Print this page
Sunday, 26 June 2022 10:36

“እየተዋጋን እናመርታለን፤ እያመረትን..?” እንዲል ደርግ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

  አገሬ ያንቺ ቅኔ፤ አይፈቱት ደረሰ
ችግኝ  ይተከላል፤ ሰው እየፈረሰ
“ይባስ አታምጣ”፤ ብዙ ክፉ ነገር የገጠማቸው ሰዎች የሚያደርሱት ፀሎት ነው፡፡
ሻሸመኔ ከተማ ላይ ሰው ተዘቅዝቆ ሲሰቀል የከተማው ነዋሪዎች ይባሰ አታምጣ ብለው ፀልየው ሊሆን ይችላል፡፡ ለፖለቲካ አላማና ግብ ድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ በተገደለ ጊዜ፣ ሻሸመኔ በአጥፊዎች ከመወረር አልዳነችም፡፡ ነዋሪዎቿ ቀደም ብሎ በተዘጋጀ ዝርዝር ስማቸው እየተጠራ፣ እምነታቸው እየታየ ከመገደል አልተረፉም፡፡
ዝዋይ፣ አጋርፋ፣ አሩሲ ነገሌ እና ሌሎችም ከተሞች እንዳልነበሩ የሆኑት፣ በህይወት የተረፉትም በአንድ ቀን ወደ ፍጹም ድህነት የተለወጡት "ክፉ አታሳየን" ብሎ የሚፀልይ ጠፍቶ ሳይሆን፤ ክፉን የሚያጠፋ መንግስት ጠፍቶ ነው፡፡ ከክፉዎቹ አንዱ ደግሞ በማይታይና በማይገለጥ ተንከባካቢ ኃይል እየተጠበቀና እየታገዘ ያለው፣ የተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ብሎ የፈረጀው "ኦነግ ሸኔ" ነው፡፡
ኦነግ ሸኔ ከጋምቤላ አማፂ ጋር ተባብሮ ሰኔ 7 ቀን 2014 ዓ.ም የጋምቤላ ክልላዊ መንግስት  ርዕሰ ከተማ የሆነችውን ጋምቤላን ወረረ። የጋምቤላ ከተማ በተወረረችበት ሰዓት ማለትም ንጋት 12፡30 ላይ ኦሮሚያ ውስጥ ደምቢ ዶሎና ግምቢ ላይም ሸኔ ወረራ አድርጓል፡፡ በግምቢና በደምቢ ዶሎ ላይ ያደረሰው ጉዳት ምን ያህል እንደሆነ የተገለጸ ነገር ባይኖርም፣ ጋምቤላ ከተማ ውስጥ ግን 40 ሰዎች መገደላቸው ተዘግቧል፡፡  
"ደካማ ነው፣ ስጋት ወደ ማይሆንበት ደረጃ አድርሰነዋል" የተባለው ኦነግ ሸኔና. እንቅስቃሴው፤ የተጣጣመ አይደለም። “ደካማ አይደለሁም” የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ የፈለገ በሚመስል መልኩ ነው አረመኔያዊ ተግባሩን እየፈጸመ የሚገኘው፡፡  
ከአራት ቀን በኋላ ሰኔ 11 ቀን 2014 ዓ.ም በምዕራብ ወለጋ ግምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ የፈፀመው አሰቃቂ ግድያ፣ በእልህና በበቀል ስሜት የተሞላ ይመስላል፡፡ ንጹሃንን ከህጻን እስከ አዋቂ በጅምላ ነው የጨፈጨፈው፡፡
ቶሌ ቀበሌ በስሩ ጉቱ፣ ጨቆርስ፣ ሳልሳው እና በገኔ የሚባሉ መንደሮች አሉ። ነዋሪዎቹ የደርግ መንግስት በወቅቱ በነበረው ድርቅ ሳቢያ ከተለያዩ አካባቢዎች አምጥቶ ያሰፈራቸው ናቸው፡፡ ያለፉትን ስልሳ ዓመታት ያሳለፉት በማረስና ለክልሉ መንግስት በመገበር ነው፡፡ በአጭር አገላለፅ ንፁህ ሲቪል ሰዎች ናቸው ማለት ነው፡፡ እነዚህ ከአፈር ጋር ታግለው የሚኖሩ ሰዎች ናቸው እጅግ በሚዘገንን ሁኔታ የተጨፈጨፉት፡፡ ሰባት ሰዓት በወሰደ ጥቃት ከ500 የማያንሱ ሰላማዊ ዜጎች (ህጻናት፣ ሴቶችና በእድሜ የገፉ አዛውንቶችን ጨምሮ) መገደላቸውን ዘገባዎች ያመለክታሉ፡፡
