከመፍጀት የበለጠ አውሬነት አለ እንዴ? እንደው ለምዶብን ነው እንጂ በወለጋ የተፈጸመውን ዓይነት አረመኔያዊ የጭካኔ ተግባር የትኛው አውሬ ፈጽሞት ያውቃል? እውነቱ ከአውሬም እጅጉን ከፍተናል፡፡
ዛሬ ላይ በመካከለኛው ምሥራቅ ለዓለም የሚተርፍ ከባድ ህመም በፍልስጤማውያንና በሀገረ እስራኤል መካከል እየተስተዋለ ነው፡፡ በየጊዜው የሚጣለው የሰዓት እላፊ፣ ወከባዎችና አሰልቺ ፍተሻዎች ራስ ምታት ናቸው፡፡ ከዛ ባለፈም የእስራኤል ወታደሮች ተኩስ፣ እስራት በሰቀቀን እንዲኖሩ አድርጓቸዋል፡፡ እስራኤላውያኑም በየጊዜው በሚደርስ የሽብር ጥቃት ምክኒያት በስጋት ይኖራሉ፣  ዙሪያ ገባችን በጠላቶቻችን ተከቧል ብለው ስለሚያስቡ፣ ሁሌም የሥጋት ቀዳዳ ለመድፈን ደፋ ቀና ይላሉ፡፡
ከአሰቃቂው የሁለተኛው ዓለም ጦርነት ፍፃሜ በኋላ በዓለም የተበተኑት ቤተ እስራኤላውያን ወደ ቀደመ የአባቶቻቸው መሬት ይመለሱ ሲል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውሳኔውን ያሳልፋል። በውሳኔው መሰረትም እ.ኤ.አ ሜይ 14 ቀን 1948 የእስራኤል መንግስት ተቋቁሞ አይሁዳውያኑ ከአለም ዙሪያ የቀደሙ አባቶቻችን ምድር ወዳሏት እስራኤል ይሰበሰባሉ፡፡ ውሳኔውን መላ የአረብ ሀገሮች በከፍተኛ ቁጣ ተቃወሙት። በዛው ውሳኔ መነሻነት አምስት የአረብ ሃገሮች እስራኤል ላይ ጦርነት ከፍተው ሽንፈትን ያስተናግዳሉ። አረቦቹ እንደ ቅኝ-ገዥ የተመለከቱት የእስራኤል መንግሥት ይዞታ፣ በዓለም ካርታ ላይ የበሬ ግንባር እንኳን ተብላ ለመጠቀስ የማትበቃ በጣም አነስተኛ ቦታ ናት፡፡ ፍልስጤማውያኑ "ጽዮናዊ ወራሪዎች" ብለው ሲጠሯቸው፣ እስራኤላውያኑ በተቃራኒው "የቅድመ አያቶቻችን የነሰለሞን መሬት እስራኤል ማለት፣ በአሜሪካ ቀይ ህንዶችን የሚቀድም እንደሌለ ሁሉ፣ እኛን በዚህ ምድር የሚቀድመን የለም" ይላሉ። ታሪካችን ከዛሬ 3300 ዓመት በላይ የሚዘልቅ ነው ይላሉ። አረቦች እ.ኤ.አ በ1967 ባደረጉት ዳግም ጦርነት በደረሰባቸው ሽንፈት፣ ዌስትባንክ እና ጋዛ በእስራኤል ቁጥጥር ሥር ዋለ፡፡ ታዲያ በዚህ ጊዜ ውስጥ የፍልስጤማውያኑ የሽብር ጥቃት፣ የእስራኤል ተቀዳሚ የደህንነትና የሠላም ስጋት የነበረ ሲሆን፣ እስራኤላውያኑ በፍልስጤማውያን ላይ የሚያደርሱት ወከባ እስራትና ግድያም በአካባቢው ላሉ ህዝቦች ከፍተኛ ሥጋት ነበር፡፡
