Monday, 27 June 2022 00:00

ፋኖ ተሰማራ - ለክፍለ ዘመኑ ምርጥ የፎቶ ሥራ

Written by  አበራ ሣህሌ
Rate this item
(1 Vote)

ባለፈው ሰሞን የስብሃት ገብረእግዚአብሔር የሥነፅሑፍ ጥበብ የሚታይበት በ1993 ዓ.ም የፃፈው “ገድለ አጎት ሆቺ ሚን” በዚህ ጋዜጣ ላይ ሰፍሮ ነበር። ያንን ታሪክ በላላ ሲባጎም ቢሆን አያይዘን በቅርቡ 50ኛ አመቱ የታሰበውን ጨምሮ ሁለት የጦርነት ምልክት የተባሉ ፎቶዎችንና ባለታሪኮቹን እንመለከታለን።
ቬትናም ሩቅ አገር ነው። ሆኖም እዛ የነበረውን ጦርነት በመቃወም የዚህ አገር ተማሪዎች ሰልፍ ወጥተዋል። ከራሳቸው የለውጥ እንቅስቃሴ ትግል ጋር በማገናኘት፥-
‘ፋኖ ተሰማራ ፋኖ ተሰማራ
እንደነ ሆ ቺ ሚን እንደ ቼ ጉቬራ’ ሲሉ ስንኝ ቋጥረዋል።
የቬትናም ጦርነት ’አንክል ሆ’ በሚባሉት ሆ ቺ ሚን ትመራ የነበረችው፥ እነ ሶቪየት ሕብረት አለሁ የሚሏት ሰሜን ቬትናም በአንድ ወገን፤ እንዲሁም በአሜሪካ ትደገፍ የነበረችው ደቡብ ቬትናም በሌላኛው ሆነው ለሃያ አመታት የተቆራቆሱበት ነው። በጦርነቱ ከሁለት ሚሊየን በላይ ቬትናማውያን እንደሞቱ ሲገመት፣ 58 ሺህ ያህል የአሜሪካ ወታደሮች ሕይወታቸውን አጥተዋል ወይም የደረሱበት አልታወቀም። ጦርነቱ ፍፃሜውን ያገኘው አሜሪካኖች ለቅቀው ሰሜኖቹ የደቡቡን ዋና ከተማ ሳይጎንን እ.ኤ.አ በ1975 ሲቆጣጠሩ ነው።

የናፓልሟ ልጅ
በቬትናም ሲካሄድ የነበረው ጦርነትን አስከፊነት በግልፅ ያሳዩት ሁለት ምስሎች በሃያኛው ክፍለዘመን የፎቶ ጋዜጠኝነት ታሪክ ልዩ ስፍራ ይሰጣቸዋል። ከቦምብ ጥቃት የሚያመልጡ ሕፃናት ፎቶ ፀረ-ጦርነት እንቅስቃሴ አነሳስቷል። ራቁቷን የምትሮጠው ፋን ቲ ኪም ፉክ ከዕለታት አንድ ቀን በአንዲት የደቡብ ቬትናም መንደር የደረሰ የናፓልም ቦምብ ጥቃትን ተከትሎ የተነሳ ፎቶ የሕይወቷ መገለጫ ሆኗል።
በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ሀገሮች እየተዘዋወረች ከጦርነት ጋር ተያይዘው በሚከሰቱ ሥነልቡናዊ ቀውሶች ላይ ንግግር የምታደርገው ኪም ፉክ፤ “አምሳ ዓመት ሆኖታል። እኔ ግን የናፓልሟ ልጅ አይደለሁም” በሚል ርዕስ በያዝነው ወር መግቢያ ላይ አምሳኛ አመቱን ስላስቆጠረው ፎቶ ኒውዮርክ ታይምስ ላይ ሀተታ አቅርባለች። “የደቡብ ቬትናም አየር ኃይል በመንደራችን ላይ ጥቃት ሲፈፅም እኔ ገና የዘጠኝ አመት ልጅ ነኝ። ናፓልሙ ያቃጥል እንደነበር እንኳ ያወቅኩት ፊልሙ ላይ ‘ተቃጠልኩ ተቃጠልኩ’ ብዬ እጮህ እንደነበር በማየቴ ነው” ትላለች።
“ኒክ ፎቶውን ካነሳ በዃላ የሕክምና እርዳታ አድርጎልኛል። ሕይወቴን ታድጓል። ለዛ ምስጋና ይገባዋል። በሌላም በኩል ከወንድሜና ከአጎቶቼ ልጆች በተለየ ራቁቴን በመሆኔ ለዘመናት ሀፍረት ተሰምቶኛል። ግን ፎቶውን ለምን አተመው? ወላጆቼ ለምን አልታደጉኝም ብዬ ሁሌም እጠይቅ ነበር። በዛ ኒክን የጠላሁባቸው ወቅቶች ነበሩ። ናፓልሙ ሰውነቴ ላይ ጥሎት ያለፈው ጠባሳ የመንፈስ ስብራት አስከትሎብኛል። የሚወደኝ ሰው አላገኝም ብዬ ብዙ ተጨንቄ ነበር።”
የሚወዳትን ማግኘት ብቻ ሳይሆን የሁለት ልጆች እናት ሆናለች። ‘ኑሮና ብልሀቱ’ ከቬትናም መንደር አስወጥቶ ኩባ አስተምሮ ከዛ ደግሞ ቋሚ መኖሪያዋ ወዳደረገችው ካናዳ ወስዷታል።
ፎቶውን ያነሳው ኒክ ኡት የተባለ የኤፒ ጋዜጠኛ ነው። በዛው አመት የፑሊትሰር ሽልማት አሸናፊ ነበር።
አሶሽየትድ ፕሬስ (ኤፒ) የ176 አመት ልምድ ያካበተ የአሜሪካ ዜና አገልግሎት ድርጅት ሲሆን ፑሊትሰር በሀንጋሪያዊ-አሜሪካዊ አሳታሚና ፖለቲከኛ ስም የሚጠራ ለምርጥ የጋዜጠኝነት ስራ የሚሰጥ ሽልማት ነው።

