Saturday, 25 June 2022 20:30

ሀቀኛ መካሪዎች የት ናችሁ!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)

  #--ዘንድሮ መቼም የመካሪውም፣ የምክሩም አይነት ለወጥወጥ ብሏል፡፡ እናላችሁ... ከጥቂት ወራት በፊት ነው አሉ፡፡ የምታከብራቸው ሁለት የሥጋ ዘመዶቿ የሆነ የሳምንቱ መጨረሻ ቀን ለጥብቅ ጉዳይ እንደሚፈልጓትና አንደኛቸው ቤት እንደሚጠብቋት ነግረዋት የተባለው ቦታ ትሄዳለች፡፡ አጠራራቸው የተለመደ ስላልነበር...ማለት ለብቻዋ ተፈልጋ ስለማታውቅ መጨናነቋ አልቀረም፡፡  ካገኘቻቸው በኋላም ጨዋታው ይጀመራል፡፡--;
             
             እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እንግዲህ ክረምት ገባ፣ (ሐምሌም መጣ! እሱም የራሱን ‘ክረምት’ ያመጣ ይሆን? በእንዲህ አይነቱ ጊዜ ነው “የሰይጣን ጆሮ አይስማው...” ማለት!) እኔ የምለው...ዝናቡ አንዳንድ ጊዜ ትንሽ ጠንከር ብሎ እየጀመረ ወዲያው የሚለሳለሰው የሆነ ምልክት ነገር መሆኑ ነው እንዴ? አሀ... ግራ ቢገባን እኮ ነው! ...ኮሚክ ዘመን ውስጥ አይደል ያለነው... ምኑንም፣ ምናምኑም እየጠቀሱ የ”አምስት ጉዳይ ለእኩለ ሌሊት፣” አይነት ትንቢቶችን የሚነግሩን በዙብና! ስሙኝማ...ዩቲዩብ ላይ ወዲህ ወዲያ ስትሉ አንዳንዴ አደናቅፏችሁ የምታርፉበት አለ አይደል! በዛ ሰሞን አንድ እንዲህ አይነት ዩቲዩብ አካውንት ላይ ዘጭ! አንድ አዲስ ይሁኑ የከረሙ ትንቢት ተናጋሪ እንጃ እንጂ የዩክሬይኑን ዜሌንስኪንና የሩስያውን ፑቲንን የዓለም መጥፊያ ምልክቶች አድርገው ሲያቀርቧቸው ነበር! እና... “ዓለም እያበቃላት ነው...” አሉ፡፡
ታዲያላችሁ...ይህ “ዓለም እያበቃላት ነው፣” የሚለው ትንቢት እኛ ዘንድ ብቻ ሳይሆን እንደ አሜሪካ ባሉት ሀገራትም በተለይ በተለያዩ አማኞች አካባቢ ደጋግሞ እየተነሳ ነው ይባላል፡፡ እኛ ሀገር ኮሚኩ ነገር...በምን መልክ እንደምትጠፋ ሁሉም የየራሱ ‘ካልኩሌሽን’ አለው፡፡ እናማ... ሁሉም የተነበየው የአጠፋፍ አይነት እንዲፈጸም ዓለም ስንት ጊዜ መጥፋት አለባት!
“የሰሞኑ ዝናብ ለስለስና ጠንከር እያለ መለዋወጡ መጪው ጊዜ ፈተና የበዛበትና አባጣ ጎርባጣ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡” (አሁን እንዲህ ማለት እኛስ ያቅተናል! ፍሬንድስ... እንሞክረው እንዴ! ...ሰዋችን እኮ ከዩቲዩብ ምናምን መቶ ሺዎች፣ ምናምን ሚሊዮን እየዛቀ ነው አሉ፡፡ አሀ..ታዲያ እኛ ዘለዓለም በሺህ ብር ዘይት ስንጨረጨር መኖር አለብን እንዴ!)
