Sunday, 26 June 2022 10:11

እንደ እያሪኮ

Written by  ሌሊሳ ግርማ
Rate this item
(0 votes)

  "--አድባሪቷ መጥታ ከእኔ ጋር ተቀምጣለች፡፡ እንደማላውቃት ያላየሁዋት ብመስልም አይቻታለሁ፡፡ ውበቷን አሰማምራ፣መቶ አምፖሏን አብርታ ነው የመጣችው፡፡ መፅሐፍ፣ ወረቀት እና ውድ እስኪርብቶ ገዝታልኝ መጥታለች፡፡ እየተቁለጨለጨች አይን አይኔን ታየኛለች፡፡ የለበሰችው ጉርድ ቀሚስ ጭኗን ያሳያል፡፡ በጣም ለመፃፍ የሚያጓጓ ባት ነው፡፡--"
 
              ድንገተኛ ድምጹን በሙሉ ማን  አጠፋው? ዛሬ ምን ተገኘና ከተማው አንድ ላይ እረጭ አለ? ትላንት ልፅፍ ነው ብዬ ስቀመጥ… ዓለሙ አንድ ላይ ተነስቶ ሲጮህብኝ አልነበር? እነዛ ዘመናቸው ሳይደርስ በእኔ ትውልድ ላይ ተለጥፈው የተወለዱ ህፃናት እሪ እያሉ ቤቴን ሲዞሩት…ጎረቤቴ ያለው ሰው በፆም ሆዱ፣ በፍስክ ምኞቱ እየጮኸ ሲያደነቁረኝ አልነበረም?... ዛሬ ታዲያ ሁለተኛ አልጽፍም ብዬ፣ ብዕሬን በድራፍት ዉጬ ከሰፈሬ በጣም ርቄ በተቀመጥኩበት…ጭጭታው ከየት መጣ?
ድምፁ እንደተቀነሰ ቴሌቪዥን ከተማው ያለ ድምፅ ከፊቴ ይንቀሳቀሳል፡፡ ችኩልነቱን በስክነት የቀየረው በደንብ እንዳስተዋለውና እንድፅፈው ነው፡፡ የፈለገ አደብ ብትገዛ አልፅፍህም፡፡ ትላንት ሳባብልህ አሻፈረኝ ብለኸኛል፡፡ ሳሰላስል አናቴ ላይ ባዶ ሙቀጫ አስቀምጠህ ወቅጠህብኛል። ስለዚህ ዛሬ ቢያምርብህም፣ ሰክነህ መፃፍ ብትሻም እኔ አልተባበርህም፡፡
አድባሪቷ ዛሬ መጥታለች፡፡ እና ምን ላድርግልሽ?! ትላንት ስጠብቅሽ፣ ብዕሬን በሰም ወልውዬ፣ ልቦናዬን ለሩቅ ምናኔ መትሬ፣ ጥሞናን ስሻ ጠፍተሽ… ዛሬ ለጩኸት የክት ረብሸኛነቴን ለብሼ ብወጣ ጭጭ ብለሽ መጣሽብኝ፡፡ ዛሬ ለጠብ ዝግጁ ነኝ፡፡ ለመናደድ ነው ቀጠሮ የያዝኩት፡፡ የትላንቱ ቀን እስቲ ወንድ ዛሬ ላይ ይምጣ!...
እይው!... እዛ ማዶ አንዱ መዶሻ ይቃጣና የተቃጣበትን ሚስማር ይዶሸዋል፡፡ ድምጽ እንዲያወጣ በኃይል ይቃጣና ሚስማሩ አናት ጋር ሲቀርብ ቀስ ብሎ ያሳርፋል፡፡ ደግሞ ቀና ይልና እኔን ያየኛል፡፡ በአይኑ ያባብለኛል። በቃ አንረብሽህም አንተ ብቻ ፃፍ…ሊለኝ ይመስላል። የፈለገ ቢመጣ ዛሬ አልፅፍም። አለቀ….!! ...ይልቅስ አንተኛው ድራፍት ድገመኝ፡፡ አዎ አስተናጋጁ እንዲሰማ ጠረጴዛውን በደንብ አድርጌ  እነርተዋለሁ። የብርጭቆው እጀታ እስኪረግፍ፡፡
ለምንድነው ጠረጴዛው እንደ እስፖንጅ ስደልቀው ትሙክ የሚለው? አራት ድራፍት ነው የጠጣኸው ሲለኝ (በጆሮዬ ተጠግቶ በሹክሹክታ) …እኔ እየጮሁኩ “ሁለት ብቻ ነው” ብዬ ክርክር መፍጠር ፈልጌአለሁ። ጣጣ የሚያመጣ ክርክር፡፡ ብርጭቆ አወራውሮ የሚያፈናክት ዓይነት፡፡