ገዳይ በየወንዙ
ጄነራል ሎን ግን እንኳን በየቦታው ሊዞር የቁርስ ቤቱ ባንኮኒ እንኳ ሊደብቀው አልቻለም። ሌላው የጦርነቱን አስከፊነት ያሳየ የሚባለው የሳይጎን ከተማ ፖሊስ አዛዥ አንድ የመንደር ኮበሌን የሚረሽንበት ምስል ነው። ይህ ፎቶ ጭካኔንና የሕይወትን ርካሽነት ሲያመለክት፣ በሌላ በኩል ደግሞ አውዱን ባለማሳየቱ ግማሽ ታሪክ ነጋሪ የሚል ትችትን አስተናግዷል። አውዱን ባጭሩ:-
በቬትናም ጦርነት ወቅት ‘የቴት ጥቃት’ የተባለው ዘመቻ እንደ አንድ ምዕራፍ ይወሰዳል። ቴት በጥር  አጋማሽ የሚከበረው የቬትናማውያን ዘመን መለወጫ ነው። ቬት ኮንግ የተባሉት ‘የአንክል ሆ’ ወዳጆች በዓሉን አስታክከው በበርካታ የደቡብ ቬትናም ከተሞች ላይ የተቀናጀ ድንገተኛ ጥቃት ይፈፅማሉ። ጥቃቱ ዓላማውን ባያሳካም በሺህ የሚቆጠሩ ሕይወታቸውን አጥተውበታል።
ዊን ቫን ሌም የተባለው ወንድማችንም በዛው አካባቢ የተያዘ ቬት ኮንግ ነው። አንድ ኮሎኔልን ከስድስት የቤተሰቡ አባላት ጋር ገድሎ ሊያመልጥ ሲል ነው የተያዘው በሚልና በሌሎችም ሀጢአቶች ይወነጀላል። በዚህ የተበሳጨው የፖሊስ አዛዥ ዊን ጎክ ሎን እዛው መንገድ ላይ ግንባሩን ብሎ ይጥለዋል። አንዳንዶች እንደሚሉት አዛዡ ግድያውን እንዲፈፅም ለአንዱ ወታደር  ትዕዛዝ ሲሰጠው በማመንታቱ ነው ርምጃውን የወሰደው። አጋጣሚ ሆኖ በቦታው ጋዜጠኞች ነበሩ። ፎቶውን ያነሳው የኤፒ ወኪል ኤዲ አዳምስ ሲሆን በፊልምም ተቀርጿል።
የተያዙ ሰዎችን ለማውጣጣት ሽጉጥ መደገን የተለመደ ስለነበር ፎቶ አንሺው ግድያውን አልጠበቀም። ኤዲ በተከታታይ ወደ አስራ አራት ፎቶዎችን ያነሳ ሲሆን ታጥቦ እስኪወጣ ምስሉ በትክክል ካሜራው ውስጥ ስለመግባቱ እርግጠኛ አልነበረም (አዎ ፎቶ በንጥረ ነገሮችና ውሃ ውስጥ ታጥቦ ነበር የሚወጣው)። የዛኑ አመት የፑሊትሰር አሸናፊ መሆን አልበዛበትም። ፎቶው የጦርነቱ አንድ ምልክት ሆኗል። የስሚዝ ኤንድ ዌሰን ስሪት የሆነው ባለ 38 ካሊበር ሽጉጥም የራሱን ዝና አግኝቷል። ሆኖም የሟች ታሪክ እዛው ሲዘጋ ገዳይ ግን በ67 ዓመቱ በሞት እስከተለየበት ጊዜ ድረስ የምስሉ እስረኛ እንደሆነ ህይወቱን ገፍቷል።
