Saturday, 02 July 2022 16:58

ኢዜማ አመራሮቹን ነገ ይመርጣል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

 የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)፤ አዳዲስ አመራሮቹን የሚመርጥበትን ጠቅላላ ጉባዔ ዛሬና ነገ የሚያካሂድ ሲሆን  በጉባኤው ከ1200 በላይ አባላት ይገኙበታል ተብሏል።
ከሶስት አመት በፊት የተመሰረተው ኢዜማ፤ በአንደኛ መደበኛ ጉባዔው የመጀመሪያ ቀን ስብሰባው ሰኔ 25 ቀን 2014 ዓ.ም በዋናነት በፓርቲው የእስካሁን ጉዞና በወቅታዊ የሀገሪቱ ሁኔታ ላይ ተወያይቶ አቋም እንደሚይዝ የተገለጸ ሲሆን በሁለተኛው ቀን ውሎው ዳግም አመራሮቹን ይመርጣል ተብሏል።
አዲስ አበባ ፒያሳ በሚገኘው ግራንድ ኤሊያና ሆቴል በሚከናወነው በዚሁ አንደኛ መደበኛ ጉባዔ ላይ ከ1200 በላይ የጉባዔ አባላት ይታደማሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ሰኔ 26 በሚካሄደው የፓርቲው ሊቀ መንበር  ም/ሊቀመንበር እንዲሁም       ላለፈው አንድ ወር ገደማ ለሊቀ መንበርነትና ም/ሊቀ መንበርነት ለመሪ እና ም/መሪነት እንዲሁም የፋይናንስ ሀላፊ ቦታዎችን ጨምሮ እጩ ሆነው የቀረቡ የፓርቲው አባላት የምረጡኝ ቅስቀሳ ሲያካሂዱ እንደሰነበቱ ይታወቃል።
ለመሪነት ውድድር የቀረቡት በአንድ በኩል የፓርቲው ም/መሪ የነበሩት አቶ አንዷለም አራጌ ለመሪነት እንዲሁም አቶ ሀብታሙ ከተማ ለምክትል መሪነት ሲቀርቡ፣ በሌላ በኩል የፓርቲው መሪ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ በድጋሚ  ለመሪነት እንዲሁም አክቲቪስት ዮሀንስ መኮንን ለምክትል መሪነት በእጩነት ቀርበዋል።
ለሊቀመንበርነትና ም/ሊቀመንበርነት ደግሞ ጥንድ ጥንድ እየሆኑ ስምንት እጩዎች የቀረቡ ሲሆን ዶ/ር ባንትያገኝ ታምራት እና አቶ የሺዋስ አድማሱ በጋራ ለሊቀ መንበርነትና ነም/ሊቀ መንበርነት፤ በተመሳሳይ አቶ የሺዋስ አሰፋ እና አቶ ተክሉ በቀለ በጋራ ለሊቀ መንበርነትና ለም/ሊቀመንበርነት፤ ዶ/ር ጫኔ ከበደ እና ዶ/ር አማኑኤል ኤርም በጋራ ለሊቀ መንበርነትና ም/ሊቀመንበርነት እንዲሁም አቶ ጌታቸው ጳውሎስ እና ወ/ሮ ኤልሳቤጥ ሉቃስ በጋራ ለሊቀ መንበርነት  ም/ሊቀመንበርነት ውድድርመቅረባቸው ታውቋል።
የቀረቡት እጩ ተወዳዳሪዎች ጉባኤተኛው በመረጣቸው ድምፅ ምረት ውጤታቸው ይታወቃል ተብሏል።

Read 13174 times