ለምንድነው የጠጣሁትን ቀንሼ ስከራከረው “ይሁንልህ” ብሎ ሸብረክ ከማለት ባላነሰ ተስማምቶ የሚሄደው?...ቀስ ብዬ ብርጭቆውን ገፍቼ መሬቱ ላይ ብጥለው ፀጥታው ይበጠበጣል። ፀጥታውን ለማጥፋት ስል የብርጭቆውን ዋጋ ብከፍል ይቀለኛል፡፡ እልህ ይዞኛል፤ ትላንት እንደ በጠበጡኝ…ዛሬ በተራቸው ጩኸት መቅመስ አለባቸው፡፡
አድባሪቷ መጥታ ከእኔ ጋር ተቀምጣለች። እንደማላውቃት ያላየሁዋት ብመስልም አይቻታለሁ፡፡ ውበቷን አሰማምራ፣ መቶ አምፖሏን አብርታ ነው የመጣችው፡፡ መፅሐፍ፣ ወረቀት እና ውድ እስኪርብቶ ገዝታልኝ መጥታለች፡፡ እየተቁለጨለጨች አይን አይኔን ታየኛለች፡፡ የለበሰችው ጉርድ ቀሚስ ጭኗን ያሳያል፡፡ በጣም ለመፃፍ የሚያጓጓ ባት ነው፡፡ ..እየፃፍኩ ብገልበው ውስጥ ሱሪዋን አገኘዋለሁ። እየጻፍኩ ባወልቀው…በጣም  የሚያረካ ድርሰት ነው ይዛ የመጣችው! ግን የፈለጋትን…መስላ ብትመጣ ዛሬ አልፅፋትም፡፡ ሌላ ፀሐፊ ጋ ትሂድ፡፡ ግን ጠንቅቄ አውቃለሁ፤ የኔይቱ አድባር ሌላ ማንም ጋ መሄድ እንደማትችል። ወይንስ ትችላለች?! ትላንት የት ነበር የሔደችው? የትኛውን ደራሲ ተኝታ ነው የመጣችው?
ድንገት ቅናት በልቤ ውስጥ ተደመረ። የመስቀል ደመራ፡፡ ግን ደመራው ፀጥ ያለ ነው። እሳት ይንቀለቀላል እንጂ ድምጽ አያወጣም! ...ለዚች ቀልቃላ አድባር… በቅናት ነዶ መንቀልቀል አያስፈልግም፡፡ “ለምን የሄድሽበት አልቀረሽም? የሄድሽው ደራሲ እንደምትፈልጊው አላደረገሽም? ነካክቶ ተወሽ?” አልኳት፡፡
ግን ምላሴን ዘይት ማን እንደቀባኝ አላውቅም፤ ቃላቶቼ እያሟለጩ ትርጉም ሳይሰጡ ተዝረክርከው ቀሩ፡፡
“እ” አለችኝ እግሯን ፈትታ እያጣመረች። ፈትታ ስታስረው …በብልጭታ የውስጥ ሱሪዋ ቀለም ይታየኛል፡፡ በጥቁር ከሰል ላይ በደንብ የተቀጣጠለ ቀይ ፍም ያየሁ መሰለኝ፡፡ በደንብ ባርገበግበው የተያያዘ ድርሰት ሊወጣው ይችላል፡፡
ሰክሬአለሁ መሰለኝ፤ የአንደበቴ መቋጠሪያው ላልቷል፡፡ የፊኛዬ መቋጠሪያ ግን በደንብ ይሠራል፡፡ ፊኛዬ ተወጥሯል፡፡ ግን ዛሬ አልጽፍም ብያለሁ፡፡ መቋጠሪያዬ ይሰራል፡፡ ዛሬም ነገም አልጽፍም፡፡ እሷም ሌላ ዘንድ ትሂድ…
እኔም ራሴን መግዛት በቅጡ ልልመድበት። እንደው በጥበብ ፍቅር ስም፤ በሷ ገላ ላይ ሰርክ የማልሰለች ኮርማ ሆኜ አርፌአለሁ። ከተማው እኔ ለእሷ ላለኝ ፍቅር ብሎ ፀጥ ቢልም እኔ ግን እሷን አልፅፍም። ወረቀት ላይ እሷን በመተኛት ዕድሜዬ አባከንኩ፡፡ እሷም ወይ… ፍሬ አላፈራች… እንዲሁ ወረቀት እና ቀለም ማልፋት ብቻ፡፡
