Saturday, 25 June 2022 00:00

የሐዘን መልዕክቶችና መግለጫዎች

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ሀገር እንደዋዛ፣ ካቧ እየተናደ፣
ማገሯ እየላላ፣
                ላዪ እየነደደ
በምሰሶው ብርታት፣
                 ለታሪክ በቆመው
በወጋግራው ድጋፍ፣
               ሊወድቅ ባዘመመው፤
ትንገዳገዳለች፣ በሰካራም መንገድ
ከታዛው ቁጭ ብሎ፣ ይታዘባል
ትውልድ፤
እኔም እንደ ትውልድ፣
አዚምሽን ተሸከምሁ
በህመምሽ ታመምሁ፤
ግፉ አደነዘዘኝ
መኖር ጎመዘዘኝ
እንቅልፌን አባረርሁ
ተኝቼ ስነቃ፣ እንዳላጣሽ ፈራሁ፤
© Zelalem Tilahun
***
እንባዬን የት ላርገው?
(በእውቀቱ_ስዩም)
ቀና በል ይሉኛል ወዴት ልበል ቀና
ከላይ ተደፍቶብኝ አገር እንደቁና
ጣራው ባጡ ቀርቦኝ
በር አልባ ግድግዳ እንደ ዝናር ከቦኝ
በጫጩት ጉልበቴ እየተወራጨሁ
እንባየን ዘግኘ ሽቅብ እየረጨሁ
ወደ አማልክት ብጮህ-ጠሎቴን
አይሰሙት
በየት በኩል ኖሬ
በየት በኩል ልሙት።
በምን ይገለጻል የትውልዴ አበሣ
ከመንበርከክ ብዛት መራመድ የረሣ
ያልፋል ተለጉሞ
ያልፋል ተከርችሞ
የጉልበቱን ኮቴ ምድር ላይ አትሞ።
ወፈፌ ቀን አልፎ እብድ ቀን ሲመጣ
ማልቀስ አመጽ ሲሆን በሸንጎ ሚያስቀጣ
እንባዬን የት ላርገው
ወዴት ልሸሽገው?
*    *    *
"--ስሜትን በሚወርር፣ ልብን በሚያሳዝን፣ ጉልበትን በሚሰብር ኀዘን ውስጥ ላሉት ወገኖቻችን፤ ትናንት ባለ ብዙ ቤተሰብ ዛሬ ሌጣ ለሆኑት፣ የክብር ሞትና መቃብር ለተነፈጉት፣ ሰው ሆነው በሰው ለተገፉት፣ ኢትዮጵያዊ ሁነው በኢትዮጵያውያን ለተሠዉት፣ አገር  ሳላቸው እንደ ባዕድ ለተቆጠሩት፣ ለደከሙበት ምድር በወርቅ ፈንታ ሰይፍ ለተከፈሉት ልጆቻችን እግዚአብሔር ያጽናችሁ በማለት፣ የሞቱትንም ደመ አቤልን ያከበረ አምላክ ደማቸውን እንዲመራመር በመለመን መልእክታችንን እንጀምራለን!
ብዙ መልካም ቃላት በሚነገሩበት፣ የጥበብ ድምፆች በሚያስተጋቡበት፣ መሠረት ፈርሶ ለጉልላት ጌጥ በምንጨነቅበት በዚህ ዘመን፣ “እንዴት ካለው ጊዜ ደረስን ማለት መመጻደቅ ባይሆን ኖሮ የሚባልበት ወቅት ሁኖ አግኝተነዋል። ትናንት ገንዘብን የሚቀሙ “እንዴት የሰውን ልፋት ይወስዳሉም" ተብለው በተወገዙበት ምድር፣ ሕይወትን የሚቀሙ፡ የሰው ዘር ቅነሳ የሚያደርጉ ግፈኞች ሲንጎማለሉ ማየት ያሳዝናል። ንጹሐን ወገኖቻችን እግዚአብሔር በሰጣቸው ማንነት ብቻ ሲሞቱ ስናይ የዝቅታችንና የመውደቃችን ልክ ማጣት ጎልቶ ይታያል። በርግጥ የሞቱት ወገኖቻችን ሰማዕታት ናቸውና ቤተ ክርስቲያን ትዘክራቸዋለች። ሰማዕት ስለ እግዚአብሔር ብሎ የሚሞት ነው። እነዚህም ወገኖቻችን እግዚአብሔር በሰጣቸው ማንነት፣ ለምን እንዲህ ተፈጠራችሁ ተብለው የሞቱ ናቸውና ሰማዕታት እንላቸዋለን። ገዳዮችም ቀጥተኛ የእግዚአብሔር ተቃዋሚዎች ናቸው።--"
(ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም  ወእጨጌ ዘመንበረ  ተክለሃይማኖት፤ በወለጋና በጋምቤላ የአገራችን ክፍል የደረሰውን አሰቃቂ የወገኖቻችን ግድያ አስመልክቶ ካስተላለፉት የኀዘን መልዕክት የተወሰደ)