እ.ኤ.አ በ1993 ደም-መቃባትን ለማስቆም በጣም ተስፋ የተጣለበት አዲስ የኦስሎ ስምምነት በኖርዌይ ዋና-ከተማ ኦስሎ ተደረሰ፡፡ የአሜሪካው የወቅቱ ፕሬዚዳንት ቢል ክሊንተን፣ የእስራኤሉ ጠ/ሚኒስትር ይሳቅ ራቢንና የፍልስጤሙ ነፃነት ግንባር (PLO) ሊቀ መንበር ያሲር አረፋት ለዓለም የምስራች አበሰሩ። ይህ አብዮታዊ የተባለው ስምምነት ከመነጋገር ባለፈም የጋራ ስምምነትና መተማመን መፍጠርን አላማ ያደረገ ነበር። ፍልስጤማውያን የተወሰደባቸው መሬት ይመለስላቸዋል፣ እንደ መንግሥት እውቅና ያገኛሉ፡፡ በተመሳሳይ የእስራኤልን ደህንነት ለማረጋገጥ አብረው ሽብርን ለማስቆም በመተጋገዝ ይሠራሉ፡፡
ለሁለቱ የእስራኤልና የፍልስጤም መሪዎች የሠላም ኖቤል በጋራ እንዲያገኙ ባደረገው በዚህ ስምምነት መሰረት፤ ፍልስጤማውያን መሪዎች "እስራኤል ከዓለም ካርታ ትጥፋ" የሚለውን አቋም ትተው የሁለት ሀገር መንግሥት መፍትሄን (Two state Solution) ተቀበሉ፡፡ እስራኤልም አፍንጫዋ ስር “የሽብር መንግሥት” ሊፈጠር የሚችልበትን ስምምነት ስለ ሠላም ስትል ተቀበለች፡፡ እስራኤላውያን ፈጥነው በሚዲያዎቻቸውና በትምህርት ቤቶች ስለ ሰላም አብዝተው መናገር ጀመሩ፡፡ ወሬው ሁሉ የ“ኦስሎ ስምምነት” ቢሆንም፣ በሁለቱም ወገን ያሉ ተቃዋሚዎች ስምምነቱን አምርረው ተቃወሙት፡፡
ታዲያ በመደምደሚያው ከስምምነቱ በኋላ ባሉ አምስት አመታት ከታለመው ሰላም በላይ እልቂትና ጥፋት በሁለቱም ወገኖች ላይ ደረሰ፡፡ ሊቀ መንበር ያሲር አረፋት “አሸባሪ” የተባለው ሃማስን ከማውገዝ ይልቅ በተደጋጋሚ በሚዲያዎች ሲያወድሱት ታዩ፤ የሽብር ጥቃቶችም ተጠናክረው ቀጠሉ፡፡ ለአቅመ አዳም ያልደረሱ ፍልስጤማውያን ለሀገራችን መስዋዕት እንሆናለን እያሉ ሲፎክሩም በቴሌቪዥን ታዩ። በዛው መጠን የእስራኤል ማዋከብና ጥቃትም ቀጠለ፡፡ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ይሳቅ ራቢን፣ በኦስሎ ስምምነት ቅር በተሰኘ ወጣት እስራኤላዊ ወታደር በአደባባይ በጥይት ተገደሉ፡፡ ታላቅ ተስፋ የተጣለበት የሠላም ስምምነት ውሃ በላው፡፡
አብዝተን ስሙን ስለጠራነው የሚመጣ ሠላም እንደሌለ ጥሩ ማሳያ!