ወደ ሌላ ጨዋታ ስንመጣ ይህን ጉድ ስሙኝማ...አንዲት እህታችን የደረሰባት የተባለ ነው፡፡ ልጅቱ... አለ አይደል... የተረጋጋች የምትባል፣ በአሁኑ ጊዜ የአብዛኞቻችን ችግር የሆነው (‘የሁላችንም’ ያልተባለው ነገ ለማኪያቶ የሚከፍል ሊጠፋ ይችላል ተብሎ አይደለም!)  የሞራል መሸርሸር ገና ያልነካት ነች፡፡ “አንዴት አይነት የተባረከች ጨዋ መሰላቻቸሁ!” የምትባል አይነት፡፡ እናላችሁ...በሙያዋ እየሠራች ከቤተሰብ ጋር ትኖራለች፡፡ ታዲያላችሁ.... አብራቸው የተማረቻቸው አንዳንድ የቅርብ ጓደኞቿ ደግሞ መኪና የሚለዋውጡ ሆነዋል፡፡ ምን መሰላችሁ... ልጅቱ በዚህ ይቺን ታክል የተለየ ስሜት አይሰማትም፡፡ ማለትም “ከጓደኞቼ በታች ሆኜ...” አይነት ስሜቶች ሽውም አይሏት፡፡ በቀኖቹ ሰዓታት እሷ ልትሄድባቸው የምትችላቸው ስፍራዎች አብራቸው ትሄዳለች፣ ትጫወታለች፣ ትዝናናለች ...ቀይ መስመሯን ቦግ አድርጋ አስምራ ማለት ነው፡፡
ዘንድሮ መቼም የመካሪውም፣ የምክሩም አይነት ለወጥወጥ ብሏል። እናላችሁ... ከጥቂት ወራት በፊት ነው አሉ። የምታከብራቸው ሁለት የሥጋ ዘመዶቿ የሆነ የሳምንቱ መጨረሻ ቀን ለጥብቅ ጉዳይ እንደሚፈልጓትና አንደኛቸው ቤት እንደሚጠብቋት ነግረዋት የተባለው ቦታ ትሄዳለች፡፡ አጠራራቸው የተለመደ ስላልነበር...ማለት ለብቻዋ ተፈልጋ ስለማታውቅ መጨናነቋ አልቀረም።  ካገኘቻቸው በኋላም ጨዋታው ይጀመራል፡፡ እሷ አሁን ያለችበት ደረጃ ላይ ሳይሆን ከፍተኛ ደረጃ ላይ መገኘት እንዳለባት እየተቀባባሉ ይነግሯታል፡፡ በጎ ምኞት አይነት ስለነበር ምንም ችግር አልነበረውም፡፡ አልፎ፣ አልፎ ከሌሎችም የምትሰማው አስተያየት ነው፡፡ ከዛ የጓደኞቿን ባለመኪኖች መሆን ያነሱና ያስደነገጣትን ነገር ይነግሯታል፡ “ለምንድነው እንደእነሱ ብልጥ የማትሆኚው?” ትባላለች፡፡
የምር ግን ዘንድሮ በራሱ የሚተማመን ሰው ማግኘት በጣም ትልቅ ዕድል ነው፡፡ አንድ ነገር ነው ያለቻችው፣ “ለምክራችሁ አመሰግናለሁ፡፡” ሄደች፡፡ እና ለተወሰኑ ቀናት ትንሽ ተሰምቷት ነበር አሉ፡፡
ምን መሰላችሁ...የጓደኞቿ ‘ብልጥነት’ የተባለውን እነዚህ ዘመዶቿን ጨምሮ “አገር የሚያውቀው” የሚባል አይነት ነው፡፡ እነሱም አንዴ ፈልገው የገቡበት ዓለም ስለሆነ ምን ይባሉ ምን ጉዳያቸው አልነበረም አሉ፡፡ ከሁሉም የሚገርመውን ስሙኝማ...መካሪዎቿ እነኚህ ከፍሪዝ ጠጉራቸው ውስጥ የከሰል ባቡር የሚመስል ጢስ የሚወጣባቸው የሚመስሉት አይነት አልነበሩም...በሀምሳዎቹ ውስጥ የሚገኙ ትዳርና ልጆች ያሏቸው አባወራዎች እንጂ! የምር ያሳዝናል ብቻ ሳይሆን ያስደነግጣልም። እንዴት ነው የገዛ ዘመዳቸውን፣ የገዛ ሥጋቸውን “ጓደኞች መረጣ ላይ ተጠንቀቂ...” አይነት ምክር እንደመስጠት ለገንዘብ ብለው በዛ በተበላሸ ህይወት ውስጥ እንድትገባ የሚመክሯት? በዚህ አይነት ነገስ የራሳቸውን ልጆች ምን ሊሏቸው ነው?
መቼም ከዕለት ዕለት የምንሰማቸው፣ አልፎ፣ አልፎም የምናያቸው ነገሮች “ለሰሚ ግራ...” የሚባሉ አይነቶች ሆነውብናል፡፡
ስሙኝማ...እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ...አብዛኞቻችን የምንደጋግማት “ወዴት እየሄድን ነው?” የምትል ነገር አለች፡፡ እንግዲህ ግራ ገብቶን ‘ጦጣ’ ስለሆንን ወዴት እየሄድን እንደሆነ አንድዬ ይወቀው ማለቱ ይሻላል፡፡ ግን ብዙዎቻችን ወዴት እየሄድን እንዳልሆነ በመላ ምት ደረጃ የምንናገርበት ጊዜ እየቀረበ ሳይሆን አይቀርም፡፡ እመኑኝ መላ ምቶቹ ደግሞ ለጆሮም፣ ለምንም የሚመቹ አይደሉም፡፡
ታዲያላችሁ...እናንተ ስለሚቀጥለው ወር ጤፍና ዘይት እንቅልፍ እያጣችሁ አፉን ሞልቶ “አንተ መቼ ነው መኪና የምትገዛው?” የሚል ሰው አያበሽቃችሁም! (እነ እንትና “እንግዲህ ባዮግራፊውን መተረክ ጀመረ!” እንዳትሉኝማ!)