***
“በንጹሃን ዜጎች ላይ በህገወጥ እና በኢ-መደበኛ ኃይሎች የሚደርስ ጥቃትና  መተዳደሪያን ማውደም ተቀባይነት የለውም። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በቤኒሻንጉልና ኦሮሚያ ክልሎች፣ ዋና ዓላማቸው ኅብረተሰቡን ማሸበር በሆኑ አካላት የተፈጸመው የሰው ልጆችን ህይወት የሚቀጥፍ  ዘግናኝ ድርጊት የምንታገሰው አይደለም። ጥቃት በደረሰባቸው አካባቢዎች ሰላምና ደህንነትን መመለስ አሁንም ቅድሚያ የምንሰጠው ተግባራችን ነው።”
(ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ)
***
"--የመንግስት ተቀዳሚ ተግባር የዜጎችን ደኅንነት ማስጠበቅ ሲሆን፤ በዚህ ወቅት መንግስት የዜጎችን ደኅንነት የማስጠበቅ  ስራውን በጥንቃቄ እንዲሰራ እንጠይቃለን፡፡
እንዲህ ህዝብን በሚያሸብሩና የዜጎችን ህይወት እንደዋዛ በሚቀጥፉ ነፍሰ በሎች ላይ እርምጃ ሲወስድ፣ በማያዳግም መንገድ እንዲሆን አልያ እንደተለመደው ነካክቶ መተው በየጊዜው የወገኖቻችንን ውድ ህይወት እያስገበረን እንደሚቀጥል  ለማሳሰብ እንወዳለን፡፡ የሚወሰዱ እርምጃዎች ተመልሰው ለህብረተሰቡ የደህንነት ስጋት መሆን በማይችሉበት ደረጃ በከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲፈፀሙም እንጠይቃለን፡፡
በወለጋ፣ በጋምቤላ እንዲሁም በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች ከፍተኛ ግፍና መከራ ለደረሰባቸው እንዲሁም ለተጨፈጨፉ ወገኖቻችን የተሰማንን ጥልቅ ሀዘን እንገልፃለን፡፡;
(ኢዜማ )
***
“በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ወለጋ ዞን፣ ግምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ፣ አሸባሪው ሸኔ በንጹሐን ወገኖች ላይ በፈጸመው ግድያ የተሰማኝን ሀዘን እየገለጽኩ፣ ለቤተሰቦቻቸውም መጽናናትን እመኛለሁ፡፡
ድርጊቱ አገራችንን ከአሸባሪዎች ለማጽዳት የጀመርነውን ዘመቻ አጠናክረን ከመቀጠል ውጪ ሌላ አማራጭ እንደሌለን ማሳያ ነው፡፡”
(የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር፤
ዶክተር ይልቃል ከፋለ)
***
ከግድያው የተረፉት በአንደበታቸው
"--በቶሌ በአንድ መስጊድ ውስጥ ብቻ 40 ሰው ነው የተገደለው። እኔ ቤት ውስጥ 12 ሰው ሞተ። ሌላው ቆስሎ ወጣ። ያው በረሃ ላይ በእግር እየሄድን ነው መድረሻ አጥተን። ሁለት ልጆች ተርፈውልኝ ነበር፤ በውሃ ጥም ተቸግረናል።--"
(ከጥቃቱ የተረፉ አንድ አዛውንት፣ ለዶቼ ቬሌ የተናገሩት)
***
«...መደበቂያ ያደረግነው መስጂዳችንን ነበር፤ ግን እዛም ገብተው 46 ሰዎችን ገደሉብን፣ የኔን ብቻ 12 ቤተሰቦች ገደሉብኝ፣ አሁን እኔንም ቢገድሉኝ ኑሮ እያልኩ እየተጸጸትኩ ነው፤ አላህ ለምን አተረፈኝ! ከዚህ በኋላ ምን ቀረኝ?..»
(ከወለጋው ጭፍጨፋ የተረፉ አባት)
***
 “...አሁን እኮ አባ ወራ ብቻውን፣ እማወራ ብቻዋን ቀርተዋል። ምን ተረፍን ይባላል? ከዚያም ብሶ ረሃብ ሊጨርሰን ነው”
(ከጥቃቱ የተረፉ የ7 ልጆች አባት፣ ለቢቢሲ የተናገሩት)
Read 1449 times