በሀገራችንም ስለ ሰላም ብዙ ቢባልም፣ ሁሉም ሠላም ወዳድ ነኝ ቢልም ከግጭትና ከጦርነት መውጣት አልቻልንም፡፡ ህፃናትን ስለ ጀግንነት ሲጠየቁ ምናልባትም ከአስሩ ታዳጊዎች ስምንቱ ከመግደል ጋር የተገናኘ ታሪክ ነው የሚናገሩት፡፡ በአብዛኛው ብሔረሰብ ቋንቋና ባህል ውስጥ ግድያን፣ ጭካኔን የሚያበረታቱ ስነ ቃሎች ሙዚቃና ትውፊቶች አሉ፡፡ ስጋዬን አሞራና ጅብ ይብላው አይነት የዘፈን ግጥሞች፤ ህፃናትንና አዛውንትን ጭምር ለጦርነት ለመቀስቀስ ይውላሉ፡፡
የሩዋንዳውን የዘር ፍጅት በሚዲያ እንዳስተባበሩትና እንደመሩት እንደ ፈርዲናንድ ናሂማና አይነት የወቅቱ የመገናኛ ብዙኃን ጋዜጠኞች፤ ዛሬ ላይ በኛው ሃገርም በመንግሥትና በግል ሚዲያዎች፣ በዩቲዩብና በሌሎች ማህበራዊ ሚዲያዎች ጥላቻን ይዘራሉ፣ ይኮተኩታሉ፣ ያርማሉ፣ አሰቃቂው አጨዳ ላይ ሲደርሱ እጃችን ንፁህ ነው ብለው ይሰወራሉ፡፡
ቀድመን የጠቀስናቸው የአሜሪካ ጥቁሮች በባርነት ተግዘው የዛሬ ነፃነታቸው  ድረስ እስኪደርሱ ብዙ የመከራ ጊዜያትን አሳልፈዋል፡፡ ብዙዎች ከሚደርስባቸው ግፍና በደል ብዛት ህይወታቸውን ያጠፉ ነበር፡፤ የአሜሪካ መስራች አባቶች የሚባሉት ጭምር በባርነት ግፍ ላይ ተሳትፎ አድርገዋል፡፡
ዛሬ ላይ በደረሱበት ዘመን ግን የአሁኑን ትውልድ አልፎ ለነገ የሚበቃ የመዓዘን ድንጋይ አስቀምጠዋል፡፡ ለዛ ትልቁን ሚና የተጫወተው በወቅቶች ውስጥ እየበሰለ የመጣው አዲሱ ትውልድ፤ የአባቶቹን ድርጊት መፀየፍ በመያዙ፣ ባርነትና የዘር መድሎ አያስፈልግም ብሎ በጋራ በመነሳቱ ነበር። ከዛሬ አልፎ የሚመጣውን ቀጣይ ትውልድ ተመልክቶ በቅን ልቦናና በመተማመን፣ እኔ ብቻ ያልኩት ካልሆነ የሚልን ያረጀ ብሂል አስቀምጦ መወያየት በመቻሉ ብርሃን አይቷል።
እኛ ሀገር የማይካደው ነገር የበደል ታሪኮች፤ ባርነት በሁሉም የሃገሪቱ ክፍል ነበሩ። ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የፍቅር እስከ መቃብሩ ልብ-ወለድ ገፀ-ባህሪ ፊታውራሪ መሸሻ ናቸው፤ ሰውየው የገዛ ወገናቸውን ገበሬውን እንዴት ይንቁ እንደነበርና ከሰውም  እንደማይቆጥሩት መመልከት ትልቅ ምሳሌ ነው። ሰውየው ገበሬ የሚበላው ቢያጣ የሚከፍለው አያጣም የሚሉ ነበሩ። ሌላ ቦታ ላይ ደግሞ ልበ-ሩህሩህና ሃይማኖተኛም ናቸው። ኢትዮጵያ ውስጥ በሁሉም አቅጣጫ የነበሩ የመደብ አለቆች በገዛ ወገናቸው ላይ ጭምር ግፍ ፈፅመዋል። ታዲያ ዛሬ ላይ ቢያንስ ነገ የሚወለዱ ልጆች የሚኖሩባትን ሀገር ለመመስረት የአኖሌም የምንሊክም ሃውልት ይፍረስ የሚሉ አካላት፣ መሳሪያ ይዘው ጫካ የገቡ ተዋጊዎች እንዲሁም የሀገሪቱ ፖለቲካ አይመለከታችሁ ተብለው ገሸሽ የተደረጉ የማህበረሰብ ክፍሎች በቅን ልቦና የነገይቱን ሀገር በማሰብ ወደ ውይይትና ድርድር በቅን ልቦና መግባት ጊዜ የማይሰጠው የቅድሚያ ተግባር መሆን አለበት፡፡