“እናላችሁ... ዘንድሮ ምክርና መካሪ አስቸጋሪ ነው፡፡”
“ስማ አንተ ዘለዓለም ዓለምህን በቃ እንዲህ ሆነህ ልትኖር ነው?”
“እንዴት ሆኜ?”
“ቤት የለህ፣ መኪና የለህ፡፡ እንደው እሱ ይቅርና አንድ ቀን የውጪ አገር ጫማ አድርገህ ታውቃለህ!” ጥያቄ እኮ አይደለም።
“እኔ የአገር ውስጥ ጫማ ተመችቶኛል።” (በእርግጥ ይሄ አባባል ሙሉ ለሙሉ እውነት ነው ለማለት ትንሽ ይከብዳል፡፡ ቂ...ቂ...ቂ...)
ስሙኝማ...እንዲህ መሰል ነገሮች ስትናገሩ የምትሰሙት ሳቅ ለጊነስ ምዝገባ እጩ ሊሆን ይችላል፡፡
መቼም አንዳንዴ...አለ አይደል... አሁንም ከስንት ጊዜ አንዴ ቢሆንም እጁ ፈታ የሚል ስለማይጠፋ ሁለት ወዳጆቻችሁ “ምሳ እንግዛልህ...” ይሏችሁና አብራችሁ ትሄዳላችሁ፡፡
ከዛ ሜኑ የሚሉት ሲመጣ ሁለቱ ልክ የሆነ ሳይንቲስትን ግኝት የሚያፈርስ አዲስ መረጃ ያገኙ ይመስል ኮስተር ብለው መስመር በመስመር ያዩታል፡፡ እናንተ ግን ያማራችሁን ስለምታውቁ ሜኗችሁ ምላሳችሁ ላይ ነች፡፡ እነሱ አንዱ “ስቴክ...” ይላል፣ ሌላኛው “ላዛኛ...” ይላል፡፡ (ቆዩኝማ... ይቺ ይቺንማ እኛም ሜኑ ሳናነብ ማለት እንችላለን! ይሞታል እንዴ!)
“አንተ ሜኑ አታይም እንዴ?”
“አያስፈልገኝም ብዬ ነው፡፡”
“እዘዛ፡፡”
“እህት ለእኔ ቦዘና ሹሮ ታመጪልኝ፡፡”
ይሄኔ ሁለቱ እየተንፈራፈሩ ሲስቁ የተንጠለጠሉት የሬስቱራንቱ አምፖሎች ሊረግፉ ምንም አይቀራቸው፡፡ (እንደውም በሆዳችሁ “ሰው እስከዚህ ድረስ እየተንዘፈዘፈ ይስቃል እንዴ! ነው ወይስ በጠዋቱ አረንጓዴዋን አድቅቀው ነው የመጡት!” ሳትሉ አትቀሩም፡፡)
“ስንት ነገር እያለ ሹሮ!”
“ያሰኘኝ እሱ ነው፡፡”
“ኸረ በፈጠረህ...እኛንም ሰው ፊት አታሳፍረን! ደግሞ እንዲህ አይነት ሬስቱራንት ሹሮ ምናምን ብሎ ነገር የለም፡፡” ይሄኔ አሳላፊዋ ጣልቃ ትገባለች፡፡
“ኸረ እኛ ቤት የሌለ ምግብ የለም!” ይመችሽማ!
ከላይ የቀረበችው ነገር ትንሽ ተነካክታ ቀረበች እንጂ  ከዚህ ጋር የሚቀራረብ ነገር የደረሰበት ሰው ሰምተናል፡፡  ምን መሰላችሁ... እኛ ‘ፓስታ ሹታ’ ተመግበን ሌላው “ቋንጣ ፍርፍር” ስላለ እኛ ዙፋን ላይ የተቀመጥን የሚመስለን ጉዶች እኮ መአት የሆነበት ዘመን ነው፡፡ እንደውም...አለ አይደል... “ስማ ሬስቱራንት ስትገባ ይሄ ቦዘና ሹሮ፣ ቋንጣ ፍርፍር ምናምን የምትለውን ሎካል ነገር ተው፣” የሚላችሁ ‘መካሪ’ ሊኖር ይችላል፡፡
“እና ምን ልዘዝ?”
“በቃ የፈረንጅ ዲሾችን እዘዝ፡፡”
“ለምን ብዬ?”
“ሰዉ ይታዘብህላ!”
ስሙኝማ...እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ፣ ከሁሉ የሚያሳዝነው ምን መሰላችሁ...ሀገር ከላይ እስከ ታች እውነተኛ መካሪ በምትፈልግበት በዋነኛው ሰዓት መካሪ ሲጠፋ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 766 times