በጦርነቱ ሰሜኖች አሸንፈው ሳይጎን ወድቃ አገሪቱ አንድ ስትሆን ግማሽ ሚሊየን የሚደርሱ ቬትናማውያን ወደ አሜሪካ ተሰድደዋል። ከነሱ መካከል የፖሊስ አዛዡ ዊን ጎክ ሎን ይገኝበታል።
ጄነራሉ ቨርጂኒያ በተባለው የአሜሪካ ግዛት ቁርስ ቤት ከፍቶ ይሰራ ነበር። ከጊዜ በዃላ ሰዎች ማንነቱን ሲያውቁ ደንበኞች መሸሽ ጀመሩ። እንደውም መፀዳጃ ቤቱ ውስጥ “ማን እንደሆንክ እናውቃለን” ብለው ፅፈውበት ነበር። “እኔ ላይ ለመፍረድ በነበርኩበት ሥፍራና ቅፅበት መገኘት ያስፈልጋል። ያኔ ምናልባት ነገሩን መረዳት ይቻል ይሆናል። አሜሪካ ውስጥ መኖር አስቸጋሪ ቢሆንብኝም በአምስት ልጆቼ እኮራለሁ።” ሲል አንድ ጊዜ ቁርስ ቤቱን ለጎበኘ ጋዜጠኛ አስረድቷል።
ሎን የፈፀመው ድርጊት የጦር ወንጀል ነው በሚል የስደተኞች ጉዳይ መሥሪያ ቤት ከሀገር ለማባረር እንቅስቃሴ ጀምሮ ነበር። እሱን በመደገፍ ፎቶ አንሺው ድምፁን አሰምቷል። በወቅቱ ፕሬዚዳንት የነበሩት ጂሚ ካርተር ሁሉ በጉዳዩ ላይ ገብተውበት በጦር ወንጀለኝነት ቢባረር ብዙ ድንጋይ ይፈነቅላል ብለው አልፈውታል።
ሎን በመጨረሻ ምግብ ቤቱን ዘግቶ ከሰዎች እይታ ርቋል። በዃላም በ1998 ዓ.ም በካንሰር ሳቢያ ሕይወቱ ሲያልፍ  ኤዲ ስለሱ ታይም መፅሔት ላይ ባሰፈረው ስንብት፤ “ጄነራሉ ቬት ኮንጉን ገድሏል። እኔ ደግሞ በካሜራዬ እሱን ገድዬዋለሁ። ፎቶዎች ትልቅ ሃይል አላቸው። ሰዎች ያምኗቸዋል። ሆኖም ግን ግማሹን እውነታ ነው ብቻ የሚናገሩት። ያ ፎቶ ያልመለሰው ጥያቄ ጄነራሉን ብትሆን ኖሮ በዛ ቦታና ሰዓት ሁለት ሶስት አሜሪካውያንን ግንባር ግንባራቸውን እያለ ሲጥል ያገኘኽውን ነፍሰ ገዳይ ምን ታደርገው ነበር የሚለውን ነው።” ብሏል፡፡ ‘ወደ ፈተናም አታግባን’!

Read 10433 times