ያ የማይሆን ከሆነ እንደ ደርጉ ቀይ ሽብርና እንደ ኢህአፓ ነጭ ሽብር ሁለቱም ለድርጊታቸው ምክንያት የሚያስቀምጡበትን፣ ነገር ግን ሀገሪቱ ያለፈችበትን የዘር ፍጆት ጥቁር ጠባሳ በአዲስ ስልትና ቴክኖሎጂ፣ በሰፋ መጠን ዳግም እየከወንን መሆኑን ግንዛቤ መውሰድ ያስፈልጋል፡፡
ሌላው ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከፍተኛ ስጋት የሆነው የሃይማኖት ተቋማትን መሰረት ያደረጉ ግጭቶች ናቸው። በሁሉም ቤተ-እምነት ውስጥ ያሉ የሃይማኖት አባቶች ከጥላቻ ይልቅ ፍቅርን፣ ከጠብ ይልቅ እርቅን፣ ከመገዳደል ይልቅ አብሮ መኖርን ሊያስተምሩና ሀገሪቱን ሊታደጉ የሚገባበት ወሳኝ የታረክ ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡
ባለፉት ጥቂት አመታት መንግሥት በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የሃይማኖታዊ ትዕይንቶች ዋና አስተባባሪና ድጋፍ ሰጪና ሆኗል። በእነዚህ ትዕይንቶች ላይ ዲያስፖራውን የእምነቱ ተከታይ የማህበረሰብ ክፍልም ጋባዥ ሆኖም ተመልክተናል፡፡ ይሄ በህገ-መንግስቱ የተጠቀሰውን የሃይማኖትና የመንግሥት ገለልተኝነት ከመፃረሩ ባሻገር አሁን ላይ ለሚከሰቱ ሃይማኖትን መሰረት ያደረጉ ግጭትና ረብሻ መነሻ ምክኒያት እየሆነ እንደመጣ መመርመር ያሻል፡፡ የሃይማኖት ተቋማትም በራሳቸው ሊያስተባብሩት የሚችሉትን ትዕይንቶች መንግሥት ሃላፊነት ወስዶ እንዲሰራላቸው መፍቀድ የለባቸውም።
በመጨረሻም ባለፋት ጥቂት አመታት ኢትዮጵያ ውስጥ በህጋዊና በህገ-ወጥ መንገድ ብዙ የጦር መሳሪያ ገብቷል፣ ታዲያ ይሄ የጦር መሳሪያ አሁን ላይ ሰላማችንን ከማረጋገጥ ይልቅ ከፍተኛ የደህንነትና የሰላም ስጋት ሆኗል። ሁሉም አካል ከገባበት የጥላቻና የግፋ-በለው ዘመቻ ቆም ብሎ ዙሪያ ገባውን መመልከት አለበት። በቴለቪዥን መስኮት ደጋግሞ የሚታየውን የጦርነት ጉሰማ መቀጠል ለባሰ እልቂት ትውልድን ማነሳሳት ነው።
ሁሉም የመገናኛ ብዙሃንና ተፅእኖ ፈጣሪ የማህበረሰብ መሪዎች እንዲሁም የማህበራዊ ሚዲያ መድረኮች ስለ ሰላም ስለ መቻቻልና አብሮ ስለመኖር እሴት ማስተማር የነገይቱን ኢትዮጵያ ለማየት ብቻ መንገድ ነው። ፈጣሪ ሃገራችንን ይጠብቅ፣ ሰላማችን እንደ ምድር አሸዋ ይብዛ፡፡



Read 2617 times