መጋባት እና ፍሬ ማፍራት ወይንም መለያየት፡፡ ይሄው ነው መፍትሔው፡፡ አንድ ቀኝ ጩኸት ሌላ ቀን ፀጥታ እያፈራረቁ ግራ ማጋባት ከእንግዲህ አይሰራም፡፡ በአፌ ከምናገረው ይበልጥ የማስበውን ማድመጥ ትችላለች አድባርዬ…. አድባሪቱ። እግሯን መከፋፈት ትታ ቀሚሷን ወደ ታች እየሰበሰበች ረዥም ቀሚስ አደረገችው፡፡ ኩርምት ብላ ማሰብ ያዘች፡፡
“እኔን ካገባህ እድሜ ልክ ፀጥታ እና ጥሞና ታገኛለህ፡፡ ግን ዕድሜ ልክህን ይህን ነው የምትሆነው…ይሄንን አውቀህ ከተቀበልክ መጋባት እንችላለን” አለችኝ፡፡
በፊት በጣም እርግጠኛ ነበርኩ - እቺን ሴት ማግባት ስለመፈለጌ፡፡ አሁን ግን ድንገት ጥርጣሬ ገባኝ፡፡ ፍሬ እፈልጋለሁ፤ ግን ከማታስተማምን አድባር ጋር ተጋብቼ፣ በአንድ መወሰን መቻሌን እርግጠኛ አይደለሁም፡፡
“ላስብበት” አልኳት፡፡
ቀጠሮ ሰጥታኝ መፅሐፍቷን እና መፃፊያ ቁሳቁሷን ይዛ ወጣች፡፡ ስትወጣ ቅር አለኝ። ቀደም ብዬ በእልህ የዋጥኩት እስክሪብቶም ደረቴን እየፋቀ ቃር ለቀቀብኝ፡፡
እሷ ስትወጣ ድንገት ከተማው ዛሬ መሆኑ ቀርቶ ትላንት ሆነ፡፡ ፀጥታው በጫጫታ ተተካ። እንደ እያሪኮ ግንብ ፀጥታው በጩኸት ፈረሰ። የብርጭቆዎቹ ኳኳታ ጆሮዬን ሰብረው ገቡ፡፡ ብርጭቆዎች መዶሻ ሆኑ፡፡ ወሬዎች እንደሚስማር የሰውን ብቸኝነት ከቡድን ወሬዎች ጋር ወስደው መስፋት ጀመሩ፡፡ ድምፆች ሲጎሉ የእኔ ድምጽ ደግሞ ውጪውን ፈርቶ አልወጣም አለ፡፡ ብርጭቆውን በቀስታ ማንሳት ጀመርኩ፡፡ የራሴ ልብ ምት መሸሸጊያ አሳጣኝ፡፡ ከሰፈሬ በጣም ብርቅም ጎረቤቶቼ የሚወቅጡት ሙቀጫ ጎልቶ የተቀመጥኩበት ቦታ ድረስ እየጮኸ ተከትሎኝ መጣ፡፡ ያ ጎማ ጎማ  የሚል እጣናቸው ሸተተኝ፡፡
አድባሪቱ ከመሄዷ በፊት ላስቆማት ወጣሁኝ፡፡ ጠረኗን ተከትዬ የዱካዋን ፊደሎች አሽትቼ፣ቆማ ገላዋን ለአላፊ አግዳሚ ወደ ምታስጎበኝበት የመንገድ መብራት ስደርስ ዋጋ እየተደራደረች ደረስኩባት፡፡ ሌላ ፀጥታን ፈላጊ አባብሎ ሊወስዳት ነው፡፡ ገና አጠገቧ ከመድረሴ… አካባቢውን በጸዳሏ ሞልታዋለች። የመንገዱን መብራት ጨረቃ አድርጋዋለች። አስፋልቱ አረንጓዴ መስክ መስሏል፡፡ የማስታወቂያ ሰሌዳ ቋሚዎቹ እንደ ሰንበሌጥ ይወዛወዛሉ፡፡
ልታስተምረኝ የፈለገችው ነገር ገባኝ። ያለ እሷ መኖር አልችልም፡፡ ከሁለታችን ኩርፊያ ጉዳቱ የሚያደላው በእኔ ላይ ነው፡፡ ሊቀድመኝ ከሚያባብልብኝ ሰው እጅ አስጥዬ አቀፍኳት። ብዙም አልተግደረደረችም። ተሳመችልኝ፡፡ ፀጥታ ተመልሶ በዓለም ላይ ሰፈነ፡፡ ወደ ቤቴ…እና ቤታችን ከንፋስ በቸኮለ  አከናነፍ ደረስን፡፡
አልጋውን ጠረጴዛ አድርጌ አዘጋጀሁት። የአንሶላውን ወረቀት ለወጥኩኝ፡፡ እንደማትጠገብ አድርጌ…ቶሎ እንዳታልቅ…. ሌሊቱን አክላ እንድትቆይ አድርጌ፣ ቀስ በቀስ እየገለፅኩ፣ እስክትሰለቸኝ ስጽፋት አደርኩኝ፡፡
(ከሌሊሳ ግርማ "ይመስላል ዘላለም" አዲስ መድበል የተወሰደ)


Read 1270 times