ይህን የግፍ ግፍ፣ ከጭካኔ በላይ ጭካኔ የታየበትን ግድያ፤ አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ “እንደ ዶሮ ጫጩት ታረዱ” ሲል የዘገበው ሲሆን ዜናውን ቀድሞ ከዘገበው ከአሜሪካ ድምጽ ጀምሮ ሌሎች ዓለም አቀፍ መገና|ኛ ብዙኃንም መረጃውን አስተጋብተውታል። ይህን አሰቃቂ ክስተት አሜሪካ፣ ኢራንና ቻይና በጥብቅ አውግዘውታል፡፡ የጥቃቱ ሰለባዎች አስቀድመው ለአካባቢው ሹማምንት ሥጋት ላይ መሆናቸውን ቢያሳውቁም ሰሚ አለማግኘታቸውን የሚጠቁሙ መረጃዎች ተሰምተዋል፡፡ ለምን ይሆን? ማጣራት ይፈልጋል፡፡
በጋምቤላ ከተማ የተገደሉትን ጨምሮ የሟቾች ቁጥር ከ600 በላይ ይሆናል፡፡ ለቶሌ ሟቾች የህሊና ፀሎት እንዲደረግ፣ በጉዳዩ ላይም ም/ቤቱ እንዲወያይበት በማለት በአብን አባላት ጥያቄ የቀረበላቸው የተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ፤ “ቀድሞ ባልተያዘ አጀንዳ አንነጋገርም” በማለታቸው ምክር ቤቱ በችግሩ ላይ ሳይነጋገር፣ የህሊና ፀሎትም ሳያደርግ ቀርቷል፡፡ አንድም የምክር ቤት አባል ቢያንስ ቢያንስ የህሊና ጸሎቱን ደግፎ ሲናገርም ማየት አልተቻለም፡፡ ከሰብአዊነት ይልቅ የፖለቲካ ሰውነታቸው የጠናባቸው የምክር ቤቱ አባላት፤ እንዴት የዜጎች ሞት አላስጨነቃቸውም? ይህም ጥያቄ ነው፡፡
ሰኔ 14 ቀን 2014 ዓ.ም መደበኛ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ መደበኛ ጉባኤውን የከፈተው የብልጽግና ፓርቲም፣ በግፍ ለተጨፈጨፉት ዜጎች የኅሊና ጸሎት ሲያደርስ አልታየም፡፡ ሊቀ መንበሩ ዶ/ር  ዐቢይ አህመድ፣ ምክትላቸው አቶ አዳም ፋራህና አቶ ደመቀ መኮንንም ይህን ጥያቄ አላነሱም፡፡ በእርግጥ ፓርቲው  ድርጊቱን ማውገዙ  ተዘግቧል፡፡
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን፣ ሰኔ 15 ቀን 2012 ዓ.ም ለተገደሉት ለእነ ዶክተር አምባቸው እንዲሁም ጋምቤላና ቶሌ ላይ ለተጨፈጨፉት ዜጎች፣ የኅሊና ፀሎት እንዲደረግ ጠይቀው ተደርጓል። ይህን አይነት ጥያቄ ለምን የብልፅግና ሥራ አስፈጻሚ ስብሰባ ላይ አላቀረቡም ራሱ ጥያቄ ነው፡፡ ጥያቄው ሌላም ጥያቄ እንድናነሳ ያደርጋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፣ እንደ ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያምና መለስ ዜናዊ፣ የእሳቸውን ፊት እያነበቡ፣ ፊታቸው ሲቀላ የሚቀላ፣ ሲጠቁር የሚጠቁር ሹማምንቶች እየፈጠሩ፣ የባለስልጣናቱን የማሰብና የመወሰን ነፃነት እየገፈፏቸው ይሆን እንዴ? ይህም ሌላ ጥያቄ ነው፡፡
በብልፅግና ሥራ አስፈፃሚ ስብሰባ ላይ ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ፣ በኦነግ ሸኔ ላይ ከፍተኛ የማጥቃት ዘመቻ መከፈቱን ተናግረዋል፡፡ አቶ ፈቃዱ ተሰማና አቶ ግርማ  የሺጥላ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ቀርበው ይህንኑ አረጋግጠዋል። የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ዶ/ር ይልቃል ከፍያለውም፣ ጥቃቱ ዘርን ከዘር ጋር ወደ ማጋጨት ለማሳደግ ተፈልጎ የተፈፀመ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በነገራችን ላይ ሚያዚያ 17 ቀን 2014 ዓ.ም በተወሰደ እርምጃ፣ ቦንፎ እየተባለ የሚጠራው የኦነግ ሸኔ ማሰልጠኛ መደምሰሱን ኮሎኔል መኮንን ፀጋዬ የተባሉ ወታደራዊ  ሃላፊ አስታውቀው ነበር፡፡ ኮሎኔሉ 43 ሰዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን፣ 60 ሰዎች እጃቸውን መስጠታቸውን ገልጸዋል። እሳቸው ተማረኩ ብለው በፎቶግራፍ ያሳዩን መሳሪያዎች ደግሞ ምኒሽር፣ አልቤን፣ ዲሞትፈር ካርባይንና ናቸው፡፡ እነዚህ ደግሞ የኦነግ ሸኔ ጦር ታጥቋቸው ከሚታዩት ጋር ምንም የማይገናኙና  ዘመን ያለፈባቸው ናቸው፡፡
ስለ ኦነግ ሸኔ በመንግስት የሚነገረውና የሚሆነው ነገር አልገናኝ ሲለኝ ሁልጊዜ ትዝ የሚለኝ፣ “አብዛኛው የኦነግ ሰራዊት የኦዴፓ ነው፡፡ ትጥቁም የኦዴፓ ነው፡፡ ኦዴፓ ኦነግ ወደ ደቡብ ክልል ሄዶ ወረራ እንዲያደርግ በደብዳቤ ፈቅዷል፤ እኔ ይህን በመተቸቴ ተባርሬያለሁ” የሚለው የጄኔራል ከማል ገልቹ ንግግር ነው፡፡ የበፊቱ ኦፒዲኦ የአሁኑ የኦሮሚያ ብልፅግና ፓርቲ  አመራሮች፣ ምን ያህል ከዚህ ችግር ነፃ ናቸው? ይህም ጥያቄ ነው፡፡
ከማህበራዊ መገናኛ ወዳገኘሁት መግቢያዬ ላይ  ወደ አቀረብኩት ግጥም ልመለስ፡፡
አገሬ ያንቺ ቅኔ፤ አይፈቱት ደረሰ
ችግኝ  ይተከላል፤ ሰው እየፈረሰ
 ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እንዲህ አይነቱን ትችት እንደማይቀበሉት ደጋግመው ተናግረዋል፡፡ መንግስት በዚህ ጦርነት መሃከል እየሰራቸው ያሉ ሥራዎችን ማንኳሰስ ፈፅሞ አልፈልግም። ሌሎችም የሚፈልጉ አይመስለኝም። እንዲያውም መንግስት የሚባለው ተቋም ትልቅ መሆኑን  የሚያረጋግጠው፣ በዚህ አገር አቀፍ ችግር ውስጥ ሆኖ እንደ አብርሆት ቤተ መፃሕፍት ያሉ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን በስኬት ማከናወን መቻሉ ነው፡፡ የእኔም ሆነ የእኔ መሰሎች ተቃውሞ የሚመነጨው የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅና የልማት ሥራውን ጎን ለጎን ለምን ማስኬድ አልተቻለም በሚለው ላይ ነው፡፡ “እየተዋጋን እናመርታለን፣ እያመረትን እንዋጋለን” እንዲል ደርግ፡፡


Read 2316 times
Administrator

Latest from Administrator